በገነት ዓለሙ

ኢሕአዴግ ከታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ያካሄደውን ‹‹የሁኔታዎች ግምገማ›› ካጠናቀቀ በኋላ፣ በተለይም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት አምስት ሰዓት የፈጀ ‹‹መግለጫ›› ግንባሩ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ችግር እንዳለበት ነግሮናል፡፡ ኢሕአዴግ ችግር አለብኝ ሲል ይህ የመጀመርያው ጊዜ አይደለም፡፡ እንዲያውም በመጀመርያው የተሃድሶ ወቅት (1993) ኢሕአዴግ በራሱና በአገዛዙ ውስጥ ስለነበሩት ድክመቶችና ችግሮች መናገሩ፣ በዚያው ጊዜም ራሱን የሚተችና ጥፋቱን የሚያምን በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥ ኢሕአዴግ ብቸኛው ነው ብሎንም ነበር፡፡

የሁለተኛውን የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ የግምገማ ወሬ፣ ዜናና ሪፖርት የተለየ የሚያደርገው ግንባሩ በሰጠው ‹‹የእምነት ክህደት ቃል›› እኔ ያልኩት ካልሆነ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የማለት ችግር ያለበት መሆኑን ነው፡፡ እኔ ብቻ ባይነት ደግሞ የኢሕአዴግ የችግሮች ሁሉ ችግር ነው፡፡

ኢሕአዴግ እኔ ብቻ ካልገዛሁ፣ ሁሉን እንቅስቃሴ ተቀጥላዬ ካላደረግሁ የሚል ድርቅናው በቀላሉ የሚበገር አይደለም፡፡ ሕዝቦች ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የተላቀቁበት ለውጥ፣ ስለዚህም የተገኘው ሥልጣን የመስዋዕትነቴ ውጤት ነው፣ የሕዝቦችን ጥቅም የምወክልና የማራምድም እኔ ብቻ ነኝ፣ እኔንና መስመሬን የተቃረነ ጠላት (የኢሠፓ ርዝራዥ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ወይም አሸባሪ) ነው የሚል ወፍራም የብረት ጡሩር የተላበሰ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ትምክህተኛን የሚንቀው ኢሕአዴግ አውራ ትምክህተኛ ሆኖ ኖሯል፡፡

ነፃ ገበያ፣ የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ባይነት በስተኋላ የመጡና ከተለወጠው የዓለም ሁኔታዎች ጋር ራሱን የማስማሚያ ዘይቤዎች ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽም፣ በተዘዋዋሪ መንገድም ከተካተቱ በኋላ ደግሞ ትርጉም የሚኖራቸው የኢሕአዴግ የበላይነት እስከተከበረ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ቂሉ ደርግ ኢኮኖሚውና ቢሮክራሲው ውስጥ ይርመሰመስ የነበረውን ጉቦ ላያሸንፈው ጠላቴ እንዳለ ሞተ፡፡ ብልጡ ኢሕአዴግ ግን በአንድ በኩል አጠፋለሁ ብሎ እየታገለ፣ በሌላ ጎን ወዳጅ አድርጎና አክብሮ ሥልጣን ለማጎልበት ሰው (ሎሌ) ለመግዣነት አዋለው (እኛም “ወሮታ” የምንለው ማዕረጉን ላለመንካት ነው)፡፡ የኢትዮጵያ ልማትና መንበረ ሥልጣን ሳይቀር የወሮታና የአርጩጫ ባህርይ ተጎናፅፏል፡፡ ልማቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣  የኢሕአዴግን ሥልጣን በክፉ እንዳያይ መሸበቢያ ወሮታው ነው፡፡  ኢሕአዴግ በልማት እስከተጋና ሕዝብን እስካማለለ ድረስም በገዥነት መንፈላሰስ ወሮታው ነው፡፡

የኢሕአዴግ የበላይነት የግድ መሆን ያለበት ነው፡፡ ይህ ከሸፈ ማለት ስንቶች የተሰውለት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማ ከሸፈ ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳይደርስ ኢሕአዴግ በሚቻለው ሥልት ሁሉ በጉልበትና በሸፍጥ መንገዶች ጭምር መዋደቅ የታጋይ ግዴታ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የተገራው፣ ተቦክቶ የተሠራው በዚህ አመለካከትና አካሄድ ነው፡፡

ስለነፃ ምርጫና ስለነፃ ፍርድ ቤት እያወሩ በተግባር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መቆጣጠር፣ ያወጡትን ሕግና ደንብ በሥውር መጣስ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ጥፋት ፈልጎ  ማጥመድና ማሸት፣ ማስፈራራት፣ አፍኖ መውሰድና ደብዛ ማጥፋት ሁሉ የማያሳፍሩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ፀሮች የመታገያ መንገዶች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ዕድገት፣ ሹመት፣ የጥቅማ ጥቅም ዕድሎችም እንዲሁ ‹‹ደጋፊ›› የማባዣ መሣሪያዎች ሆነው አገልግለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ነፃ የብዙኃን መድረኮችን አላበረታታ ያለው፣ ኋላም ያጠፋውና በምትካቸው በብዛት የራሱን ‹‹አደረጃጀት›› የፈጠረው፣ በግል ጋዜጦች፣ በ(ኢ)ሠመጉ፣ ወዘተ የሚወጡ ዘገባዎችን ጉድፍ መመልከቻ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ፣ የጠላት ጥቃት እንደተፈጸመበት አድርጎ ሲያይ የቆየውና ለተወሰነ ጊዜ ቦግ ብሎ እስከ አዟሪ ድረስ የወረደ የሥራ ዕድል ጭምር ፈጥሮ የነበረውን የኅትመት ሚዲያ የሰነከለው ከእነዚህ ችግሮች የተነሳ ነው፡፡ የሙያ/የብዙኃን ማኅበራቱን ተቆጣጥሮ የራሱ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ ማድረግ ሲቻለው፣ ‹‹ከፖለቲካ ነፃ የሚሆን የለም›› እያለ አልጠመድ ያለውን ማኅበር ደግሞ ‹‹ከበስተጀርባው የፖለቲካ ዓላማ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ሥራ የሚሠራ›› ብሎ እየፈረጀ፣ እየሰረሰረና ሌላ ተለጣፊ ፈጥሮ ንትርክ ውስጥ እየከተተ ወይም እያገደ ወይም እያደከመ በመተው የጀመረው የመጀመርያ ምዕራፍ ለአሁኑ የለየለት ‹‹ዕድገት›› አብቆቶታል፡፡፡ ዛሬ አደረጃጀት ማለት የኢሕአዴግ ሥጋና ደም፣ ሥርና ጅማት ሆነው የሚያገለግሉ ያለቀላቸውን ዕቅዶቹንና ውሳኔዎቹን በኮንፈረንስ፣ በስብሰባ የሕዝብ ውሳኔ/አስተያየት እያደረገ የሚያቀርብባቸው ለሕዝባዊ አሠራሩ ማረጋገጫነት የሚጠቅምባቸው የራሱ ፍጡሮች ናቸው፡፡

የኢሕአዴግ እኔ ብቻ ልክ ባይነት ደግሞ ዴሞክራሲው ላይ አደጋ አድርሷል፡፡ አገርን ለፍጅት አደጋ አጋልጧል፡፡ የሰብዕና ዝቅጠት አስከትሏል፡፡ የመንግሥት አገልግሎትን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲዘፈቅ አድርጓል፡፡ በተለይ በሰብዕና ላይ የደረሰው ጉዳትና ድቀት አገርን በከፋ አደጋ ውስጥ ጥሏል፡፡ ነፍስ በማስመሰል ሥለት ተገዝግዛ ሽባ ሆናለች፡፡ ከሽባነትም በላይ የመንግሥት፣ የፓርቲና የአለቃ ንብረት ሆናለች፡፡ ያመኑበትን ፊት ለፊት ተናግሮ የመኖር ክብር ጠፍቷል፡፡ የዝምታ፣ የምንተዳዬና የማረጥረጥ ኑሮ ውጦናል፡፡   

የአንድ አገር በዕድገትና በልማት የመቀጠል ዕጣ በዋናነት በዜጎቿ ሰብዕና መፋፋት ወይም መደህየት የሚወሰን ነው፡፡ የሰው ልማት ሲባል ልዩ ልዩ ሙያዎችን በተለያየ ብስለት እያስታጠቁ ለሥራ ገበያ መመገብ ብቻ አይደለም፡፡ ስምር በሆነ ሰብዕና (በሀቀኝነት፣ በታታሪነት፣ በቅንነት፣ ለሙያና ለህሊና በመታመን) የበለፀጉ ሰዎችን በማፍራት ረገድ አንድ አገር ያላትን ማህፀን በማለምለም ላይ መሥራት የሰው ልማትን ቁልፍ ማግኘት ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የያዘው መንገድ ይህንን ቁልፍ የሚያሳጣ ብቻ ሳይሆን አቆርቁዞ ለውድቀት የሚዳርግ ነው፡፡

የይፋና የጓዳ የፖለቲካ መድረካችን ዝጉርጉር ሐሳቦችን ከማፍራትና ከመፈልፈል ጋር አልተዋወቅ ያለው፣ ከፖለቲካ በመለስ ባሉ ጉዳዮች እንኳን ከራሳችን የተለየ ሐሳብ ለመስማት ቻይነት ያሳጣን፣ ሐሳባችን ሲተች ኩርፊያን፣ ሐሜትን፣ ጥቃትንና መሠሪነትን መሣሪያ ከማድረግ ከጥንት ከጠዋት ሕይወታችን መልሰን መውጣት ያልቻልነው፣ የተለየና የሚቃረን ሐሳብን የማቅረብ ነፃነትን ጥቅሜ ብሎ የማድመጥ፣ የመከራከርና ቅያሜ ሳይቋጥሩ የመለያየት ፀጋ የራቀን፣ ኢሕአዴግን ራሱን ‹‹ውስጠ ዴሞክራሲ›› ያሳጣው ሰብዕናችን ላይ የተሠራው ጥፋትና ክፋት ነው፡፡

የእኔ መስመርና አቋም ብቻ ትክክል፣ ሌላው አጥፊ ብሎ የደመደመ አመለካከት ሁሌ ትክክለኛ መሆን እንደማይቻል መቀበል የተሳነውና ከጥፋቶች ለመማር የማያስችል ነው፡፡ ኢሕአዴግ በትግልና በገዥነት ታሪኩ ውስጥ ያለፈባቸውን ጥፋቶችና ስህተቶች በጥሞና ቢያስተውል እንኳ፣ ከእኔ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ባይነትን እርግፍ አድርጎ ለመጣልና አቋሙን ሁሌም በጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶ ለመፈተሽና ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ ሐሳቦችን በተከፈተ አዕምሮ ወደ መመርመር ለመሸጋገር ከበቂ በላይ ትምህርት ባገኘ ነበር፡፡ የልማት ትልም ከተለያዩ አስተሳሰቦች፣ ጥናቶችና ትችቶች ጋር ተገጣጥሞ መፈተሹ እንከኖችን ለማጣራትና ትክክለኛ ሐሳቦችን ለማበልፀግ የሚቻልበት ሒደት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነት ሒደት ርቆ ብቸኛ አስተሳሰብ የመሆን እንቅስቃሴ ዞሮ ዞሮ የሕዝብ ህሊናን አውሮ በላዩ ከመንፈራጠጥ ዓላማ አያመልጥም፡፡ የልማታችን መቀጠል የሚሻው የአንድ ቡድን ሥልጣንን መተኪያ የለሽነት ሳይሆን፣ ሥልጣን ላይ ማንም ወጣ ማን ሐሳብን፣ ዕውቀትንና ችሎታን ሳይሰስቱ ማዋጣትን፣ የሁላችንንም አስተዋጽኦ አስተባብሮና ጨምቆ ለማሠማራት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠርን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች መሆናቸውን፣ ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ብቻ እንዲታመኑና እንዲገዙ ኃላፊነትን ያሸክማል፡፡ ኢሕአዴግ ግን የፓርቲ አባላቱ እንደራሴዎች ታማኝነታቸው ለፓርቲያቸው አቋም ነው ይላል፡፡ መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን የሚሰፍርላቸው ፓርቲው ነው፡፡ ምሳሌ ልስጥ፣ በ2007 ዓ.ም. ጥቅምት 20ዎች ውስጥ የሕግ አውጪ፣ የሕግ ተርጓሚና የአስፈጻሚ መስተጋብርን በተመለከተ በተካሄደ ውይይት ላይ የኢሕአዴጉ ሰው፣ በኢሕአዴግ ውስጥ የፖሊሲ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ ልዩነት እንዲኖር እንደማይፈቀድ፣ ግራ ቀኝ የሚጎትት የፖሊሲ ልዩነት ያለው ሰው አማራጩ ፓርቲ መልቀቅ እንደሆነ፣ በተቆመለት ፖሊሲ አፈጻጸምና በአስፈጻሚው አሠራር ላይ ግን መከራከር እንደሚቻል ገልጸውልናል፡፡ በአንድ ወቅት ስህተት ያሉት ፖሊሲና አቋም በሌላ ጊዜ ትክክል ሊሆን፣ ልክ ብለው የያዙትም ስህተት ሊሆን ከመቻሉ እውነት ጋር ኢሕአዴግ እንደተለያየ፣ በሐሳብ ፍጭት ፖሊሲን በመፈተሽ ፈንታ ታቦት ከተደረገ ፖሊሲ ያፈነገጠ ሐሳብን ከፓርቲ እያበረረ የሚኖር እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ከውስጥ ወደ ውጭ ወጥቶ በሌሎች ፓርቲዎችና በኅብረተሰቡ ላይ የተጫነውም ይኸው አንድ ዓይነት አቋም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከያዘው ታቦት አቋም ውጪ የሆኑ ሌሎች አቋሞች የጠላት አቋሞች ሆኑ፡፡ ኅብረተሰብም የኢሕአዴግን ፖሊሲ ሳይነካ አፈጻጸምን ብቻ እየተቸ እንዲሰግድ ተፈረደበት፡፡ ኢሕአዴግ ከራሱ ፓርቲ ውጪ (ከተቃራኒም አካባቢ) ሊገኝ የሚችል ትክክለኛ ነገርን እንዳያይ ራሱን ከመዝጋትም አልፎ፣ ሕዝብ አንድ ፓርቲ ቢያጠፋ ወደ ሌላው ዞሮ ገዥ እንዳያማርጥ መንገድ ዘግቷል፡፡ ከኢሕአዴግም ሆነ ከተቃዋሚዎቹ በኩል ተቃራኒ አቋም በቅን ዓይን አለመታየቱም፣ ከሁለት በኩል ያሉ/ሊኖሩ የሚችሉ በጎና ትክክለኛ ነገሮችን ፈልፍሎ የማየትና አንድ ላይ የመሸረብ የዕውቀት ሒደትን አፍኖ ቆይቷል፡፡ በነፃ ማሰብ (ማወዳደር፣ ማነፃፀር፣ ማንጠር) የኅብረተሰቡ ትርታ እንዳይሆን፣ በማውገዝና በማወደስ መሀል ብቻ እንዲወዛወዝ ዳርጓል፡፡ ቁጥራችን ከ100 ሚሊዮን ያለፈ፣ ብዙ ቋንቋዎች የምንናገር ሰፊ አገር ነን፡፡ በሐሳበ ብዙነት ረገድ ግን ጠበናል፣ ትንሽ ሆነናል፡፡ ብዝኃነት ውሸት ሆኗል፡፡

ፕሮፓጋንዳ፣ ስለላና ግልብልብነት ሰቅዞናል፡፡ ኢሕአዴጋዊው ‹‹ትክክለኛ›› መስመርና ‹‹ተደናቂ›› የትግል መሪነት በየአቅጣጫው (በ‹‹ሥልጠና›› በኮንፈረንስ፣ በመገናኛ ብዙኃንና በሰው በሰው) አዕምሮን እየወረረ ያጥባል፣ በሌላ በኩል አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ቀደም፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ዓይንና ጆሮ የሌለው መንግሥት አይደለም›› እንዳሉት ዓይንና ጆሮ ያልተዘረጋበትና ያልሰረገበት የሕይወት ዘርፍ የለም፡፡

አዳዲስ አዕምሮ የሚፈራበት ትምህርት ቤት ውስጥ (ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ድረስ) የመንግሥት ዓይንና ጆሮ (ሠራተኛ፣ ተማሪ፣ አስተማሪ ሆኖ) እየተርመሰመሰ መተንፍሻና መላወሻ አሳጥቷል፡፡ በዚህ ላይ በገፍ የተስፋፉት ትምህርት ቤቶች፣ ብቃትና ፈጠራዊነት ባላቸው መምህራን ማነስና ተጠንቶና ለፈተና ተተፍቶ በሚረሳ የትምህርት ዘይቤ የተጠመዱ ናቸው፡፡ ወጣቶቿ በየብስለት ደረጃቸው ማሰብን (ማስተዋል፣ መረጃን በፈርጅ መለየት/ማዛመድ፣ መተንተን፣ መፈተሽና ንጥር ሐሳብ ማርቀቅ) አለመማራቸው፣ በፍላጎትና በእውነተኛ ስሜት ነገሮችን የመሥራት ልምምድ በአግባቡ አለማዳበራቸው፣ በየደረጃቸው ስለአገራቸው ጉዳዮች በነፃነት እንዲወያዩና ኃላፊነት የመሸከም ልምምድ እንዲያደርጉ አለመለቀቃቸው፣ እንዲያውም ከመንግሥታዊው መስመር ዘወር ያለ ሙከራ ሲያደርጉ በጥርጣሬ መታየታቸው፣ ሊቃውንቱም የዚህ ዓይነት ባህል ለማስተላለፍ ድልድይ የመሆን ኃላፊነት እየተወጡ አለመሆናቸው፣ ከዚህ ሁሉ ይበልጥ ዋናው ጥረት የእበላ ባይነትና አጨብጫቢነት መጫወቻ እንዲሆኑ በመግራት ላይ ማተኮሩ አገሪቷን የተረካቢ ደሃ እያደረጋት ነው፡፡

የግልብልብ ትምህርት ውጤት የሆኑ ጥራት የለሾች ተመልሰው አስተማሪ የሚሆኑበት፣ ጥቂት በሳሎች ቢገኙ በመንግሥታዊ ፖለቲካ አጉላሊነትና በአስተዳዳራዊ አድልኦ እየተመረሩ የሚለቁበት፣ ጭራሽ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ እናስተምር ብለው ሲያመለክቱ ለርዕዮተ ዓለማችን ጠንቅ ይሆናሉ በሚል ፍርኃት በደጅ እንዲቀሩ የሚደረግበትም ጉድ አለ፡፡ በቁሳቁስና በባለሙያ ዝግጀት ልክ ያልተመጠነው ‹‹የትምህርት መስፋፋት (ቤት ሠርቶ ገፍ ተማሪ መቀበል) በራሱ ለጥራት ጥበቃ ወጥመድ ሆኗል፡፡ ለየደረጃው የሚገባውን ዕውቀት ያሟሉትን እየለየን እናሳልፍ ቢባል የሚወድቅ/የሚከለስ ገፍ በገፍ ሆኖ ተስፋፋ የተባለው ትምህርት የውድቀት ጉረኖ ሊሆን ነው፡፡ እና ከዚህ ቅሌት ለመዳን እየገፉ ማሳለፍና ሦስት ፌርማታ ላይ (አሥረኛና አሥራ ሁለተኛ ላይ በወዳቂነት፣ ኮሌጅ የዘለቁትን ደግሞ ዲፕሎማና ድግሪ አስይዞ) ማራገፍ ዘዴ ተብሎ ተይዟል፡፡ እናም በነጥብ ጭመራ፣ በኩረጃና ማለፊያ በማሳነስ እየተገፉ ማለፍ የተንሰራፋበት ጥራትና ብቃት የለሽነት ከተማሪነት ወደ አስተማሪነት፣ ከአስተማሪነት እንደገና ወደ ተማሪዎች እየተጋባ ብቃት የለሽነትን ማራባቱን ቀጥሏል፡፡

ማንኛውም ሰው ከተራ እስከ መሪ ድረስ በሁሉም ነገር ባለዕውቀት ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ ነገር የበሰለ ባለዕውቀት ሆኖ በሌላው ነገር ዕውቀቱ ቁንፅል ቢሆን አያስገርምም፡፡ ቁንፅልነትና ልቅምቃሚነት የሚኮራበት ሰብዕና ሲሆን፣ አስተሳሰብም አንደበትም አንዱን በወጉ ያልጨበጠ ጉራማይሌ ከመሆን አልፎ፣ ሁሉም ዘንድ አለሁበት፣ ከእኔ በላይ አዋቂ ላሳር ካለ ግን አጉል ነው፡፡ ዛሬ በየባንኮኒው፣ በየጋዜጣና በየሬዲዮው ሜዳ አልበቃው ያለው ይኸው የቁንፅልፅል ምላሳምነትና አብጠልጣይነት ነው፡፡ በ‹‹ልማታዊ›› መስመር በኩል ቢሄድ ቁንፅልነት ሃሳዊ ሎጂክና መታበይን ተሞልቶ ፕሮፓጋንዳን ሀቅ እያደረገና ተቃዋሚን እያበሻቀጠ ይጎርፋል፡፡ ገመናን ለመሸፈንና ለፕሮፓጋንዳ እንደሚሆን አድርጎ እውነትን መተርጎምና መደርገም (የፈረንሣይ የፀረ ሽብር ሕግ፣ የጀርመን ‹‹የሐሰት ዜና›› ሕግ ዜናዎች፣ የኢቢሲ ሜኑ ቋሚ አጀንዳዎችና ደንበኞች ናቸው) ፖለቲካዊ ባልሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮችም ውስጥ ቁንፅል ሊቅነት፣ ትዳርና ፍቅር አቃኚ፣ የሥነ ልቡና ቁስል አካሚ ሆኗል፡፡ በተቃውሞ ሥነ ጽሑፍም በኩል ቁንፅልፅሎሽ ተፎካካሪ የለውም፡፡ መሰለኝንና ፍንጭን ሁሉ ወደ አለቀና ወደ ደቀቀ ሀቅ እስከ መቀየር ተዓምር ይሠራል፡፡ ሚሊዮኖች የሚያዳምጡትን ሬዲዮ የመንደር ቡናንና ሐሜትን በማንቃረሪያነት ደረጃ አውርዶ መጠቀም የማያሳፍር ሙያ ሆነዋል፡፡ 

የኢሕአዴግ የልማት ፍሬ በግንባታ መስክ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ደርግ ያለቡጢ፣ ያለማሰርና ያለጥይት በቀር ሌላ መሣሪያ የማያውቅ አባ ዳምጠው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ግን ሁሉን ነገር (የሥራ ዕድልን፣ የሙያ ማሻሻያ ዕድልን፣ የውጭ ትምህርት ዕድልን፣ የዕድገትና የጭማሪ ዕድልን፣ ዝውውርን፣ ሹመትን፣ ታክስና ግብርን፣ የመንግሥት ቤት ኪራይን፣ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድልን፣ መሬት የማግኘት ዕድልን፣ ወዘተ፣ ወዘተ) ወደ ‹‹አብዮታዊ›› የትግል መሣሪያነት ለውጦ፣ ሁሉንም ዓይነት ነገሮች በአንድ ጊዜ አርጩሜም ወሮታም መሆን እንዲችሉ አደረጋቸው፡፡ ኢሕአዴግንና መስመሩን ሊተናነቅ ለደፈረ አርጩሜ ሆነው ልክ እስኪገባ ይሸነቁጡታል፡፡ ኢሕአዴግን ላከበረና ላጫፈረ ደግሞ ወሮታ ሆነው ይጠቅሙታል፡፡ ቂሉ ደርግ ኢኮኖሚውና ቢሮክራሲው ውስጥ ይርመሰመስ የነበረውን ጉቦ ላያሸንፈው ጠላቴ እንዳለ ሞተ፡፡ ብልጡ ኢሕአዴግ ግን በአንድ በኩል አጠፋለሁ ብሎ እየታገለ፣ በሌላ ጎን ወዳጅ አድርጎና አክብሮ ሥልጣን ለማጎልበት ሰው (ሎሌ) ለመግዣነት አዋለው (እኛም “ወሮታ” የምንለው ማዕረጉን ላለመንካት ነው)፡፡ የኢትዮጵያ ልማትና መንበረ ሥልጣን ሳይቀር የወሮታና የአርጩጫ ባህርይ ተጎናፅፏል፡፡ ልማቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣  የኢሕአዴግን ሥልጣን በክፉ እንዳያይ መሸበቢያ ወሮታው ነው፡፡  ኢሕአዴግ በልማት እስከተጋና ሕዝብን እስካማለለ ድረስም በገዥነት መንፈላሰስ ወሮታው ነው፡፡

የገንዘብና የቁስ ጥቅሞችን መንሳትና ማጉረስ የገዥነት ችግሮችን ለማቃለል በቂ አይሆንም፡፡ ሰደፍና አፈሙዝ የሚያስፈልግበትም ጊዜ አለ፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› እና ‹‹ሕዝባዊ›› እንደመሆኑ ፀረ ሕዝቡ ደርግ ‹‹አድምቶ›› የተጠቀመበት ደረቅ የድቆሳ ሥልት ላይ መጠምጠም ያንሰዋል፡፡ በአንድ በኩል በኋላቀር ባህል በተሟሸ አዕምሮ ላይ ያረፈ ማርክሲዝም ያስገኘውና የደብተራና የመኳንንት ሸርን ከማትባት ያላለፈ የአብዮተኛነት ነባር ቅርስ አለ፡፡ ከሥልጣን ማሳደድ ጋር የሚስማማው “የእኔ ሐሳብ አመራሩን ካልያዘ ትግሉ ይሸነፋል›› ባይነት ባላንጣ ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ሳይችል ሲቀር፣ በሸር መንገድ መገላገል በ1960ዎች የከተማ ተራማጆች ውስጥ እንደ ነበረ ሁሉ በረሃ በገባው ሕወሓት ውስጥም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ከሻዕቢያ ጋር መዋል ሌላ ሥልጠና ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ለሸር ትንሳዔን ያስገኘልን “ሶሻሊስት” ተብዬ ገዥነት በዓለም ውስጥ ቀን ጎድሎበት (ሥልጣን ላይ መውጣት/መቆየት የአሜሪካን ተቀናቃኝ የለሽ ምርቃት የሚሻበት ጊዜ መጥቶ) ‹‹ማርክሲስት ሌኒኒስት ነኝ… የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ የከበርቴ ነው…” ባይነትን ወደ ሆድ ከትቶ፣ ‹‹አሳታፊነት››ንና የብዙ ፓርቲ ሥርዓትን መቀበል ግድ ያደረገ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተጣብቆ ሥልጣን ላይ የወጣውና አፍና ልብ የተፈናገጠበት ኢሕአዴግ የይስሙላውንም እውነተኛ ፍላጎቱንም አብሮ ለማስተናገድ ቅርፊትና ቡጥ ባለው (ከላይ ስሞ ከውስጥ በሚነክስ፣ ከላይ አልቅሶ ከውስጥ በሚስቅ፣ ወዘተ) ሥልት መጠበብ ግድ ይለው ነበር፡፡ እናም ደርግ በአባ ዳምጤነት ያባከነውን የዘመነ አፄ የሸርና የደባ ፀጋችንን ኢሕአዴግ አብዮታዊ ተሃድሶ ሰጥቶና ወደ ፋብሪካነት አሸጋግሮ ከመሀል አገር እስከ ዳር አገር ድረስ እየተባዛ እንዲሠራ አደረገው፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ይቅርታ እጠይቃለሁ ጥፋቴን    አምኛለሁ›› ካለ ይህን በዝርዝር መናዘዝ ይገባዋል፡፡

ሽርና ደባ የማይለብሰው ልብስ የለም፡፡ ቅን ውይይትን ተመስሎ ሊመጣ ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ ገና አዲስ አበባ በገባ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አቶ መለስ ዜናዊ ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ጋር ሰዎች ደብለቅ አድርገው ያካሄዱት ታሪካዊ ውይይት ሁለመና ፍሬው ‹‹አማራ የለም›› የምትል ቃልን በፕሮፌሰሩ አፍ የማስነገር ሸር ነበር፡፡ የሰኔ 1983 ዓ.ም. ኮንፈረንስም፣ “አሳታፊነት”ና የኢሕአዴግ የበላይነት ሰምና ወርቅ ሆነው የተስማሙበት ጥበብ ነበር፡፡

የግብፁ መሐመድ ሙርሲ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የዓባይን ግድብ ግንባታ በግብፅ ጥቅም የመጣ አድርጎ መዛቱና በጊዜው የኢትዮጵያ መንግሥትና የተወሰኑ ተቃዋሚዎች መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዚያ ወቅት ግድቡን የተቻኮለና መዘዘኛ አድርገው ካዩት ጋር ተተቻችቶም ቢሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ተገቢ ይሆን የነበረው፣ ኢትዮጵያ ከፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት በቀር ጎረቤቶቿን የመጉዳት ዓላማ እንደሌላት በማሳወቅ ዙሪያ ሁሉንም ፓርቲዎች ያስተቃቀፈ አቋም መያዝ ነበር፡፡ በኢቲቪ ላይ ታይቶ የነበረው ውይይት ውስጥ ኢሕአዴግ በአቶ ሽመልስ ከማል በኩል ያደርግ የነበረው ጥረት ሁሉ ግን ተቃዋሚዎችን ከሕዝብ በመነጠል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በተለይ የውይይቱ መዝጊያ ሆኖ አየር ላይ ተበትኖ የነበረው ቃል የግብፅ ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎችን እንረዳለን እስከ ማለት የደፈሩት፣ ተቃዋሚዎች ላይ ምን ክፍተት ቢያዩ ነው? በምን ቢገምቷቸው? የሚል ነበር፡፡

ተንኮል ድርድርን ተመስሎም ሊመጣ ይችላል፡፡ በአንድ ወቅት ድርድር ከጠየቀው የመድረክ ቡድን ጋር ኢሕአዴግ ለመደራደር የወደደ መስሎ ከኢዴፓና ከመኢአድ ጋር መድረክን አገጣጥሞ ያናጨበትና ታሪካዊ የፓርቲዎች ስምምነት የተፈጸመ እያስመሰለ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብን (በኋላ ሕግ የሆነውን) ያወጣበት ተውኔት አንድ ምሳሌ ነው፡፡ የአሁኑም ድርድር ሙትና ቁስለኛ እያስመዘገበ ነው፡፡

ሸር ቃለ መጠይቅ ወይም ጥያቄ ሆኖም ብቅ ይላል፡፡ መሬት አይሸጥም እየተባለ ግን የግል ይዞታ ያህል ጣሪያ በነካ ዋጋ በሚቆነደድበት አገር፣ መሬት በግል ይያዝ ባይና በሕዝብ እጅ ይቆይ ባይ ቡድኖች፣ ብሔርተኛና ብሔርተኛ ያልሆኑ ቡድኖች የፖለቲካ ጥምረት መፍጠራቸውን እንደ ጉድ እያብጠለጠለ የብተና ሴራን አገልግሏል፡፡ በ2007 ዓ.ም. የምርጫ ውድድር ዘመን ውስጥ፣ “ምርጫ ብታሸንፉ ሌላውንም በሥልጣን ታሳትፋላችሁ?” የሚል ጥያቄ ለመድረኩ መሪ ቀርቦለት አዎ ሲል፣ “እንዴት ነው ታዲያ የሕዝብ ድምፅ የምታስከብሩት?” የሚል ጥያቄ ሲከተለው ታዝበናል፡፡ ይህ እንግዲህ ከደጋፊ ሕዝብ ጋር የማጋጨት ሸር መሆኑ ነው፡፡ ቅን አዕምሮ ላለው ግን የሕዝብን ድጋፍና ድምፅ ማግኘት ከአቋም እንደሚመነጭ ማስተዋል አይከብድም፡፡ በዚሁ የ2007 ዓ.ም. ምርጫ የውድድር ዘመን ውስጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅቶት በነበረው አንድ ውይይት ላይ የኢትዮጵያውን “ሶሻል ዴሞክራቲክ” ፓርቲ አጣድፈውት የነበሩት ከድጎማ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ጠይቆ ከማወቅ ይልቅ፣ ፓርቲውን የአውሮፓ ኢንዱስትሪያዊ አገሮች ቅጂ (በኢትዮጵያ በሌለ ኢኮኖሚያዊ መሠረት ላይ የሚቃዥ) አድርጎ የማዋደቅ ዓላማ የነበራቸው ነበሩ፡፡ (ተከራካሪውም የሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ታሪክ ከድጎማ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነና የኢትዮጵያው ፓርቲም የሚሰፈረው ዛሬ በአውሮፓ ባለው አቋም መሆን እንደማይገባው አስረግጦ፣ ሶሻል ዴሞክራሲያዊነቱ ምን ላይ እንዳተኮረ የሚጠይቅ ጥያቄን በመመለስ ላይ በመወሰን ፋንታ ከተንኮል ጥያቄ ጋር ከመባዘን አላመለጠም ነበር፡፡)

ሸርና ሽወዳ ሕግም ሆኖ ያስተዳድራል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ መንግሥትን ስለሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም ሳይባል፣ ከአገር ርዕስነት በስተቀር በማስተዳደሩ ውስጥ የሌለበት ፕሬዚዳንት የርዕስነት ቆይታ በሁለት የምርጫ ዘመን መገደቡ ማደናገሪያ ብጤ መሆኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሕግ (ቁጥር 573/2000) እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግ (ቁጥር 621/2001) ከውጭ ጣልቃ ገብነትና ፈትፋችነት የአገርን ፖለቲካ በመጠበቅ መልክ ውስጥ የአንድ ቡድን የገዥነት ጥቅም የተጠቀለለባቸው ምርጥ ሕጎች ናቸው (ተፎካካሪና አጋላጭ የማድረቅ ጠቀሜታቸው ተብሎ ያለቀ ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ አንገባም)፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ የዋስትና መብት ድንጋጌዎች ላይ የተደረጉት አፍራሽና አድኃሪ ሕጎችና ተግባሮች፣ በ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ ውስጥ በሥውር ተጭኖ ያለፈው የሚዲያ ሕግ ድንጋጌ፣ በሚዲያ ንግድ በመሳተፍ መብት ውስጥ ባለቤትነትንና አዘጋጅነትን እንዳይደራረሱ አድርጎ በመመርያና በተግባር መወሰን፣ ወዘተ የዚህ ሸር ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ሸር ያካሄደው ስም ማጥፋትና ያደረሰው መከፋፈል፣ በአስተዳደራዊ ዕርምጃና ውሳኔ ውስጥ፣ በፖሊስ ሥራ ውስጥ፣ በዓቃቤ ሕግና በፍርድ ሥራዎች ውስጥ እየሰረገ ያሳየውን ሙያ እንዘርዝር ብንል ቦታ አይበቃንም፡፡ በጥቅሉ ከብዴሕ (NDU)፣ ከመአሕድ፣ ከኦነግ፣ ከቅንጅት፣ ከቀድሞ ኦብኮና ኦፌዴን፣ በኋላም ከእነ መኢአድና ከመድረክ ጋር የተካሄዱ ቁርቁሶችን የሕወሓት ክፍፍልን ተከትሎ የተከናወነው የሥልጣን ፍንቀላ፣ እነዚህን በሙሉ በተመለከተ ከአደባባይ እስከ ወህኒ ድረስ የተፈጸሙ ታሪኮችን ብንቃኝ ምን ያህል በሸር እንደከበርን መረዳት ይቻላል፡፡

ወዳጅ ሆኖ እያማ ነገር የሚጠነስሰው፣ መጠጥ አጠጥቶና አስክሮ መጥለፊያ የሚሆን ነውር የሚያሠራው ወይም የሚያስደበድበው፣ የኮንትሮባንድ ነጋዴ መስሎና በርካሽ ዋጋ ጠመንጃ ግዛኝ ብሎ አግባብቶ እጅ ከፍንጅ የሚያሲዘው ወይም በወንጀል የተጠረጠሩበትን ያለፈ ታሪክ ጎርጉሮ የሚቀሰቅሰው የሸር ዓይነት ሁሉ ውስጥ እንግባ ብንል፣ በአገሪቱ ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ በአንድ ዓመት የተፈጸመው እንኳ ወፍራም መጽሐፍ ሳይወጣው አይቀርም፡፡ የመረራ ጉዲናን የፕሮፌሰርነት ጥያቄ አሰነካክለው ያስቀሩትን የተንኮል ብጤዎች (እስራቱን ትተን) በየትኛውም የአገሪቱ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ጥርስ የገቡ ዜጎችን ሲያጠቁ ልናገኛቸው እንችላለን፡፡

ከትልቅ ሹም አንስቶ እስከ ትንሹ የቀበሌ አስተዳዳሪና ካድሬ ድረስ የሚፈልቀው ሐሳብና ቋንቋ ከአንድ ሰው የሚወጣ እንደሚመሰለን ሁሉ፣ ከዳር እዳር የሚፈጸመው ዓይነት ብዙ ሸርና ሽወዳም ከአንድ ሰው አንጎል የሚፈልቅ ያህል ይመሳሰልብናል፡፡ የዛሬውን አያድርገውና ኢሕአዴግ ራሱ ብዙ ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት ግንባር ሆኖ ከሚታየን ይልቅ አንድ ወጥ ፓርቲ፣ ከአንድ ወጥ ፓርቲም ይልቅ 26 ዓመታት አብሮን የኖረ (እንዴት እንደሚያስብ፣ እንዴት እንደሚያወራ፣ እንዴት እንዲሚስቅ፣ እንዴት እንደሚያሸምቅ በቅርብ የምናቀው) አንድ ግለሰብ መስሎ ይሰማናል፡፡ እናም ልካችንን አውቀን “በልምጭና በካሮት” እየሾርን የሚጠበቅብንን የማድረግ ወይ መሾጥሾጥን የማብዛት (የሰርከስ እንስሳት) ዓይነት ኑሮ ተላምዶናል፡፡ ለኢሕአዴግ ድጋፍም ቅዋሜም ሳይኖረን፣ የመምረጥ ፍላጎት እንኳ ሳይኖረን፣ ያላንዳች ስሜት ኢሕአዴግን እስከ መምረጥ ድረስ በድናችንን የምንቀሳቀስ ሁሉ በርክተናል፡፡

ነፍስ ያለው የፖለቲካ ውይይት በኢትዮጵያ ታምሞ አልጋ ላይ ከዋለ ረዥም ጊዜ ሆኖታል፡፡ ከ1953 ዓ.ም. የታኅሳስ ግርግር በኋላ እያደገ የመጣው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፖለቲካ ቀመስ እንቅስቃሴ የመኝታ ቤት፣ የአዳራሽና የሜዳ ውይይቶችን እስከ መውለድና ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከማሸጋገር ድረስ ተራምዶ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ መውደቅና ለ1966 ዓ.ም. አብዮት መፈንዳት የድርሻውን አዋጥቷል፡፡ በአብዮቱ ሒደትም ውይይት በመላ ኅብረተሰቡ ውስጥ ቢዛመትም፣ እስከ ዕድገት በኅብረት ዘመቻ ጊዜ እንደ ምንም ሲንገዳገድ ቆይቶ በደርግ አፈናና በተራማጆቹ ፍጥጫ ከመታነቅና መቀመቅ ከመውረድ አልተረፈም፡፡

ተራማጆቹ ቡድኖች በአካሄድና በደርግ ላይ ያሳዩት የአቋም መለያየት በክህደትና በጠላትነት ከተተረጎመ በኋላ የነበረው ውይይት፣ በተፃረሩ አቋሞች ውስጥ ብጤ ለብጤ የሚካሄዱ ወይም ለየጎራው አባላትና ደጋፊዎች የማሰባሰብ ተግባር ነበር፡፡ በተፃረሩ ረድፎች መሀል ውስጥ ቢካሄድ እንኳ ጉዳዩ ተወያቶ ፍሬ ነገር ከማግኘት ይልቅ ጠላትን የማጋለጥ፣ የመኮርኮም፣ የማስጠመድ ከመሆን አላመለጠም፡፡ የሐሳብ ፈለጎች ሁሉ መታወቂያ ወጥቶላቸው ያለሠፈራቸው ሲከሰቱ ማሸማቀቅ ይደርስባቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ያለው ሁኔታ በመሠረቱ አልተለወጠም፡፡ የእኔ ሐሳቦችን “የፊዲስት/ የባንዶች” ወይም “የዲሞዎች/የአናርኪቶች” አቋም በማለት ይካሄድ የነበረው ማሸማቀቅ፣ ዛሬ ደግሞ “የወያኔ/የጎሰኛ…” እና ‹‹የፀረ ሕዝቦች/የትምክህተኞች/የገበያ አክራሪዎች…” አመለካከት፣ ወዘተ ወደሚል ፍረጃ ተቀይሯል፡፡

እንደ ትናንቱ ድብቅ መሆን ሳያስፈልግ፣ ዛሬ ባለችው ከሲታ የሐሳብና የመደራጀት ነፃነት መሠረት ሕጋዊ ተቃዋሚ መሆን ቢቻልም፣ ከደርግ ፈላጭ ቆራጭነት ጊዜ በተሻለ በአደባባይ የመወያየት/የመከራከር ዕድል ቢኖርም፣ የተቀናቃኞች ወይይት ዞሮ ዞሮ በጠላቶች መካከል የሚካሄድ እንደ መሆኑ ቅንነት የሌለበት፣ “ማነውና ነው እሱ እንዲህ የሚለው? ዛሬ ከየት ተገለጠለት? እስከ ዛሬ ድረስ ምነው አልታገለ? ይህንን ሲል/ሲሠራ የነበረ ፓርቲ እንዴት ሊታመን ይችላል? ወዘተ” በማለት ዋና ጥያቄን አስተው ማጠልሺያ በሚሹ፣ ከአንዲት ስንጥር ተነስተው፣ “ይህን ካደረገማ እንዲህ ነው ማለት ነው” እያሉ ሙሉ ባህርይን በሚጠነቁሉ ወይ ስንጥሩን አጠቃላይ አድርገው በሚሾሙ ወልጋዳ የአስተሳሳብ መንገዶች የተሞሉ ናቸው፡፡ መወያየት ቢቻልም ከተራ የተቃውሞ ደጋፊ አንስቶ “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” እስከሚባልለት ተቃዋሚ ድረስ ከፍርኃት ጋር መኖር የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ግለሰቡ/እንደ ድርጅቱ የቅዋሜ አሥጊነት ደረጃ ቀለልና ከበድ የሚል ቁንጥጫ አይታጣምና፡፡ 

በጥቅሉ ዛሬ ብዙ ገጽታ ባላቸው የአብዮታዊ ጥቃቶች ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ልምዶች ምክንያት እንኳን ተቃዋሚ መሆን፣ እንኳን የተቃዋሚ ደጋፊ መሆን፣ የገዥውን ቡድን አቋም መተቸት እንኳ አስፈሪ ሆኗል፡፡ ጥርስ ውስጥ ገብቶ መቀጮ ላለመቅመስ ቅዋሜን በሆድ መደበቅና በአፍ ለገዥው ፓርቲ ፖለቲካ ደጋፊ መምሰልና ማንቧቸር እንደ ዘመነ ደርግ ዛሬም የደራ የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡ ሥልጠናና ሴሚናሩ ሁሉ የዚህ ዓይነት ዘይቤ መድረክ ነው፡፡ ለፓርቲ አባልነት ተጠይቆ እሺ/እንቢ ማለት (እንደ ኢሠፓ ጊዜ ብታሰርስ ብሎ እስከ መሥጋት ባያደርስም) ጥቅምን የማቃናት ወይም ጥቅምን የማስጠቃት ምርጫ ሆኖ ሰዎችን ይቃኛል፡፡ ዛሬ  “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ብቸኛው ልማታዊ ታቦት የሆንበት ዘመን መጣ፡፡ ኢሕአዴግ በአንድ ሳጥን ውስጥ ተዘግቶ የራሱን ድምጥ እያዳመጠ ከዚህ የተለየ ሌላ ድምፅ የለም፣ መኖርም አይችልም ብሎ ቀጠለ፡፡ በራሱ ውስጥም የተሻለና የተለየ ሐሳብና የተሻለ ችሎታን በክርክር የማንጠር ወይም በድምፅ የመለየት እስትንፋስ አጣ፡፡ የኢሕአዴግ የመስዋትነት፣ የአሸናፊነት የትክክለኛነት ኩራትና ተመኪነት አድሏዊነትንና አለማወቅን ምሽጉ አድርጎ ትዕቢትን መተንፈስ ማለትም ሌሎችን መናቅና ማንኳሰስ ኑሮ ውስጥ በመግባቱ ትምክህተኛ ሆኖ አረፈው፡፡ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ የማድረግ የጨዋታ ሕግ እኔ ላይ አብዮታዊና ልማታዊ፣ መንግሥት ውስጥ አይሠራም ብሎ ‹‹አወጀ››፡፡ ራሱን ከዴሞክራሲ የጨዋታ ሕግ በላይ አደረገ፡፡ የተጠናወተው እኔ ብቻ ልክ ዳፍንቱ ጥፋቱን እንዳያምን (ስህተት ነው የሚለው) ከጥፋቱም እንዳይማር ከለከለው፡፡

ራሱን በማምለክና ሌላውን በመናቅና በማውገዝ ዴሞክራሲውን አዳፍኖ፣ ልቦናውን ደፍኖ ‹‹አማራጭ›› በሌለው በብቸኛው የገዛ ራሱ ጎዳና ‹‹ወደፊት በሉልኝ . . . ›› እያለ ቀጠለ፡፡ ሁሉንም የፓርላማ ወንበር አሟጥጦ ላሸነፈበት ለምርጫ 2007 በቃ፡፡ ከእንቅልፉ የቀሰቀሰው ለጥልቅ ተሃድሶ፣ ለእንደገና የጥልቅ ተሃድሶ (የፓርቲ ሱባዔ) ያበቃው መንገሽገሽ የተዘረገፈበት የሕዝብ ተቃውሞ አደባባይ ከወጣ ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ወዲህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አልወሰደም፡፡ ኢሕአዴግ ገዥነቱ የሰመረለትና ሕዝቡንም በልማት የረታ የመሰለው የምርጫ 2007 ውጤት የሆነው 5ኛውን ፓርላማ አደራጀ፡፡ ፓርላማው ሥራ በጀመረ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መንግሥታዊውን /ኢሕአዴጋዊውን የልማትና የዴሞክራሲ ተመፃዳቂነት እየዘነጣጠለ የ2008 ዓ.ም. ቁጣ ተስፋፋ፡፡ ቁጣው ስንት ዓይነት ክምር፣ ብሶትና ሮሮ ሲጠራቀምና ውስጥ ውስጡን ሲንተከተክ እንደኖረ፣ ሕዝቦች ድረስ የዘለቀና እርስ በርስ ሊያተራምስ ጫፍ የደረሰ መቃቃር ምን ያህል ግት እንዳበጀ ግልጽ ወጣ፡፡

ኢሕአዴግ የገዛ ራሱን ክስረቶች በሙሉ ተቀብሏል ወይ? ከራሱ ውጪ ሌሎች ወገኖችን የማድመጥ ለውጥ ያደርጋል ወይ? ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ከሚል አመለካከት ይገላገላል ወይ? መሰሪ መንገዶችን፣ በሥልጣን መባለግን እንደ ትግል መሣሪያ የመጠቀም የሠለጠነበትን ዘይቤውን እርግፍ አድርጎ ይጥላል ወይ? ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን የመገንባትና ሙስናን የመዋጋት፣ እንዲሁም አገር የማዳን ሚና መጫወት የሚቻለው እነዚህን ጥያቄዎች በአዎንታና በእርግጠኝነት ሲመልስ ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *