… ዓላማው የተገን ጠያቂዎችን ማመልከቻ በአፍሪቃ መመርመር ነው። ማክሮ የሚመሯት ፈረንሳይ 3000 ሰዎች ከሁለቱ አገሮች የመውሰድ ውጥን አላት። ይህ ግን አዲስ ሐሳብ አይደለም። በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. አሜሪካ በተመሳሳይ መንገድ የተመረጡ 523 ሰዎችን ወስዳለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻድ ላይ የጉዞ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ ግን ከጥር እስከ መስከረም ባለው ጊዜ አሜሪካ የወሰደችው 99 ብቻ ነበር…

በርካታ ቻዳውያን በአንድ ጉዳይ ተገርመዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ በቻድ የተገን ፈላጊዎች ማዕከል ለማቋቋም ማቀዳቸው ከተሰማ ጀምሮ የስደት ጉዳይ በአገሪቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። መሬት ላይ ግን ጉዳዩ ትኩረት አልተሰጠውም።

ፈረንሳይ በቻድ የስደተኞች መጠለያ መገንባት ትሻለች

ማሪ ላርለም በቻድ ዋና ከተማ ንጃሜና ከአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ ከሚገኘው ቢሯዋ ተቀምጣለች። የቻድ የመሰረታዊ መብቶች ማስፋፊ ማኅበር ኃላፊ ስትሆን ከ118 የሥራ ባልደረቦቿ ጋር ትምህርት እና ድህነት በመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ትሰራለች። የምትሰራበት ድርጅት በሕግ ጉዳዮች የማማከር ሥራንም ያከናዉናል። ስደትን በሚመለከት ግን አይሰሩም ነበር። 
«አውሮጳ ስደትን አስመልክታ በሰፊው ትሰራለች። ነገር ግን እዚህ ትልቅ ጉዳይ አይደለም።» ትላለች ላርለም። 

14 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ቻድ በስደት ላይ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ዉይይት ዋነኛ መነጋገሪያ የሆነችው ድንገት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ የጥገኝነት ማዕከል በአገሪቱ ለማቋቋም ባደረጉት ሙከራ ሳቢያ ነው። እንዲህ አይነቱ ማዕከል በቻድ ጎረቤት ኒጀርም ታቅዷል። ዓላማው የተገን ጠያቂዎችን ማመልከቻ በአፍሪቃ መመርመር ነው። ማክሮ የሚመሯት ፈረንሳይ 3000 ሰዎች ከሁለቱ አገሮች የመውሰድ ውጥን አላት። ይህ ግን አዲስ ሐሳብ አይደለም። በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. አሜሪካ በተመሳሳይ መንገድ የተመረጡ 523 ሰዎችን ወስዳለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻድ ላይ የጉዞ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ ግን ከጥር እስከ መስከረም ባለው ጊዜ አሜሪካ የወሰደችው 99 ብቻ ነበር።

 ‘የተሻለ የደኅንነት ጥበቃ’

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ቃል አቀባይ ራሒማ ዲያኔ ተገን ጠያቂዎች አፍሪቃ ዉስጥ እያሉ ጉዳያቸውን የመመልከቱን ሐሳብ ይደግፉታል። «ይሕ ማለት ስደተኞቹ የተሻለ የደኅንነት ጥበቃ ያገኛሉ ማለት ነው።» የፈረንሳይ እቅድ በአገሪቱ የስደተኞች እና አገር አልባ ሰዎች የደኅንነት ጥበቃ ቢሮ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በዚህ ደረጃ የተገን ጠያቂዎች ማዕከሉ ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። ቋሚ ቢሮ ይኑረው አይኑረው የሚለውም አልለየለትም። 

Tschad Flüchtlingslager (DW/D. Blaise)

ባለፈው ጥቅምት ወር የፈረንሳይ ባለስልጣናት ከ200 በላይ ተገን ጠያቂዎችን አነጋግረዋል። ቁጥሩ ግን በቻድ ከሚኖሩ 407,996  ስደተኞች አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከ322,000 በላይ የሚሆኑት ከቀያቸው ተፈናቅለው በቻድ ለመጠለል የተገደዱት በዳርፉር የርስ በርስ ጦርነት ተገፍተው ነው። መሥራት አይፈቀድላቸውም። እንደ ኢብራሒማ ዲያኔ ሁኔታው ዛሬም አልተለወጠም። 
«በብዙ አገሮች ሁኔታው ወደ ነበረበት አልተመለሰም። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ ናይጄሪያ እና በቻድ ሐይቅ ቀጣና ያለውን ሁኔታ መመልከት እንችላለን።»
ማዕከላቱ አዳዲስ ስደተኞችን ይስቡ ይሆን?

በቻድ የተቃውሞ ፖለቲከኛው ቤራል ምባይኮቦ ግን ተገን ፈላጊዎችን በአንድ ቦታ የሚያሰባስብ ማዕከል የመገንባቱን ሐሳብ ይቃወማሉ። የቻድ አርበኞች ለሪፐብሊኩ የተባለው እንቅስቃሴ አባል ናቸው።  «ተጨማሪ በርካታ ሰዎችን ይስባሉ ብለን እናስባለን። የተገን ማመልከቻ ማቅረብ የፈለገ ሰው ሁሉ ወደ ቻድ ሊመጣ ይችላል።» 
ቻድ የስደተኞች መሸጋገሪያ ትሆናለች የሚል ሥጋትም አለ። ባለፈው ዓመት የቻዱ ፕሬዛዳንት ኢድሪስ ዴቤ ጀርመንን ሲጎበኙ ከኒጀር የተሰደዱ 90 በመቶ ሰዎች ሊቢያ የደረሱት አገራቸውን አቋርጠው መሆኑን ተናግረው ነበር። የፕሬዝዳንቱን ሐሳብ እውነተኛነት ለማረጋገጥ የሚረዳ መረጃ ግን የለም።

 በፍራይቡርግ የአርኖልድ ቤርግሽትራሰር ማዕከል ተመራማሪው ሔልጋ ዲኮው ግን ሌላ ሐሳብ አላቸው። «ቻድ እንደመሸጋገሪያ አገር ያን ያክል የጎላ ሚና የላትም። የስደት መስመሮች አገሪቱን አልፈው ይሔዳሉ። ብዙዎቹ ቻዳውያን እጅግ ደሐ በመሆናቸው ወደ አውሮጳ ለመጓዝ የሚያስፈልገውን ገንዘብ መክፈል አይችሉም።»

Niger Agadez Sahara Flüchtlinge (Reuters/Akintunde Akinleye)

ለመሰደድ እንኳ የማያበቃ ድኅነት

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት ቻድ ከዓለም ሦስተኛዋ ደሐ አገር ስትሆን በዓለም አቀፉ ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በማሽቆልቆሉ ምክንያት ኤኮኖሚዋ ቀውስ ውስጥ ይገኛል።  
ምባይኮቦ እንደሚሉት «ሰዎች የዕለት ተለት የኑሮ ትግል እና ፈታኙ ማኅበራዊ ሕይወት ይበልጥ ያሳስባቸዋል።» ይህ ደግሞ የመናገር ነፃነትን በመሳሰሉ መሰረታዊ መብቶች ላይ በየጊዜው እየከፋ የሚሔደውን ገደብ ይጨምራል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል «በመጥፋት እና በመጭቆና መካከል» ይመድበዋል። ማሪ እንደምትለዉ የስደት ጉዳይ በአገሯ መነጋገሪያ ያልሆነበት ሌላ ምክንያት አለ። «የቻድ ሕዝብ ከአገሩ የመውጣት ልምድ የለውም።» 

ይሁንና በንጃሜና ስደት እና ቻድ የድንገቴ ትኩረት ማዕከል የሆኑበት ፖለቲካዊ ስልት አለ የሚል ጉምጉምታ ይደመጣል። በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 2015 ዓ.ም. ከተካሔደው የቫሌታ ጉባኤ ጀምሮ «ሰዎች ከአገሮቻቸው የሚሰደዱባቸውን ምክንያቶች ለመግታት» በሚል ለታቀዱ ፕሮጀክቶች በርካታ ገንዘብ ይሰጣል። ባለፈው መስከረም በፓሪስ ከተካሔደ ስብሰባ በኋላ እስከ 15.2 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ ገንዘብ ቃል እንደተገባላቸው ተናግረው ነበር። ለማነፃጸር ያክል ግን የቻድ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዩሮ በታች ነው። 

ካትሪን ጌንስለር/እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *