የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በወሰነው መሰረት በፌደራል ደረጃ በተለይም በሽብር፣ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሀይማኖት አክራሪነት እና በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 417 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወሰነ።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ ከታራሚዎቹ መካከል 298 በፌደራል ማረሚያ ቤት የሚገኙ እና 119 በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ናቸው በይቅርታ እንዲለቀቁ የተወሰነው። የታራሚዎቹ ዝርዝር በይቅርታ ቦርድ ለሀገሪቱ ርእሰ ብሔር ቀርቦ ከፀደቀ እና ተገቢውን የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ህብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉም ነው የተገለፀው። እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው መካከልም እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ ይገኙበታል።

በተመሳሳይ ጉዳያቸው በህግ በመታየት ላይ የነበሩ 329 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ ተወስኗል። በዚሁ መሰረት 278 በፌደራል፣ 18 በአማራ ክልል እና 33 በትግራይ ክልል የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ እንዲለቀቁ ተወስኗል።

ቀደም ሲል በመጀመሪያ ዙር የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋርጦ ከእስር መለቀቃቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ መግለፁ ይታወሳል። ከእነዚህ ክሳቸው ተቋርጦ ከተለቀቁ ተጠርጣሪዎች መካከል 115ቱ በፌደራል ደረጃ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ 413 ደግሞ በደቡብ ክልል ናቸው።

በመቀጠልም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለ2 ሺህ 345 የህግ ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች ይቅርታ እና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ ማድረጉ ይታወሳል። በተመሳሳይ በአማራ ክልል የ598 ተጠርጣሪዎች ክስ ሲቋረጥ ለ2 ሺህ 905 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።

ፋና

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *