በሶማልያ መንግሥት አንፃር የሚዋጋው አሸባብ  ዜጎች ልጆቻቸውን ለውጊያ ተግባር ለቡድኑ እንዲያስረክቡ በማስገደድ ላይ መሆኑን የመብት ተሟጋቹ ቡድን ሂውመን ራይትስ ዎች አሸባብ አስታወቀ። ህጻናትን የመመልመሉን ዘመቻ ባለፈው ዓመት የጀመረው አሸባብ፣ በማይተባበሩ ወላጆች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ ዛቻውን አጠናክሯል። 

«አሸባብ ህጻናትን በተዋጊነት እንዲያገለግሉ እንዳያስገድድ ጥረት መደረግ አለበት»

አሸባብ በስምንት እና 15 ዓመት መካከል ያሉ ህጻናትን ለመመልመያ «ልጆቻችሁን ስጡን ወይም የሚከተለውን ጥቃት ተጋፈጡ።» የሚል የማስፈራሪያ አነጋገር ይጠቀማል። ይህን ያስታወቀው ባለፉት ጥቂት ጊዚያት ወንዶች እና ሴቶች ልጆቻቸውን ለውጊያ ስልጠና እና ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ትምህርት እንዲሰጡ አሸባብ ጠይቆናል ያሉ ቤተሰቦችን እና አንዳንድ መምህራንን ያነጋገረው ሂውመን ራይትስ ዎች ነው። ከነዚሁ መካከል በሰሜን ምዕራብ ሞቃዲሾ በቡርሃካባ ቀበሌ የሚኖር አንድ መምህር የአሸባብ ሚሊሺያዎች ለዚሁ ዓላማቸ ማሳኪያ እያሉ ወደየትምህርት ቤቶቹ እንደሚሄዱ አስታውቋል።
« ሚሊሺያዎቹ መምህራኑን ከክፍል አስወጥተው በአንድ ቢሮ ውስጥ ይቆልፉባቸዋል። ከዚያ ወደመማሪያው ክፍል ይመለሱ እና የሚፈልጓቸውን ህጻናት ተማሪዎች መርጠው ይወስዳሉ። መምህራኑ ሚሊሺያዎቹ ህጻናቱን ወዴት እንደሚወስዷቸው ሲጠይቁም ለቅዱስ ጦርነት በማለት ይመልሱላቸዋል። አንዳንድ መምህራን እንዳሉት ደግሞ አትጠይቁ ወይም እንተኩስባችኋለሁ ይሏቸዋል። »Somalia Binnenflüchtlinge in Dollow, Kinder mit Koran (Reuters/Z. Bensemra)

ሂውመን ራይትስ ዎች እንደሚለው፣ ታጣቂው ቡድን በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች እጎአ ከ2015 ዓም ወዲህ ብዙ የሀይማኖት ትምህርት ቤቶችን ከፍቷል፣ በሌሎች ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትንም መምህራን የቡድኑን የትምህርት ስርዓት እንዲከተሉ ግፊት አሳርፏል።  
በቡርሃካባ ቀበሌ ከሁለት ትምህርት ቤቶች ባለፈው ዓመት ቢያንስ 50 ወንዶች እና ሴቶች ህጻናትን ቡሎ ፉላይ ወደተባለ መንደር በግዳጅ ተወስደዋል። በአንድ ሌላ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን ለአሸባብ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ መምህር ከሚሊሺያዎቹ ዛቻ እንደደረሰበት ያካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የሂውማን ራይትስ ዎች የህጻናት መብት ተመልካች ክፍል ዋና ኃላፊ ዛማ ኔፍ ይህ አካሄድ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል። 

Somalia Krieg Regierungstruppen in Burhakaba (AP)የቡርሃካባ ቀበሌ

« ባለፉት ሁለት ዓመታት በአሸባብ የታገቱ ህጻናት ቁጥር በጣም በጉልህ ጨምሯል። ህጻናት ከትምህርት ቤታቸው ፣ ከቤታቸው እና ከሰፈራቸው ተወስደዋል፣ የትኛውም ቦታ አስተማማኝ አይደለም። አሸባብ ህጻናቱን በተዋጊነት እንዲያገለግሉ ያስገድዳል። » 
ይህ መጥፎ እጣ እንዳይደርስባቸው እያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ቤታቸውን እየለቀቁ  መሸሻቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች አመልክቷል። የሶማልያ መንግሥት እና የተመ የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ የህጻናቱን ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሰሩ በሂውመን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ተመራማሪ ሌቲሻ ባደር  ተማጽነዋል።
«  እርግጥ፣ በመጀመሪያ ደረጃ የምናቀርበው ሀሳብ አሸባብ ምልመላውን እንዲያቆም፣ ለውጊያ ተግባር የሚጠቀምባቸውን ህጻናት እንዲለቅ ነው የምንጠይቀው፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም፣ የሶማልያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ተዋናዮች የአሸባብን ምልመላ ለመሸሽ ሲሉ የተፈናቀሉት ህጻናት ከለላ  የሚያገኙበትን እና ትምህርት የሚከታተሉበትን ሁኔታ  እንዲያረጋግጡ እንጠይቃለን። ከዚህ በተጨማሪ  ግን የሶማልያ ጦር ኃይላት ሆኑ ሌሎች በአሸባብ የምልመላ ዘመቻ አንጻር ርምጃ በመውሰድ ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን ከለላ መስጠት ይኖርባቸዋል። »

አንድሩ ዋሲክ

አርያም ተክሌ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *