ስነልቦናን መጠበቅ ጤናማ ስሜትን እና አስተሳሰብን የማዳበር ልማድ ማለት ነው፡፡ ይህም በጎ እና አወንታዊ አመለካከትን፣ አስተሳሰብን፣ ስሜትን እና ድርጊትን የሚያካትት ሲሆን ዋነኛ አላማውም የስነ-ልቦና ቀውስንና የአእምሮ ጤና መታዎክን መከላከል ነው ለዛሬም ለቅዳሚታችን ከአንድ ስለስነ ልቦና ከተፃፈ ፁሀፍ ቀንጨብ አድርገን እንመልከት ፦

ሰዎች በራሳቸው እስር ቤት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርገው ትልቁ አጥር ደግሞ ፍርሃት፣ ፀፀት፣ ጥርጣሬ፣ አለማመን፣ አለመተማመን፣ ተስፋ ቢስ መሆን ነው፡፡ ሌላዉ ችግር፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን የተሸከምናቸውን ዝባዝንኬዎች እንኳ መመልከት እና መጣል አለመቻላችን ነው፡፡ ይህም ማለት ያለንን ሃብት(የአስተሳሰብና ችግር የመፍታት) አቅማችንን መጠቀም አንችልም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ሀሳብ ማሳያ አንድ ታሪክ እንመልከት፦

አንድ ግራ የተጋባ ሰው ማለቂያ የሌለው በሚመስል ጎዳና ላይ እየተጎተት ይጓዝ ነበር፡፡ይህ ሰው ሊደፋው የደረሰ የሚመሰል የሸክም ዓይነት ተሸክሟል፡፡ ጆንያ ሙሉ አሸዋ በጀርባው አዝሏል፤በዉሃ የተሞላ ወፍራም የዉሃ ፕላስቲክም በሰውነቱ ላይ ጠምጥሟል፤ በቀኝ እጁ ቅርፅ አልባ ድንጋይ ይዟል፤ በግራው ደግሞ ትልቅ ሸክላ አንጠልጥሏ፤በአንገቱ ዙሪያ አሮጌና የተበጣጠሰ ገመድ ጠምጥሟል፤ በእግሮቹ ላይ ደግሞ የዛጉ ሰንሰለቶችን አደግድጎ ቁርጭምጭሚቱ እስከሚደማ በአቧራማ እና አሻዋማ መንገድ ላይ ይኸን ሁሉ ኮተት ተሸክሞ ይጎተታል፤በራሱ ላይ ደግሞ ያልበሰለ ዱባ ተሸክሞ እንዳይወድቅበት ፈርቶ መከራውን ያያል፡፡

አንድ እርምጃ በተራመደ ቁጥር ሰንሰለቱ ጩኸቱ ብቻ ይሰቀጥጣል፡፡እያማረረ እና እያላዘነ የአርባ ቀን እድሉንም እየረገመ በዝግታ ወደፊት ይራመዳል፡፡ አንድ በአጠገቡ የሚያልፍ ሰው አንተ ሰው እንደዚህ ደክሞህ ይህን የሚያክል ሸክላ እጅህ እስከሚገነጠል ማንጠልጠልህ ለምን ይሆን? ብሎ ጠየቀው፡፡ ዉሉ የጠጠፋበትና ግራ የተጋባው ሰው ምን የማልረባ ደደብ ነኝ እሰከ አሁን አላየሁትም ነበር ብሎ መለሰ፡፡ እሱንም ሲወረውር ትንሽ ቀለል አለው፡፡ እንደ ገናም በመንገዱ ላይ ብዙ ርቀት ከተጓዘ በኋላ አንድ ገበሬ አገኘውና አንተ ሰው በደንብ ያልበሰለ ዱባ ተሸክመህ መቸገርህ ለምን ይሆን? እነዚህን ከባባድ እና ወደኋላ የሚጎትቱህን ብረቶችስ መሸከምህ ለምን ? ብሎ ጠየቀው፡፡ 
ዉሉ የተጠፋበትም ሰው ስለጠቆምከኝ አመሰግናለሁ፡፡ እስካአሁን አላስተዋልሁትም ነበር ብሎ ሰንሰለቱንም አወለቀ ያልበሰለዉንም ዱባ ወረወረ፡፡ የበለጠም ቀለል አለው፡፡ ነገር ግን በተጓዘ ቁጥር ህመሙና ስቃዩ በዛበት፡፡ ሌላ ገበሬ ከማሳው ብቅ ሲልም ሰዉየውን በአግራሞት ተመለከተው፡፡ 
አንተ ሰው ጆንያ ሙሉ አሸዋ ተሸክመሃልሳ? መንገድህ በሙሉ ተዝቆ የማያልቅ አሸዋ አይደለም እንዴ?የምትሄድበት መንገድ አሸዋ ሙሉ እንደሆነ አይታይህም? ትልቁ የዉሃ ጎማህም ልክ የሰሃራ በረሃን የምታቋርጥ ነው እኮ ያስመሰለህ፡፡ በመንገዱ ዳር ኩልል ብሎ የሚፈሰውን የምንጭ ውሃ አልተመለከትከውምን? ሰዉየዉም ይህን ሲሰማ ካላቅሙ የተሸከመውን የውሃ ላስቲክ መሬት ላይ ዘረገፈው፡፡ ወደዚያው ቆም ብሎ በመጥለቅ ላይ ያለችውን ፀሃይ ይመለከት ጀመር፡፡ በምትጠልቀው ፀሐይ ብርሃን ውስጥ ራሱን መመልከት ጀመረ፡፡ ከባዱን ድንጋይ አሁንም ተሸክሞታል፤አላራምድ እንዳለውም ገባው፡፡ ወረወረዉም፡፡ ከድክሙ ሁሉ ተገላገለ፡፡ በነፋሻማው ምሽትም በነፃነት ማደሪያ ፍለጋ ጉዞዉን ቀጠለ፡፡

በመጨረሻም ልክ እንደዚህ ሰው የማይጠቅሙንንና ወደኋላ የሚጎትቱንን የስሜት እና የአስተሳሰብ ጓዞች ለመጣል ድፍረት ይኑረን፡፡አቅማችንንም እንጠቀም፡፡በትክክል የማይጠቅሙን መሆነቸውንም እንመልከት፡፡ በእርግግጥ የማይጠቅሙን ከሆኑ ጨክነን ለመጣል እንመን፡፡ ያን ጊዜ ጨለማው ብርሃን ይሆናል፡፡ግራ የሆነብንም ቀኝ ይሆናል፡፡ ርምጃችንም ፈጣን ይሆናል፡፡

ቸር ይግጠመን  Fikr Kiya መልካም ቅዳ–ሜ #jonitsegaye

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *