ወደ ነፈሰበት ነፋሽ የፖለቲከኞች..

ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው ብላችሁ ራሳችሁን ስትጠይቁ በእኛ ሀገር ፖለቲካ ማለት ስልጣን እንጂ ለህዝብ ማሰብንም ሆነ ስለህዝብ መታገልን አያካትትም፡፡ ለህዝብ የሚያስቡት ጥቂቶቹ እስር ቤት ገብተዋል፡፡ ገሚሶቹ በግሩፕ አድማ ተደርጎባቸው ተደብቀውና ተገልለው ነው ያሉት፡፡ ተቀናጅተው እነሱን ካልመሰሉ..ከእነሱ ሀሳብ ካፈነገጡ በእነሱ ቦይ ካልፈሰሱ እንዲገለሉ በሚያደርጉት፣ በሚያሳድሙ የፖለቲካ ማፍያዎች ታፍነው ነው ያሉት፡፡

ይሁን ብለው ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ብለው ጊዜ እስኪፈታላቸው በዝምታ ዝም ብለዋል፡፡ ዶ/ር ታዬ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ድምጻዊት አቦነሽ አድነው፣ ዶክተር ማሪቱ ለገሰ (ነፍሱን ይማር አሰፋ ጨቦ) ..ከብዙ ጥቂቶቸ በፖለቲካ ቲፎዘኞች የተገለሉ ናቸው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ጋንጊስተሮች ለህዝብ ነው የምናስበው ብለው ደጋፊ አሰባስበው ወደ ነፈሰበት የሚያነፍሱ አፈ ቃላጤነታቸውን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ወንበር እንጂ ለህዝብ የማያስቡ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ለህዝብ የሚሰሩትን ጠላት አድርገው እስር የከተቱም አሉ፡፡

ተቃዋሚ ነኝ ያለ ኢትዮጵያን እወዳለሁ፣ ህዝቡን ከወያኔ ጎጠኛ ስርዓት ነጻ አወጣለሁ የሚል ኢትዮጵያዊነትን ያነገበ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ በብሔርም፣ በጎሳ፣ በጎጥም.. የተዋቀረው ተቃዋሚውም ሆነ የወያኔ ተለጣፊው የህዝቡ ቁስል ካላመማቸው አላማቸው ወንበር እንጂ ነጻነት አይደለም፡፡ የነጻነት ታጋይ ነኝ የሚል የህዝቡ ቁስለት ካላቆሰለው ለማን ነው የሚታገለው? ለማነው ነጻነቱ? ስደተኛው በየቦታው የማንም መጫወቻ ሲሆን አንድ ቀን ለኢትዮጵያዊያን ድምጽ አሰምቻለሁ የሚል የፖለቲካ ፓርቲ የታለን?

ወያኔና ግብረአበሮቹ ሆኑ ተቃዋሚ ነን ባዬች በኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በድኖች ናቸው፡፡ በድን ሙቶች፡፡ የፖለቲካ ማራገቢያ ከሆነ ግን አንዱ ኡኡኡኡኡ ሲሊ በስሜታዊነትም በአጋፋሪነትም ተከትለናቸው እንጮሀለን፡፡ መጮህ ይሄ ነው የፖለቲካ ትርፋቸው፡፡ ትርፋችን..

Related stories   የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

አውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ነበርን ሲሉ እንሰማለን፡፡ ለህዝቡ ምንም ላይፈይዱ ከሆነ የህዝቡን በስደት መንገላታት በየቦታው መደፋት አስረድተው አንድ ነገር ጠብ ካላረጉ ወንበር አሙቀው ተመለሱ እንጂ ምን ፈየዱ? በፓርላማ አባላት የሚስቁ ቁጭ ብለው አጨብጭበው ወጡ ብለው የሚሳለቁ እነሱ በየስብሰባው አድማቂ ሆነው አጨብጭበው ሲወጡ እንጂ ምን ጠብ ሲያደርጉ ታዩ? ‹‹አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀንበር ጥልቅ..›› የሚያስተርቱ ናቸው፡፡

የመን ያን ሁሉ ስቃይ ሲታይ አረ ተዉ ወገን ነው ያለ አንድ የለም፡፡ ድረሱልን ድምጽ ሁኑን ብንል አንድም የሰማን የለም፡፡ አውሮፓ ህብረት ላይ..የአሜሪካ ኮንግረስ..የሰብዓዊ መብቶች ስብሰባ ላይ ተገኘን ብላችሁ አንድ ቀን ስለ ወገን አንስታችሁ ታውቃላችሁ? አሁን በሊቢያ ጉዳይም እንዲሁ ዲዳ ሆናችሁ ማየት ያሳፍራል፡፡

የመገናኛ ብዙሀኖቹም እንዲሁ ድኩም ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ወደሚነፍሱበት ሀሳብ ካልነፈስክ ድምጽ አይሆኑህም፡፡ በአንድ ወቅት ስድስት ኢትዮጵያዊያን የመን ውስጥ በአይ ኤስ አይ ኤስ(ደዓሽ) ሲታረዱ አለም ሲያስተጋባ ሲያወግዝ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ዘገባዎችን ጭምር አድርገን ብንልክላቸው አላማቸው አይደለም እና በዝምታ አለፉት፡፡ ይሄ ነው ወገናዊነት እንግዲህ

….ይሄኔ አውሮፓ ቢሆን ይሄኔ አሜሪካና አውስትራሊያ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቢሆን የታረዱት ጩኸታቸው መከራ…የገደል ማሚቱዎችም ማስተጋባታቸው ለጉድ ነበረ፡፡ እዛ ዶላር አለ መዋጮ የሚያዋጡ ናቸው፡፡ ነገ ድጋፍ ተብለው ኪሳቸው ይታያል፡፡ የመን እና ሱዳን ብሎም ሊቢያ የሚሄድ ሚስኪን ኢትዮጵያዊ ምን ጠብ ሊለው ይጮህለታል? ካለፈው ተሞክሮ አይተውታል ምንም አያዋጣም የሊቢያው ችግር….የሚያስገኘው ነገር የለም፡፡

ወያኔም ቢሆን የሚያገኘውን ገንዘብ እንጂ ዜጋ አስቦ አያውቅም፡፡ ለማንም ግድ የሌለውና ተዉ ወገኔን አትንኩ የማይለው ገቢውን በዚህም በዛም ስለማያጣው ነው፡፡ ፍላጎቱ ገንዘብ እንጂ ዜጋ አይደለም፡፡ የመንም ሆነ ሱዳን ኤምባሲ ብቅ ሲባል የቦንድ የግድ…በግድ የልማት ማህበር…ኪስ እንደመበርበር…እያለ የዜጋውን ኪስ ያጥባል፡፡

ወያኔ ለዜጋው ቢጮህም ባይጮህም ገቢ ነው ፍላጎቱ። በአረብ ሀገራት ይህ ሁሉ ስቃይ እያለ ኡኡኡኡአ ድረሱልን እየተባለ ዳግም የሚሸጥበትን..ዳግም ዘመናዊ ባርነት የሚያስፋፋበትን ያስባል፡፡ የኤጀንሲ ህግ ይላል፡፡ ገንዘብ ይገኝ እንጂ…

በሊቢያ ያሉ አረመኔ የባሪያ ፍንገላ አራማጆች ምናችን ናቸው? ወገናችን አይደሉም፡፡ ወገናችን ያልናቸው የራሳችን መንግስት ለአረብ ሀገራት ከሸጠን በኋላ ተረግጣችሁ፣ ተወግራችሁ፣ ሲፈልጉ እየገደሏችሁ ኑሩ ብሎ እህቶቻችንን እየሸጠ አይደል? በዘመናዊ የባሪያ ንግድ ላይ የተሳተፈ ስለሆነ እንዴት የባሪያ ንግድን ይቃወም?

የሌሎቹ ሀገር ዜጎቻቸውን ለማትረፍ ጥረት ያደርጋሉ።…የእኛዎቹ ግን አንዴ ኩዌት አንዴ ሳዑዲ እያሉ የአሰሪና ሰራተኛ ውል ስምምነት ቅብርጥሴ ይላሉ። ለዘመናዊ ባርነት የሚሸጧቸውን ሊያመቻቹ፡፡

ስጋ መሀል ልፋጭነት ወገን መሀል በአድነት ቢሰማህ አትዘን። ወገኔ ስልጣን ላይ ያለውም ሆነ ከስልጣኑ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉት ወንበር ናፋቂዎች እንጂ ነጻነት አሳቢዎች አይደሉም፡፡ ነጻነት ናፋቂ ቢሆኑ ለማነው ያ ነጻነት? ለህዝብ? ዛሬ ሲያልቅ እለቅ ብለህ ዝም ላልከው ዛሬ የማንም መጫወቻ ሲሆን ዝም ላልከው ህዝብ ነው ነጻነት? ሀገር እያለን ሀገር እንደሌለን በስደት ተንከራታች ሆነናል፡፡ወገንህ ስትጮህ ባንተ ጩኸት ዳንኪራ የሚመታ ከሆነ ወገን አልባነት ቢሰማህ ምን ይደንቃል? በሊቢያ ያሉ ወገኖች በዚህ ሰዓት ምን ሊሰማቸው እንደሚችል እናስብ እስኪ…..

ነጻነት..ነጻነት…ዲሞክራሲ የከፍታ ዘመን ብላችሁ ጩኸታችንን የማትሰሙ በእንባችን የኪሳችሁን ችግኝ የምታለመልሙ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሊቢያ ያለውን ዜጋ ካላሰባችሁት አታሞዋችሁ ቅኝቱ የተዛባ መሰረቱ የተናጋ አፍ ላይ የከተመ አይሆንምን? አንድም ለመብላት አንድም ለማውራት….ተቃዋሚ ለህዝቡ ነጻነት የሚታገል የለም እንጂ ቢኖር ህዝብ ከሚባሉት ጥቂቶቹ ሊቢያ ያሉት ዜጎች ናቸው እና ድምጽ ያስሙ ነበር፡፡

ወይኔ መንግስት ማጣት ወይኔ ለህዝብ ነጻነት የሚታገል ማጣት….ምስኪን የትም ወደቆ ቀሪ ህዝብ…

ለወንበር እንጂ የህዝብ ፍቅር የሌላቸው ፖለቲከኞች…ስለሊቢያ……

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?

በግሩም ተ/ሀይማኖት

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *