ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለተለያዩ ሱሶች አጋላጭ የሆኑ የንግድ ተቋማት ከትምህርት ተቋማት የሚኖራቸውን ርቀት የሚወስን ደንብ ተዘጋጀ

የትምህርት ሚኒስቴር ለተለያዩ ሱሶች አጋላጭነት ያላቸው የንግድ ተቋማት ከትምህርት ተቋማት የሚኖራቸውን ረቀት የሚወስን ደንብ ማዘጋጀቱ ገለፀ።

በየጊዜው በትምህርት ተቋማት አካባቢ ተማሪዎችን ለአደንዛዥ እጽ እና ለመጤ ጎጂ ባህሎች የሚያጋልጡ የራቁት ጭፈራ ቤቶች እና ሌሎችም መስፋፋታቸው ነው የሚገለጸው።

ይህም በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘንድ በስፋት ይስተዋላል። ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፥ የንግድ ማእከላቱ በዩኒቨርስቲ በር ላይ ስለሚገኙ በተማሪዎች የአደንዛዥ እጽ አጋላጭ ሁኔታዎች መስፋፋት ከፍ ማለቱን ነግረዉናል።

በተጨማሪ በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ የመጤ ጎጂ ባህሎች የሚፀባረቅባቸው የራቁት ጭፈራ ቤቶች መበራከት፣ አደንዛዥ እጽ የሚዘወተርባቸው ማአከላት መሰፋፋት አሳሳቢ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መካላከያ እና መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ አስማረ በበኩላቸው፥ በዩንቨርሲቲው አቅራቢያው የሚገኙ እና ተማሪዎችን ለአደንዛዥ እጽ የሚያጋልጡ የንግድ ማእከላት ላይ አቅጣጫ እንዲሰጥ ሆነ እንዲስተካከል በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ቢገለፅም የተወሰደ እርምጃ ግን የለም ይላሉ። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በዩኒቨርስቲው በርካታ ለአደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት የተጋለጡ ተማሪዎች ይገኛሉ።

ተማሪዎችን ከአደንዛዥ እፅ ሱስ ለመመለስ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ያሉ ሲሆን፥ በዛው የማገገሚያ ማእከላት ለመስራት በእቅድ መያዙንም አስታውሰዋል። 

ይሁን እንጂ በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች በአቅራቢያ ያሉ ለአደንዛዥ እጽ የሚያጋልጡ ስቆችን ከአካባቢው የማንሳት ስራ ባይሰራም በመቐለ ዩኒቨርስቲ ግን ተግባራዊ ሆኗል።

በዚህም የንግድ ማእካላቱ ከዩኒቨርስቲው አካባቢ እንዲርቁ የተደረገ ሲሆን፥ በተጓዳኝ ደግሞ በዩኒቨርስቲው ውስጥ 70 ለተማሪዎች አስፈላጊ ግብአቶች የሚቀርቡበት የመሸጫ ማእካላት ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ስለሆነም በዩኒቨርስቲው ምርምር እና የማህበረሰብ ግንኙነት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፎትየን አባይ፥ በሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም እንዲህ ያለ ተግባር ሊሰራ ይገባል ባይ ናቸው።

የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ እርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፥ ከአደንዛዥ እጽ እና ከጎጂ መጤ ባህሎች ተማሪዎችን ለመከላከል ሲባል የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻም በዩኒቨርስቲዎች አቅራቢያ ለተማሪዎች የሚጠቅሙ የንግድ ተቋማት ናቸው ሊመሰረቱ የሚገባ።

የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ወጣቶች እና ታዳጊዎች ከተለያዩ ሱሶች የፀዱ፣ በስነ ምግባር የታነጹ፥ አገር ወዳድ እና በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ የሚረዱ ጉዳዮች በስርአተ ትምህርት እንዲካተቱ ማድረግ ላይ ያተኮረ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።

በዚህ መልኩ የትምህርት ሚኒስቴር የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባት በተደጋጋሚ ጥናት በማድረግ ደንቦችን አዘጋጅቷል።

ይህ ደንብ በዩኒቨርስቲ አካባቢ የሚገኙ የሱስ አጋላጭ የንግድ ማእከላት በምን እርቀት ላይ መገኘት አለባቸው የሚሉ እና በክበባት አደረጃጀት ላይ ያተኮረ ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር ጉዳዮች ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ከተማ መስቀላ፥ በትምህርት ቤቶች ጥናት ተደርጎ በመጨረሱ አሁን ላይ የደምብ ዝግጅት እያደርግን ነው ብለዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ደንብ ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ ግልጽ ባይሆንም በባለድርሻ አካላት በዘርፉ እየተዘጋጀ ያለው ማሻሻያ አዋጅን ተከትሎ ተግባራዊ ይደረጋል ተብለዋል።

ንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ በትምህርት ተቋማት አቅራቢያ የሚስተዋለውን የአደንዛዥ እፅ መሸጫ፣ የራቁት ጭፈራ ቤት እና ሌሎችንም መስፋፋትን ተከትሎ የንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ስርአቱን ፈትሾ የፍቃድ አሰጣጥ ላይ ማስተካከያ ማድረጉን ገልጿል።

በንግድ ሚኒስቴር የሚንስትሩ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንዱ አዱኛ፥ በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮች በመለየት ማስተካከያ ይደረጋል ነው የሚሉት።

ይህም በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ እና ለሱስ አጋላጭ የንግድ ተቋማትን በማስቀረት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።

በታሪክ አዱኛ – ፋና ብሮድካስቲንግ

Related stories   የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ