የፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ታህሳስ 20/2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከሳሽ የፌደራል አቃቤ ህግ የኦፌኮ ፕሬዚዳንት በሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ላቀረበው ክስ ተጨማሪ ገላጭ ማስረጃዎች አሉኝ በሚል ያቀረበውን 10 የድምጽና የምስል የሲዲ ማስረጃዎች ተቀብሏል፡፡

አቃቤ ህግ እነዚህን ማስረጃዎች በተጨማሪነት ያቀረበው ሙሉ የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ከተሰሙና መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የተከሳሽ ጠበቆች ማስረጃዎቹ በማስረጃነት እንዳይያዙ በሚል ለፍርድ ቤቱ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ በትናንትናው ውሎው አቃቤ ህግ ገላጭ ማስረጃዎች በሚል ዘግይቶ ያቀረባቸው የሲዲ ድምጽ ወምስል ማስረጃዎች የመዝገቡ አካል ሆነው በማስረጃነት ሊያዙ ይገባል ወይስ አይገባም በሚል የግራ ቀኝ ክርክሩን አዳምጧል፡፡
በመሆኑም ፍ/ቤቱ በዛሬው ውሎው ብይን የሰጠ ሲሆን፣ ብይኑም የተከሳሽን ተቃውሞ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ በማድረግ የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን በማስረጃነት የተቀበለ ሆኗል፡፡ ማስረጃዎቹ በማረጃነት እንዲያዙ የተሰጠውን ብይን ተከትሎ የተከሳሽ ጠበቆች ማስረጃዎቹ ለተከሳሽ እንዲደርሳቸው ፍ/ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ በበኩሉ ማስረጃዎቹ ‹በባህሪያቸው የአመጽ ቅስቀሳን መልዕክት የሚያሳዩ በመሆናቸውና በግልጽ ለተከሳሽ ቢደርሳቸው ለሌላ አካል ተመሳሳይ ወንጀል መፈጸሚያ አላማ ሊውሉ ይችላሉ› በሚል የማስረጃዎቹን ለተከሳሽ እንዲደርስ የሚለውን ተቃውሟል፡፡ ‹‹ፍ/ቤቱ ማስረጃዎቹን በጽ/ቤት ተመልክቶ እንዲወስንልን ነው የምናመለክተው›› ብሏል አቃቤ ህግ፡፡ ጠበቆቹ በበኩላቸው ማስረጃዎቹ ለተከሳሽ የማይደርሱ ከሆነ በግልጽ በደንበኛችን ላይ ተጽዕኖ እየተደረገባቸው ስለመሆኑ ማሳያ ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን በችሎት አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው መንግስት ‹‹እኛ ባጠፋነው፣ በእኛ የመልካም አስተዳደር ችግር የተነሳ ተቃውሞ ነው›› በሚል ይቅርታ በጠየቀበትና ‹‹በተቃውሞ ድንጋይ የወረወራችሁብን ወጣቶች ስራ ስላልፈጠርንላችሁ ነው፣ የእኛው ጥፋት ነው›› በሚል በጀት ይዞ ወጣቶችን ወደስራ አስገባለሁ ባለበት ጉዳይ ላይ በተመሰረተባቸው ክስ አላግባብ እየተንገላቱ መሆናቸውን በችሎት ተናግረዋል፡፡

ፍ/ቤቱ ማስረጃዎቹ ለተከሳሽ ሊደርሱ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ለመወሰን ለታህሳስ 23/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የአቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን ለማድመጥ በሚል ደግሞ ሌላ ቀጠሮ ለታህሳስ 25/2010 ከሰዓት በኋላ ቀጠሮ ይዟል፡፡
በሌላ በኩል ዶ/ር መረራ በቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር የጠያቂ ገደብ እንደተጣለባቸው በመግለጽ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍ/ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም ዶ/ር መረራ ጉዲና በእስር ቤቱ አስተዳደር ገደብ እንዲደረግ የሚፈቅድ ህግ ከሌለ በስተቀር በሁሉም ሊጎበኛቸው በሚፈልጉ ወዳጅ፣ ዘመድ ሁሉ እንዲጠየቁ እንዲፈቀድ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ማናቸውም ህጋዊ የውል ስምምነት ያለው ጠበቃቸው የሆነ ሁሉ በእስር ቤቱ ተገኝቶ እንዲያነጋግራቸው እንዲደረግ ታዝዟል፡፡

Ethiopia Human Rights Project

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *