ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

አዲግራት ዩኒቨርስቲ – ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻችን እንሂድ አሉ!! አማራ ክልል ሙሉ መረጃ አልሰጠም

ዛጎል ዜና -በርካቶች አዝነዋል። አልቀስዋል። አገር የሚገነቡ የተማሩ ትውልዶች በብሄር ተቧድነው በአንድነት የትምህርት ገበታቸው ላይ መቀመጥ የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ። ይህ ነው የመለስ ሌጋሲ፣ ይህ ነው ግብር የሚገባለት የመለስ ውርስ። ይህንን ውርስ ያራገፈብንን ሰው ” ታላቁ፣ አስተዋዩ መሪ” የሚባለው። የአገሪቱ የጎሳ ፖለቲካና ጎሳ ላይ የተቸከለ “ፌደራሊዝም” ዛሬም ድረስ ጥፋቱ የማይታየው በጉዳዩ ለሚጠቀሙት ብቻ ነውና ሁሉም ወገኖች ልብ ሊገዙ ይገባል። በማስተዋል መራመደም አስፈላጊ ነው… ሲሉ ገለልተኛ ወገኖች የፍርሃት አስተያየት ይሰጣሉ።

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው ችግር መልኩን ኢህአዴግ እንዳስቀመጠው የጎሳ ፖለቲካ ካመሳሰለ ቆይቷል። ይህንን ተከትሎ ከትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሌላ ክልል ለትምህርት የሚሄዱ ዜጎች ዋስትና አልባ ሆነዋል። ቤተሰብም ጭንቀት ውስጥ ነው።
በትግራይ ዩኒቨርስቲ ትምህርቷን የምትከታተል የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ለዛጎል እንዳለችው ” ሁሉም ነገር ልክ አይደለም። የከፋ ችግር ከፊት ለፊት ይታየኛል” ሌላዋ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ” ካልሆነ በህግ ደረጃ ሁሉም በየአካባቢው እንዲማር ሊደነገግ ይገባል” ትላለች።
ከአዲግራት ያነጋገርነው ሌላ ተማሪ እንደሚለው ከሆነ ” ችግሩ አሁን የተፈጠረ አይደለም። የቆየ የፖለቲካው ጣጣና ፖለቲካውን ተከትሎ የተጠራቀመው ቂም ውጤት ነው። አሁን ከበርካታ ውትወታና ማግባባት በሁዋላ አንጻራዊ መረጋጋት ቢኖርም፣ ነገ ለሚሆነው ዋስትና የለም” ሲል ስጋቱን ይገልጻል።
ይህ ወጣት እንደሚለው ነገ በሌሎች ክልሎች፣ በተለይም አማራና ኦሮሚያ ክልል አንድ የትግራይ ተወላጅ ላይ ችግር ቡደርስ ነገሮች ሙሉ በሙሉ መልካቸውን እንደሚቀየሩ ነው። ስለመፍትሄ ለተጠየቀው ” ሁሉም ተማሪ ማለት ይቻላል አሁን ክልሉን መልቀቅ ይፈልጋል። ስለዚህ ክልሎች ይህንን ጉዳይ ተነጋገረው መፍትሄ ቢፈልጉለት የተሻለ ይሆናል” ሲል ለጊዜው ነገሮች እስኪላሉ በአስቸኳይ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ይጠይቃል።
በትምህርት ጥራት ቁልቁል የበረረው የአገሪቱ ዩኒቨርስቲ ዛሬ በጎሳ ላይ የተቸከለው የኢህአዴግ ፖለቲካ ዋስትና አልባ አድርጎታል።በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት አቁመዋል። ከየአቅጣጫው የሚረጨው የጎሳና የዘር እንዲሁም የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች የናጡት የከፈተኛ ትምህርት ተቋም የመቱ ዩኒቨርስቲን ካመሰ በሁዋላ አሁን አዲግራት ደርሷል።
የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የተሟላ መረጃ በማይሰጥ መልኩ የልጆቻቸውን ምስል በሚለጥፉበት የግል የፌስ ቡክ ገጻቸው የሚከተለውን አስፈረዋል

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ ትናንት ምሽት የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን ከዩኒቨርሲቲው መረጃ ደርሶናል። ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር የዋሉ መሆኑን ተረድተናል። ህይወቱ ያለፈውን ተማሪ ማንነት እና ዝርዝር መረጃ ከዩኒቨርሲቲው ማግኘት አልቻልንም ። መረጃው እንደደረሰን የምናሳውቅ ሲሆን በየአካባቢው ጉዳዩን የብሔር መልክ ለማስያዝ እየተሰራ ሰለሆነ ይህ ጉዳይ ማንንም የማይጠቅም። ስለሆነ ፤ማንም አትራፊም ስለ ማይሆን በመተሳሰብ እና በማስተዋል መንቀሳቀስ እንደሚገባ እናሳስባለን። በዚህ አጋጣሚ ህይወቱ ላለፈው ተማሪ ቤተሰቦች ፣ ጓደኞች እና ወዳጆች መፅናናትን እንመኛለን።
ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም

በድጋሚ አሻሽለው ይህንን አስነበቡ

ሰሞኑን በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው ግጭት ህይወቱ ያለፈው ተማሪ ሀብታሙ ያለው ስንሻው የተባለ የ2ኛ ዓመት የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበረ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ የሟች አስከሬን ወደ ቤተሰቦቹ ተልኳል፡፡ ተማሪ ሀብታሙ ያለው በምዕራብ ጎጃም ዞን በደጋ ዳሞት ወረዳ ድኩል ካና ቀበሌ ተወልዶ ያደገ ነበር፡፡
የክልሉ መንግስት የነገ ተስፋ በሆነው ተማሪ ሀብታሙ ህይወት ማለፍ ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ይህንን አስነዋሪ ተግባር የፈፀሙ አካላት ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግም ያሳስባል፡፡ ለተማሪ ሀብታሙ ያለው ወላጆች፤ቤተሰቦች እና ጓደኞች መፅናናትንም ይመኛል፡፡
በዚህ አጋጣሚ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን ከየአካባቢው መጥተው የሚማሩ ተማሪዎች የሁላችን፤የኛው የራሳችን ናቸው እና ያለምንም ልዩነት ጥብቃ ልናደርግላቸው እና ጥላ ከለላ በመሆን ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል !!
ታህሳስ 2 ቀን 2010 ዓ.ም

በትግራይ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ተገደለ የተባለው ተማሪ እንዴት ሞተ? በምን መልኩ ተገደለ? አስከሬን ምርመራ ከተደረገ ከአስከሬኑ ጋር ለቤተሰቦቹ ስለሚላክ እንዴት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ይህን አልጠቆሙም? የሚሉትና የክልሉ አቋም ምን እንደሆነ፣ ራሱ የትግራይ ክልል እና የአዲግራት ዩኒቨርስቲ ስለ ግድያው ምን አለ? የሚለውን እንደ አንድ የመገናኛ ባለሙያና ሃላፊነት ያለበት ካድሬ በአግባቡ አለማሳወቃቸው ከፍተኛ ትችት እንዲሰነዘርባቸው አድርጓል።
ጽሁፉን በለጠፉበት የፌስ ቡክ ገጻቸው ስር ዘለፋና የሰላ ትችት የተወረወረባቸው አቶ ንጉሱ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ባልተስተካከለ ቋንቋ፣ ባልተብራራ ሃረግ፣ እጅግ ውድ ጉዳዮችን በራሳቸው የግል የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ሲለጥፉና “በክልሉ መንግስት ስም” የሃዘን መግለጫ ሲያሰሙ ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በራሱ ስም ኦፊሳላዊ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ ብቻ እንዲህ ያሉትን ለዩ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች ቢያሰራጭ አግባብ እንደሚሆን አስተያየት የሰጡ አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የስንሻውን ህልፈት ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ቅሬታ ውስጥ ውስጡን እየጋመ ነው። ለዛጎል መረጃ የሰጡ እንዳሉት ይህ ፖለቲካው የወለደው ቂምና ጥላቻ የከፋ ችግር ሳያስከትል ከወዲሁ መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል።
ከወራት በፊት በአምቦ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በስጋት ሳቢያ ወደ ክልላቸው እንዲዛወሩ መጠየቃቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ይፋ መሆኑ አይዘነጋም። በሶማሊ ክልል የሚማሩ የኦሮሞ ተወላጆች ክልሉን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።
በርካቶች አዝነዋል። አልቀስዋል። አገር የሚገነቡ የተማሩ ትውልዶች በብሄር ተቧድነው በአንድነት የትምህርት ገበታቸው ላይ መቀመጥ የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ። ይህ ነው የመለስ ሌጋሲ፣ ይህ ነው ግብር የሚገባለት የመለስ ውርስ። ይህንን ውርስ ያራገፈብንን ሰው ” ታላቁ፣ አስተዋዩ መሪ” የሚባለው። የአገሪቱ የጎሳ ፖለቲካና ጎሳ ላይ የተቸከለ “ፌደራሊዝም” ዛሬም ድረስ ጥፋቱ የማይታየው በጉዳዩ ለሚጠቀሙት ብቻ ነውና ሁሉም ወገኖች ልብ ሊገዙ ይገባል። በማስተዋል መራመደም አስፈላጊ ነው… ሲሉ ገለልተኛ ወገኖች የፍርሃት አስተያየት ይሰጣሉ።

አዲግራት.jpg

ከአቶ ንጉሱ ይልቅ የተሻለ መረጃና ፍንጭ እንዲሁም ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ መረጃ የሰጠው ዳንኤል ብርሃኔ ነው። ይህ ማለት አቶ ንጉሱ ወይ መረጃ የላቸውም፣ አለያም የመርዶ ነጋሪ ስራ ነው የሚሰሩት፣ አልያም የሚያውቁትን እንኳን ለማሳውቅ አቅምና ፍላጎት የላቸውም። ይህ የሳቸው ተግባር የሚያሳየው የሾማቸውን ብአዴንን ወርድና ቁመት ነውና እንደተለመደው ከማዘን የዘለለ የሚባል ነገር አለመኖሩን ጉዳዩን የሚከታተሉ ይናገራሉ።

Related stories   በአቡነ ማቲያስ መልዕክት ሳቢያ - ሲኖዶስ በመቆጣቱ አስቸኳይ ስብሰባ ተደርጎ የተግሳጽና የማስተካከያ መግለጫ ሊሰጥ ነው

የስንሻው ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተማሪዎች መሞታቸውን አንዳንድ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። ይሁንና የጀርመን ሬዲዮ ዘጋቢ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ፅ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ከበደ የተጠቀሰው ተማሪ መሞቱን አረጋግጠው ጉዳዩ መጋነኑን አመልክተዋል።  ግጭቱ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን በሚያከብሩ ተማሪዎች መካከል በመበሻሸቅ የተጀመረ መሆኑንን አመልክተዋል። አያይዘውም 100 የሚሆኑ ተማሪዎች ቅጥር ግቢውን ለቀው ለመውጣት መጠየቃቸውን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።

Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው

“በመበሻሸቅ የተጀመረ ነው” ያሉት ግጭት ወደ ድንጋይ መወራወር ማምራቱንም የተናገሩት ሃላፊው። “የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እያከበሩ የነበሩ ልጆች ሰብሰብ ብለው እየጨፈሩ ነበር። በመበሻሸቅ ነገር ተጀመረ፤ ከዛ አንድ ሁለት ልጆች ተጣሉ እና ድንጋይ መወራወር ተጀመረ። ነገሩ ሰፋ ሲል የጸጥታ ኃይሎች ገብተው በቁጥጥር ሥር ውሏል። በነበረው ግጭት አንድ ተማሪ ሕይወቱ አልፏል።”
አቶ ዮሐንስ በግርግሩ የተደናገጡ ወደ 100 ገደማ ተማሪዎች ቅጥር ግቢውን ለቀው ለመውጣት መጠየቃቸውን ተናግረዋል። አቶ ዮሐንስ የአገር ሽማግሌዎች፤ የሐይማኖት አባቶች እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር “አነጋግረዋቸው ልጆቹን አሳምነን ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ እያደረግን ነው” ብለዋል። በግጭቱ ብሔርን ያማከለ ጥቃት ስለመፈጸሙ የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ በፍጹም ሲሉ አስተባብለዋል። በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጨው መረጃም “የተጋነነ እና ሐቁን የማይገልፅ ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።

Related stories   አየር ሃይል " ትዕግስትም ልክ አለው" ሲል ለሱዳን ምክረ ሃሳብ ሰጠ

የብሄር ብሄረሰቦች በዓልን ተንተርሶ በመበሻሸቅ የተነሳ ግጭቱ መነሳቱን፣ ወይም የግጭቱ መነሻ የብሄር ብሄረሰቦችን በዓል ተከትሎ በተጀመረ መበሻሸቅ መሆኑንን ያስረዱት ሃላፊው አቶ ዮሐንስ  “በግጭቱ ብሔርን ያማከለ ጥቃት ስለመፈጸሙ” ተጠይቀው በፍጹም ማለታቸው ጠያቂውንም ሆነ መላሹን ትዝብት ላይ የጣለ ሆኗል። በብሄር በሄረሰብ ጉዳይ ሳቢያ ተነሳ የተባለ ብሽሽቅ ብሄርን መሰረት ያላደረገ ምን ዓይነት ግጭት ሊነሳ ይችላል? ሲሉ የሚጠይቁ ክፍሎች ሃላፊው እርስ በርስ የሚጋጭ መግለጫ መስጠታቸው ሊሸሸግ እንደማይችል ገልጸዋል።

ለጥንቃቄ ሲባል ጉዳዩን ለማላዘብ ሌላ አግባብ መጠቀም አንድ ነገር ሆኖ ሳለ እንዲህ አይነት የሃሳብ ግጭት አግባብ እንዳልሆነ የጠቆሙት ክፍሎች ” ተማሪዎቹ ለቤተሰቦቻቸውና ለባልደረቦቻቸው እንደሚገልጹት ጉዳዩ ወደ ከረረ ቀውስ እንዳይሸጋገር በጊዜ ወደ ቤተሰቦአቸው የሚሄዱበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል” ባይ ናቸው።

ምስል- ማህበራዊ ገጾች