ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ኢህአዴግን ጨምሮ አብዛኛው የጎሳና የዘር ድርጅቶች በሕዝብ ስም መማልና ሳይወከሉ የሕዝብ ውክልና ሲጎናጸፉ ማየት የተለምደ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ባይኖርም መገንጠል በሚል ሂሳብ ሲባክን የነበርረው ኦነግ ሳይሳካለት የአንድ ትውልድ እድሜ በልቶ ለአምስት ተከፍሎ ደብዛው ጠፍቷል። በውል የሚታይ ስራ እንደማይሰራ የሚነገርለት የኤርትራው ኦነጎችም አርጅተው ስለመረሳታቸው እንጂ ስለተስፋቸው አይሰማም። አሁን  በትግሉ ውስጥ ፊት ቆሞ ያለው ቄሮ የኦሮሞ ወጣቶች  ትግል ነው።

ቄሮ ከጀመረው የሰላማዊ ትግል ጎዳና ፈቀቅ ይላል ወይስ በዛው ይቀጥላል የሚለው በግልጽ ባይታወቅም ለኢህአዴግ ራስ ምታት ሆኖበታል። የህወሃት ንብረት ላይ ትኩረት አድርጎ ርምጃ የሚወስደው ይህ ንቅናቄ የታች መዋቅሮችን እንደበላቸው መነገር ከጀመረ ከርሟል። መዋቀሩ ወደ ሌሎች ክልሎችም እየሰፋ ህብረት እያደረገም እንደሆነ ይሰማል።

ቀደም ባለው የትግል ሃሳብና አካሄድ ” ስተናል” ያሉ ሲንጠባጠቡ፣ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ሲቀላቀሉ፣ የተቀሩት አዲስ መልክ ይዘው ተነሱ። የኦሮሞን ትግል በሚዲያ፣ በህቡዕ አደረጃጀትና በማህበራዊ ገጾች በማጀብ ያጋጋሉት አዲስ ሃይሎች የሚታወቅ የፖለቲካ ፓርቲ ባይኖራቸውም ትግሉን ስለማጋማቸው ኢህአዴግ ራሱ እውቅና የሰጠው ነው።

በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመታት ኦሮሚያ ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩት ፋኖዎች ” ቄሮ” በታችኛው ደረጃ የመንግስትን መዋቅር እጃቸው እስከማስገባት፣ በቀጥታ መመሪያ እስከመስጠት ደርሰዋል። የኦህዴድን መዋቅር ስብረዋል። በተለይም በክልሉ ነዋሪዎች ላይ የተካሄዱት ግድያ፣ እስር፣ ማሰቃየት ከፈጠረው የጎሸ ስሜት ጋር ተዳምሮ የቄሮ እንቅስቃሴ እንደተጠናከረና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን በርካቶች የሚናገሩት ሃቅ ነው።

ይህ በህቡዕ ተጠንስሶ እንደ ሰደድ እሳት የሰፋው እንቅስቃሴ ለመግታት አቋም መያዙን ሪፖርተር ዘግቧል። የሚወርድለትን መመሪያ የሚተገብረው፣ ትግሉ አገር ቤት መሆን አለበት ከሚሉ ወገኖች ጋር ትሥሥር እንዳለው የሚነገርለት ቄሮ ማለት የኦሮሞ ወጣቶች ሃይል ነው። ሪፖርተር እንዳለው የፌደራል ፖሊስ ይህንን ሃይል ሊመረምር ቆርጦ ተነስቷል። 

ዜናውን የሰሙ እንዳሉት ” ኢህአዴግ እስካሁንስ ቢሆን ምን እያደረገ ነበር?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “በሃይል ለመቆጣጠር ሞክሮ አልቻለም። በሚገድለው መጠን፣ በሚያስረው መጠን ትግሉ እየከረረ ነው” ሲሉ አሁን የፌደራል ፖሊስ ምርመራ የቄሮን ሃይል ሊገታው እንደማይችል ይገልጻሉ። የአውስትራሊያው ነዋሪና ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ እንዳለው ” ቄሮ ድፍን የኦሮሚያ የለውጥ ሃይል ነው። ይህንን ኢህአዴግም ያውቀዋል። የሚበጀው ይህንን ሃይል ምን እንደሚፈልግ ስለሚታወቅ ምላሽ መስጠት እንጂ ሌላው ተሞክሮ ከሽፏል። አነጣጥሮ ከመግደል የዘለለ …. ” 

ፌዴራል ፖሊስ ‹‹ቄሮ›› ተብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ ጥልቅ ምርመራ መጀመሩ ተሰማ

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹ቄሮ›› ተብሎ በሚጠራው የኦሮሞ ወጣቶች ቡድን እንቅስቃሴ ላይ ጥልቅ ምርመራ መጀመሩን ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች አመለከቱ፡፡

‹‹ቄሮ›› በሚል ስያሜ የሚታወቅ የኦሮሞ ወጣቶች ህቡዕ እንቅስቃሴ በምሥራቅ ሐረርጌ መንሰራፋቱን፣ በአካባቢው የመንግሥት መዋቅርን ተልዕኮ የመንጠቅ አዝማሚያ የያዘ እንቅስቃሴ ማከናወን ከጀመረ ወራት መቆጠራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን ከጂቡቲ ወደብ የሚያገናኘው ዋና መንገድ በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመበላሸቱ ሾፌሮች ከአዋሽ በድሬዳዋ አድርገው ወደ ጂቡቲ የሚያደርጉት ጉዞ በዚህ የወጣቶች ቡድን አልፎ አልፎ እየተስተጓጎለ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ መንገዶችን በመዝጋት የከባድ ተሽከርካሪዎችን ጉዞ የማሰናከል፣ እንዲሁም ጭነቶችን በማራገፍ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የማከፋፈል ተግባሮች መፈጸማቸውን፣ የአካባቢውን የመንግሥት መዋቅር የማዘዝና ትዕዛዙን በማይፈጽሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በኅዳር ወር መጨረሻ አካባቢ ጋራ ሙለታ በሚባል አካባቢ ከሚገኝ እስር ቤት እስረኞችን የማስለቀቅ ድርጊት መፈጸሙንም ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት በዚህ የወጣቶች ቡድን ላይ ምርመራ መጀመሩን፣ ይህንን ምርመራ የሚያከናውን ግብረ ኃይልም መቀመጫውን በድሬዳዋ ከተማ አድርጎ መሰማራቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግጭት ዜጎች እንዴት ሊፈናቀሉ እንደቻሉ ምርመራ እንዲያደርግ ያሰማራው ሱፐርቪዥን ቡድን ያጠናቀረውን ሪፖርት፣ ሐሙስ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ባቀረበበት ወቅት የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሰፋ በዩም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ራሱን ‹‹ቄሮ›› ብሎ የሚጠራው የወጣቶች እንቅስቃሴ በምሥራቅ ሐረርጌ ሥጋት የፈጠረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ተልዕኮ የማስተጓጎልና አንዳንዴም ግብግብ ውስጥ ሲገባ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የወጣቶች እንቀስቃሴ ውስጥ የአካባቢ ሚሊሻዎች፣ አንዳንድ የአካባቢው ፖሊሶችና የወረዳ አመራሮች ተሳትፎ ስለማድረጋቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ የመንግሥት ተሽከርካሪዎችም ጥቅም ላይ ውለው እንደታዩ አብራርተዋል፡፡ ይህ ኃይል እንዴት ተደራጀ? ዓላማው ምንድነው? የሚለውን የተጀመረው ምርመራ በጥልቀት ዘልቆ የሚመልሰው ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ጠናቀረውግምን- T2

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *