የአሜሪካ ኤምባሲ ለላሊባለው ቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ቤተክርስትያን ጥበቃ ይውል ዘንድ 13.7 ሚሊዮን ብር መስጠቱን ኤምባሲው በላከው መግለጫ አስታውቋል። ፕሮጀክት ይፋ የሆነው ቅዳሜ እለት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደ ማርያምና በአሜሪካው አምባሳደር ማይክል ሬይኖር ነው።

ከዚህ የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የአለም ቅርስ ፈንድ የሰጠው 119500 ዶላርም ለቤተክርስትያኑ ጥበቃ ስራ እንደሚውል ታውቋል። በቤተክርስትያኑ ላይ የሚደረጉ የጥበቃ ስራዎች ቀደም ሲል እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ላሊበላ ላይ የተሞከሩ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።

በፕሮጀክቱ የአካባቢው የግንባታ ባለሙያዎችም እንደሚሰለጥኑና የጥበቃ ስልቱን ለወደፊቱ እንዲተገብሩ እንደሚደረግም ተገልጿል። ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ዝግጅት ላይ አምባሳደር ሬይኖር እነዚህ ቤተክርስትያኖች ከመቼውም በላይ አስፈላጊ እንደሆኑና፤ የሚደረግላቸው ጥበቃም እንዲሁ አስፈላጊ ሆነው እንዲቀጥሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

” እየሰራን ያለነው የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክ አካል ለመጠበቅ ብቻ አይደለም።ይልቁንም የዛሬ የኢትዮጵያ ባህልና ሃይማኖት አካልን ነው”በማለት የኢትዮጵያ ባህል ከብዙ ምክንያቶች መካከል በብዝሃነቱ ልዩ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል። አምባሳደሩ እንደዚህ ካሉ የኢትዮጵያ እሴቶች ባሻገር በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካዊ አመለካከትን መግለፅንና የሃሳብ ልዩነትን ማቻቻል ላይም ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2003 ጀምሮ የአሜሪካ ኤምባሲ ለዘጠኝ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ድጋፍ ማድረጉም በመግለጫው ተገልጿል።

BBC – Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *