“Our true nationality is mankind.”H.G.

” ገለልተኛ ይሆናል ለተባለው” ምርጫ ቦርድ ወ/ሮ ሳሚያ ተመደቡ፤

ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩትና በ2009 ናይጀሪያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ሳሚያ ዘከሪያ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆኑ። ገለልተኛ ሆኖ ይቋቋማል የተባለው ምርጫ ቦርድ “ ድርድር” የሚባለው ስብሰባ ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ ኢህአዴግ በራሱ ታማኝ አዋቅሮታል።

ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማራ በቆጠራ መጥፋቱን አስመልክቶ ታሪካዊ መልስ በመስጠት የሚታወቁት ወ/ሮ ሳሚያ፣  “ከ37 አመት በላይ ባገለገልኩበት ማእከላዊ ስታስትቲክስ ኤጀንሲ ስራዬ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ነው፤በብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንኑ ለማስቀጠል እሰራለሁ፤ መንግስት እና ህዝብ የጣለብኝን ሀላፊነትም በብቃት ለመወጣት ጥረት አደርጋለሁ” በማለት ለፋና ተናግረዋል። የፋና ዜና ከዚህ በታች የአዲስ ተሿሚዎችን ዝርዝር ይዟል።

አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ

ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሾመ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባው ነው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የቀረበለትን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ሰባት የቦርድ አባላትን ሹመት ያፀደቀው።

በዚህ መሰረት፦

• አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

• አቶ ደሞዜ ማሜ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል

ምክት ቤቱ በተጨማሪም የሰባት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባላትን ሹመት አፅድቋል።

ሰባቱን የቦርድ አባላትም፦

1 ቀሲስ በላይ መኮንን

2 ወይዘሮ የሺሀረግ ዳምጤ

3 ፕሮፌሰር ፍቴን አባይ

4 ወይዘሮ ፀሃይ መንክር

5 አቶ ተካልኝ ገ/ስላሴ

6 አቶ ጀማል መሀመድ

7 አቶ ሀብቴ ፍቸላ ናቸው።

አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ከ1972 እስክ 1998 በኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስትቲክስ ኤጀንሲ ውስጥ ከቡድን መሪነት አንስቶ እስከ ምክትል ስራ አስኪያጅነት ሰርተዋል። ከ1998 እስከ 2009 ዓ.ም ደግሞ የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል።

አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አምባሳደር ሳሚያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “ከ37 አመት በላይ ባገለገልኩበት ማእከላዊ ስታስትቲክስ ኤጀንሲ ስራዬ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ነው” ብለዋል። “በብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንኑ ለማስቀጠል እሰራለሁ፤ መንግስት እና ህዝብ የጣለብኝን ሀላፊነትም በብቃት ለመወጣት ጥረት አደርጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።

በፋሲካው ታደሰ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኤፒ ለቅጥፈቱ ይቅርታ አልጠየቀም – ምርጫ ተራዘመ፤ለምን?
0Shares
0