በኢትዮጵያ በሚገኙ 30 ሺ 605 ትምህርት ቤቶች ላይ ዓለም አቀፍ የትምህርት ጥራት መለኪያን በመያዝ በተደረገ ጥናት፤ 11 በመቶ ያህሉ ደረጃ አራት፣ 65 በመቶ ደረጃ ሦስት 24 በመቶው ደግሞ ደረጃ ሁለትና አንድ ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ በከተማዋ ካሉ ትምህርት ቤቶች 75 በመቶው ደረጃ ሦስት ሲሆኑ፤ በመለኪያው ከፍተኛ በሆነው ደረጃ አራት ግን አንድም ትምህርት ቤት አለመግባቱን በትምህርት ሚኒስቴር የእቅድና ሀብት ማስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ግርማ አስታውቀዋል። የደረጃው ወሳኝ መመዘኛ የሆኑት የሰው ኃይል፣ የትምህርት አሰጣጥ፣ መሰረተ ልማትና ሌሎች መሳሪያዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ አባተ በበኩላቸው፤ በትምህርት ግብዓትና መሳሪዎች፣ በመምህራንና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች፣ በፋይናንስ አቅም፣ በመማሪያና ማረፊያ ክፍሎች፣ በተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ደረጃ መለኪያ ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ባሉ አንድ ሺህ 612 ትምህርት ቤቶች ላይ ጥናት መደረጉን ይገልጻሉ። በውጤቱም 25 በመቶ ብቁ ሲሆኑ፤ 75 በመቶ ከደረጃ በታች ሆነው ተገኝተዋል። አንድም ትምህርት ቤት ግን ከፍተኛ ደረጃ ሊገባ አልቻለም ነው ያሉት።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሳይንስ ትምህርት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ጸጋዬ፤ በትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶች ላይ በመማር ማስተማር፣ በግብዓት እና የተማሪዎች ውጤት ላይ ጥናት ማድርጋቸውንና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሆነ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚሰጡ ትምህርቶች ላይ ደካማ ውጤት መኖሩን በጥናቱ ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ።

በአገር አቀፍ ደረጃ እአአ ከ2000 ጀምሮ አራተኛ ስምንተኛ እንዲሁም ከ2010 ጀምሮ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የሚደረገው የዳሳሳ ጥናት የተማሪዎች ውጤቱ ሃምሳ በመቶ በታች መሆኑን አረጋግጧል። በተመሳሳይም በ2008 .ም በተደረገ ጥናት የስምንተኛ ክፍል ተማረዎች አማካይ ውጤት 41 ነጥብ መሆኑ ታውቋል ነው የሚሉት። ዳይሬከተሩ እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል ያሉ መምህራንን ብቃት ለማረጋገጥ በተሰጠ ፈተና በአማካይ የተገኘው ውጤት ከ50 በመቶ በታች ነው።

በአብዛኛው ተማሪ ትምህርት ምንም ጥቅም የለውም የሚል አመለካከት መኖሩና የመማር ፍላጎት አናሳ መሆን፤ የወላጆች ክትትል አነስተኛነት፣ የትምህርት አመራር እና የአማዛዘን ችግር፣ በክፍል ውጤት የመኩራራትና ወረዳዎችና ትምህርት ቤቶች በውሽት ሪፖርት የሚሸለሙበት ሁኔታ መኖሩን በጥናቱ አረጋግጠናል ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ።

በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሥነ ጥበብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ጌታቸው አበበ፤ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ተማሪዎች በተግባር ትምህርት የተሟላ ባይሆኑም በንድፈ ሃሳብ ችግር እንደሌለባቸው በማንሳት፤ አሁን ግን የተማሪዎች የንድፈ ሃሳብ አቅም እየተዳከመ መጥቷል ይላሉ። «በፊት ይሰጥ የነበረውን ፈተና አሁን ላይ ብናወጣ የሚቀጥል ተማሪ ማግኘት ሊቸግር ይችላል። አሁን ካሉት ተማሪዎች አንፃር ቀደም ባሉት ዓመታት ወድቃችኋል ተብለው የተባረሩት ተማሪዎች አቅም ያላቸው እንደነበሩ መምህራን ይናገራሉ» በማለት የችግሩን ጥልቀት ያብራራሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ባደረጉት ጥናት፤ የትምህርት ጥራት መጓደሉ አንድም ከመምህራን ብቃት ጋር መያያዙን ይገልጹና፤ የመምህራን ምልመላና ስልጠና ችግር ያለበት፣ የሚሰጣቸው ስልጠና መሬት ላይ ካለው ዕውነታ ጋር የማይጣጣም ነው ሲሉ ለትምህርት ጥራት አበይት ምክንያት የሚሉትን ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰሩ ባካሄዱት ጥናት የትምህርት ስርዓቱ በእውቅት የሚያጨናንቅ እንጂ የህይወት ልምድን የሚያስጨብጥና በስነምግባር የሚቀርጽ አለመሆኑን፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተዘንግቶ መቆየትና አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ትኩረት አለመሰጠቱን፣ የትምህርት ሰንሰለቱ በአግባቡ አለመተሳሰሩን፣ ክትትል እና ድጋፉ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን፣ ከፌዴራል እስከ ትምህርት ቤት ያለው የትምህርት አመራር በችሎታና በብቃት እየተመደበ አለመሆኑን፣ ትምህርቱ በሚፈለገው ልክ በቴክኖሎጂ አለመታገዙን ማረጋገጣቸውን ያብራራሉ። ይህም ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ያለው የትምህርት ጥራት ችግር ውስጥ ያለ መሆኑን አሳይቷል ይላሉ።

የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ኤሊያስ፤ በሚኒስቴሩ ግምገማም መሰረት በአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ችግር አለ የሚል ድምዳሜ መኖሩን ይገልጻሉ። ይህንን ችግር ለመፍታትም የመምህራን አቅም ግንባታ፣ ስርዓተ ትምህርት የማሻሻል፣ ለትምህርት ቤቶች በቂ ፋይንስ የመመደብ፣ ህብረተሰቡን የሚያሳትፉ ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን በመጥቀስ እነዚህ ተግባራት የትምህርት ጥራት ያመጣሉ ብለዋል።

ከዚህ ውጪ ግን በፕሮፌሰር ጥሩሰው «መምሀራን ምልመላና ስልጠና ላይ ችግር አለበት» በሚለው ድምዳሜ እንደማይስማሙ ይገልጻሉ። ስልጠናው የሚሰጣቸው በመማር ማስተማሩ መነሻነት ሊያስተምሩት የሚገባው መነሻ ተደርጎ ነው። በመምህራን ስልጠና የልቀት ማዕከል የሚሆኑ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ተወስደው እየተሠራ ነው። እውቅት ላይ እንጂ ሥነምግባር ላይ ጉድለት አለ የሚለውም፤ በርካታ ውጤቶች እንዳሉ ሁሉ ድክመቶች መኖራቸው በጥናት ተለይቶ የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። እንደ አጠቃላይ በትምህርት ጥራት ላይ ጉድለት ቢኖርም በርካታ ውጤቶች መኖራቸውን በማንሳት የምሁራኑን ሃሳብ ይሞግታሉ።

ፕሮፌሰር ጥሩሰው ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት መንግሥት በትምህርት አመራር የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በውድድር፣ በእውቅትና በክህሎት መመደብ አለበት፣ በተቋማት መካከልም ሰንሰለቱን የጠበቀ ግንኙነት መፍጠርና ማጠናከር፣ ሥርዓተ ትምህርቱን ከአገር አቅጣጫ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ማድረግ፣ የአገር ውስጥ ቋንቋዎችም ሆኖ የውጭ ቋንቋዎች አሰጣጡን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማድረግ፣ በቋሚነት ለመምህራን ብቻ ስልጠና የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች እራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ማስቻል፣ የመምህራን ስልጠና የሚሰጡ ኮሌጆችንም አሰለጣጠናቸውን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በጊዜና በጥራቱ እንዲካሄድ ማድርግና በየደረጃው ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባ ይመክራሉ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ሙሉጌታም የፕሮፌሰሩን የመፍትሄ ሃሳብ ይጋሩና፤ መምህራን ከስልጠና በኋላ ወደ ሥራ ሲገቡ ክትትልና የማብቃት ስርዓትን በተመዘነ መልኩ መፈጸም፣ ለአስተማሪው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ እውቀት ብቻ ሳይሆን ክህሎትን የሚያዳብር የትምህርት ስርዓት መከተል፣ የወላጆች ክትትልና የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት መፍጠርና ሌሎች ነገሮችንም ታሳቢ በማድረግ በትምህርት ጥራት ያለውን ችግር መፍታት እንደሚገባ ይገልጻሉ።

የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ጌታቸው፤በአገር ደረጃ የትምህርት ጥራት ለማምጣት ግብዓትና ምቹ ትምህርት ቤቶችን ማዘጋጀትና ለሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች የሚሆኑ የተግባር መመሪያ ቤተ ሙከራዎችን ማዘጋጀት፣ ወደ መምህርነት ሙያ የሚመጡ ባለሙያዎችን ብቃት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ከ30 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ተደራሽ በማድርግ ረገድ ኢትዮጵያ የሚሌኒየም ግቡን ማሳከቷ ይታወቃል።

ምሁራኑ የአገር ልማት የሚመጣው የሰውን ሀሳብ ወደ ተግባር በመቀየር ነው። ለዚህ ደግሞ ብቁና ጥራት ያለው እውቅት የጨበጠ ዜጋ ማፍራት ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነና አሁን ያለው የጥራት ችግር ካልተፈታ፤ የአገሪቱን እድገት ማስቀጠልም ሆነ ማፋጠን አይቻልም፤ ማህበራዊ ቀውስም ይፈጠራል። የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ ችግሩን ለመፍታት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የትምህርት ጥራቱን ያመጡታል የሚል እምነት አላቸው።

 አዲስ ዘመን በአጎናፍር ገዛኸኝ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሳይቲስት - ችግር የመፍታት አቅም እንዳለህ ከተሰማህ ፣ያንን ፍጥነት መቀነስ በእውነቱ መልካም አይደለም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *