“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሀሰት ክስ ሰለባዎች

 +ጌታቸው ሽፈራው
  • በቃጠሎው ወቅት አጠገባችን ሜዳ ላይ በጥይት የተገደሉ ወንድሞቻችን የጥይቱ ምልክት እንዳይታይ አሻራውን ለማጥፋት እና ከተጠያቂነት ለመዳን ሲሉ እየተቃጠለ በነበረ ቤት ውስጥ ከተው በእሳት አክስለዋቸዋል።
  • ሸዋሮቢት ተወስደን ኢሰብአዊ ድርጊት እንደተፈፀመብን፣ ጥፍራችን በፒንሳ እንደተነቀለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሀውልት የተሰራለት የቶርች ገረፋ እንደተፈፀመብን፣ ውስጥ እግራችን እና ጀርባችንን በሚስማር እንደተበሳሳ… ተረጋግጧል።

ሚስባህ ከድር ዑመር (በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ 22ኛ ተከሳሽ

Qilinto, Ethiopia’s Maximum Security Prison

በሙስና ወንጀል ተጠርጥሬ ዐቃቤ ሕግ የዋስትና መብቴን ከልክሎኝ በጊዜ ቀጠሮ ከ3 አመት በላይ ከታሰርኩ በኋላ ነፃ ተብያለሁ። በመታሰሬ ምክንያት ስራዬ ተበላሽቶብኛል። ቤተሰቦቼ ተበትነዋል። የማይተካ እድሜዬን ባልሰራሁት ስራ በከንቱ በእስር ቤት አሳልፌያለሁ። ዐቃቤ ሕግ በፈፀመው ስህተት እየተጠየቀ አይደለም። በሀሰት 3 አመት በላይ ታስሬ ነፃ ስባል ካሳ የምጠይቅበት የህግ አግባብ እንኳን የለም። ዐቃቤ ሕግ የፈለገውን ሰው ላይ ዋስትና በሚያስከለክል ከባድ ክስ መስርቶ፣ እንደፈለገው እያሰረ፣ በጊዜ ቀጠሮ ዜጎችን ያጉላላል። በዚህ ሀገር የዐቃቤ ሕግ ስልጣን ገደብ አጥቷል።

እኔ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ጋሰሬ ቀበሌ መሬት በሊዝ ወስጄ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ዲዛይን አስፀድቄ፣ የግንባታ ፈቃድ አውጥቼ፣ ዋቤ ኢኮ ሎጅ የሚባል ብዙ ሚሊዮን ገንዘብ አፍስሼ እየገነባሁ እያለሁ በሀሰት በሙስና ወንጀል ታስሬ ቆይቻለሁ። በሀሰት በታሰርኩበት ነፃ ተብዬ የምፈታ ሰው ማረሚያ ቤት ውስጥ ሆነህ የግንቦት 7አባል ሆነህ፣ ነሃሴ 28/2008ዓም በቂሊንጦ እስር ቤት በተነሳው እሳት ቃጠሎ ለሰው ህይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ምክንያት ሆነሃል፣ ለ”ዱርዬው ቡድን” የገንዘብ ድጋፍ አድርገሃል፣፣ ተልዕኮ ተቀብለህ ተልዕኮ ሰጥተሃል ተብዬ በሀሰት ለፖለቲካ መልስ ማገዶ ሆነኛለሁ።

የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጅ በመሆኔ ብቻ የግንቦት 7 አመራሮች ስም በመጥራት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ዶ/ር ታደሰ ብሩ ዘመዶችህ ናቸው፣ስለነሱ የምታውቀውን አውጣ እየተባልኩ ከምርመራ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ በደል ተፈፅሞብኛል። የተፈፀመብን በደልም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ጭምር የተረጋገጠ ነው። እኛ (38ቱ ተከሳሾች) በሌላ አካል ሀጥያት በማንነታችን ምክንያት ነው የተከሰስነው። ሌላ አካል በፈፀመው እኛ ማገዶ ሆነናል። የጉራጌ እና የአማራ ተወላጆች በግንቦት 7፣ የኦሮሞ ተወላጆች ኦነግ፣ ድምፃችን ይሰማ ብለው በመጠየቃቸው የታሰሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች አልሻባብ፣ በወንጀል ተከሰው የታሰሩ የድሃ ልጆች ደግሞ “የዱርዬ ቡድን” እና ከላይ የጠቀስኳቸው ድርጅቶች “ተላላኪ” በሚል ተከሰናል። ወንጀሉን የፈፀሙትን፣ ወንድሞቻችንን የገደሉብን የህወሓት አባሎች ከተጠያቂነት ለማዳን ሲባል ብቻ በማንነታችን ተለይተን በሀሰት ተከሰናል።

ለክሱ ባለቤት ሊሰጠው ይገባል። እኛ ምስክሮች ነው መሆን ያለብን። እንኳን ከጥይትና እሳት ተረፋችሁ መባል ሲገባን በሀሰት መከሰሳችን አግባብ አይደለም። ጓደኞቻችን ፊታችን ላይ ተገድለውብን ሀዘኑ ሳይወጣልን እኛም በሀሰት ክስ መሰቃየት የለብንም። እኛ የተሸከምነው የሌላ ሰው ሀጥያት ነው። ነሃሴ 28/2008ዓም ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ወቅት በጥይት ሲገድል እና ሲያስገድል የነበረው የማረሚያ ቤቱ ጥበቃና ደህንነት ኃላፊ የነበረው ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ አብርሃ ወንድሞቻችንን የገደለውና ያስገደለው ሳያንስ፣ በሀሰት ከቦታው ያልነበሩ ተከሳሾች ላይ መስክሯል።

ነገር ግን ሀሰት እውነትን አትቀድምም። ሞቱ ከተባሉት በክስ ዝርዝራችን ያልተጠቀሰ “ቴዎድሮስ” የሚባል እስረኛ ተገድሏል ብሏል። ይህም ጠያቂ ዘመድ የሌላቸው ሞቱ ከተባሉት 23 ግለሰቦች ስም ዝርዝር ያልተካተቱይህም መሆኑን፣ በቃጠሎው ከሞቱት በላይ ዜጎች መገደላቸውን በግልፅ የሚያስረዳ ነው።

ዐቃቤ ሕግም ሆነ ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ ለፖለቲካ መልስ እንጅ የወንድሞቻችን ሞት አያስጨንቃቸውም። ቢያስጭንቃቸውና እውነት እንዲወጣ ቢፈልጉ ኖሮ ቴዎድሮስ የተባለው ሟች 24ኛ ተደርጎ ከሟቾች ስም ዝርዝር ጋር አብሮ መቅረብ ነበረበት። ነገር ግን የሟች ቤተሰቦች ልጃቸውም ማን እንደገደለባቸው ስለሚያውቁ አንድም ቀን እንኳ ችሎት ቀርበው፣ ጉዳይ ተብለን በሀሰት የተከሰስነውን ጉዳይ ተከታትለው አያውቁም።

በቃጠሎው ወቅት አጠገባችን ሜዳ ላይ በጥይት የተገደሉ ወንድሞቻችን የጥይቱ ምልክት እንዳይታይ አሻራውን ለማጥፋት እና ከተጠያቂነት ለመዳን ሲሉ እየተቃጠለ በነበረ ቤት ውስጥ ከተው በእሳት አክስለዋቸዋል። በክዝ መዝገብ ላይ የሟቾች ፎቶ ማስረጃ ላይ ሳይ በጣም ደንግጫለሁ። በወንድሞቻችን ላይ የግፍ ግፍ ተፈፅሟል።ይህ እውነት አንድ ቀን ይወጣል። የክስ ማስረጃው ላይ የሟቾቹን አስከሬን ፎረንሲክ ማንሳት ሲገባው አለማንሳቱ ተገለፆአል። ይህም ሆን ተብሎ እውነቱን ለመደበቅ የተሰራ ሴራ ነው።

ዐቃቤ ሕጉ በምርመራ ወቅት ሸዋሮቢት እንደነበሩ በችሎት ፊት አምነዋል። ነገር ግን ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት የሄድኩት በተከሳሾች ላይ የሚፈፀም በደል ካለ ለማጣራት ነው ብለዋል። እኚህ ዐቃቤ ሕግ አንድም ቀን በእኛ ላይ ስለተፈፀመው ኢሰብአዊ ድርጊት ለችሎት አላስረዱልንም። በተቃራኒው ያለምንም ተፅዕኖ ቃላችን እንደሰጠን ዋሽተው መስክረዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ግን እኛ ከተመረመርን ከ10 ወር በኋላ ባካሄደው ምርመራ ወደ ሸዋሮቢት ተወስደን ኢሰብአዊ ድርጊት እንደተፈፀመብን፣ ጥፍራችን በፒንሳ እንደተነቀለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሀውልት የተሰራለት የቶርች ገረፋ እንደተፈፀመብን፣ ውስጥ እግራችን እና ጀርባችንን በሚስማር እንደተበሳሳ… …ወዘተ በዝርዝር አረጋግጧል። እኚህ ዐቃቤ ሕግ በትኩስ ቁስላችን፣ በምርመራ ወቅት ያዩትን ክደዋል። ታዲያ ማን ነው ትክክል? ተሳሽ ዐቃቤ ሕግ ወይስ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ሪፖርት ያቀረበው ሪፖርት? ጠባሳ ሆኖ የቀረውን ገላችንን ለፍርድ እተወዋለሁ።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0