ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያውያን “የመጀመሪያው” ማለት ያበዛሉ በሚል እንታማለን፡፡ እኔ ግን ሃሜቱንም ሆነ ቀልዱን አልቀበለውም፡፡ የመጀመሪያው ማለት የምናበዛውም በምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በብዙ ነገሮች ቀዳሚ የሆንን የመጀመሪያ ህዝቦች ነንና፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ እንዲያው በእኛ ላይ ተጋነነ እንጂ በሆነ ነገር ቀድሞ መገኘትና የመጀመሪያው ማለት የማይወድ አገርና ህዝብ ያለ አይመስለኝም፡፡
 የመጀመሪያው ከማለትም አልፈው በሁሉም ነገር “አባት” ነን ማለት የሚወዱት ምዕራባውያንስ ምን ይባሉ? የባዮሎጂ አባት፣ የፊዚክስ አባት፣ የጂኦግራፊ አባት …ኧረ ምን አባት ያልሆኑበት የትምህርት ዓይነት አለ፡፡

ለማንኛውም እነርሱ አባት፣ አባት ማለታቸውን ካልተዉ እኛም የመጀመሪያ ነን ማለታችን አንተውም፡፡ ደግሞስ ምናለበት የመጀመሪያው ብንል “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” ተብሎ የለ፡፡ እናም ለዛሬው በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ የመጀመሪያው አጭር ልብ ወለድ ድርሰት እንደሆነ የሚነገርለትን የተመስገን ገብሬን “የጉለሌው ሰካራም” የተባለውን አጭር ልብ ወለድ ቀንጨብ አድርገን እናቃምሳችሁ፡፡ 
በጉለሌ የነበረው የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሠፈር ለታጠቁ ሰዎች፤ ተበጀ ሰካራሙ፣ ዶሮ ነጋዴው ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል፡፡ የህይወቱ ታሪክ ፍጹም ገድል ነው፡፡ ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው፡፡ የራሱን ጠጉር ውሃ ወይም መቀስ ነክቶት አያውቅም፡፡ ማለዳ አይናገርም፡፡ በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ማታ ሲራገም ወይም ሲሳደብ፣ ሲፎክር ወይም ሲያቅራራ ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም ማታ ላገኘው ሁሉ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ 
ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኘው ሁሉ ጋር ማታ ይስቃል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው ዓይነት እንደ ወታደር ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው፡፡ ከሰላምታው ጋር ድምጥ ትሰማላችሁ፡፡ ከአፉ ከሚወጣው ግን አንድ ቃል መለየት አትችሉም፡፡ ቡና በተፈላ ጊዜ በጉለሌ በየምድጃው ሥር ሰካራሙ የተጫወተው ሰው ሁሉ የተነገረው በተበጀ ላይ ነው፡፡ መልኩን አይተውት ላወቁ ባልቴቶች እንኳን ከፍንጃል ቡናውን ፉት እያሉ የሌላውን ሰካራም ተረት በተበጀ ላይ ያላክኩት ነበር፡፡ በጠባዩ ከተባለበት የባሰ ሰካራም ይሁን ወይም የተሻለ ጉለሌ ባህር ዛፍ ውስጥ ወጥቶ እንደ አዲስ እንግዳ ሰው ሆኖ ለአዲስ አበባ ታይቷል፡፡ 
ከድሮው የእንጨት ጉምሩክ አጠገብ ወደ ምስራቅ ሲል ካለው ወንዝ ማዶ ድልድዩን ወደ ምስራቅ ተሻግሮ መጀመሪያ የሚገኘው አነስተኛ ሳር ክዳን ቤት የተበጀ ቤት ማለት ያ ነው፡፡ በዚያው በቤቱ በዚያው በጉለሌ በሰፈሩ ኖሩ፡፡ እንጨት ተሸክሞ አፈሩን ቆፍሮ ቤቱን የሰራው እርሱ ነው፡፡ ዋጋ ከፍሎ አስከድኖታል፡፡ ተበጀን ኩራት ተሰማው፡፡ ቆይቶ ደግሞ ዓይኖቹ እንባ አዘሉ፡፡ በጉንጩም የእንባ ዘለላ ወረደው፡፡ በግራ እጁ መዳፍ ከጉንጩ የተንከባለለውን እንባ ጨፈለቀው፡፡ ዓይኖቹ እንባ ያፈሰሱ ለራሱ ጎጆ ስላለው ነው፡፡ ሊነገር በማይችል ደስታ ልቡ ተለውሷል፡፡ 
ዝናቡ ያባረራቸውም ከቤቱ ጥግ ሊጠለሉ ይችላሉ፡፡ ቤት የእግዚአብሄር ነውና ወዠብ እንዳገኛቸው ከቤት ውስጥ ዝናቡ እስኪያባራ ይቆያሉ፡፡ ተበጀን “ቤትህን ይባርክ” ሊሉት ነው፡፡ “እንግዲህ መንገደኛው ሁሉ ‘የማን ቤት ነው’  ብሎ ሲጠይቅ የተበጀ ሊባል ነው” አለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ “ ‘ተበጀ የትኛው ነው?’ ሲባል ‘ዶሮ ነጋዴው’ ሊባል ነው” አለ፡፡ “ ‘ዶሮ ነጋዴው የትኛው ነው?’ ሲባል ‘ያ የጉለሌው ሰካራም’ ሊባል ሊባል ነው፡፡ አወይ! እኔ ተበጀ ተበላሽቻለሁ” አለና ደነገጠ፡፡  “ከዚህ በኋላ ስለ ቤቱ ክብር  እንኳ መጠጥ መተው ይገባኛል” አለ፡፡   
   መጠጥ ለመተው እንኳ ያሰበበት የመጀመሪያው ጊዜው ይኼው ነው፡፡ ሰካራምነት ጉዳት መሆኑ ተሰምቶት እንደሆነ ይናገር፤ ስለ ቤቱ ክብር መግለፁ ግን ዳር ይቆይ፡፡ ስለ ቤቱ ክብር ምን ያውቃል? ዶሮ ነጋዴው ተበጀ፣ ሰካራሙ ተበጀ አይደለምን? ሰካራሙ ተበጀ የሰራውን የገዛ ቤቱን ከፍቶ፣ ገባና ኩራዙን አስቀምጦ፣ ክብሪቱን ለመጫር ሲያወጣ በሃሳብ ተሰቅዞ እንደዚህ አሰበ፤ “መምረጥ አለብኝ፡፡ ከዚህ ቤት ያለው መጠጥ  ሁሉ አንድ ሳይቀር እየወጣ ይፍሰስ፡፡ከዚህ በኋላ ክብሪቱም ኩራዙም በቤቱ ይደር፡፡ በአዲሱም ቤት ብርሃን ይዙርበት፡፡ አለዚያም በአዲሱ ቤት መጠጥ ዙርበት፡፡ ኩራዙና ክብሪቱ ከቤት ይውጣና ይፍሰስ፡፡ ሊደረግ የሚገባ ከሁለቱ አንዱ ነው እንጂ፤ በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት በአንድነት  ይህች ውሸት” አለና ሳቀ፡፡ 
ከሁለቱ አንዱን ለማድረግ ሳይቆርጥ መብራቱን አቃጠለና ተቀመጠ፡፡ እንደገና ደግሞ እንደዚህ አሰበ፡፡ “አያድርገውና ዛሬ ሰክሬ ይህ ቤት ቢቃጠልብኝ፣ አመዱን አይቶ በሰካራሙ ተበጀ ላይ ለመሳቅ ድፍን ጉለሌ፣ ነገ ከዚህ ነው የሚቆም! ጉለሌ ምን ባለኝ? ወሬ ከማቡካት፣ በቀር ጉለሌ ምን ሥራ አለው? ለአዲስ አበባም የስድስት፣ ወር መሳቂያ በሆንኩ ነበር፡፡ መንገድ አላፊዎችም ነገ በዚህ ሲያልፉ አመዱን አይተው ይህ የተቃጠለው ቤት የማን ቤት ነው? ሲሉ የተበጀ ነው ሊባል ነው፡፡
    በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት በአንድነት ይህች ውሸት!” ወደ ውጭ እንደ እርም ወርውሮት የነበረውን የመጠጥ ጠርሙስ ሁሉ በጨለማው ዳብሶ አንድ በአንድ ለቃቀማቸው፡፡ አንዱን ግን ቀና አደረገና ከአፍንጫው አስጠግቶ አሸተተው፡፡ በጠርሙሱ ቅርፅ የመጠጡን ዓይነት አወቀው፡፡ ዊስኪ ነበርና ስለዚህ ነው ሰው እንዳይሰማ ቀስ ብሎ የሳቀ፡፡ የጠርሙሱን ግማሽ ከጠጣ በኋላ ግን በአፉ ቡሽ ቢወትፉበት ለሳቁ መጠን የለውም፡፡ “ጉለሌ ተኝቷልና ከዚሁ  ከባህር ዛፍ ሥር ቁጭ ብዬ ብጠጣ የሚታዘበኝ የለም” አለና አሰበ፡፡
እውነቱን ነው ጉለሌስ ተኝቶ አልነበር፡፡ ነገር ግን አሁን እርሱ ጠጥቶ የሰከረ እንደሆነ ጉለሌን ሊቀሰቅሰው ነው፡፡ እርሱ ከጠጣ በጉለሌ ማን ይተኛል? ጠርሙሱን ከከፈተው በኋላ ብርጭቆ ያስፈልገው እንደነበር ትዝ አለው፡፡ ሦስት የሚሆን ደህና ጉንጭ ጠርሙሱን ከአፉ አስጠግቶ ጨለጠ፡፡ከዚያ በኋላ የሚጠጣበት ብርጭቆ ሊያመጣ አሰበ፡፡ ቀጠለናም በሦስት ጉንጭ ምን ያህል ጠርሙሱን እንዳጎደለው ለማወቅ ጠርሙሱን ቀና አድርጎ በጨረቃዋ ተመለከተ፡፡ “ለዚህችስ ብርጭቆ ማምጣት አያሻም” እያለ ጠርሙሱን አምቦጨቦጨው፡፡ 
በቀኝ እጁ መሬቱን ተመርኩዞ የቀረውን ጅው አድርጎ ወደ ውስጥ ወረወረው፡፡ ባዶውን ጠርሙስ ደግሞ በእጁ እየጠነቆለ፤ “አንተን ደግሞ ለአንድ ዶሮ፣ ለውጨ መያዢያ አስዝሃለሁ የዊስኪ ቅርፊቱም  ዋጋ አለው አይጣልም” እያለ እንዲህ ሲጠጣ ሌሊቱን አጋመሰው፡፡ ቀጥሎ ከእግሩ በታች የወደቀውን ጠርሙስ እየቆጠረ፤ “ይህን ሁሉ እንደጠጣሁት አላምንምና በጉለሌ አፍርሳታ ይደረግልኝ፤ እነ ናቄ እነ ተሰማ አጎቴም ይጠጣሉ” አለ፡፡
  የጠርሙሱ መጠጥ ሁሉ እስኪያልቅ ድረስ ከዚያው ከዛፉ ሥር ተቀምጦ ያን ተንካራ ትምባሆውን ከአፉ አለየውም፡፡ በሳቀ ጊዜ ብቻ መልሶ ዝም እስኪል ድረስ መጠጡ ወይም ትምባሆው ከአፉ ያቋርጣል፡፡ የመጠጥና ትምባሆ ጊዜው ተበጀ ይህ ነው፡፡ ማለዳ በቀዝቃዛ ውሃ ታጠበ፡፡ ቋንጣም እንቁላልም ጠበሰና በዳቦ በላ፡፡ “ለአባ ተክለ አረጋይ አልናገርምና  ነፍሴ ሆይ ግድ የለም” አለ፡፡
የነፍስ አባቱን ማለቱ ነው፡፡ ምናልባት በዓመት እንኳ አንዴ ጠይቋቸው ወይም ጠይቀውት አያውቁም፡፤ እርሱንም አያደርሰውም፤ እርሳቸውም ከበአታቸው አይወጡም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የዛሬውን እሁድ እረፍት አደርገዋለሁ ያለ እንደሆነ እግሩን ደህና አድርጎ የሚታጠብበት ቀን ማለት ነው፡፡ ደክሞት ነበርና ደህና እንቅልፍ ተኝቶ ነበር፡፡ ዝናቡን፣ ነጎድጓዱን፣ ጎርፉን ውሃ ሙላቱን አልሰማም፡፡ አንዳች ነገር ሰማ፡፡ ዘፈንና እልልታ የሰማ መሰለው፡፡ ትናንት የጠጣው መጠት ኃይል መሰለውና ይህስ እብደት ነው እንጂ ስካር አይደለም አለና ተመልሶ ተኛ፡፡ እኔም ይህን ያህል ካልኩ ላብቃ። መነሻዬ በደራሲ ተመስገን ገብሬ በ1940 ዓ.ም ከታተመው “የጉለሌው ሰካራም” ላይ የመጀመሪያው አጭር ልብ ወለድ መጽሃፍ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ፣ የመጀመሪያ ገጾች ላይ ተቀንጭቦ ለእናንተ የቀረበ ነው።     

ይበል ካሳ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *