“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢህአዴግን ማዕከላዊ ላስታውሳችሁ!

ይህ ማዕከላዊ ውስጥ የተፈፀመ ነው። በደርግ ጊዜ የነበረ ሰው የፃፈው አይደለም። እኔ (ጌታቸው ሺፈራው) በ2006 ዓም አበበ ካሴን እስር ቤት ሄጄ አነጋግሬ የፃፍኩት ነው። በኢህአዴግ ዘመን የተፈፀመ ነው። ማዕከላዊ የተነቀለውን የአበበ የአንድ እግር ጣቱ ጥፍር እጄ ገብቶ፣ የነገረ ኢትዮጵያ ቢሮ ውስጥ ነበር። ከመታሰሬ በፊት። አሁን የት እንዳለ አላውቅም! በኢህአዴግ ዘመን የደረሰውን ሰቆቃ ግን ላስታውሳችሁ!

ስም: አበበ ካሴ 
እድሜ: 41
አድራሻ: ሰሜን ጎንደር/ አርማጭሆ
አሁን በእስር የምገኝበት: ቂሊንጦ(አሁን ቃሊቲ ማረምያ ቤትአሁን)
ጥር 12/ 2006 ዓ/ም ከተያዝኩ በሁዋላ ወደማዕከላዊ ወሰዱኝ:: በማዕከላዊ እስር ቤት ከ5 ወር በላይ ታስሬለሁ፡፡ ከዚህ መካከል 4 ወር ከ25 ቀናት በጨለማ ቤት ተቆልፎብኝ ቆይቻለሁ፡፡ ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት የሁሉም እግርና እጆቼ ጥፍሮች ተነቅለዋል፡፡ አንዳንድ ቀን እጄ ላይ የሆነ ነገር ስለሚወጉኝ ጥፍሮቼ ሲነቀሉ አላውቅም፡፡ ስነቃ ነው መነቀላቸውን የማውቀው፡፡ ከዛም ቁስሉን እየነካኩ ያሰቃዩኛል፡፡ ማደንዛዣ ለምን እንደሚወጉኝ አላውቅም፡፡ ጥፍሮቼን ሲነቅሉኝ ብቻ ሳይሆን ሌላ ጊዜም ራሴን እንድስት ያደርጉኛል፡፡ እጅና እግሬን አስረው እጅግ በጣም በሚቀዘቅዝ ቦታ ውስጥ ያስቆሙኛል፡፡

ለብዙ ሰዓት በጣም ቀዝቃዛ የሆነ ቦታ ላይ እስክደነዝዝ ቆሜ እውላለሁ፡፡ እስኪበቃቸው ከደበደቡ በኋላ እጅና እግሬን አስረው ከምርመራ ክፍሉ በታች በሚገኝ ምድር ቤት ክፍል ውስጥ ያለ ጉድጓድ ላይ ጥለውኝ ይሄዳሉ፡፡ ጉድጓዱ ጉንዳንን ጨምሮ ተባዮች ያሉት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እግሬንና እጄን አስረው ዘቅዝቀውኝ ይሄዳሉ፡፡ የመጣው ሁሉ ዝዋዥዌ እንደሚጫወት ህፃን ወዲያና ወዲህ ያደርገኛል፡፡ ገልብጠው አስረው ሲዘቀዝቁኝ በአብዛኛው ራሴን እስታለሁ፡፡ እግርና እጄን ከወንበር ጋር ያስሩኛል፡፡

ከወንዶች በተጨማሪ ሴቶችም ይመረምሩኛል፡፡ ሴቶቹ የሚመረምሩኝ ራቁቴን አርገው ነው፡፡ እነሱም ራቁታቸውን ሆነው ነው የሚመረምሩኝ፡፡ አሁን ለመናገር የማልደፈርው አፀያፊ ነገርም ፈፅመውብኛል፡፡ ይህን አፀያፊ ነገር የሚፈፅሙት አደንዛዥ እፅ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ በአይኔ አይቻቸዋለሁ፡፡ መርማሪዎቹ ሰውነቴን በኤሌክትሪክ አቃጥለውኛል፡፡

ኤሌክትሪኩን የሚሰኩት ደረቴና የውስጥ እግሬ ላይ ነው፡፡ በዚህም የውስጥ እግሬ ተገልብጦ ሌላ ሰውነት አምጥቶ ነበር፡፡ እጄን ወደ ላይ አስረው ብልቴ ላይ ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል፡፡ ሴቶቹ ሀይላንዱን የሚበቃቸውን ያህል ያወዛውዙታል፡፡ በዚህም ምክንያት የዘር ፍሬየን ከጥቅም ውጭ አድርገው ዘሬን እንዳልተካ አድርገውኛል፡፡ ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም ነበር:: ይህን ያህል አሰቃይተው ከጥቅም ውጭ ስሆን ቂልንጦ ወስደው ጣሉኝ፡፡ 11 ወር ያህል አልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ በኤሌክትሪክ ግርፊያው ምክንያት ግራ ሰውነቴ ሽባ ሆኖ ነበር፡፡ ግራ እግሬ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡፡ በምርኩዝ ነበር የምሄደው፡፡እረጅም ግዜ እያነከስኩ ነበር የምሄደው፡፡

በተለይ ማዕከላዊ ውስጥ ይህን ያህል ያሰቃዩኝ ምግንያቱ አንደኛ አብረውኝ ስለነበሩት ጏዶቼ እንዲሁም ስለ ድርጅቱ(ግንቦት 7) ሚስጥር እንድሰጣቸው ነው:: ፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚያሰቃዩኝ የት የት ቦታ ነው የሰለጠንከው እያሉ ነው፡፡
ቂልንጦ ከገባሁ በኋላም ያሰቃዩኝ ነበር:፡ ወጣቶች እንዳይቀርቡኝ ያስፈራሩዋቸዋል፡፡ ማንም ጠርቶ እንዳይጠይቀኝ ተደርጏል:: ፡ ጨለማ ክፍል ወስደውም አስረውኝ ያውቃሉ፡፡ እነሱ ደብድበው ከጥቅም ውጭ ካደረጉኝ በኋላ የምደገፍበትን ምርኩዝም ቀምተውኛል፡፡ቂልንጦ በነበርኩበት ክፍል ውስጥ እንድተኛበት የተሰጠኝ ቦታ ሽንት ቤቱ አጠገብ ነው፡፡ ሽንት እየሸተተኝ እተኛ ነበር፡፡ ‹‹ወደ ሌላ ቦታ ቀይሩኝ!›› ስላቸው ‹‹ደግሞ ለአንተ ይህ አንሶህ ነው?›› ይሉኛል፡፡ ያ ሁሉ ድብደባ ደርሶብኝ አልጋ ላይ በነበርኩበት ወቅት ወጣቶቹ ህክምና እንዳገኝ ወደ ሀኪም ቤቱ ወሰዱኝ፡፡ እነሱ ግን ‹‹ለአንተ ህክምና ሳይሆን ጥይት ነበር የሚገባህ›› ብለው መለሱኝ፡፡ እንዲህ እያሉ ለምን እንደማይገድሉኝ ይገርመኛል፡፡

አሁን በምገኝበት በቃሊቲ ማጎርያ ቤት ለብዙ ግዜ በጨለማ ቤት አስረውኝ ነበር::ከዛ ካስወጡኝ በሁዋላም ግብረ ሰዶም ፈፃሚዎች ከሚገኙበት ቦታ አብረው አስረውኛል:: 
ይህ በኔ ላይ የሚፈፅሙት በደል ሁሉ ሆም ብለው ነው:: አንድም በቀል ነው ሁለተኛም የአካል እና የዐይምሮ ሰቆቃ በኔ ላይ ለመፈፀም ነው::
ይህ የደረሰብኝ በደል ለኢትዬጵያ ህዝብ አንድነት በመታገሌ ነው:: ይህን ህዝብ ሊያውቅልኝ ይገባል:: ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈፀምብን ሀገራችንን ባልን ነው:: እኔ ለመሞትም ነበር በርሃ የገባሁት:: ነገር ግን እግዚአብሄር ያዘዘልኝ ይህ ነው እና ሁሉንም እቀበላለሁ:: እኛ እስረኞች ይህ ሁሉ በደል እየተፈፀመብንም ጠንካሮች ነን:: ያ ወኔያችን ከኛ ጋር ነው:: እኛ ተስፋ የምንቆርጠው ትግሉ የቀዘቀዘ እና ጠያቂ ያጣን ግዜ ነው:: የኢትዬጵያ ህዝብ ቁስላችን ሊያመው ስቃያችን ሊገባው ይገባል::

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0