(ይገረም አለሙ)

ወያኔ አልጋውን የሚያሳጣው የመሰለው አስጨናቂ ነገር ሲገጥመው ከወንበር በመለስ ማናቸውንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ 

ወያኔ አልጋውን የሚያሳጣው የመሰለው አስጨናቂ ነገር ሲገጥመው ከወንበር በመለስ ማናቸውንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ወንዙን ሲሻገር ከጭንቀቱ ተንፈስ ሲልም የገባውን ቃል ሲሽር የተናገረውን እስከመናገሩም ሲረሳ አስተውለናል፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬም በሚነገረው ልቡ የሚማልለው ወያኔ ይለወጣል ከወያኔ ሰፈር የዴሞክራሲ ጸበል ይፈልቃል ብሎ ተስፋ የሚያደርገው ሰው ቀላል ባለመሆኑ ወያኔ እርስ በእርሱ እየተባላም ኢትዮፕያንና ኢትዮጵያውያንን እየበላም  በግዛት ወንበሩ ላይ አለ ይቀጥላልም፡፡

የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ለአስራ ምናምን ቀን ተሰብስበን በጥልቀት ተሀድሰን ልዩነቶቻችን አስወግደን ምናምን ባሉበት አስተውሎ ላየው ግን እንኳን መስማማት መከባበር እንደራቃቸው በግልጽ ባመላከተው መግለጫቸው ለእኛ ማደንዘዣ ሰጥተው ለማለፍ እስረኛ እንፈታለን ማእከላዊን እንዘጋለን ወዘተ አሉ፣ሰማነ ተቀበልነ፤አራገብነ፡፡ እኛ ይህን ቁም ነገር ብለን ወስደን አጀንዳ አድርገን ይዘን ስንወቅጥ ስንሰልቅ እነርሱ ተንፈስ ብለው እድሜ ማረዘሚያ ስራቸውን ይሰራሉ፡፡

እንደው ለመሆኑ ይህን ልብ ብላችሁታል! ሀገሪቱ ወደ ደም አፋሳሽ ችግር የገባችው ሥራ አስፈጻሚው ተገቢ አመራር መስጠት ባለመቻሉ ነው ምናምን ምናምን ካሉ በኋላ የሚፈቱት እስረኞች የሁለት ቀን ተሀድሶ ይሰጣቸዋል አሉን፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለት እውነት ከሆነ ንስሀ መግባት ነው፤ ያለ ንስሀ ደግሞ ኃጢአት አይስተሰረይም፡፡ የእነርሱ መታደስ ግን ምንም ሆነን ምን ወንበራችን አንዴት ነው አስጠብቀን መቀጠል የምንችለው የሚለውን መነሻም መድረሻም ያደረገ በመሆኑ ነግግራቸው ሁሉ ግዜ ለመግዣና ትኩሳት ለማብረጃ እንጂ ከእምነት የመነጨ ባለመሆኑ የአንዱ ንግግር ከአንዱ ብቻ ሳይ በአንድ ሰው አንደበት የሚነገረውም ርስ በርሱ የሚጣረስ ነው፡፡

የችግሩ ምንጭ እነርሱ፤ ምክንያቱ ደግሞ አመራር መስጠት አለመቻላቸው ከሆነ በርግጥም ይህን የተናገሩት አምነውበት ከሆነ ሲሆን በጅምላ ካልሆነም በተናጠል ዋና ዋናዎቹ ሥልጣን መልቀቅ ነበር ትክክለኛው ርምጃ፡፡ ያ ቀረና የሀገሬ ሰው “መበደሉን እንኳን ነጭ ለባሽ በደሏል ነገር ግን ካሳውን ገበሬ ይካስ” እንደሚለው ሆነና  እስረኞች የሚፈቱት ተሀድሶ እየተሰጣቸው ነው ተባለ፡፡ ምን አይነት ተሀድሶ ደከምንም ጠነከርን፣ ዴሞክራሲያዊ ሆንም አንባገነን፣ዘረፍንም ሰረቅን   የእኛን አመራር መቃወም አይቻልም ዝም ብላችሁ መገዛት ነው ያለባችሁ ነው ተሀድሶው፡፡ እንቆቅልሽ፡፡

የአቶ ኃይለማሪያምን አመራር ጥንብ እርኩሱን ለማውጣትና ችግሩን ሁሉ በርሱ ላይ ለጥፈው ሸውደው ለማለፍ የሞከሩት ሰዎች ችግር ብለው ላነሱዋቸው ነገሮች ሁሉ መሰረት የሆነው ነገር ግን ሊነኩት አልቻሉም አልደፈሩም፡፡ ከችግሮች አንዱ መርህ አልባ ግንኙነት እንደሆነና በዚህም ህውኃት በእህት ድርጅቶች ውስጥ እጁን በማስገባት ይሰራ ነበር ያሉትን በተሻለ ድፍረት የነገሩን አቶ ለማ መገርሳም ቢሆኑ የችግሩን ምጭ መንካት አልቻሉም፡፡ችግሩ ደግሞ መሰረቱ ካለተደረመሰና ከምንጩ ካልደረቀ በስተቀር እስረኛም  ተፈታ ማእከላዊም ሙዚየም ሆነ እነ አቶ ለማ መገርሳም ስለ ኢትዮጵዊነት ደሰኮሩ የትም መድረስ አይቻልም፡፡

እልባት የሚያሻው የችግሩ ስረ መሰረት  የደደቢቱ እምነትና የመለስ ዜናዊ የሴራ መትት ናቸው፡፡ ነገር ግን  ሀገሪቱ ለዚህ የበቃችው ከመነሻው ደደቢት ላይ ይዘን የተነሳነው እምነት የተሳሳተ ስለነበር መንግስት ለመሆን ከበቃን በኋላም የመለስ አመራር በአንድነት ላይ ሳይሆን በልዩነት ላይ አትኩሮ በመስራቱ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር የቻለ አንድም ሰው የለም፡፡ ይህን አይደለም አሁንም ህውኃት የሆኑ ተባረውም ሆነ አፈንግጠው የወጡትም አይናገሩትም፤ በተለይ የደደቢቱን፡፡ ከእህት ተብየዎቹም ድርጅቶች ቢሆን ይህ አልተባለም ሊባልም አይችልም፡፡ ምን አልባትም በግምገማው ላይም አልተነሳ ይሆናል፡፡ ይህ ባለሆነበት ወይንም የችግሩ ስረ መሰረት ይህ መሆኑ ባልታመነበት ከእምትም ታልፎ የደደቢትን እምነት አስተሳሰብ ማጽዳት ባልተቻለበት የሚነገረው ሁሉ ከመነገር አያልፍም፡፡

ማእከላዊ ቢዘጋ እነ ጌታቸው ልብ ውስጥ ህንጻውን የገነባው የደደቢት አምነት እስካለ ድረስ የትም ቦታ ማእከላዊ ነው፡፡ዛሬ ሙቀት ለማብረጃ ወትሮም መታሰር ያልነበረባቸው ሰዎች ቢፈቱ በህውኃቶች ውስጥ በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመው የደደቢት አስተሳሰብ እስካለ ድረስ ከእስር ነጻ አንሆንም፡፡ መርህ አልባ ግንኙነት ተብሎ ቢነገርም እነ አባይ ጸሀየ መንፈስ ውስጥ የሰረጸው ደደቢት ውልድ አመለካከት  እስካልተወገደ ድረስ በገሀድ የሚታየውና በማን አለብኝነት የሚተገበረው ይቀር  እንደሁ  እንጂ ህውኃቶች በተካኑበት  የማተራመስ እኩይ ዘዴያቸው መስራታቸው አይቆምም፡፡ ለነገሩ የህውኃት ሰርጎ ገብነት በማመመስና በማተራመስ ብቻ አይቆምም ማሰርም መግደልም ድረስ ይዘልቃል፡፡ ለወያኔ ከተመቹ አንደ ሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት መንደላለቅ፣ አልመች ካሉ ደግሞ እንደ ያረጋል አይሸሹም በውህኒ መማቀቅ አለ፡፡ እነ ለማ የያዙት መንገድ በእምነት ከልባቸው ከሆነ ከወያኔ ሴራ አንድዬ ይጠብቃቸው፡፡

የችግሮች ሁሉ ምክንያቱ  እነዛ ስድስት ሆነን ጀመርን የሚሉትና በሂደት በእያንዳንዱ የህውኃት አባል ውጥ ያሰረ         ጹት ደደቢት ላይ የተቋጠረው እምነት መሆኑ ታምኖ ካላጸዳ በስተቀር የሚባለው ሁሉ የውሸት የውሸት ለመሆኑ  ብዙ በቀባጠሩ ማግስት ያውም በጥምቀት ኃይማኖታዊ ክብረ በአል ላይ  የንጹሀን ደም ማፍሰሳቸው አብይ ማሳያ ነው፡፡ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ ነው የሚባለው፡፡

ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ አይደለም መስራትም እንችላለን የሚለውን ቃል እብሪት፤ የፖለቲካ ስካርና የአሸናፊነት ጀብደኝነት ተደራርበው አቅሉን አሳጥተውት ከነበረው ስዬ አብርሀ አንደበት አንስማው እንጂ የወያኔዎች እምነት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ልክ እናስገባቸዋለን የሚለው የአባይ ጸሀዬ አባባልም የዚሁ ተቀጥላ ነው፡፡

ስለ ደደቢት እምነት አመለካከት መዘርዘር አይጠበቅብኝም ፡፡በ1998 ዓም አሜሪካን ሀገር የተቃዊሚ ፓርቲዎች ህብረት በተፈጠረ ግዜ አቶ መለስ እሳትና ውኃ እንዴት አብሮ ይሆናል በማለት ያውም  ፓርላማ ላይ የተናገረውን ብንረሳ እንኳን  በምርቃና የሚናገረው ጌታቸው ረዳ እሳትና ጭድ ያለውን የምንረሳ አይመሰለኝም፡፡ ይሄ ዝም ብሎ አፍ አድጦ ቃላት አምልጦ የተነገረ አይደለም፡፡የደደቢቱ እምነት ውጤት እንጂ፡፡

አብዩ ቁም ነገር ወያኔን ከደደቢት እምነቱ በውድም በግድም ማለያየት የሚቻል አለሆኑ ነው፡፡ ዛሬ ለደረስንበት ስከፊ ሁኔታ ያበቃን የችግራችን ማእከላዊ ነጥብ  ከመነሻው ይዘነው የተነሳነው እምነት ከሀገራዊነት ይልቅ ክልላዊነትን፤ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣  ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ትግራዊነትን፣ ከጋራ ተጠቃሚነት ይልቅ ትጋራይን ማልማትን ወዘተ መነሻ ያደረገ ስለነበረ ነው ብሎ ማመን የ17 አመቱን የበረሃ ትግል አንዴትነትና የሀያ ሰባት አመቱን በመንግስትነት የተፈጸሙ ድርጊቶች ጥያቄ ወስጥ የሚያስገባ ይሆናልና ያንን ስህተት ነበር ብሎ መቀበል ለወያኔ በሊማሊሞ ማቋረጥ ነው፡፡ እህት የሚባሉት ድርጅቶችም ከወያኔ ሞግዚትነት ያልተላቀቁ በመሆናቸው ይህን አያደርጉትም፡፡ ሌላው ቢቀር በህገ መንግስት የሰፈረ ስልጣናቸውን ተጠቀመው  በግዛታቸው ውስጥ በወያኔ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ማስቆም ያልቻሉ ናቸውና፡

አናም መፍትሄው አንድና አንድ ነው፡፡ቢቻል ተባብሮ ባይቻል ተከባብሮ በአንድ ጎራ ተሰልፎ ጠንክሮ የሚፈጽመው ጠፋ እንጂ፡፡ ለወያኔ የማባበያ ፣ የማደናገሪያ፣ ግዜ የመግዣ ዲስኩርም ሆነ ተግባር ጆሮ ሳይሰጡና ቀልብን ሳያማልሉ ወያኔን ከህዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ላለመላክ የወሰነው የማይታዘዝና የማያጎበድድ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ነው"አንዳርጋቸው ፅጌ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *