ሌሞንዴ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ቻይና በአዲስ አበባ የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ላለፉት አምስት ዓመታት ስትሰልልና የህብረቱንም መረጃ ስትመነትፍ ቆይታለች ሲል ከሰሞኑ ያሰራጨው መረጃ ውዝግብን አስነስቷል።እንደዘገባው ከሆነ ቻይና የህብረቱን መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለመሰለል ያበቃት ፅህፈትቤቱን ገንብታ ለአፍሪካ ሀገራት ስታስረክብ የተጠቀመችባቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ስለላን ጭምር የሚያከናውኑ መሆናቸው ነው።

ቻይና ይሄንኑ ሥለላዋን በዋነኝነት የምታከናውነው በህንፃው ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጡትን ኮምፒዩተሮች በመጠቀም መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፤ መረጃው አዲስ አበባ ከሚገኘው የህብረቱ ፅህፈት ቤት ሰርቨር በቀጥታ ወደ ሻንጋይ የሚላክ መሆኑን ጨምሮ ይገልፃል። ይህም ሥለላ ህንፃው በይፋ ከተመረቀበት እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ሲከናወን የነበረ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ያመለክታል።

ድርጊቱ በ2017 የህብረቱ ፅህፈት ቤት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንጂነሮች በፅህፈት ቤቱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ውስጥ አንዳንድ እንግዳ ነገሮችን ከተመለከቱ በኋላ የተደረሰበት መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ይገልፃል። ህንፃው ሙሉ በሙሉ በቻይና መንግስት ከመገንባቱ ባሻገር ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂም ቻይና ሰራሽ መሆኑን ያመለከተው ሌሞንድ፤ የቻይና ኢንጂነሮች ሆን ብለው የስለላ መሳሪያዎች በህንፃው ውስጥ እንዲካተቱ ያደረጉ መሆኑን በዚሁ ዘገባው አመልክቷል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ይህ መረጃ መውጣት እንደጀመረ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው የነበሩትን ኮምፒዩተሮች ለመቀየር ተገዷል። ከዚያ በኋላም በህንፃው ውስጥ በተደረጉ የፍተሻ ሥራዎችም የድምፅ ማጉያዎች ሳይቀሩ በየግድግዳውና ጠረጴዛዎች ውስጥ ሳይቀር ተቀብረው መገኘታቸውን ሌሞንዴን ዋቢ ያደረገው የዘ ጋርዲያን ዘገባ አመልክቷል። ጋዜጣው ምንጭ ያደረገው ማንነታቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የህብረቱን ፅህፈት ምንጮች መሆኑን የ ዘ ጋርዲያን ዘገባ ጨምሮ ይገልፃል።

በአፍሪካ ህብረት የቻይና አምባሳደር ኩዋንግ ውሊን በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት ዘገባው ሀሰት መሆኑን ገልፀው፤ ይህ አይነቱ መረጃ የቻይና አፍሪካ ወዳጃዊ ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑን ገልፀዋል። ዘገባው ሆን ተብሎ በአፍሪካ ቻይና ግንኙነት ላይ አሉታዊ ጫናን ለማሳደር የተሸረበ ሴራ መሆኑን አምባሳደሩ ጨምረው አመልክተዋል።

ቻይና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዙሪያ በተለያዩ ሀገራት የምትሰራቸውን ሥራዎች ተአማኒነት እንድታጣ በማድረግ ጉዳት ሊያደርስባት ይችላል የሚል ሥጋትን አሳድሯል። የአፍሪካ ህብረት በዚሁ ዙሪያ በሰጠው ማብራሪያ ዘገባውን ውድቅ ያደረገ መሆኑን ይሄው የ ዘ ጋርዲያን ዘገባ ይገልፃል።

በአዲስ አበባ በህብረቱ ስብሰባ ላይ የነበሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም የሌሞንድን ዘገባ ያጣጣሉት መሆኑ ታውቋል። ቻይና የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤትን በ2 መቶ ሚሊዮን ዶላር በመገንባት ለአፍሪካ ህብረት ያስረከበችው እ.ኤአ በ2012 ነበር። ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ጥብቅ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በ2015ቱ የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለአፍሪካ ሀገራት 60 ቢሊዮን ዶላር በኢንቨስትመንትና በእርዳታ መልክ ገንዘብ የምትለቅ መሆኗን በፕሬዝዳንት ዢንግ አማካኝነት መግለጿ የሚታወስ ነው።

ከሰንደቅ ጋዜጣ ተወሰደ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *