(በጌታቸው ሺፈራው)

~ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለአቶ ደመቀ መኮንን መጥርያ አልወጣም

የአማራ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር አቶ ሙሉጌታ ወርቁ፣ የጎንደር ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል እና ስለ ህዝባዊ አመፁ ማስረዳት ይችላሉ የተባሉ ባለስልጣናት እና የፖሊስ አዛዦች በእነ ንግስት ይርጋ ተፈራ ክስ መዝገብ ስር ለተከሰሱት 6 ግለሰቦች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አዟል።

ባለስልጣናቱ ህዝባዊ አመፁ በመልካም አስተዳደር ችግር የተነሳ ግጭት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት በሚዲያ ቀርበው ያስረዱ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ህዝባዊ አመፁን ከ”ሽብር” ወንጀል ጋር በማገናኘት ተከሳሾቹ ላይ የ”ሽብር” ክስ መስርቶባቸዋል። በተጨማሪም ተከሳሾች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሩ ሲሆን የሁለቱ ባለስልጣናት መጥርያ አልወጣም ተብሏል።

በእነ ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱት ንግስት ይርጋ ተፈራ፣ አለምነህ ዋሴ ገ/ማርያም፣ ቴዎድሮስ ተላይ ቁሜ፣ አወቀ አባተ ገበየሁ፣ በላይነህ አለምነህ አበጀ እና ያሬድ ግርማ ኃይሌ ናቸው።

ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት በህዝባዊ አመፁ እጃቸው እንዳለበት እና የ”ሽብር ወንጀል” ፈፅመናል ብለው በሀሰት እንዲያምኑ ለማድረግ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ሲገልፁ የቆዩ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ንግስት ይርጋ ጥፍሮቿ እንደተነቀሉ በክስ መቃወሚያዋ ላይ ተገልፆአል። ሌሎች ተከሳሾችም ያልፈፀሙትን ፈፅማችሁታል ተብለው በደል እንደደረሰባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

ከባለስልጣናት ባሻገር የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ፕሮፌሰፈር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ያዕቆም ኃይለማርያም እና ሌሎች ምሁራንም በተከሳሾቹ በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረዋል። ምስክሮቹ ለታህሳስ 12/2010 ዓም ቀርበው እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ ተፅፎ የነበር ቢሆንም መጥርያው ዘግይቶ በመውጣቱ አልደረሳቸውም። ታህሰስ 12/2010 ዓም ተከሳሾቹ ተነጣጥለን ወደ ችሎት አንገባም በማለታቸው ጉዳዩ ሳይታይ ቀርቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የ3 ቀን ውሎ

(በጌታቸው ሺፈራው)

~ዛሬ ታህሳስ 13/2010 ዓም፣ ተከሳሾች ችሎት ውስጥ ተገኝተዋል። ሆኖም ዳኞች ባለመገኘታቸው ተከሳሾች ወደ ቂሊንጦ ተመልሰዋል።

~ታህሳስ 12/2010 ዓም በችሎቱ ቀጠሮ የነበራቸው ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ውስጥ ከሚገኘው የእስኞች ጊዜያዊ ማቆያ እንዲቀመጡ ተደርጎ በየተራ ወደ ችሎት እየገቡ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ስለተፈለገ፣ እስረኞቹ ሁላችንም በችሎት ገብተን ነው ጉዳያችን መታየት ያለበት፣ በመዝገብ ተነጣጥለን ወደ ችሎት አንገባም በሚል ተነጣጥለው እንዲገቡ ሲጠየቁ ተቃውመው ወደ ቂሊንጦ ተመልሰዋል። ዳኞችም ቀጠሮም ሳይሰጡ ተመልሰዋል።

~ታህሳስ 11/2010 ዓ•ም

° በጠዋቱ የፍርድ ቤት የስራ ሰዓት እነ ጎይቶም ርስቃይ ላቀረቡት የክስ መቃወሚያ ብይን ይነበብ ሲባል፣ ተከሳሾቹ፣ ብይኑ ከመነበቡ በፊት ሀሳብ እንዳላቸው በመግለፅ እንዲናገሩ ጠየቁ። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ብይኑ የተሰራ ስለሆነ ይነበብ ሲል ተከሳሾች በዳኛ ዘርዓይ ወ/ ሰንበት መዳኘት እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱም ተቃውሞ በተነሳባቸው ዳኛ ዘርዓይ አማካኝነት ብይኑን ማንበብ ቀጠለ። ተከሳሾች ፊታቸውን በማዞር፣ ጆሯቸውን በእጃቸው በመድፈን ችሎቱን “አናይም፣ አንሰማም” ብለው ተቃውመዋል። ተከሳሾቹም ችሎቱን አናይም፣ አንሰማም ብለው ብይኑ ተነቧል።

° ታህሳስ 11/2010 ዓም በፍርድ ቤቱ የከሰዓት የስራ ጊዜ እነ የሻገር ወ/ ሚካኤል (35) ተከሳሾችም የመቃወሚያ ብይን ለማንበብ ስማቸው ሲጠራ አብዛኛዎች “አቤት” ባለማለታቸው ችሎት ውስጥ እያሉ “አልቀረቡም” ተብለው በፍርድ ቤቱ ተመዝግበዋል። ተቃውሞ የተነሳባቸው ዳኛ ዘርዓይ ብይን ለማንበብ ሲሞክሩ ተከሳሾቹ ባሰሙት ተቃውሞ ብይኑ ሳይነበብ ቀርቷል። ቀድመው ወደ ችሎት የገቡት ችሎት ታዳሚዎች እንዲወጡ፣ ውጭ የነበሩትም እንዳይገቡ ተደርጓል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *