“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከቂሊንጦ ገሃነም የተላከ ደብዳቤ

 “እስረኞች በማረሚያ ቤቱ አዛዦች ትዕዛዝ በተርከፈከፈባቸው የሩምታ ተኩስ የተገደሉ ከመሆናቸውም በላይ አስከሬናቸው እስኪከስል በእሳት እንዲበላ ተደርጓል። በወቅቱ ድርጊቱን ያየንና የምናውቅ ሰዎች አሁንም ድረስ አእምሯችን ይረብሸናል።”

~”ይህን ወንጀል የፈፀሙት ኃላፊዎች ሆነው በዚህ ጉዳይ የድሃ ልጆች ከባድ የ”ሽብር” ክስ የተከሰስን መሆኑ፣ የተገደሉት ወንድሞቻችን በእሳት ከስለው፣ ተረሽነው እውነታው ዝም ተብሎ መታለፉ “ሀገር አለን ወይ? ሕዝብና ወገንስ አለን ወይ?” ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል።”

(ጌታቸር እሸቴ፣ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ 31ኛ ተከሳሽ)

ይህን ደብዳቤ የምልክላችሁ የቂሊንጦ ገሃነም ድርጊቶች የሚመለከታችሁ ሁሉ ስለ ቂሊንጦ ገሃነም እውነታውን መርምራችሁ እንድታወጡልን ነው።

ነሃሴ 28/2008 ዓም የቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ ቤት ተብሎ የሚታወቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች የቀጠሮ ተመላላሽ ተጠርጣሪዎች ማቆያ ላይ በደረሰ እሳት ቃጠሎ ወቅት ለ30 ደቂቃ ያህል በተደረገ የክላሽና የመትረየስ እሩምታ ተኩስ ማረፊያ ቤቱ ወዲያውኑ ወደ ገሃነምነት ተቀይሯል።

በዚህ ቃጠሎ ወቅት በተደረገ ተኩስ ማረሚያ ቤቱ ባመነው እንኳ 23 ተገድሏል። እነዚህ እስረኞች በማረሚያ ቤቱ አዛዦች ትዕዛዝ በተርከፈከፈባቸው የሩምታ ተኩስ የተገደሉ ከመሆናቸውም በላይ አስከሬናቸው እስኪከስል በእሳት እንዲበላ ተደርጓል። በወቅቱ ድርጊቱን ያየንና የምናውቅ ሰዎች አሁንም ድረስ አእምሯችን ይረብሸናል። እነዚህ ዘግናኝ ድርጊቶች በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ተፈፅመው እኛ በሀሰት ተከሰንበታል።

ይህ ወንጀል በማረሚያ ቤቱ የተፈፀመ መሆኑ በግልፅ እየታወቀ፣ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ (38 ተከሳሾች) “ሽብር” ወንጀል ተብለን ተከሰን እየተመላለስንበት ነው። ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል አንዱ እኔ ጌታቸር እሸቴ ስሆን በ30 ደቂቃ ውስጥ 9 ሰዎችን ገድለሃል ተብዬ ለማመን በሚከብድ የሀሰት ወንጀል ተከስሻለሁ።

በሀገራችን ባለስልጣናት ሰው እየገደሉ እና እየረሸኑ ድሆች የእነሱን ሀጥያት ያለ ሀጥያታቸው እንዲሸከሙ እንደሚያደርጉ እኔ ላይ የደረረሰው አንድ ማሳያ ይሆናል። ከኢትዮጵያ ህዝብ አይን ያልተደበቀ ወንጀልን ኃላፊነት ለመውሰድ ምንም ወንጀል ያልሰራን የድሃ ልጆች ተጠያቂ መደረጋችን፣ የባለስልጣናቱን ወንጀል ለመሸፈን እኛ የፖለቲካ መልስና ሰለባ መሆናችን በጣም አሳዝኖኛል፣ ህዝብ፣ ወገንና ተቆርቋሪ አለን ለማለት ይቸግረኛል!

እግዚያብሔር በዙፋኑ ላይ እያለ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበገሬነት እና የዓለም ሕዝብ ለሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት ቃል ኪዳን በተግባባበት ሁኔታ ይህን የመሰለ ግፍ በአደባባይ ሲፈፀምብን በዝምታው አዝኛለሁ!

ዜጎችን እየገደሉ፣ እየረሸኑ ዜጎችን ያለ ስራቸው የእነሱን ወንጀል የሚያሸክሙትና የፖለቲካ መልስ የሚያደርጉትን ባለስልጣናት አንድ ቀን የሰማይና ምድር ገዥ የሆነው አምላክ እንደሚያጋልጣቸው ተስፋ አለኝ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበገሬነት የራሱ መንግስታትም ሆነ የውጭ ጠላት በሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን አረመኔያዊ ድርጊት እና በደል በመታገል እንደሆነ ከታሪክ የምንረዳው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የቂሊንጦን የገሃነም ድርጊት ዝም ብሎ መመልከቱም የሚያሳዝን ነው። አንድ ድሃ በ30 ደቂቃ ውስጥ 9 ሰው ገድለሃል ተብሎ የፖለቲካ መልስ መስጫ እና የሀሰት ክስ ሰለባ ሲሆን ሕዝብ በተለይም ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዝምታ እጅግ አሳዝኖኛል። የቂሊንጦ ደህንነትና ጥበቃ ኃላፊ ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ አብርሃ ጥፋቱ የራሳቸው መሆኑን የሚያሳይ ምስክርነት መስክሯል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መንግስት ጥፋተኝነቱን ሙሉ በሙሉ እንዲያምን ከጎናችን እንድትሆኑ እጠይቃለሁ። ሚዲያዎች፣ ሌሎች ግለሰቦችም ይህን በደላችን ለዓለም ህዝብ እንድታደርሱልን አደራ እላለሁ።

እንዲሁም የዓለም ሕዝብ፣ በተለይም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ግለሰቦችም ሆናችሁ ተቋማት ከሀገራችን ጋር ስለ ሰው ልጆች ሠላም፣ ደህንነትና ክብር ጉዳይ በገባችሁት የዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን መሰረት የቂሊንጦ ገሃነም የግፍ ድርጊትን መንግስት እኔ ነኝ መንስኤው በማለት ማመን መጀመሩን በመረዳት እኛ ድሃዎቹ የመንግስት ባለስልጣናት እና ካድሬዎች የወንጀል ድርጊት የፖለቲካ መልስ መሆናችን አውቃችሁ ግፊት እንድታደርጉ እጠይቃለሁ። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆናችሁ ይህን የገሃነም ድርጊት ማን እንደፈፀመው መርምራችሁ እውነቱን እንድታወጡልን አመለክታለሁ።

በአጠቃላይ ይህን ወንጀል የፈፀሙት ኃላፊዎች ሆነው በዚህ ጉዳይ የድሃ ልጆች ከባድ የ”ሽብር” ክስ የተከሰስን መሆኑ፣ የተገደሉት ወንድሞቻችን በእሳት ከስለው፣ ተረሽነው እውነታው ዝም ተብሎ መታለፉ “ሀገር አለን ወይ? ሕዝብና ወገንስ አለን ወይ?” ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል። የኢትዮጵያ እና የዓለም ሕዝብ እውነታውን እንዲመረምር፣ ትክክለኛ ፍርዱን እንዲሰጥ አሁንም በአክብሮት እጠይቃለሁ!

እግዚያብሔር በቂሊንጦ ኃላፊዎች የተረሸኑትን ወንድሞቻችን ነፍስ በመንግስቱ ያስባቸው!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0