ያለንበት ዘመን ሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረበትና የዓለም ህዝቦች እየተቀራረቡ የመጡበት ዓለም አንድ መንደር የሆነችበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅትም የህዝብ ግንኙነት ሚና የጐላ መሆን እንዳለበት ዕሙን ነው፡፡

በርካታ ሰዎች ለህዝብ ግንኙነት ወጥ ትርጉም ሲሰጡት አይታይም በሚል በመስኩ እጃቸውን ያስገቡ ምሁራን በድርሳናቸው ሲያወሱ ተመልክቻለሁ፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ዘርፉ ወጥ ትርጉም የጠፋበት ብቻ ሳይሆን በአገራችን ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠው የሙያ ዘርፍ መሆኑን በድፍረት እናገራለሁ፡፡

ሙያው ወጥ የሆነ ትርጉም የማይሰጥበት ምክንያት የሰዎችን ሐሣብ አንድ ማድረግ ከባድ ስለሚሆን ነው ቢባልም በአንፃራዊነት ስመለከተው ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር የሚለዋወጥ በመሆኑ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል አጭርና ግልጽ ትርጉም መስጠት ባለመቻሉ እንደሆነ  ብገነዘብም ይህን ልዩነት ለማጥበብና ወደ አንድ ሐሳብ ለማምጣት በማሰብ እንግሊዝ ውስጥ የሚገኘው የህዝብ ግንኙነት ተቋም (Institution of public relations) እ.ኤ.አ በ1948 ህዝብ ግንኙነትን እንደሚከተለው ተርጉሞታል፡፡ “የህዝብ ግንኙነት ማለት በአንድ ተቋምና (organization) በተጠቃሚው ህዝብ መካከል የጋራ መግባባት እንዲኖር ታስቦበት በዕቅድ የሚመራና ቀጣይነት ያለው አቅም በመገንባት ጠንካራ ግንኙነት የሚፈጥር ሙያ ነው።” በማለት አስፍሯል፡፡

የህዝብ ግንኙነት ከላይ ከተሰጠው ትርጉም እንደምናየው በአንድ አገልግሎት ሰጭ ተቋም ወይም ድርጅትና በማህበረሰቡ መካከል ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር ውጤታማነትን ለማግኘት የሚያስችል ሙያ መሆኑን ነው፡፡ የህዝብ ግንኙነት  የማህበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ህይወት አስፈላጊ  የሆነና  በአንድ ሃሣብ፣ ምርት፣ የፖለቲካ ድርጅት… ወዘተ. ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን የሚተነትን፣ የሚያዳብርና የሚፈጽም የሥራ አመራር አካል ነው፡፡

የህዝብ ግንኙነት ሙያ በተቋማትና በተገልጋዩች መካከል የሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር በመንግስት በፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ተግባራት ላይ መግባባትና የሚፈጥርና የአገር ገጽታ የሚገነባ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው፡፡

ይህን ያህል ስለ ሕዝብ ግንኙነት ሙያ ሀሳቤን ካካፈልኳችሁ ወደ ተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ላምራ፡፡ የኛ አገር ሕዝብ ግንኙነት ሙያ ከአሽከርነት ብዙም የዘለለ አይደለም፡፡ በመስኩ የተጻፉ መጽሀፍት የሚሉት ሌላ መንግስት የሚለው ሌላ እንደሆነ የሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ዛሬ ነጋ ጠባ በአገሪቱ ባሉ ከተሞች የሚነሱት ተቃውሞዎች፣ የርስ በርስ አለመግባባቶች፣ ግጭቶች፣ …. መነሻቸው ሌላም አይደለም፡፡ በመንግስትና በሕዝቡ መካከል የተደራጀና የተጠናቀረ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ካለመስራት የመጣ ቀውስ ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ያም ብቻ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ባሉ ክልሎች የተፈበረኩ ሚዲያዎች፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤቶችና በመንግስት ተቋማት የተደራጁ የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሮችም በተቋቋሙበት ልክ የህዝብ ግንኙነት ሥራ ከመስራት ይልቅ በገዥው መንግስት የሚራመዱ ሐሳቦችን ብቻ አንጠልጥለው በማራገባቸው ይህን ያህል ዘመን መንግስትና ሕዝብ ሳይገናኝ ቆይቷል፡፡ የግንኙነት አድማሱ በመስፋቱ መሪና ተመሪው ባለመተዋወቁ የየራሳቸውን ጎዳና ተያይዘውታል፡፡ ይህ ለብቻ ጉዞ የት እንደሚያደርስ የሚጠፋን አይመስለኝም፡፡ በየዕለቱ ከአራቱ ማዕዘናት የሚደመጡ ወሬዎች ልብ ይሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ የመንግስት ጋዜጠኞችን፣ በየጽ/ቤቱ ያሉትን ኮሚኒኬተሮችንና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ሰላይ፣ ደህንነት፣ ተላላኪ፣ ወሬ አቀባይ፣… የሚል ታርጋ እንዲለጠፍባቸው ተገዷል፡፡

ለዚህ ማሳያ በአማራ ክልል የተዋቀረው የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩን ብቻ ማንሳት በቂ ይመስለኛል፡፡ የክልሉ መንግስት ሆነ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚዲያውንም ሆነ የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት መዋቅሩን በበላይነት ቢመራውም የህዝብ ግንኙነት መዋቅሩ በሴክተሩ አመራር፣ በባለሙያውና በህዝቡ ውስጥ እንዲመጣ የሚጠበቀው የአስተሳሰብ ለውጥ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እየተከታተለ ውጤት ማምጣት የሚችልበትን አቅጣጫ በማስቀመጥና የህዝብን አስተሳሰብ የመለወጡን ሥራ በባለቤትነት ይዞ በመንቀሳቀስ በኩል ጋት ያህል አልተቀሳቀሰም፡፡

ያልተግባባና ያልተደራጀ ህዝብ ምንም ያህል የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጥ ለማምጣት ፍላጐቱና ተነሳሽነቱ ቢኖረውም በሕዝብ ግንኙነት ሥራ ካልተሟሸ በተግባር የሚመጣው ውጤት መግባባትንም ሆነ ገጽታን አይገነባም፡፡ ይህ እየታወቀ የዘርፉን መዋቅር በተሻለ ባለሙያ ማደራጀትና የህዝብ ግንኙነት ተግባሩ በሚፈለገው መጠንና ጥራት እንዲከናወን ማመቻቸት ሲገባ በክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አቅራቢነት ክልሉን በበላይነት በሚመራው ድርጅት በብአዴን አጽዳቂነት ማንም መንገደኛ አልፎ ሂያጅ ከጎዳና እየተጎተተ ከሲቨል ሰርቪስ መመሪያ ውጭ በሹመት የሚገባበት የሙያ ዘርፍ ሆኗል፡፡

በዚህ የተነሳ የክልሉ መንግስት በክልሉ ባሉ ከተሞች ሰርክ ኩሽ ባለ ቁጥር፣ ሕዝቡ ብሶቱን ሲያሰማ፣ አደባባይ ወጥቶ ሐሳቡን ሲገልጽ፣… ተገቢውን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ባለመስራታችን ነው የሚለውን አባዜ ለመግታት ይመስላል ሰሞኑን በየተቋማቱ ያሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተቋማቱ ኃላፊዎቻቸው በድብቅ የሚገመገሙበት አቅጣጫ ቀይሷል፡፡

መቅደም የሚገባው ጉዳይ ይህ አይደለም ባይ ነኝ፡፡  የክልሉ የህዝብ ግንኙነት መዋቅር በእያንዳንዱ ተቋም ወይም መ/ቤት ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ያደረገ መዋቅር በመዘርጋት በየደረጃው ያለውን ህብረተሰብ በአግባቡ አደራጅቶ በማንቀሳቀስ የአካባቢውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ሀሳቦችን ማመንጨትና ማስረጽ የሚችል የተሟላ የሕዝብ ግንኙነት ሙያና ስዕብና የተላበሰ ባለሙያ መመደብ ሲገባ ገና ለገና የፖለቲካ ቀረቤታና ትርፉ እየተለካ ዜና አዳምጦ የማያውቀውን ማንንም ግፋፎ በዚህ መስክ ማሰማራትና በድብቅ ገምግሞ በክልሉ የጋራ መግባባትና መልካም ገጽታ እገነባለሁ ብሎ ማሰብ ሌላ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ይጠይቃል፡፡

ከዚህ አንጻር የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት መዋቅር ስቃኝ በሌሎች የሥራ መደቦች ምደባ ያጡ ባለሙያዎችና ለድርጅቱ አፋሽ አጎንባሽ ግለሰቦች የሚናኙበት በመሆኑ መንግስትም ከሕዝብ  ሕዝብም ከመንግስት ጋር ሳይተዋወቁ እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል፡፡

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትም የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩን ከማስተካከል ይልቅ ሁሉን ልፍጀው በሚል ህሳቤ ከእውነታ ያፈነገጠ የሕዝብ አመኔታ የጎደላቸው ዘገባና መረጃ በማስተላለፍ ተጠምዷል፡፡ በዚህ የተነሳ ገሚሱ የመንግስት ተቋማት ያለ ሕዝብ ግንኙነት ሲመራ የተወሰኑት መ/ቤቶች ደግሞ በመስኩ እዚህ ግባ የሚባል ክህሎት በሌላቸው ግለሰቦች በመመራቱ ከመግባባት ይልቅ መራራቅ፣ ገጽታ ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ በመሆኑ የአመለካከት አንድነት ዳብዛው ጠፍቷል፡፡  ስለዚህ የክልሉ መንግስት መዋቅሩን የሚመሩት ኃላፊዎች በሚስጢር ከመገምገም ይልቅ ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ጀምሮ ያለውን የሕዝብ ግንኙነት መዋቅር ፈትሾ ማስተካከል ይገባዋል፡፡ የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀት ሲባል ደግሞ ተግባራትን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በቂ የሙያው ክህሎት ያለው የሰው ኃይልና የበጀት አጠቃቀም ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት እላለሁ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *