ሳዑዲ አረቢያ በሙስና ላይ በከፈተችው ከፍተኛ ዘመቻ እስካሁን 107 ቢሊዮን ዶላር ማስመለሷን የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጹ፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ አብዛኞቹ ቢፈቱም ሃምሳ ስድስቱ ግን አሁንም በምርመራ ላይ እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሼህ ሳዑድ አል ሞጀብ ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው 381 የሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ ያደረጉትን ፍተሻ ማጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ ሃምሳ ስድስቱን በማስቀረት ሌሎቹ ተለቅቀዋል ብለዋል፡፡
ከተለቀቁት ውስጥ ንጽህናቸው የተረጋጋጠ እንዳሉ ሁሉ የሙስና ከሱን አምነው ከመንግስት ጋር ስምምነት የፈጸሙ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ተርጣሪዎቹ በገንዘብ እና በንብረት መልኩ ለመንግስት ለመመለስ ስምምነት ላይ የደረሱበት የሀብት መጠን 107 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ ሳዑዲ ረቢያ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ በሙስና ጠርጥራ ካሰረቻቸው ልዑላን፣ ንጉሳውያን ቤተሰቦች፣ ቱጃሮች እና የቀድሞ ሚኒስትሮች ይገኙበታል፡፡
የሙስና ዘመቻው ሰለባ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼህ መሐመድ አላሙዲ ከሚፈቱት ውስጥ አንዱ እንደሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቅርብ አማካሪያቸው ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ አላሙዲን እስከ ትላንት ምሽት ድረስ ታሳሪዎች በቆዩበት ሪትዝ ካርልተን ሆቴል እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ “መቼ ይፈታሉ” ለሚለው ጥያቄ “በእነዚህ ሁለት ቀናት” ከማለት ውጭ በእርግጠኝነት ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡ ይሁን እና ዛሬ ከቀትር በኋላ ድረስ ስለመፈታት አለመፈታተቸው ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልተቻለም።