በሐማሬሳ የመጀመሪያ ውሎዬ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ወልዳ ምንም ሳትበላ በማለዳ ሻይ በዳቦ ለመብላት የምትጠብቅ አራስ በማየታቸው እንዳለቀሱ ይናገራሉ። ወ/ሮ ማሚቱ ይዘው በሄዱት ጥቂት ቅቤ ገንፎ አገንፍተው ፀጉሯንም እንደቀቧት ይናገራሉ። እርዳታቸውንም በአንድ ዙር አላበቁም። BBC Amharic

ወ/ሮ ማሚቱ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል በድንበር ግጭት ተፈናቅለው በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰፍረው የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን እየመገቡ ነው። ከሶማሊያ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን ሰቆቃ የሰሙት በሚያመልኩበት ቤተ-ክርስቲያን በኩል እነደሆነ ይናገራሉ።

”የቤተ-ክርስቲያናችን ቄስ ተፈናቃዮቹ እንጀራ አማረን እያሉ እንደነበረ እያነቡ ሲነግሩኝ እነዚህን ሰዎችማ እንጀራ ማብላት አያቅተኝም ብዬ ምኞታቸውን ለማሳካት ወሰንኩኝ” ብለው

በመቀጠልም ”አንዳንድ ሰዎች እርዳታ አደረጉልኝ ሲሉ፤ በመጀመሪያ ዙር ስድስት ሺህ እንጀራ በመጫን በሌሊት ከአዲስ አበባ ተነስቼ በማለዳ ሐማሬሳ ደረስኩኝ፤ የሰማሁትና ያየሁት ግን አይገናኝም ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሐማሬሳ የመጀመሪያ ውሎዬ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ወልዳ ምንም ሳትበላ በማለዳ ሻይ በዳቦ ለመብላት የምትጠብቅ አራስ በማየታቸው እንዳለቀሱ ይናገራሉ። ወ/ሮ ማሚቱ ይዘው በሄዱት ጥቂት ቅቤ ገንፎ አገንፍተው ፀጉሯንም እንደቀቧት ይናገራሉ። እርዳታቸውንም በአንድ ዙር አላበቁም።

በሁለተኛው ዙር ከወለዱ ሦስት ወር ያላለፋቸው ከ120 በላይ አራሶችን ገንፎ አብልተው ቅቤ ቀብተዋል። በዚህ የእናትነት እርዳታቸው ተፈናቃዮቹ ወዳሉበት መጠለያዎች አምስት ጊዜ ተመላልሰዋል። ባለፈው ሰኞም አስር ሺህ እንጀራ በመኪና ጭነው ድሬ-ዳዋ ወደሚገኝ መጠለያ ተጉዘዋል።

”እኔ ሀብታም አይደለሁም። ባለኝ ጥቂት ነገር የምችለውን በማድረጌ ያገኘሁት ጥቅም የአዕምሮ እረፍት ነውና በሱም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የተራበን ሰው ማብላት ችያለሁ” ይላሉ ወ/ሮ ማሚቱ።

ቢችሉና በየሳምንቱ እየተመላለሱ ቢመግቡ ምኞታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። “በመጠለያዎቹ ውስጥ የሚገኙት የተፈናቃዮች ምርቃት ስንቅ ነው” በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል። ምስራቅ ወለጋ የተወለዱት ወሮ ማሚቱ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ ከኩማሜ የተሰኘ ምግብ ቤት ባለቤት ናቸው።

”ትዝ ይለኛል በልጅነቴ ከቤት እንቁላል ሰርቄ እየጠበስኩ ሰዎችን አበላ ነበር። በዚህም ምክንያት በወላጆቼ ቤት የነበሩት ሠራተኞች ተቆጥተውኝ እያለቀስኩ ሳለ አባቴ ደርሶ ሁለተኛ እንዳይነኩኝ በማስጠንቀቅ የፈለግኩትን ሰው ማብላት እንደምችል ነግረውኝ ነበር። ከዚያም በየወሩ ሰው የማበላበትን አንድ ዘምቢል እንቁላል ይገዙልኝ ነበር” በማለት የልጅነት ጊዜያቸውን ያስታውሳሉ።

በልጅነታቸው ሰውን መርዳትና ያላቸውን ማካፈል ይወዱ ነበር ይላል ወንድማቸው ሂንሴኔ መኩሪያ። “እናታችን ለሰው ታዝንና መርዳት ትወድ ነበር፤ እህቴም ይህንን ፀባይ ከእርሷ የወረሰችው ሳይሆን አይቀርም” ይላል። እያደረጉ ባሉት የእርዳታ ሥራ የቤተሰባቸው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንና ባለቤታቸውም ይህንን ተግባራቸውን እንደሚደግፈው ይናገራል።

እነዚህ ተፈናቃዮች ደሳሳ ጎጆም ብትሆን መኖሪያ ሊፈለግላቸው እንደሚገባና ሌሎች ሰዎችም ተፈናቃዮቹን በመመገብ የሚገኘውን እርካታ እንዲያጣጥሙ በማለት መልዕክት ያስተላልፋሉ።

ወ/ሮ ማሚቱ እያደረጉት ባሉት ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን በሐማሬሳ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ተወካይ አቶ ፋሕሚ አብዱ ይናገራሉ።

“ቀንና ሌሊት በመጓዝ በሺዎች የሚቆጠር እንጀራ ለወራት ቆርሶ መመገብ ያማራቸውን ተፈናቃዮች መግባለች። እርሷ ብቻዋን ‘የኦሮሞዎች እናት’ ናት ስለዚህ መመስገን አለባት” ይላሉ።

የሕፃናት ሥነ-ልቦና

እነዚህ ተፈናቃዮች ባረፉባቸው መጠለያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ይገኛሉ። “እነዚህ ሕፃናት እየሰሙና እያዩ ያሉት ነገር ሥነ-ልቦናቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ግምት ውስጥ ያስገባ አካል ያለ አይመስለኝም” ይላሉ ወ/ሮ ማሚቱ።

“እዛ ካየኋቸውና ካሳዘኑኝ ነገሮች አንዱ ሕፃናት ስለ አባታቸው መሞት በቀላሉ ሲያወሩ መስማቴ ነው” ይላሉ። ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እነዚህ ሕፃናት ያሉበትን እንዲረሱ ወደሚያውቋቸው ትምህርት ቤቶች ሄደው መጽሐፍት መለመን ጀመሩ፤ ባገኙትም ድጋፍ ደብተርና እስክብሪቶ ሰብስበው ወደ ሐማሬሳ መጠለያ እንደተመለሱ ይናገራሉ።

መጠለያ ውስጥ ካገኟቸውም 14 መምህራን ጋር ሕፃናቱን ስድስት ቦታ በመክፈልና በማስተማር ያሉበትን ሁኔታ እንዲረሱ ለማድረግ መሞከራቸውን ነግረውናል። ሆኖም ሕፃናቱ ያሉበት ሁኔታና በሥነ-ልቦናቸው ላይ እየደረሰባቸው ያለው ጉዳት ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ነው ይላሉ ወ/ሮ ማሚቱ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በትግራይ 3.5 ሚሊዮን ተረጂዎች የዕለት ቀለብና ተመሳሳይ እርዳታ እየተደረገላቸው ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *