ኤርሚያስ ለገሰ በቅርቡ የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ተስተካካይ የሆነና ከሌሎች ጨቋኝ ህጐች (የፕሬስ ህግ፣ የፀረ ሽብርተኝነት ህግ) ጋር እርስ በራስ የሚመጋገብ አዋጅ ሊወጣ ያቆበቆበ ይመስላል። የአዋጁም ስያሜ የማህበራዊ ሚዲያ ህግ” ሊባል ይችላል። ይሄ ህግ ህውሓት የአርማጌዶ ፍልሚያ ጀምሬያለሁ በማለት በድርጅታዊ መግለጫው የገለፀውን ወደ ተግባር ለመቀየር የታሰበ ነው። እንደታዘብኩት ከሆነ ለዚህ አደገኛ ህግ ለመውጣት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎች እየተሰሩ ነው። አንዳንድ ማሳያዎችን አንስተን ጉዳዩን እንመልከተው።

የመጀመሪያው የኢህአዴግ ቢሮ ሶሻል ሚዲያ የደቀነው ፈተና እና ልንከተለው የሚገባ የትግል ስልት” በሚል ወደ 20 ገፅ የሚደርስ ፅሁፍ አውጥቶ ውይይት ማድረጉን እንመለከታለን። በሰነዱ ላይ ካድሬውን እና አባላቱ እንዲሁም የህውሃት የፌስቡክ ሰራዊት ( ኮካ) እንዲሰለጥኑበት ተደርጓል። ሰነዱ እንደመሰከረው ሶሻል ሚዲያው የህውሃት አገዛዝን ፈተና ላይ ጥሎታል።በዚህ ምክንያት ” ሶሻል ሚዲያ ያስፈልጋል ወይ?” የሚል ጥያቄ የሰነዱ መሰረታዊ ነጥብ ሆኗል። በገፅ ሁለት ላይ ” ሶሻል ሚዲያ ያስፈልጋል ወይ?” በሚል ርዕስ የሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን፣

ሶሻል ሚዲያውን በመጠቀም ሀገር እና ህገ መንግስታዊ ስርአት ለማፍረስ የድርጅታችን እና የስርአታችን ጠላቶች ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በህዝቦች መካከል እርስ በራስ መቃቃር እንዲፈጠር ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለው አመኔታ እንዲቀንስ ለማድረግ፣ በድርጅቱ ውስጥ የርስ በርስ መቃቃር እንዲፈጠር እና ሐይል እንዲዳከም መደበኛ የመንግስት ስራ እንዲስተጓጐል ማህበራዊ ግንኙነት እንዲቆም ወዘተ ሞክረዋል። በዚህ ምክንያት በድርጅቱ ውስጥ ይህን ሁላ ችግር ያመጣው ሶሻል ሚዲያ በመሆኑ መንግስት ለምን አይዘጋውም በሚል የሚቀርቡ ሀሳቦችም እንዳሉ ይታወቃል” ይላል።

የህውሃት/ ኢህአዴግ አባላት እየተወያዩበት ያለው ይህ ሰነድ ” ሶሻል ሚዲያው ለጥፋት አላማ የሚውል ከሆነ መንግስትን ከስልጣን መውረድ ብቻ ሳይሆን ሀገር የማፍረስ አቅም እንዳለው ሊታወቅ ይገባል” በማለት ያስጠነቅቃል። በአረብ አገራት በተለይም በቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ የተካሄዱ ብጥብጦች በኃላም መንግስት እንዲለወጥ የተደረገው አብዬት የፌስቡክ ሪቮሊውሽን እስከ መባል መድረሱን ሰነዱ ያስታውሳል። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የሶሻል ሚዲያ ተጠቃሚዎች የጋራ ጠላታቸው የትግራይ ነፃ አውጭ ( ህውሓት) እንደሆነ በገፅ 8 ላይ እንዲህ በማለት ይገልፃል፣

ሶሻል ሚዲያ በመጠቀም በድርጅታችን ወይም መንግስታችን ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ግለሰቦች የጋራ ጠላታችን ብለው የሚያስቡት አካል ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እንደሆነ ያነሳሉ። ኢህአዴግ አራት በእኩልነት መርህ ላይ በመመስረት የመሰረቱት ድርጅት ሲሆን ሕውሓት ከሌሎች ድርጅት የሚበልጥበት ወይም የሚያንስበት አሰራር ሊኖር እንደማይችል የድርጅቱን ታሪክ ከወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ የሚያዩ አካላት ያረጋገጡት ነው” ይላል።

ይህ የህውሓት ዶክመንት በመደምደሚያው ላይ ቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ይጠቁማል። ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ ሰነዱ ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁ ሀይሎችን ( ሰነዱ ” አፍራሽ ሀይሎች” ይላቸዋል) ተጠያቂ እንዲሆኑ መስራት እንደሚያስፈልግ ያስጠነቅቃል። ከድርጊታቸው ጋር የሚመጣጠን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ያስገነዝባል።

***

ለማህበራዊ ሚዲያው ሕግ መውጣት ዝግጅት እንዳለ የሚጠቁመው ሁለተኛው ምልክት የፓርቲው ልሳኖች እና ሚዲያዎች የሚያወጡት ዘገባ ነው። ልሳኖቹ የህጉን መውጣት አስፈላጊነት ለማሳየት የሚከተሉት ስልትም ወዴት እየተሄደ እንደሆነ የሚጠቁም ነው። ለምሳሌ ENN የተባለው የህውሃት ንብረት የሆነው ቴሌቪዥን የህጉ መኖር አስፈላጊነት ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጋበዛቸው ሰዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል፣ የራሳቸው ማህበራዊ መሰረት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ግለሰቦችን ነው። እነዚህ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ተሳትፎ ለማድረግ የራሳቸው መጦመሪያ አውድ ያላቸው ናቸው። በሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችም ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ የኢትዬጲያ ህዝብ ያውቃቸዋል።

እነዚህ ሰዎች የህውሃትን የጀርባ ሴራ አያውቁትም ተብሎ የሚታሰብ ባይሆንም አገዛዙ ያዘጋጀውን ሸምቀቆ እና ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ መሳሪያ ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ላያስቡት ይችላል። ስገምት በቅን ልቦና እየተናገሩ ይሆናል። እንደውም አሁን ላይ ቆመህ በሚወጣው አዋጅ የመጀመሪያ ገመድ የሚጠልቅላቸው እነማን ይሆናሉ ተብዬ ብጠየቅ ከእነዚህ ግለሰቦች ውስጥ የቅድሚያ የምሰጣቸው ይኖራሉ። ለአገዛዙ ከሚያቀርቡት ጠንካራ ጥያቄ እና ሙግት በመነሳት።በተጨማሪም የህውሃት የፌስቡክ አስተኳሾች ” እንቶኔ እንዲህ አይነት ፅሁፍ አስፍሮ ለምን ዝም ይባላል?” በማለት ሲዝቱባቸው አይቻለው። አሁንም ቢሆን የትግራይ ነፃ አውጪ ያዘመታቸው የፌስቡክ ደፈጣ ተዋጊዎች በየጊዜው በሚያወጧቸው መጣጥፎች ላይ ቋጥኝ የሚወረውሩት በእነሱ ላይ በመሆኑ ለህጉ የቅድሚያ ሰለባነት እያዘጋጇቸው ይመስለኛል።

በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት ጨቋኝ አዋጆችን ህውሃት ሲያወጣ የተከተለው አንዱ ስልት ይሄ ነበር። የበጐ አድራጐት አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ የፕሬስ ህጉ በዚህ መልኩ የፕሮፐጋንዳ ስራዎች ተሰርቶባቸዋል። በኢትዬጲያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች የህጐቹን ምንነት እና ከጀርባ ያዘለውን ፍላጐት ሳይመለከቱ አስተያየት ሲሰጡ ነበር። አዋጆቹ ከወጡም በኃላ የፕሮፐጋንዳ ማሽኖቹ በሰሯቸው ዶክመንተሪዎች ውስጥ በግብአትነት ውለዋል። ለኢህአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ ሳይቀር በጥቅም ላይ ውለዋል። መቼም አገዛዙ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኝነት ወንጀል አድርጐ ሲያሳድድ፣ ሲያስርና ምድረበዳ አድርጐ ለተመለከተ የዛን ወቅት በየዋህነት አስተያየት የሰጡ ሰዎች የእግር እሳት ሳይሆንባቸው አይቀርም። በተመሳሳይ ሁኔታ የሽብርተኝነት ህግ እንዲወጣ አስተያየት የሰጡ ሰዎች ዛሬ በዚህ ህግ ውስጥ የሰፈሩ ጨቋኝ እና ጨካኝ ድንጋጌዎች ያደረሱትን ጉዳት ሲመለከቱ መቆጨታቸው የሚቀር አይደለም።

***

ለሶሻል ሚዲያው ህግ መውጣት ሶስተኛ ምልክት ተደርጐ ሊወሰድ የሚችለው በትላንትናው እለት የህውሓት የሚዲያ መቆጣጠሪያ አውድማ ( “የብሮድካስት ባለስልጣን” የሚል መንግስታዊ ካባ እንዲለብስ የተደረገው ተቋም) መሪነት የተደረገው ኮንፍረንስ ነው። ” የማህበራዊ ሚዲያው የህግ ማዕቀፍ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ስብሰባ የማህበራዊ ትስስር ሚዲያው መተዳደሪያ የህግ ማዕቀፍ ሊወጣለት ይገባል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። በኮንፍረንሱ ከኢትዬጲያ ህዝብ ውስጥ 53 ሚሊዬን የግል የሞባይል ስልክ ( ዳታ ያለው) እንደሆነ ተበስሯል። እንዲሁም 16 ሚሊዬኑ የሶሻል ሚዲያው ተጠቃሚ እንደሆነ ተገልጿል። ህውሓት መቼም የቁጥር ነገር አይሆንለትም። በቁጥር መቀቀያ ቶፋው እንደ ጉም ይዘግነዋል።

የኮንፍረንሱን ዋና ማእከላዊ መልእክት ስንመለከት ባለፋት ሁለት አመታት በኢትዬጲያ ለነበሩት ግጭቶች ሶሻል ሚዲው ዋነኛ ተዋናይ እንደሆነ የተገለጠበት ነበር። ከዛም ባሻገር ሶሻል ሚዲያው ኢትዬጲያዊ እሴቶችን በመሸርሸር ሰዎች እንደሰው እንዳይታዩ ክፋትን የሚያለማምድ ነው ተብሏል። ሶሻል ሚዲያው ግጭትን የሚቀሰቅስና የሚያስፋፋ፣ የሀይማኖት ንትርክን የሚጋብዝ እንደሆነ ተወስቷል። ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰብአዊነት የሌለው አፍራሽ የግለኝነት ባህሪ ያዳብራሉ ተብሏል። እናም እንደዚህ አሉታዊ ነገሮች ላይ ለምን ማተኮር አስፈለገ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ለወደፊት የሚወጣው ህግ ምን አይነት ይዘት ይኖረዋል የሚለውን በቀላሉ መገመት ይችላል። እንሰሳይቱ ” ሳታማኸኝ ብላኝ!” እንዳለችው ማለት ነው።

***

ለጨቋኝ ህጉ መውጣት ገፊ ምክንያት ምንድነው?

የመጀመሪያውና ቀዳሚው ምክንያት ህውሃት በመቀሌ ያደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እና ድርጅታዊ ኮንፍረንስ የደረሰበት ድምዳሜ ነው። የኮንፍረንሱ መግለጫ በግልፅ እንዳመላከተው ህውሓት ለማድረግ የተዘጋጀው ጦርነት የመጨረሻውን ነው። ስያሜውንም የአርማጌዶን ጦርነት ብሎታል። እርግጥ ህውሃት አርማጌዶንን ሲያውጅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የዛሬ 17 አመት አቶ መለስ ነብስ ውጭ፣ ነብስ ግቢ ውስጥ ሰጥሞ ሲያገኘው አርማጌዶንን አውጆ ነበር። ይሄንን አዋጅ የአቶ መለስ ገድል የተገለፀበት የአቶ በረከት ” የሁለት ምርጫዎች ወግ” መፅሀፍ ላይ በገፅ 31 ላይ ፣

ኢህአዴጐች ጥገኛ ዝቅጠት በአገራችን ከተንሰራፋ ሊከተል ስለሚችለው አደጋ የሚሰጡት ምላሽ አርማጌዶን የሚል ነው። አርማጌዶን በጥንታዊ ሃይማኖታዊ መፅሀፍ ሰፍሮ የሚገኝ በመናፍቃንና በአማንያን መካከል የመጨረሻው ወሳኝ ፍልሚያ የሚካሄድበት ቦታ ነው። ይህ ተምሳሌታዊ አገላለፅ የተመረጠበት ምክንያት በኢትዬጲያ ጥገኛ ዝቅጠት ከተንሰራፋ ተወደደም ተጠላም አገራችን ከማትወጣው ቀውስ ውስጥ ትዘፈቃለች ለማለት ነው” ይላል።

ዛሬ ህውሓት በመግለጫው ላይ በድጋሚ የአርማጌዶን የመጨረሻ ወሳኝ ፍልሚያ ላይ እንደገባ ይፋ አድርጓል። በአብዬታዊ ዲሞክራሲ አዳኝነትን በተቀበሉ (አማኒያን) እና አብዬታዊ ዲሞክራሲ እንደ ህይወት መመሪያ ባልወሰዱ( መናፍቃን) መካከል የሞት የሽረት ትግል መቀጣጠሉን በአደባባይ ገልጠዋል። በሌላ አገላለፅ ከኢትዬጲያ ህዝብ ውስጥ አብዬታዊ ዲሞክራሲን አምኖ እና ተጠምቆ አዳኙ አድርጐ የወሰደ ( ከመቶሺህ የማይበልጠው) በቀረው 100 ሚሊዬን ህዝብ ላይ ጦርነት አውጇል። ይሄንንም ጦርነት በድል አድራጊነት ለመወጣት ጊዜ የለንም በሚል በፍጥነት መሮጥ እንዳለባቸው በደም አስምረውታል። የሶሻል ሚዲያው ህግም ህውሓት ከተደቀነበት የአርማጌዶን የህልውና አደጋና ከአደጋው ለማምለጥ የሚካሄድ የአቦ ሸማኔ ሩጫ ትጥቅ ሆኖ የሚያገለግል ነው። ለመቶ ሜትር ሩጫው ከሚያገለግሉ ትጥቆች ዋነኛው!!

ዛሬ በብሮድካስት ባለስልጣን በተካሄደው የማህበራዊ ሚዲያ የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊነት” ኮንፍረንስ ላይ የህውሓት ቁልፍ ሰዎችን በፊት መስመር ተሰልፈው ሲፋለሙ ለማየት የቻልነው በዚህ ምክንያት ነው። 6 ቁጥር ለብሶ የሚያከፋፍለው ሽማግሌው ስብሃት ነጋ፣…5 ቁጥር የለበሰችው የወንድሙ ልጅ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሔር( ሞንጆሪኖ)፣…1 ቁጥር የለበሰው የፓርላማው ንጉስ እና የብሮድካስት ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አስመላሽ ወ/ስላሴ፣… 7 እና 11 ቁጥር የለበሱት የብሮድካስት ዋና እና ምክትል ዴሬክተር ዘርአይ አስገዶም እና ልዑል ገብሩ ( ሁለቱም ህውሃቶች)፣ …8 ቁጥር የለበሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ተቆጣጣሪ( ዛዲግ አብርሃ)፣… መጠባበቂያ ወንበር ላይ የተቀመጠው የሰብአዊ መብት ዴሬክተር ዶ/ር አዲሱ ገ/ እግዚአብሔር( ህውሓት)፣.. የፋና ስራ አስኪያጅ ወልዱ ይመስል( ህውሓት) ፣… የዋልታ ኢንፎርሜሽን ሀላፊ አልማዝ (ህውሓት) በቅድሚያ የደም መስመር ተሰልፈው እና ጐላ ብለው የታዩት እኩልነትንና የበጣም እኩልነትን ለማድመቅ አይደለም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *