“Our true nationality is mankind.”H.G.

በጎራዴው የሚኖር በጎራዴ ይሞታል

የስነ አእምሮ ጠበብት አምባገነኖች በሃይል ፣ ፍርሃት እና ጭንቀት ጥምረት የተሰሩ እንደሆኑ ያምናሉ ። ሃይለኞች አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ሃይልን ቀንሰው ጭንቀትና ፍርሃትን ይደምራሉ ።

Alemayehu Gebeyehu 

ይህ ማለት ግን ወደተስተካከለ ሰብዕና ይመጣሉ ማለት አይደለም ። ለበርካታ ወንጀል ፣ ለንጹሃን ስቃይና ሞት ምክንያት ሆነው እንኳ በመጨረሻው ሰዓት ራሳቸው ላይ መጨከን ይፈራሉ ። ማለት አይፀፀቱም … ራሳቸውን ጥፋተኛ አያደርጉም… ራሳቸውን አይቀጡም ። በጣም ጥቂቶች ናቸው በሃይል ተጀምረው በሃይል የሚያልቁት ። አንደኛው ምሳሌ አዶልፍ ሂትለር ይመስለኛል ። የወጣችው ፀሃይ እየጠለቀች መሆኑን ሲረዳ ፍርሃትንና ጭንቀትን ተሞርኩዞ ሃይልን ለራስ ጥቅም ያዋለ ። ራሱ ላይ መተኮሱ ብቻ ሳይሆን የአርባ ሰዓታት ሚስቱም እንድትሞት አጃግኗልና ።

በጎራዴው የሚኖር በጎራዴ ይሞታል ይባላል ። አምባገነን መሪዎች የራሳቸውን ዓለም ቀጥቅጠው ይገዛሉ ፤ በስተመጨረሻ ደግሞ እንደ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ተዘቅዝቀው ይሰቀላሉ… እንደ ጋዳፊ ተቀጥቅጠው ይሞታሉ ወይም እንደ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ተዋርደው ከሀገር ይባረራሉ ።

Image result for mugabe when he was young

ልክ እንደ ዙምባቤው ሮበርቱ ሙጋቤ የጋምቢያው መሪ ያህያ ጃሞ በምርጫ ተሸንፎ ስልጣኑን አለቅም ብሎ ነበር ። ህዝቡ ግን የዋዛ አልነበረም ። አንፈልግህም ፣ በቃን ብሎ መቀመጫ መተንፈሻ ሲያሳጣው የዘረፈውን ዘርፎ ወደ ኢኬቶሪያል ጊኒ ተሰደደ ። የላይቤሪያው ቻርልስ ቴይለር ከስልጣን ሲወገድ ተዋርዶ ወደ ናይጄሪያ አቀና ። የሰው ደም የትም ሄደህ ይከተልሃልና ዓለማቀፉ ፍርድቤት ለቀም አድርጎ የ50 አመት እስር አከናነበው ።

ዛሬ ሶማሊያ ፍርክስክሏ እንዲወጣ አዎንታዊ ሚና የተጫወተው ዚያድ ባሬ ወንበሩን እንዳጣ ወደ ናይጄሪያ ነበር የተሰደደው ። እዛው እንዳለ ሞተ ። የሂትለር አፍሪካዊ እኩያ የሆነው ኤዲ አሚን ዳዳ ሳኡዲ አረቢያ ለመሰደድ ተገዷል ። ህገመንግስታዊው ፍትህ ቢዘለውም ህገ ሰማዩ ፍትህ ግን በከፋ የኩላሊት በሽታ አማካኝነት ጎብኝቶት ነበር – ሲሞትም 220 ኪ.ግራም ያህል አብጦ ነበር ።

በኩዴታ ዙፋን ላይ ወጥቶ በኩዴታ የተባረረው ሞቡቱ ሴሴኮ ወደ ሞሮኮ ተባሮ በፕሮስቴት ካንሰር ነው ያረፈው ። አንድ እድለኛ አምባገነን አለ ከተባለ የሱዳኑ ጋፋር ኒሜሪ ነው ። በመፈንቅለ መንግስት ከተወገደ በኋላ የተጋዘው ወደ ግብጽ ነበር ። በ1999 ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ተፈቅዶለት በ2000 በተካሄደው ምርጫ ሁሉ መወዳደር ችሏል – ከ10 በመቶ በታች ድምጽ አገኘ እንጂ ። በ2009 ሲያርፍም በሀገሩ ህዝብና አፈር ለመቀበር ችሏል ።

የቡርኪናፋሶ ብሌስ ካምፓወሬና የኢትዮጽያው መንግስቱ ሃይለማርያም በአይቮሪኮስትና በዙምባብዌ በስደተኝነት ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ ። ሁይማን ራይት ዎች ካምፓወሬን ለፍትህ ማቅረብ የሚፈልግ ሲሆን መንግስቱ ሃይለማርያም በሌለበት የሞት ፍርድ ተበይኖበታል ። ቡርኪናፋሶ ለካምፓወሬ የዜግነት መታወቂያ ሰጥታለች ፤ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ደግሞ የቡርኪናፋሶ ዜጋ ለፍርድ ጉዳይ ተበሎ ለሌላ ሀገር ተላልፎ አይሰጥም ።

መንግስቱ ሃይለማርያም በየአምስት አመቱ ፍቃዱ እየታደሰ እንጂ ይህን ያህል ግዜ ኖሮ የዜግነት ካርድ አላገኝም – ርግጥ ነው ራሱ ሳይፈልግ ቀርቶም ይሆናል ። እናም የሀገሩ « እንግዳ » ሆኖ ነው ተከብሮ እየኖረ የሚገኘው ። ሮበርቱ ሙጋቤ ተላልፎ ይሰጠን የሚለውን ተደጋጋሚ ጥያቄ ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል ። ዋናው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍ ስልጣን ላይ ካለ ደግሞ መንግስቱን ማንም አይነካውም ። የተቃዋሚው ድርጅት ኤም ዲ ሲ ግን በተደጋጋሚ እንደሚናገረው ‹ የኢትዮጽያ ፍትህ የአፍሪካ ፍትህ › በመሆኑ ስልጣኑን ከጨበጠ መንግስቱ ተላልፎ መሰጠቱ አያጠያይቅም ።

ስደት ፣ ውርደትና ውሻዊ ሞት የአምባገነኖች የመጨረሻ እጣ ፈንታ ነው ። የወቅቱ አነጋጋሪ መሪ ሮበርቱ ሙጋቤ ሆኗል ። የሚመራው ድርጅት/ ዛኑ ፒ ኤፍ / እሱን ቤቱ ቁጭ አድርጎ ከስልጣን መወገዱን እየጨፈረ ቢያውጅም ሙጋቤ የሞቀውም ሆነ የበረደው አይመስልም ። ጨዋ ወይም ብልጣ ብልጥ ኩዴታ ባደረገው ጦር ሰራዊት መሸሻ የሚሆን የማርያም መንገድ ተበጅቶለት ፣ ስልጣኑን የማስረከቢያ ቀነ ገደብ ተቆርጦሎት እንኳ ከወንበሬ አልነቃነቅም ብሏል ። እንግዲህ ስደትን አልቀበልም የሚለው ሙጋቤ ወደ ውርደትና ያልተጠበቀ መጨረሻ ማምራቱ አይቀሬ ይመስላል ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0