አገሬ አዲስ  – ህዳር 20 ቀን 2010 ዓም /29-11-2017

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጠላቶቿ የማይሰብቁት ጦር፣የማይሸርቡት ተንኮል የለም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙሃን የዜና መስመሮች  ለማወቅ እንደቻልነው የጀርመን ሉተራን የእምነት ተቋም በጥናትና ምርምር ስም የተከበረውን ቅዱስ መጽሃፍ የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ ኢትዮጵያ የምትባለው ለዘመናት የታሪክና የእምነት ባለቤት የሆነችው አገር ቀጣዩ ትውልዷ እንኳንስ ታሪኳን ስሟንም እንዳያቅና እንዲረሳ ብሎም ፈራርሳ እንዳልነበረች እንድትሆን የማድረግ ሴራ በሚያራምደው በአገር በቀሉ የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጪ(ኦነግ) ነኝ በሚለው  ቅጥረኛው ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅት አባል በንቲ ኦጁሉ በተባለው ፓስተር በኩል መጽሃፍ ቅዱስን በመከለስ የጥፋት ዘመቻውን ይፋ አድርጓል።

የፈረንጆቹ የካቶሊክና የሉተራኑ የእምነት ተቋማት ኢትዮጵያን የማፈራረሱ ስራ ዛሬ ወይም ትናንትና የጀመሩት ሳይሆን ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል።ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት ፖርቱጋሎች የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን እምነት አጥፍተው በራሳቸው የካቶሊክ እምነት ለመተካትና አገሪቱን በመዳፋቸው ስር ለማስገባት ያደረጉት ሙከራ በብሩህ መሪዎቿና የቤተክስርስቲያኗ ካህናት ትግል ሊከሽፍ ችሏል።ከዚያም በዃላ በተከታታይ አገሪቱን ለመያዝ በሃይማኖት ዙሪያ አያሌ ሙከራዎች ብሎም ደም ያፋሰሱ ጦርነቶች ተካሂደዋል።የጣልያንን ወራሪ ጦር ታንኩን ጠበል እረጭቶ ባርኮ የላከው የካቶሊኩ ጳጳስ ነበር።ከዚሁ ኢትዮጵያን ከማፈራረሱ ጋር አንዷ ዒላማ የሆነችው  ከአገር ወዳድ ጎን ለጎን  እንደ አንድ ወታደራዊ ተቋም ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት የቆመችውና በጦር ሜዳ ላይ የዋለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነበረች፤ አሁንም ነች።ቤተክርስቲያኗን ማፈራረስ አገሪቱን ለማፈራረስ የሚደረገውን ሙከራ ሁሉ ውጤታማ ያድርገዋል ብለው ስለሚገምቱ የግንባር ጦራቸውን የሚያሰልፉት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ነው።

የኢትዮጵያ አንድነትና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ መሆናቸውን  አይክዱም።የሁሉንም ጎሳ ተወላጅ  በእምነት ሃረግ አስተሳስራና  ሰብስባ፣ በዛፍ፣በወንዝ፣በቋጥኝና ተራራ.. ያምን የነበረውን ከጣኦት እምልኮ አላቃ፣በአንድ አምላክ ስም አጥምቃ፣የአንድ አገር  ብሔራዊ ስሜትን  ያጎናጸፈች፣ የሚግባባበትን ቋንቋ አዳብራ ያሰራጨች፣ያስተማረች፣ከትንሽነት ትልቅነትን የዘከረች፣ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነች የሃይማኖት ተቋም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነች።

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ በፊት የአምላክን መኖር የተቀበለች፣በሕገ-ልቦና፣በብሉይ ኪዳን ሕገ-ኦሪትና በአዲስ ኪዳን የወንጌል ሕገ-ክርስቲያን እምነት ከፈጣሪ ጋር ተሳስራ የኖረች አገር ናት።ለኦሪታውያን የተሰጠውን ያምላክ ቃልኪዳንና ሕግጋት ለሰፈረበት ጽላት(ታቦት) (arc of the convenants)ማረፊያ፣ከክርስቶስም እልፈት በዃላ ግማደ መስቀሉ የተገለጠበትና ያረፈበት አገር በመሆኗ ልዩ ያደርጋታል።ቅናት ያደረባቸው ነጮች  ያንኑ ያምላክ ስጦታ ለመንጠቅ ያላሰለሰ ሙከራ እንዳደረጉ አይካድም።ይህ ትልቅ የእምነት ትርጉምና በገንዘብ የማይተመን ዋጋ ያለው ቅርስ በአክሱም ገዳም ውስጥ መኖሩ ይወራል  እንጂ በጣልያኖች ወይም በእንግሊዞች ተሰርቆ ላለመውጣቱ ወይም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ያገሪቱን ቅርስና የታሪክ ንብረት መዝረፍና መሸጥ ልማዱ ያደረገው የወያኔ ቡድን ላለመሸጡ ማስረጃ የለም።  አልፎ አልፎ ጽላቱ እንግሊዝ አገር ፣ሰኮትላንድ ውስጥ እንደሚገኝ የሚናፈሰው ወሬ ካለምንም ፍንጭ የሚነገር አይደለም። በአክሱም  መኖሩንም በዓይኑ አይቶ ያረጋገጠ  የለም።እንኳንስ በቅርበት የዘረፋ ቀጠና ውስጥ ባሉት የአክሱም፣የላሊበላ፣የግሸን ማርያም፣የሓይቅ እስጢፋኖስ፣የዋልድባ ገዳማት ቀርቶ በርቀት ባሉት የደብረሊባኖስ፣የተልባበ ማርያም፣የተንታ ሚካኤል ደብርና ገዳማት ውስጥ ያሉትም ቅርሶች ከወያኔ ዘረፋ አልዳኑም። በወያኔ ጊዜ አይደረግም አይባልም፤እንኳንስ ቅርስ አገርም የሚሸጥ ሸቀጥ ሆኗል።

ቅኝ አገዛዝ በተከታታይ ደረጃ እንዲሁም መልክ እያደገ የመጣ ሂደት ነው፤በመጀመሪያ አገር በማሰስና በፍለጋ ስም(Expedition/Exploration) ሰላይ ቀሳውስቱን በማሰማራትና በማስፈር እንዲሁም በንግድ ልውውጥ ለወረራ ማደላደል፣

ቀጣዩ  በወታደር ሃይል በመውረር አገርን በቅኝ ግዛትነት መያዝ(Anexetion/colonization)ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ሃብቱን መዝረፍ ብቻ ሳይሆን ያገሩን ሕዝብ እንደ ዕቃ እየቀጠቀጡ እንደ እንስሳ ለጉመውና በሰንሰለት አስረው፣ ባርያ አድርጎ መሸጥ መለወጥ።

አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ኔዎ ሊበራል የፖለቲካ ፍልስፍና ግሎባላይዜሽን(Globilization) በሚል ፈሊጥ ነጋዴዎችን በማዝመት የአገርን የተፈጥሮ ሃብት መመዝበር፣ ለም መሬት እየያዙ ለአገሩ ሕዝብ ገበያ የምግብ ፍጆታ የማይውሉ  ለውጭ አገር ገበያ የሚሆኑ የቅንጦት ምርቶችን አበባና ትምባሆ የመሳሰሉትን በማምረት መሬትና ጅረቶችን በኬሚካል መበከል።በአገሪቱ ሃብትና የሕዝብ ጉልበት የተቋቋሙ የምርት ተቋማትን በርካሽ ዋጋና በአገር ውስጥ የባንክ ብድር እየገዙ ኢንቨስትመንት (investment)በሚል ጭንብል በመቆጣጠር  የምርት ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢው እንደኮበለለ እንዲቀር ማድረግ። የአገር ነጻ ኤኮኖሚ እንዳያድግና ጥገኛ እንዲሆን መሰናክል መፍጠር፤ ለዚያም አገር በቀል ተባባሪዎችን ስልጣን ላይ በማስቀመጥ የእጅ ዙር አገዛዝ (Neo-colonialism) ሕጋዊነት እንዲኖረው ማድረግ የዘመኑ ስልት ሆኗል።ከዱሮው የሚለየው ወታደር ሳያዘምቱ፣ጥይት ሳይተኩሱ በባንዳዎች ፊርማ የጸደቀ ስምምነት መሆኑ ብቻ ነው። የሚመረቱ ጥቂት ምርቶች ቢኖሩ ገቢያቸው ለልማት ሳይሆን በሚቀሰቅሱት የጎሳ ግጭት ምክንያት እነሱ በሚያመርቱት የጦር መሳሪያ ግዥ ላይ እንዲውልና ይበልጥ ድህነትና ቀውስ እንዲከሰት ማድረግ ከመሰረታዊው የቅኝ ግዛት ወረራ ዓላማ የተለዬ  አይደለም።

ሰላማዊና ረዳት መስለው በመግባት ውስጥ ውስጡን እየቦረቦሩ በእምነት የተሳሰረውን ሕዝብ ማለያየቱ ከጣልያኖች ወረራ በዃላ በተለይም ላለፉት ሃምሳ ዓመታት እያደገ የመጣ መሆኑን ታዝበናል። በአሜሪካኖች፣በጀርመኖች፣በስዊድኖች፣በእንግሊዞች የካቶሊክ፣የፕሮቴስታንት ልዩ ልዩ ሴክቶች እምነት ለበስ የስለላ ድርጅቶች ያደረሱት መከፋፈል ውጤቱ አሁን የምናዬው ሃቅ ነው።ድሃውን ሕዝብ በድህነቱ፣የከፋውን በብሶቱ፣ባለው ደካማ ጎን እየገቡ አገሪቱን ለማፈራረስ ካላቸው ዓላማ ጎን እንዲሰለፍ በመጀመሪያ የራሱ አገርና የማንነቱ መግለጫ የሆነውን፣አያት ቅድመ አያቶቹ  አክብረው የያዙትን ሃይማኖት፣ባህልና ታሪክ እንዲጠላና እንዲርቅ ብሎም ለጥፋት ተባባሪ እንዲሆን አድርገውታል።የአንድ አገር ሕዝብ የሚተሳሰርባቸውን እሴቶቹን እየናዱና እየበጣጠሱ ማራራቅ ብሎም እርስ በርሱ እየተጋጬ  ሃይሉ መንምኖ ለወረራ አመቺ ሆኖ የሚገኝበትን ስልት የመቀየሱ ተግባር በታሪክ  የታዬ ተደጋጋሚ ድርጊት ነው።ሊግባባ የሚችልበትን ቋንቋ እንዳይናገር፣የጋራ ምልክትና የማንነቱ መግለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ እንዳያውለበልብ፣የስነምርምርና ስነጽሁፍ ባለቤት የሚያደርገውን የራሱን ፊደል አጥፍቶ በባእዳኑ ፊደል እንዲተካና ጥገኛ እንዲሆን፣ በአጠቃላይ ታሪክ አልባ ማድረጉ አገር የማጥፋቱ ሂደት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው።

ለዚህ ደባ የማይመቸውንና አገሪቱን አሳልፎ ያልሰጠውን ሕዝብ በተለይም አማራውን ለማዳከም ሲሉ ከሃይማኖቱ ጋር ያለውን ትስስር በቅድሚያ መበጠስ እንዳለባቸው በማመን የእምነቱን ተከታይ ዃላቀርና አውሬ አስመስለው በመሳል ሌላው ወገኑ እንዲፈራውና እንዲጠላው ብሎም እንዲርቀው ያላቋረጠ ቅስቀሳና የተሳሳተ ስብከት ሲነዙ ኖረዋል።በአሁኑ ስርዓት የነጮቹ ሃይማኖት በተለይም የፕሮቴስታንቶቹ ካለምንም ቁጥጥር በፈለጉበት ቦታ የመስፋፋት እድልና ነጻነቱ የተጠበቀ  ሆኗል።በቅርቡ በዚሁ በፈረንጆቹ ሃይማኖት ተኮትኩቶ ያደገው   ጠ/ሚኒስትር ነኝ ባዩ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለአሜሪካ ሚሲዮናውያን ከስድስት ሽህ በላይ የሚሆኑ የፕሮቴስታንት ተቋማት/የጸሎት ቤቶች እንዲመሰረቱ ፈቃድና ተስፋ ሰጥቷቸዋል።ይህ ትልቅ የወረራ ውል  በቅድሚያ  ተፈጻሚ የሚሆነው በፈረደበት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲሆን ወደ ሌሎቹም ያገሪቱ ክፍሎች እንደ እባብ እየተሳበ የማይደርስበት ሁኔታ የለም።የደቡብም ሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፈጣሪው እንግዳና ባዳ አይደለም፤በሚያምንበት መንገድ አምላኬ ነው ከሚለው ጋር ሲገናኝ የኖረ ሕዝብ ነው። አሁን የሚፈልገው ቢኖር የኑሮ ሸክሙን የሚያቃልልለት፣ሰብአዊና የዜግነት መብቱን የሚያስከብርለት፣ልጆቹ ለቁም ነገር የሚበቁበት፣ህክምናና ትምህርት የሚያገኝበት ፣ከእርሃብ የሚገላገልበት ዘመናዊ እርሻና  የሚሰማራበት ልዩ ልዩ የስራ መስኮች  እንዲፈጠሩለት፣ሌሎች አገሮች ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስ የሚያበቃው  ስርዓት እንዲሰፍን እንጂ ፈረንጆች ሰብስበው የሚያደነቁሩበት የጸሎት ቤት እንዲስፋፋበት አይደለም።

የፈረንጆቹ ዓላማ ደሃውን ሕዝብ ስትሞት  የገነት ቤት ባለቤት ትሆናለህ በሚል ፈሊጥ በህይወት የያዘውን የመሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት እንዲያጣ የማድረግ ብልሃት ነው።ይህንን ብልሃት ከደረሰባቸው በዃላ የተገነዘቡት አንዱ የነጻነት ታጋይ የሆኑት የደቡብ አፍሪካው ቄስ ዲስሞንት ቱቱ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል”ነጮቹ እኛን ከመከራ ለማዳንና ለመርዳት የመጡ መስለው ሰበኩን፤እኛም በቀና መንፈስ ተቀበልናቸው።ውስጥ ለውስጥ አለያይተው እርስ በርሳችን እንድንጋጭ፣በአንድነት እንዳንቆም አደረጉን። መጽሃፍ ቅዱስ ሰጥተውን ዓይናችንን ጨፍነንና ወደላይ አንጋጠን  አምላክ! አምላክ! ስንል ከስር መሬታችንን ወሰዱት፤ የተፈጥሮ ሃብታችንን፣ማዕድናችንን መዝብረው ወደ አገራቸው አስኮበለሉት፤ ዓይናችንን ገልጠን ወደታች ስንመለከት የተረፈ ነገር የለም፤ከመጽሃፉ ቅዱሱ በቀር  የያዝነው ነገር የለም፤ባዶአችንን  አስቀሩን፤በአገራችን የበታችና ሁለተኛ ዜጋ፣የበይ ተመልካች  አደረጉን።”በማለት የነጮቹን መሰሪ ስራ አጋልጠውታል።

ኢትዮጵያም  በዘመነ ወያኔ የውጭ ባለሃብቶች መፈንጫ ሆናለች።የፈረንጆቹ የካቶሊክና የፕሮቴስታንቱ ሃይማኖት እንዲስፋፋ ሲደረግ  አገር በቀሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ግን እንዲከስም ፣ ተቋሙ ሃይማኖቱን በማያስከብሩ በካድሬ ጳጳሳት ተይዞ እድገቱ እንዲገታና አቅመቢስ እንዲሆን ተደርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከላይ እስከታች ቆብ በጫኑ የወያኔ ሹሞች ታግታለች።ምዕመናን የሚሰበሰቡባት ሳትሆን ገንዘብ የሚሰበሰብባት የንግድ ተቋም ሆናለች።ለሃይማኖታቸው የሚቆሙት አባቶች ፣ቀሳውስትና ዲያቆናት የጥቃት ሰለባዎች ሆነዋል። በጥቅምና በፍርሃት ታውረው ለወያኔ ስርዓት ቡራኬ ከሚሰጡት በስተቀር ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው በቤተክህነቷ አስተዳደር ቀርቶ በደጀ-ሰላም ዙሪያ እንዲውሉ አይፈቀድላቸውም።እጣ ፈንታቸው እስራትና ስደት ሆኗል።

ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ጋር ተሳስሮ የኖረውም የእስልምና ሃይማኖት ከዚሁ ደባ አላመለጠም።ለእምነት መብታቸው የተነሱትን አትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ስርዓቱ በአክራሪነትና በሽብርተኛነት ፈርጆ፣ ሲገል፣ሲያቆስል ፣ሲያሳድድ፣የቀሩትንም በየእስር ቤቱ አጉሮ ሲያሰቃይ ኖሯል።አሁንም እያሰቃዬ ነው። በመረጧቸው መሪዎቻቸው ምትክ የራሱን ስልጣን አስከባሪ አድር ባዮች ተክቶ እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ ሆነዋል።በአገር ወዳዶቹ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጀርባ በስማቸው የሚነግዱና የሚንቀሳቀሱ የኦነግ አክራሪ ሙስሊሞችም እንደ ፕሮቴስታንቱ ፓስተር ኦጀሎ ተነስተው ከክርስቲያኑ ወገኖቻቸው ጋር አብረው እንዳይሰለፉ የሚያደርጉት ጥረት አገር ከማፈራረሱ ሴራ ጋር የተያያዘ ነው።

ኢትዮጵያ እራሷን ጠብቃ ሌሎቹም ያፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ መዳፍ እንዲወጡ ባደረገችው ያላሰለሰ ትግል የነጮቹ ወራሪ መንግሥታት ዋናዋ ጠላታቸው አድርገዋታል።ጥርሳቸውን ከነከሱባትና የበቀል ክንዳቸውንም ካነሱባት ውለው አድረዋል።

በቀጥታ ወረራ ሊሳካላቸው ያልቻለውን በተዘዋዋሪ አገር በቀል ባንዳዎችን ስልጣን ላይ በማውጣትና በማጠናከር ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሁለገብ ዘመቻ ከፍተዋል፤ ከሚሰሩት የመበታተን ስራ አንዱ ይህ ሰሞኑን በኦነግ ቄስ ነኝ ባይ ግለሰብና በአለቆቹ በጀርመን ሉተራን ቄሶች ትእዛዝ ተከልሶ የወጣው መጽሓፍ ቅዱስ ነው።በዚህ መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ለዘመናት በሁሉም ሲሰበክና ተቀባይነት ኖሮት የዘለቀው የኢትዮጵያንና የፈጣሪን ግንኙነት የሚያወሳውን የተደጋገመ ታሪክ አውጥቶ በሌላ ኩሽ በሚል ስም  እንዲተካ ተደርጎ ቀርቧል።ከአርባ ስምንት ጊዜ በላይ የተጠቀሰው ስሟ በሌላ ተተክቶ እንዲጠራ ተደርጓል።ዘመቻው እንኳንስ በአገር ደረጃ በስምም ደረጃ እንዳትታወቅ የማድረግ የስነልቦና ጦርነት ነው።ኢትዮጵያን እንደ አገርና ለፈጣሪ ቅርበት ያለው ሕዝብ የሚኖርባት አገር እንደሆነች የክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን የሙስሊሙም፣የአይሁዱም፣የቡድሃውም እምነት ተከታዮች ከቅዱስ መጽሃፍቶቻቸው ውስጥ  የሰፈረ ሃቅ መሆኑን የሚመሰክሩት  ነው።የእነዚህ የተለያዩ እምነት ተከታዮች እምነታቸውንም በነጻነት የሚከተሉባት አገር ናት።ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በኩሽ መለወጥ ማለት ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የተቀበሉትን  የእያንዳንዱን እምነት ከጥያቄ ውስጥ ማስገባትና ሁሉንም  ቅዱስ መጽሃፍትን መከለስ ማለት ነው።

ኢትዮጵያ የክርስቲያን አገር ብቻም ሳትሆን የአይሁድ በተለይም  የእስልምና  እምነት ተከታዮች እምነታቸውን ያዳኑባት፣ ያስፋፉባትና ያሰራጩባት ብሎም በነብዩ ሞሃመድ የተመሰከረላት የክርስቲያን አገር በመሆኗ አትዮጵያዊው ሙስሊም የሚኮራባትና የሚጠብቃት አገሩ ናት።ከዚያም አልፎ ተርፎ በመጀመሪያው ሰዓት የነብዩ ሞሃመድ ተከታይ፣ቃል አቀባይና የሶላቱ አብሳሪ የነበረው የቢላል አገር ነች። እስላምና ክርስቲያኑ አገሩ በጠላት ስትወረር  ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይለየው እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ትከሻ ለትከሻ ገጥሞ አብሮ እንደተዋጋውና ህይወቱን በጦር ሜዳ አሳልፎ እንደሰጠው ሁሉ በሰላም ጊዜ ሃይማኖቱ ሳያግደው ተጋብቶ ፣ወልዶ ከብዶ የኖረ ሕዝብ ነው። የክርስትና እምነት ሲጠቃ ፣የእምነቱ መጽሃፍ ሲበረዝ ፣ሙስሊሙ ለምን ብሎ ከሚጠቃው ወገኑ ጎን ይሰለፋል እንጂ አያገባኝም አይልም።።ነገም የራሱ የእምነት መጽሃፉ፣ቅዱስ ቁርአን ስለኢትዮጵያ በሚገልጸው የነብዩ ሙሃመድ የአደራ መልእክት የተነሳ  ሊበረዝበትና ሊከለስበት የማይችልበት ዋስትና የለውም።በዚህ መልክ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተመዘዘው ሳንጃ በራሱም ላይ የተመዘዘ ነው።ኢትዮጵያ ከሌለች ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን እስላሙም፣ይሁዳውም፣ካቶሊኩም፣ፕሮቴስታንቱም፣አማኙም ፣አላማኙም አገረቢስ ይሆናል።ዛሬ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያኑና በእምነቱ ላይ የተመዘዘው የጥፋት አዋጅ ነገ በተራው የሌላው እምነት ተከታይ እጣ ፈንታ ይሆናል።ስልቱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ የሆኑትን ሁሉ በየተራ የማጥፋት ስልት እንደሆነ መረዳት ይገባል።ኦነግ ከፍላጎቱ ውጭ የሆነውን የኦሮሞ ተወላጅ በተለይም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የሆነውን በጠላትነት ፈርጆ እንደሚያጠፋው ጥርጥር የለውም።ኦሮሞ ነው ብሎ አይምረውም።ምናልባት እምነቱን ክዶ ወደ ኦነግ የጥፋት ፖለቲካ ከቀየረ ይተርፍ ይሆናል።ያም መትረፍ ከተባለ ነው።

ከዚሁ ከኦነግ የጥፋት ዘመቻ ጋር የተያያዘው ሌላው በስልጣን ላይ ያለው አገር አጥፊው ቡድን የሚነዛው ዘመቻ ነው።ወያኔም አገር ለማፈራረሱ ዓላማው የመጀመሪያ የክተት አዋጅ ያወጀበት በዚሁ  ኦነግ በተነሳበት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ላይ ነው።ይህ እምነት ፍጹም ኢትዮጵያዊ ፣በኢትዮጵያውያን የእምነት አባቶች  ፍልስፍናና ስርዓት የዳበረ፣ ከሕዝቡ ታሪክ፣ባህልና ስነልቦና ጋር በማይላቀቅ ድርና ማግ የተወሳሰበ በመሆኑ የኢትዮጵያ ደጀን ሆኖ ስለሚቆጠር የጥፋቱ እርምጃ ያተኮረው በእምነቱ ላይ መሆኑን የወያኔ መሪዎች ሳይደብቁ በይፋ ገልጸውታል።ለአገሪቱ አንድነት የጀርባ አጥንት ነው ብለው የሚቆጥሩትንና የሚፈሩትን “የአማራውን ማህበረሰብና የኦርቶዶክሱን እምነት አከርካሪውን ሰብረነዋል” ሲሉ በአደባባይ ተመጻድቀዋል። የሌላ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ አማራም መኖሩን ዘንግተውታል።በአማራው ክርስቲያን ላይ ጦር ሲመዘዝ አማራ የሆነው ሙስሊም ወይም ፕሮቴስታንት ወይም ካቶሊክ በሰላም ይኖራል ማለት አይደለም።ባማራነቱ የጥቃቱ ሰለባ ይሆናል። የዘነጉት ነገር ቢኖር እንወክለዋለን የሚሉት አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ መሆኑን ነው።እሱንስ አክርካሪቱን ሰብረውታል ?ወይስ ሊሰብሩት የቀን ቀጠሮ ይዘውለታል? የትግራይ ተወላጆችስ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታቸው ሲነካ ለምን ዝም አሉ?ዘር ከእምነት ይልቃል ሆኖባቸው ይሆን?

መጽሃፍ ቅዱሱን በመከለስ ስም የተደረገውን ይህንን የነጮችና የተባባሪዎቻቸውን  የጥፋት ዘመቻ ሁላችንም ልንቃወምና ልናወግዝ ይገባል።ይህ የፖለቲካ ድርጅት የፖሊሲ ጥያቄ ሳይሆን፣ የአገርና የሕዝብ ታሪክና ህልውና ጥያቄ ነው።ስለዚህ ለእውነትና ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመ የፖለቲካ ድርጅት ሁሉ ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል።አገር ከሌለች ስለለውጥ የሚናገሩበትና  ለስልጣን የሚታገሉበት ቦታ አይኖርም።

ለአገራቸው አንድነት ለእውነትና ለፍትሕ የቆሙ የሁሉም እምነት ተከታይ፣በተለይም የፕሮቴስታንት ተከታይ የሆነ ሊያወግዘውና ከዚህ አይነቱ መርዛማ ትምህርት እራሱን ሊያርቅ ይገባዋል። ይህ የኦነግ ቄስ ያቀረበው የክህደትና ክለሳ ስራ የፕሮቴስታንት ተከታዮችና በተለይም የኦሮሞ ልጆች ሊኮሩበትና ሊያከብሩት የሚገባ ሳይንሳዊ ግኝት አይደለም፤የአዋቂነት ውጤት ሳይሆን  ስውር የነጮችን  ገመድ በአንገት ላይ ጠምጥሞ መጓዝና እራስን ለባርነት አሳልፎ መስጠት ማለት ነው።ስለሆነም በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ የኦሮሞ ተወላጆች  በስማቸው የሚደረገውን አገርና እምነት የማጥፋት ሙከራ ሊታገሉት ይገባል።

ምንም እንኳን ኩሽ የሚለው ቃል ከእብራይስጥ ቋንቋ የጥቁር ሕዝብን ነገድ የሚያመለክት  ቢሆንም ፣ያ ስያሜ ደግሞ ከሁሉም በፊት በስነልቦና፣በኦሪትና(ብሉይ ኪዳን) በአዲስ ኪዳን እምነት ከፈጣሪ ጋር የቆዬ ግንኙነት የነበረውን አገርና ሕዝብ አመላካች ነው።ለዚያ ደግሞ የስርዓትና የእምነት ባለቤት የሆነችው  የጥቁር አገር ኢትዮጵያ ናት።መጽሃፍ ቅዱስ(ብሉይ ኪዳን) ከሂብሩ ወደ ግሪክ የተተረጎመው  ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3-1ኛው  ምአተ ዓመት(BC)ሲሆን ሴፕቷጊንት(Septuagint) በሚል ሲሰየም የተጻፈውም በኮይን(Koine) በተባለው የግሪክ ቋንቋ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ በተከታታይ በተለያዩ ጊዜያት በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ በተለያዩ ተርጓሚዎች ተርጉሟል።አዲስ ኪዳን በመጀመሪያው ክፍለ-ዘመን ላይ ወደ ግሪክ የተተረጎመ ሲሆን ከዚያ በፊት ብሉይ ኪዳንን  ግሪኮች ሲተረጉሙት ኩሽ የሚለውን የጥቁር የነገድ አጠራርና ስያሜ  ለመግለጽ ኢትዮጵያ (የተቃጠለ ፊት ያለው ሕዝብ)ብለው ተርጉመውታል።ይህ የጥቁር ሕዝብ የሚኖበትም አገር በነገዱ ስም ኢትዮጵያ ተብሎ ለመጠራት በቃ።ይህም ስያሜ ላለፉት ብዙ ዘመናት ጸንቶ ለእኛ ትውልድ ተረፈ።ለወደፊቱ ትውልድ እንዲተርፍ ማድረግ የአሁኑ ትውልድ ድርሻ ነው።ይህንን አጠራር ፈረንጆቹም ተቀብለውት ኖረዋል።አሁን ኩሽ የሚለው ስያሜ ከቀረ ከሁለት ሽህ ዓመት በዃላ ተመልሶ ማምጣቱና መጽሐፍ ቅዱሱን መከለሱ ለእምነቱ ጥራት ታስቦ ሳይሆን በሚጠሏትና ለማፈራረስ በሚፈልጓት አገር ኢትዮጵያ በሚለው ስም ስለተተካ ብቻ ነው።ኩሽ የሚለው ቃል ኢትዮጵያ በሚለው ፈንታ በጀርመን ወይም በእንግሊዞች በሚለው ቢተካ ኖሮ ስህተት ነው ብለው ለማረም አይነሱም ነበር።

የሰሞኑ የካቶሊኮች ውጣ ውረድ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የካቶሊክ ቀሳውስቶች ኢትዮጵያን በማፈራረሱ የተረባረቡትን ወያኔንና ሻእብያን ለማስታረቅ ከላይ እታች እያሉ ነው።በወያኔ ጥያቄ፣በቫቲካን ትዕዛዝ የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ማህበር የተባለው ድርጅት በሰላምና እርቅ ሰበብ በመካከላቸው ያለውን የጥቅም ቅራኔ አሶግደው ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉበት፣ በአንድ ግንባር እንዲሰለፉ ለማድረግ በአሜሪካና እንግሊዞች የተደገፈውን  ስልት ተግባራዊ ለማድረግ የሚስማሙበትን የእርቅ ሃሳብ ይዘው አሥመራና መቀሌ ገባ ወጣ በማለት ላይ ናቸው። እነዚህ ጳጳሳት ላለፉት ዓመታት ሁለቱም አምባገነንና ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች በሚቆጣጠሩት መሬት የሚኖሩ በሽህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ደም ሲፈስ፣በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሲፈናቀሉና ሲሰደዱ፣በሽዎች የሚቆጠሩ በየእስር ቤቱ ሲሰቃዩና ሰብአዊ መብታቸው ሲደፈር፣ በአምላክ ምስል የተፈጠረው የሰው ልጅ በነዚሁ ጸረ ሃይማኖት በሆኑት ቡድኖች  ለመከራ ሲጋለጥ ምንም ያልተሰማቸውና ለምን ይሆናል ብለው ያልጠየቁ የካቶሊክ ቀሳውስት ክብደት የሰጡትና የተጨነቁበት ጉዳይ ቢኖር የሁለቱ አምባ ገነን ቡድኖች መራራቅ ነው። ብዙ አትዮጵያውያን ደማቸውን ያፈሰሱበትና መስዋእት የሆኑበት የባድሜ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ያደረጉት የሰላም ጥረት አልነበረም።ይባስ ብለው የግጭቱ ሽፋን የሆነውን የባድሜን መሬት ለሻእብያ የእርቁ ገጸ-በረከት እንዲሆን ቀሳውስቱ ያቀረቡት አንዱ ሃሳብ መሆኑ ይፋ ሆኗል።አሁን ለዚህ እሩጫ ያነሳሳቸው ነገር በሁለቱም አምባ ገነኖች ላይ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከቀጠለ ሁለቱ የነጮቹ ተወካይ ቡድኖች ከስልጣናቸው ሊወገዱ ስለሚችሉና በሕዝቡ መካከል የተከሉት  የጥላቻና የልዩነት ግምብ ተደርምሶ ሕዝቡ የተቀማውን አንድነት አስመልሶ ኢትዮጵያ ሳትፈራርስ በአዲስ ስርዓት ፈረንጆቹ እንደልባቸው የማይፈነጩባት ጠንካራ አገር ሆና ትቀጥላለች፤ሌላውም የአፍሪካ አገር እንደ ቀድሞው የሷን ፈለግ ይከተላል የሚለው ስጋት ነው።

በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ስርዓት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቀውስ ውስጥ ተነክሮ ይገኛል። መሪዎቹ ቡድን ለይተው እርስ በራሳቸው እየተወነጃጀሉ የስልጣን ሽኩቻ ገጥመዋል።በዚህ ሽኩቻ አንዱ የበላይ ቢሆን ሌላው እንደማይተኛና ሁሉም የስርዓቱ ወንጀለኞች በመሆናቸው ንጹህ ሆኖ የሚተርፍ እንደማይኖር የታወቀ ነው።የቅደም ተከተል ጉዳይ እንደሆነ የሚያመላክቱ ፍንጮች እየታዩ ነው። ድርጅቱ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ የነበሩና እስከ አሁን ድረስ በድርጅቱ ውስጥ ያሉት ሁሉም  በሙስና የተጨማለቁ፣የግድያ ወንጀል የፈጸሙ፣በሕዝብ ላይ እልቂት (ጀኖሳይድ)ያከናወኑ፣የአገር ዳር ድንበር አሳልፈው የሰጡ፣ብሔራዊ ክህደት የፈጸሙ ናቸው።በየጊዜው መናቆራቸው በስልጣን ውጣ ውረድ ምክንያት እንጂ በዓላማ ልዩነት አይደለም።  ከውስጣቸው ደፍሮ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል አይገኝም።ለዚህ ቀውስ የዳረጋቸው የሕዝቡ አልገዛም ባይነት ነው።የሕዝቡ ጥያቄ እከሌ ወርዶ እከሌ ይሾም አይደለም፤የእነሱ መስማማት ወይም  መጣላት የሕዝቡን ጥያቄ አይመልስም።የሚፈልገው  ለውጥ እስካልመጣ ድረስ የሕዝቡ ትግል ይቀጥላል።

የነጮቹ መንግሥታት በሚፈልጉት መንገድ የወያኔ ስርዓት ማንሰራራት ካቃተው ሌላ አማራጭ መፍጠራቸው አይቀርም።ወያኔ ጠፍጥፎ በተቃዋሚ ስም በግምጃ ቤቱ ካስቀመጣቸው ውስጥ አንዳንዶቹን ወደ መድረኩ እንዲወጡ በማድረግ፣ከውጭም በተቃዋሚ ስም የነጮቹን ጥቅም የሚያስጠብቁ “ነጭ አምላኩ” የሆኑትን ቡድኖችና ምሁራን በማካተት የፓርላማ ወንበር እንዲያገኙ በማድረግ በስም የተለዬ  መንግስት ለመመስረት ይፈልጉ ይሆናል።ለዚያም ከአንዳንዶቹ የድርጅት መሪዎች ጋር በድብቅ ውይይት ማካሄዳቸው ታውቋል።ያ ከሆነ ደግሞ በአዲስ ጉልበት አገራችን ስትታሽ ትኖራለች ማለት ነው።      ይህም ካልሰራላቸው ትግራይንና ኤርትራን በማቀላቀል ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ቀድሞ ያሰቡት የትግራይ ትግርኛ መንግሥት ማቋቋም ይሆናል። የሚፈልጉትም ሌላው በየፊናው ተበታትኖ በደካማ አቅሙ ሊቋቋም የማይችለው የእጅዙር አገዛዝ መረብ ውስጥ እንዲወድቅ ስለሆነ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ እንደሚያደርጉ ማሰቡና መዘጋጀቱ ብልህነት ነው።

ከዚህ ሁሉ ቀውስ ለመውጣት ያለው ብቸኛ አማራጭ አገር ወዳድ የሆነው ሃይል በየጎሳው መሰለፉን ትቶ፣ የፖለቲካ መስመር ልዩነቱን ወደ ጎን አስቀምጦ አገር በማዳኑ ላይ ሃይሉን በማስተባበር መታገል ብቻ ነው።የየጎሳው እኩልነት የሚረጋገጠውና  የፖለቲካ ጥያቄው መልስ የሚያገኘው በራሱና በሕዝቡ ብቻ የሚተማመን በፍልስፍና እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ መርሃ ግብር ያለው፣በሁለመናው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድም የፖለቲካ ድርጅት በሕዝቡ ምርጫ ስልጣኑን ሲረከብ ብቻ ነው።ለዚያ ደግሞ አንድ ብቻ ሳይሆን ከሶስት ያልበለጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የምርጫ ምህዳሩን ያሰፋዋል።እነዚህ ፓርቲዎች በመስመር ቢለያዩም በአገር ጥቅምና አንድነት ላይ ግን በአንድነት የሚቆሙ መሆን ይኖርባቸዋል። በውጭ አገር በርቀት ሳይሆን በአገር ውስጥ ሆነው  የተበታተኑትን ሕዝባዊ ትግሎች ማያያዝና መምራት ይጠበቅባቸዋል።የፖለቲካ ድርጅቶቹም ሆኑ ለውጥ ናፋቂው ኢትዮጵያዊ  አደገኛውን የጎሳ ፖለቲካ መዋጋት ለስርዓት ለውጡ መሰረት መሆኑን ተረድተው የሚገባውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አሁን በቡድን ተከፋፍሎ በተበታተነ የጭፍራ መልኩ የሚደረገው ትግል ለውድቀት እንጂ ለድል እንደማያበቃ ሊገነዘቡት ይገባል።

ኢትዮጵያን ከተከፈተባት ዘርፈ ብዙ ጥቃት እንከላከል!

አገሬ አዲስ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *