• ችግር እየደረሰብኝ ያለው በዳኛ ዘርዓይ ምክንያት ነው
  • እየተረዳሁት ያለሁት ማረሚያ ቤቱ ፍርድ ቤቱን እያዘዘው እንደሆነ ነው

የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መብራቱ ጌታሁን ዛሬ በፍርድ ቤት የተናገሩት

በጌታቸው ሺፈራው — “በእስር ቤት ብዙ ችግር እየደረሰብኝ ነው። ጨለማ ቤት ውስጥ ነው ያለሁት። ይህን ችግር እያደረሰብኝ ያለውን የቀኝ ዳኛው (ዳኛ ዮሃንስ ጌሲአብ) ያውቁታል። ይህ ችግር እየደረሰብኝ ያለው በዳኛ ዘርዓይ ምክንያት ነው። በወልቃይት ጉዳይ ላይ የሚከራከር ዳኛ ለምን ዳኛ ሆኖ ይከራከራል ብየ በመናገሬ ነው። ከፍርድ ቤት እንደተመለስኩ ነው ለምን ፍርድ ቤት ትናገራለህ ተብዬ ጨለማ ቤት የገባሁት። ህዳር 26/2010 ዓም የገባሁ አሁንም ጨለማ ቤት ውስጥ ነኝ። ማዕከላዊ አይኔ ላይ ጉዳት ደርሶብኛል። አሁን ጨለማ ቤት ትልቅ ችግር የዓይኔ ጉዳይ ነው። ሆን ተብሎ ሞራል ለመጉዳትም ነው። የታሰርኩት ከአእምሮ ሕሙማን ጋር ነው። ችሎቱ አቅም ካለው ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልኝ። ፍርድ ቤቱ በችሎቱ የሚታዘዝ ከሆነ ግን ልወቀውና ያስገባሁትን ማመልከቻ ይመለስልኝ።

ፍርድቤት ማለት በስመ እግዚያብሔር፣ በስላሶች ተምሳሌት የተሰየመ ነው። አሁን እየተረዳሁት ያለሁ ግን ማረሚያ ቤቱ ፍርድ ቤቱን እያዘዘው እንደሆነ ነው። መፍትሔ የማትሰጡኝ ከሆነ ያስገባሁትን ማመልከቻ ይመለስልኝና ፍትህ የለም ብዬ ለሚመለከተው እንዲያውቅ አደርጋለሁ።” 1ኛ ተከሳሽ መብራቱ ጌታሁን (ፎቶ የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል)Ethiopian political prisoner, Mebratu Getachun.

— አቶ መብራቱ ጌታሁን ከአሁን ቀደም የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀመባቸው ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልሰጠም። ዛሬ የካቲት 1/2010 ዓም የዋለው ችሎት አቤቱታውን እንደገና እንደሚያየው ገልፆአል። ጠበቃ አለልኝ ምህረቱ ታህሳስ 38/2010 ዓም አቶ መብራቱ ጌታሁን ጨለማ ቤት መግባታቸውንና ሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ በፅሁፍ ያቅርቡ ባላቸው መሰረት አቅርበው እንደነበር ገልፀዋል። ሆኖም በፅ/ቤት በኩል ትዕዛዙ ለማረሚያ ቤት መላክ አለመላኩን ይከታተሉ ተብለው ሁለት ጊዜ ተመላልሰው ቢያስታውሱም ትዕዛዙ አለመላኩን ገልፀዋል። የዛሬውም አቤቱታም በችሎት እንዲታይና እንዲታዘዝ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አይቶ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልፆአል።

— አቶ መብራቱ ጌታሁን ጨለማ ቤት እንድገባ ምክንያት ሆነዋል ያሏቸው ዳኛ ዘርዓይ በችሎት አልተገኙም። እሳቸውን ተክተው ስሜነህ በላቸው የግራ ዳኛ፣ ሌሊሴ ደሳለኝ የመሃል ደኛ፣ እና የመሃል ዳኛ የነበሩት ዮሃንስ ጌሲአብ የቀኝ ዳኛ ሆነው ተሰይመዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ መብራቱ ሲናገሩ ሊያቋርጣቸው የነበር ቢሆንም አቶ መብራቱ “በዝርዝር እንድናገር ይፈቀድልኝ” ባሉት መሰረት ንግግራቸውን አስጨርሷቸዋል።

— አቶ መብራቱ ጌታሁን ከህዳር 26/2010 ዓም ጀምሮ ከቤሰተብ ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ፣ ባለፈው ቀጠሮውም በማረሚያ ቤት መጠየቅ እንደማይችሉ በመግለፃቸው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያገናኝ ቢያዝም ፖሊስ ትዕዛዙን እንዳልፈፀመ ተገልፆአል። በመሆኑም በዛሬው ዕለት ቤተሰቦቻቸውን በችሎት እንዲያገኙ ካልተፈቀደላቸው የትም ሊያገኙዋቸው እንደማይችሉ በመግለፃቸው በችሎት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ ጠይቀው ለተወሰነ ደቂቃ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ ተደርጓል።

በእነ መብራቱ ጌታሁን ክስ መዝገብ ጉዳያቸው እያታየ የሚገኘው አቶ መብራቱ ጌታሁን፣ አቶ ጌታቸው አደመ እና አቶ አታላይ ዛፌ ሲሆን አቶ አለነ ሻማ እና አቶ ነጋ ባንተይሁን ከእስር ተፈትተዋል። እነ መብራቱ ይከላከሉ አይከላከሉ የሚለውን ለመበየን ለየካቲት 12/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *