ዛሬ ባለንበት ሁኔታ የትግሉ ዋና ዒላማ ገዥው ቡድን ሳይሆን ለብቻዬ ልግዛ ሲል፣ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ያደረሰው ብልሽት በመሆኑ አቅጣጫን ሳይስቱ መንግሥታዊ አውታሩ (የደኅንነት፣ የመከላከያ፣ የፍትሕ፣ የምርጫ፣ የመረጃና የፕሮፖጋንዳ ተቋሙ ሁሉ) ከየትኛውም ቡድን ይዞታነት እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ችሮታነት እንዲያከትም በመታገል ላይ ማተኮርና ኢሕአዴግን ሰንጎ የትግሉ አካል እስከማድረግ የሰፋ ሥልት መጠቀም ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡ reporter

በገነት ዓለሙ

ስለሕዝቦች ልዕልናና ስለዴሞክራሲ ድል መምታት እነሆ አሁንም 27 ዓመት ላይ ሆነን እያወራን ቢሆንም፣ ዛሬም የፀረ ዴሞክራሲ የአፈና ዘይቤዎች እንደደላቸው ናቸው፡፡ አሁንም የሕዝብ ቅሬታዎች መተንፈሻ አጥተው መጠራቀማቸውና አጋጣሚ እየጠበቁ መፈንዳታቸው አልተቋረጠም፡፡ ስለጥበትና ስለትምክህት አደገኛነት ለዓመታት ስናወራ ብንኖርም፣ ዛሬም አገሪቷን የሚንጧትን ችግሮች መስፋፋታቸውን ማዳከምና አደጋቸውን ማምከን አልተሳካልንም፡፡

ልዩነትን በውይይት፣ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ፍጥርጥርና ጨዋነት ያጣ ሥርዓት ውስጥ እንድንኖር በራሳችን ላይ ስለፈረድን፣ ልዩነታችን አብሮ ለመሥራት አያስችለንም ተባብለን ሰላም ያጣ ሕይወት ውስጥ ገብተናል፡፡ ጠባብና አጫጭር ጥቅሞች ሕዝቦችን የከፋፈሉበት የጥላቻ ንፋስም ሕዝብ ውስጥ ገብቶ ዕይታን ያሳሳተበት ሁኔታ ሳይታከም ባለበት የሚፈነዳ ቁጣ ሥጋት የሚሆነው ለአገዛዙ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለሕዝቡም ሰላም፣ ደኅንነትና ህልውና ጭምር ነው፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያና በአማራ ቀጥሎም በመላው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ በአማራ ወልዲያ፣ ቆቦ፣ መርሳ፣ ወዘተ የተከሰቱ የብሶት ቁጣዎችና እነሱ ውስጥም ብልጭ እያሉ እየከፉ የመጡ ጭፍን ጥቃቶች፣ የእርስ በርስ ፍጅት አገሩ ሩቅ እንዳልሆነ ደጋግመው የተሰሙ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው፡፡

ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተናገጃ መድረክ እስከቸገራቸው ድረስ፣ አዘናግተው ወደ ቁጣዎች መቀየራቸውና ጥፋት ማድረሳቸው አይቀርም፡፡ በቅሬታዎቹ ውስጥ የሕዝቦችን ግንኙነት ያቆሳሰለ ነገር ካለ ደግሞ ጉዳዩ መንገድ ስቶ ሊያደርስ የሚችለው ጥፋት አደገኛ ነው፡፡ ያውጣን የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህ ግን ከአደጋ አያድንም፡፡ ከአደጋ የሚያድነን መዘዞችን ከነመርዛቸው መንቀል ነው፡፡

የዚህ ሁሉ መነሻና የጥበብ መጀመርያ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ውስጥ ሙጥኝ ማለት ነው፡፡ ያለውን ይዞ እንዳለቀሰው ብልጥ ልጅ ብልህ ትግልም ካለው መንግሥት ሊያገኝ የሚችለውን እየለቀመ ለበለጠ ድል ይዋደቃል፡፡ የትጥቅ ትግል ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጋር አገርን አብሮ ያደቃል፡፡ ለረዥም ዓመታት ሲተኩሱ ፈንጂ ሲዘሩና መሠረተ ልማት ሲያወድሙ ኖረው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ መልሶ ግንባታ ማለት በዛሬው ዘመን ዕብደት ነው፡፡ የትናንትናው የኢሕአዴግ በዚህ መስመር የሄደ ትግል ራሱ ከጥያቄ ውጭና ከንግግር በላይ አይደለም፡፡ አሸባሪ የትግል ሥልት ቀርቶ የሕዝብና የውጭ የፖለቲካ ድጋፍን የሚጎዳ የትግልም ዓይነት ክፉ ነው፡፡ እንኳን ሰበብና መንገድ አግኝቶ ያልሠሩትን ሠሩ እያለ መበከል የሚቻለው ገዥው ቡድን ቁጣን አፍዝዞ ‹‹ፀረ ልማቶችን›› የመመንጠር ሽፋን እንዲያገኝ መፍቀድ አያስፈልግም፡፡ በአፍራሽ የትግል ሥልት ላይ የማያወላውልና በተግባር የሚዘልቅ አቋም ካልወሰዱ በአሸባሪነት መወንጀል አይመክንም፡፡ ዴሞክራሲም ቅርብ አይሆንም፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣን ቢወርድ እንኳን ከዚያ ወዲያ በምርጫ ተወዳድሮ ያሸነፈ ይምራ ተብሎ የሚተው ያለቀለት ነገር አለመኖሩን የራሱ የኢሕአዴግ ድል፣ የሽግግሩ ዘመን ዝግጅት ታሪክ ደህና አድርጎ አስተምሮናል፡፡

በተለይ ዛሬ ባለንበት ሁኔታ የትግሉ ዋና ዒላማ ገዥው ቡድን ሳይሆን ለብቻዬ ልግዛ ሲል፣ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ያደረሰው ብልሽት በመሆኑ አቅጣጫን ሳይስቱ መንግሥታዊ አውታሩ (የደኅንነት፣ የመከላከያ፣ የፍትሕ፣ የምርጫ፣ የመረጃና የፕሮፖጋንዳ ተቋሙ ሁሉ) ከየትኛውም ቡድን ይዞታነት እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ችሮታነት እንዲያከትም በመታገል ላይ ማተኮርና ኢሕአዴግን ሰንጎ የትግሉ አካል እስከማድረግ የሰፋ ሥልት መጠቀም ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡

የዚህን አባባል እውነታነት አሁን ድረስ የዘለቁት ድኅረ 2008 ዓ.ም. የሕዝብ ተቃውሞ የአካሄድ ፈለጎች አረጋግጠዋል፡፡ በሕዝብ ተቃውሞ ውስጥ ሥውር እጅ ገባበትም አልገባበትም በእልህ ምክንያት ይሁን የትግል ታክቲክ ተብሎ በልማት ነክ ተቋማት ላይ የተካሄዱ አውዳሚ፣ አሰናካይና መዝባሪ ጥቃቶች የሕዝብን ልብ ከፋፍለዋል፡፡ ድንጋጤና ግራ መጋባትን አስከትለዋል፡፡ አሥር ወራት ለቆየው ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ለመንግሥት የእንዳሻው ዕርምጃ ተገቢነት ጥሩ ማመካኛ ሆነዋል፡፡ ተቃውሞው እንዲጨናገፍም ጠቅመዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከገዥው ፓርቲ አፍቃሪዎች ባሻገር በተቃውሞው የጥፋት ሥራዎች የተቆጡና ያዘኑ ሁሉ ደግፈውታል፡፡

በስንት መከራ የተገነቡ ተቋማትን አጠፋፍቶና አጋይቶ ከዜሮ መጀመር (እንደዚያ ብሎ ነገር እና ዕድል ካለ) ዛሬ አዋጭና ይበል የሚባልለት መንገድ አይደለም፡፡ የተቃውሞ ወገኖች በጋራ ትልም የተገናኙበትና ሕዝብን አንድ ላይ ማሰለፍ የቻሉበት ሁኔታ በሌለበት፣ የተራገበ የዚህ ዓይነት በጥላቻና በውድመት የቀለመ አካሄድ ዴሞክራሲና ሰላም ውስጥ ለማስገባቱ ፈጽሞ መተማመን አይቻልም፡፡ ከፖለቲካ ፍላጎቶች ወንጋራነት ሌላ ውድመቱ በራሱ የሚያስታቅፈው ችግርና ፈተና ወደ መናጨት ለመሄድ ስንቅ ይሆናል፡፡ ተዘንግቶ ከሆነ ከጦርነት ጥይት የበለጠ የኢኮኖሚ መንኮት (መንኮታኮት) በፍዳ ጥይቱ ብዙ ሰው እንዳመሰና እንደረፈረፈ መለስ ብሎ ድኅረ 1967 ዓ.ም. የ17 ዓመት ትግል መቃኘት ይኖርብናል፡፡

በ2008 ዓ.ም. (እስከ 2009) ተቃውሞ ውስጥ የተከሰተው የኢኮኖሚ አውታራትን የማውደም የትግል ሥልት የቅብጥብጥ ፖለቲከኝነት አንዱ መገለጫ ነበር፡፡ መከረኛው ‹‹ወያኔ አልቆለታል!›› በሚል ሆይ ሆይታ ሕዝብ ግፋ በለው ተባለ፡፡ ያልተግባቡ የፖለቲካ መስመሮች ከጥላቻዎች ጋራ ተጋግዘው መፋጀትን ያስከትላሉ የሚል ጭንቀት ነገሠ፡፡ ይህ ጭንቀት ሲመጣ ደግሞ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጪው ጊዜ ብሩህ እንጂ አስፈሪ አይደለም›› ተባለ፡፡ በምልክት መነጋገርን እስከ መከልከል የሰፋ (አሁንም ባህል ሆኖ የሚገዛ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላም ምን አዲስ ነገር መጣ? ኢትዮጵያ እኮ ዘለዓለሟን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነች ማለት መጣ፡፡ እነዚህ ሁሉ የማውደም ታክቲክ ባልንጀራሞች ነበሩ፡፡

እነዚህን ሁሉ ያዋደዳቸው ደግሞ በምንም ዘዴና በየትኛውም የመስዋዕትነት ክፍያና ዋጋ (ሕዝብን አካልቦና አስክሮ በመማገድ ጭምር) ገዥውን ኃይል የማስወገድ ቅብጥብጥነት ነው፡፡ ይህ ቅብጥብጥነት የነገሠው ደግሞ ልዩ ልዩ የሕዝብ ፍላጎቶችን፣ አስተሳሰብንና ቁጣዎችን አቅንቶ በአንድ አቅጣጫ ያንቀሳቀሰ የጋራ ፖለቲካ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ የቴሌና የኢንተርኔት ግንኙነትን እንደ ቤት አምፖል የሚቆጣጠረውን፣ ግዙፍ የደኅንነት መረብና የታጠቀ ኃይል የሚያንቀሳቅሰውን መንግሥት መጣል ይቻላል የሚል እምነትና ቅዠት ውስጥ የገባውም ይኸው እሳት ከመለኮስ፣ ድንጋይ ከመወርወር፣ መንገድ ከመዝጋት በቀር ሌላ ኃይል ያልነበረውና የሌለው የተበታተነ ቁጣ ነው፡፡ የታጠቀው ኃይል መከፋፈል ውስጥ የገባ የሚመስላቸው ድንገት ከነበሩና አሁንም ካሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ልምድ ወዲህ በሠራዊቱ ውስጥ ንፋስ እንዳይገባ ንቁ ዓይን የማይቦዝንና የማያባራ የማጥራት ሥራ የሚካሄድ መሆኑን የማይገነዘቡና የማያውቁ ናቸው፡፡

የተቃውሞው ፖለቲካ በፀጥታ ኃይሉ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ልብ የማሸፈት ለውጥ ሳያስከትል አልቀረም የሚል እምነት ከነበረና ካለም፣ የተቃውሞው ፖለቲካ ራሱ እኔ ራሴ ምን ያህል ከጉድፍ ተላቅቄያለሁ? ምን ያህል የጋራ ውል ፈጥሬ ሕዝቦችን ከማደናገር ገላግያለሁ? ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ሠራዊቱ በገዥውና በተቃውሞ ወገን የተፈነከተበት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን መጪው ጊዜ ከብሩህነት ይልቅ የውጭ እጅ ሁሉ ወደገባበት የእርስ በርስ መጫረስ የመቀየሩ ዕድል ከፍ ያለ ሊሆን መቻሉም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ድንገት መንግሥት የተንኮታኮተበት ሁኔታ ተከስቶ ቢሆን ኖሮም ይኖር የነበረው የፖለቲካ ተግባር ግድብ በሰበረ የቁጣ ማዕበል ውስጥ ታንኳ ለመቅዘፍ እንደ መሞከር ከባድ ነው፡፡ በውስጣችን ያሉ የተወነጋገሩ ፍላጎቶች፣ እልሆችና በቀሎች የሚፍጥሩት አዙሪት የሚያዝ የሚለቀቅ እስኪጠፋ መፈታተናቸው የማይቀር ነው፡፡

በዚህ ምክንያት የዛሬው የኢትዮጵያ እውነታ ከቁሳዊ ልማት ጋር የዴሞክራሲና የእኩልነት ግንባታ እንዲጣጣም ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ዓላማ አኳያ የተቃውሞ ትግል ከጥፋት ርቆ፣ ለውንጀላና ለድቆሳ እንዳይመች ሆኖ ፍሬ እንዲሰጥ በማብቃት ላይ ማተኮር አለበት፡፡ እዚህ ላይ የማያተኩር የተቃውሞ ፖለቲካ ተሳስቶ ማሳሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

በተለይ ከውጭ በሚለቀቁ የተለያዩ የተቃውሞ የመገናኛ ብዙኃን መድረኮች ላይ እንደሚታየው (ኢሳት፣ ኦኤምኤን) ኢሕአዴግን ከመጣል በቀር እርስ በርስ የማይጣጣሙ የፖለቲካ ፍላጎቶች ይረጫሉ፡፡ የፖለቲካ አዝማሚያዎችን በበሰለና በተረጋጋ ስሜት እየቦረቦሩ ሕዝብን ወደ አንድ አቅጣጫ የማምጣት ሥራ እንኳ አይያያዝላቸውም፡፡ በኢሕአዴግ ላይ የተያዘውም አቋም በጎ ሥራውን ሁሉ ጨለማ ውስጥ የከተተ ለአገሪቷና ለሕዝቦቿ ችግር እንጂ መፍትሔ ሊሆን የማይችል አድርጎ በመጥመድና በማስጠመድ የተሞላ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አውጋዥነት ከገዥው ፓርቲና ከደጋፊዎቹ በኩል የዴሞክራሲ ለውጠኝነት ተፈልቅቆና ፈክቶ እንዳይወጣ፣ ይልቁንም ጭራሹን እንዲመክንና ሁሉም ሥልጣን ላይ ሙጭጭ በማለት ዙሪያ እንዲረባረብ (‹‹አብዮትዊት እናት አገር ወይም ሞት!›› ዓይነት) የሚገፋ ነው፡፡ ገዥው ቡድን አገርን ከዳር እስከዳር ሸፍኖ የመግዛት አቅም ያጣበት ደረጃ ላይ ቢደረስ እንኳን ‹‹ወዮልህ! መትረፊያ የለህም!›› በሚል ፍርኃት እየተመራ እንደ ሶሪያው በሽር አል አሳድ አንድ ራሱ እስኪተርፍ ድረስ ትንቅንቅ እንዲገጥም የሚጋብዝ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የሞቼ እገኛለሁ ትንቅንቅ ውስጥ ደግሞ ስንት የሚዘገንን የመከፋፈልና የመላተም ጥፋት ከየትኛውም አቅጣጫ ሊከሰት እንደሚችል ለመገንዘብ ሶሪያ ድረስ መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ሳይነሳ መቅረት የሌለበት፣ ነገር ግን መነገሩ ራሱ የሚያስፈራና ከንግግር በላይ ሆኖ ውስጣችን የመረቀዘ የአገር ሕመም አለ፡፡ ቀስ ብለን እንነጋገርበት፡፡

‹‹የዱሮ ሥርዓት ለመመለስ የሚሻው የአማራ ትምክህት›› የሚል ማብቂያ ያጣ የካድሬ ውትወታና መጤዎችን (በተለይም አማሮችን) የማፈናቀል ዶሴ እስከ ዛሬ ድረስ አለመዘጋቱ እስከዚህ ድረስ አማራ በምን ኃጢያቱ ነው የተጠመደው? ከማንም በበለጠ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ደሙን ስላፈሰሰ ነው? የሚል እንቆቅልሽ ፈጥሯል፡፡ የፍቅሬ ቶለሳ ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ሐረግ›› የሚል መጽሐፍም በአንድ በኩል የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ በሕወሓትና በትግራውያን ዘንድም፣ ትግራዊን የደመኛ ያህል የሚያይ ጥላቻ የተስፋፋውስ ለምን? የትግራይ ልጆች ከማንም ይበልጥ በፀረ ደርግ ትግል መስዋዕትነት ከፍለው ለሁሉም የተረፈ ለውጥ ስላመጡና አሁንም ለኢትዮጵያ ልማት በግንባር ቀደምነት እየተዋደቁ መሆናቸው ጥፋት ሆኖ? የሚል ግራ መጋባት አለ፡፡ ተራው አማራና ትግራዊ በእነዚህ እንቆቅልሾች ውስጥ ቢወዘወዝ አያስገርምም፡፡

ትምህርት የዘለቁ አማራና ትግራዊ ፖለቲከኞች እንቆቅሉሽን እንደ ጋቢ ተከናንበውት (በዘረኞች እኩይነት እያመካኙ) መቆየታቸው ግን እውነቱን ለመጨበጥ ካለመቻል ይልቅ፣ እውነቱን ከመሸሽና በማላከኪያ ራስን ከማታለል የመጣነው፡፡ በየትኛውም ኅብረ ብሔራዊ አገር ውስጥ ሥልጣነ መንግሥት ከአንድ ወይም ከጥቂት ማኅበረሰቦች በመጡ ገዥዎች የበላይነት ሥር እስከወደቀ ድረስ ለገዢዎቹ መገኛ ማኅበረሰቦች የሚተርፍ ጥላቻ እንደሚፈጠር፣ ‹‹የእኔ ወገኖች ሥልጣን ያዙ›› የሚል መመካት ብዙ ማናለብኝነት እየወለደ ጥላቻንና ብግነትን እንደሚያራባ በኢትዮጵያ የትናንትናና የዛሬ ኑሮ ውስጥ ማጤን ከባድ አይደለም፡፡ የአማራና የትግራይ ብዙ ትምህርት ቀመሶች ግን ይህን ማስተዋልና መቀበል ሲተናነቃቸው ይታያል፡፡

ለአማራ መጠመድ የሥረ መሠረት መዘዝ የነበረው አማራ ገዥዎች የተከማቹበት ቅድመ ኢሕአዴግ አገዛዝ እንደነበር ሊካድ አይችልም፡፡ ከአገዛዙ መገርሰስ በኋላም ‹‹ነፍጠኞች››ን የመበቀል ስሜትን፣ ግጭትንና መፈናቀልን የማይመለጥ ያደረገው ችግሩ ትክክለኛና አርቆ አስተዋይ የፖለቲካ አያያዝ አለማግኘቱ ነበር፡፡ ከዚያም ወዲያ በተለያየ ዘዴ ‹‹መጤ›› መግፋትና ማባረር ብቅ ጥልቅ ሲል የቆየው ሥልጣን ላይ የወጣ ጎሰኝነት ‹‹ፀረ ትምክህት ትግል››ን የግል ዝርፊያን ለመሸፈን፣ የሕዝብ ቅዋሜን ለማደናገርና ዓላማ ለማሳት ስለሚጠቀምበት ነበር፡፡ ከመአሕድ ጀምሮ ብሔርተኝነት ጠንቄ ያለ የፖለቲካ ስብስብ መልክ እየቀያየረ መቀጠሉም ለዚህ ዓይነቱ አጭበርባሪ ቀዘፋ መገልገለያ ሆኗል፡፡ እነዚህ እውነቶች በቅጡ አልተጨበጡም፡፡ ‹‹ሰው በላ››ን ሥርዓት በሚያመጣ ‹‹የአማራ ትምክህት›› የሚያስፈራራውን የዛሬ ገዥዎች ብልጣ ብልጥነትን እንደምን ማክሸፍ ይቻላል የሚለው ጥያቄም በአማራ ፖለቲከኞች ዘንድ እስካሁን መልስ አላገኘም፡፡

ለኢትዮጵያ የተከፈለውን መስዋዕትነት ከሌላው የማስበለጥ ማናህሎኝነትም ጥላቻን ለማሳፈርም ሆነ ለማስወገድ የማይጠቅም፣ እንዲያውም ትዝብት ላይ ሊጥልና ጥላቻን ሊያብስ የሚችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ረዥም የአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ አማራነትን ዘርግቶ ለማየት ቢሞከር የሚደረስበት መደምደሚያ ራሱ በራሱ እየተዋለደ የመጣ ሕዝብ ዘንድ ሳይሆን፣ ከብዙ ምንጮች የተዘማመደ ጥንቅር ዘንድ ነው፡፡ የጎጃሜነትን፣ የወሎዬነትን፣ የጎንደሬነትን፣ የመንዜነትን፣ የምንጃሬነትን፣ ወዘተ የቅርብ ታሪካዊ ጀርባ ጫን ብንለው ኦሮሞነት፣ አገውነትና ትግሬነት እዚያና እዚህ ፍጭጭ ይላል፡፡ በሌላ በኩል፣ የ‹‹አማራ›› ስያሜ ነባር አጠቃቀም ከሥፍራ አመልካችነቱ ሌላ፣ ቢያንስ ክርስትናን የሚከተሉ ማኅበረሰቦችን ሁሉ የሚሸፍን እንደመሆኑ ‹‹አማራ›› እያለ የሚያወሳን ትረካ ሁሉ፣ ለአንድ ዓይነተኛ ብሔረሰብ መስጠት ስህተት ላይ መውደቅ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሰሜን እስከ ታች ድረስ በተሳተፉበት የፀረ ፋሽስት አርበኝነት ጊዜ፣ በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረን የትግል መደብዘዝ ለአማሮች የትግል ብልጫ ማነፃፀሪያ ለማድረግ መሞከር ጅልነት ወይም ሚዛን መሳት ነው፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ላይ የፈጠረው ማስኮረፍ፣ በሰሜንና በደቡብ የነበረው የመሬት ሥሪት ልዩነት፣ ወራሪው ጣሊያን ጭሰኝነትን መሰረዙ፣ የአርበኝነት ትግሉ ደግሞ ባያሌው ከመኳንንታዊ መሪነት አለመራቁና ጭሰኝነት ዳግም የማይመለስበትን ሥርዓት የማቋቋም ዓላማን አለማንገቡ፣ በአንድ ላይ የአርበኝነት ትግሉን ፋይዳ ፋሽስቶች ያስወገዱትን ጭሰኝነት እንደገና ለማስመለስ ከመዋደቅ ጋር አመሳስሎት ነበር፡፡  እንደዚህ ያለው አይውጡት አይተፉት የሆነ ሁኔታ የፋሽስት ወራሪው ከፋፋይነት ተጨምሮበት፣ በተወሰነ አካባቢ ላይ ፈጥሮት የነበረው መፍዘዝ በለጥኩ ብሎ ለመመፃደቅ እንደማይመች መረዳት ይበጃል፡፡

ከኢሕአዴግ ሥልጣን ወደዚህ በትግራዊ ብሔረሰብ ላይ ያረፈው ‹‹ቅያሜ›› መንኮታኮትም የግድ ሕወሓትን ማንቀርን አይጠይቅም፡፡ ወይም ኢሕአዴግ ከሥልጣን እስኪወርድ ድረስ መዘግየት አይኖርበትም፡፡ የአገሪቱ ሥልጣነ መንግሥት ምሰሶዎች ከቡድን ታማኝነት ያለቀውስ እንዲፀዱና ለመላው ሕዝቦች ሉዓላዊነት ብቻ እንዲያድሩ ሆነው እንዲታነፁ በፓርቲ ውስጥና ከፓርቲ ውጪ መታገል፣ እንዲሁም የግለሰቦችን ጥላቻ አበራካች እብሪቶች ያለ ጎሰኛ ሽፋን ማጋለጥ ጎልቶ ቢወጣ የሚመጣው የበጎ ስሜት ለውጥ ፈጣን ከመሆኑም በላይ፣ ጥላቻን አፍረክርኮ ሆድ ለሆድ ለመገናኘት የሚያስችል ነው፡፡ ይህንን የመሰለ መልካም ውጤት ከሚያስገኝ እንቅስቃሴ ብዙ ሰዎችን ገትተው የያዙት ችግሮች፣ ተከታዩ ውጤት በጎ ስለመሆኑ እርግጠኛ አለመሆን (አገዘዙን ገለልተኛ አደርጋሁ ሲባል በቀል በትግራዊ ላይ ሊዘምት ቢችልስ የሚል ሥጋት)፣ እንዲሁም ይችን መሰሏን ‹‹ፍርኃት›› በማናፈስ ውስጥ ተሸሽጎ የሚካሄድ ጥቅም አባራሪነት ናቸው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን በእነዚህ ችግሮች ውስጥ አንቀላፍቶ መቆየትና አለመቆየት፣ ፈንጂ ቀብሮ አጋጣሚ እስኪረግጠውና እስኪያፈነዳው  በመጠበቅና ከወዲሁ በብልሀት በማምከን መሀል ምርጫ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡

በአጠቃላይ በጥላቻዎች ተነክሶና ተከፋፍሎ መኖር ለማንም የደኅንነት ዋስትናም መፍትሔም አይሆንም፡፡ የብሔረሰቦች መብቶች ተጨባጭነት የሚያገኙትና የሚዘልቁት ከሕዝቦች የጋራ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ጋር በደንብ መግባባት እስከቻሉ ድረስ ነው፡፡ የብሔረሰቤ ሰው ይግዛኝ ወይም የገዛ ራሴ ጅብ ይብላኝ በሚል ዕይታ ውስጥ መቅለጥ ተከፋፍሎ ለመረገጥ መመቻቸት ነው፡፡ የጋራ መብቶችን ማጣት የብቻ መብትንም ማጣት ነው፡፡ የንዑሳንና የመጤ ማኅበረሰቦች መብት እንዲረገጥ መፍቀድ የራስንም መብት ማስረገጥ ነው፡፡ የሕዝቦችን ኃይል የሚከፋፍል የጥላቻ፣ የበደልና የኩርፊያ ተጋሪ ሆኖ ተቃራኒ ሐሳብን በውንጀላና በዱላ ከማጥቃት ድርጊት ለመውጣትና ተደማምጦ ለመወያየት ሳይጣጣሩ፣ ዴሞክራሲንና ነፃነትን ለማግኘት መጓጓትም ፉርሽ ጅምር፣ ከንቱ ምኞት ነው፡፡

      ኢትዮጵያዊያን የውሸት ያልሆነ የምር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይሻሉ፡፡ ወደዚህ የሚያመራው የዴሞክራሲ ትግል ስኬት በአምባገነንነትና በዴሞክራሲ መካከል የሚደረገው ትንቅንቅ ወደ እርስ በርስ ውጊያ ወይም ትርምስ እንዳይዘቅጥ ከሚያደርግ የፖለቲካ መግባባት ጋር ማያያዝን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መላ ሕዝቦቿን አስተባብሮና አትምሞ ወደዚህ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ የሚያደርሰን አለ አይባል ነገር እንዲያ ያለ የሕዝቦችን ቀልብ ሰብስቦ የያዘ፣ ያያያዘና ማንቀሳቀስ የቻለ የተቃውሞ ፓርቲ ወይም ግንባር የለም፡፡ በአጥለቅላቂ የተቃውሞ ፍንዳታ ያለውን መንግሥት በታትኖ ወደ ዴሞክራሲ በመድረስ ዘዴ ላይ መተማመን የማንችልበት ወደ ባሰ ውድቀት የሚያንሸራትተን ጣጣችንና ገመናችን ደግሞ ብዙ ነው፡፡ በተበጣጠሱ የፖለቲካ ፍላጎቶች መከፋፈላችንና በጥላቻዎች መመዝመዛችን ትልቁ ሕመማችንና ገመናችን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ሥልጣን ለማርዘም ቢሆነኝ ተብሎ ከገዥ ቡድን ሊመጣ የሚችል በግርግር አስደንብሮ ፀጥ የማድረግ ታክቲክ፣ ወይም ከተቃዋሚ በኩል ግርግርን እንዳቋራጭ የለውጥ መንገድ የመጠቀም ሙከራ የማይጠፋ የፖለቲካ ቀውስ ማቀጣጠያ ሊሆን ይችላል፡፡ የውጭ ጠላት ሰላማችንን የሚያጠፋው ቀዳዳና መንጠልጠያ እስካገኘ ድረስ ነውና የውጭ ጠላት ሰርጎ ገብም የጥላቻ ገመናችንን የእርስ በርስ ፍጀት መለኮሻ አድርጎ በቀላሉ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

      የውጭውን እንተወውና ራሳችን በምናካሂደው ተቃውሞ ውስጥ በውስጣችን ተሸፋፍነው የቆዩ የገዛ የጥላቻ ዝንባሌዎቻችን ደምፍላት አስክሮ ሊታረም ወደማይቻል መባላት ውስጥ ሊወስደን ይችላል፡፡ የዚህን አደጋ ምልክቶችም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዛሬም በአማራ ክልል ውስጥ በሚያስደነግጥ ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ይህን በቀላል ብልጭታ ሊለኮስና እንደ ቋያ እሳት ሊዛመት የሚችል ገመና ይዘን፣ በደርግ ዓይነት አወዳደቅ አገዛዝን ከእነ ሠራዊቱና ከእነ ፀጥታው ንዶና በታትኖ እንደገና በመገንባት ዓይነት ዴሞክራሲን ማቋቋም ከከፋ አደጋ ጋር ቁማር  ጨዋታ መግጠም ነው፡፡ ከራሳችን ውስጥ ከሚነሳ ትርምስና እሳት ሌላ፣ ከላይ የሻዕቢያ መንግሥት ቂምና የዓባይ ግድብን የህልውናዬ ጠንቅ ያለ ሥውርና ግልጽ የተንኮል ምናልባት አለ፡፡ ከግርጌ የአልሸባብ ቂም፣ ከጎን ወደኛ ሊፈስ የሚችል የደቡብ ሱዳን ትርምስ፣ ዙሪያውን ደግሞ ግርግርና ቀውስ እያነፈነፈ ሰተት ብቅ የሚል አሸባሪነት አለ፡፡ ይህ ሁሉ ከመዘማመዱ በፊት ገና መታመስ ሲመጣ ኢኮኖሚያችን ላይ ስብራት ይከተላል፡፡ በመከራ የተጀማመረ የውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ይበረግጋል፡፡ የቱሪዝም ገቢ ይደርቃል፡፡ የልማት አውታራት ለውድመት ይጋለጣሉ፡፡

      የዚህ አማራጭ ግን እንዲህ ዓይነቱን አደጋ ከመጋበዝ የኢሕአዴግን አገዛዝ ባልተለወጠ ዘይቤው እንደመጣብን እንቻለው አይደለም፡፡ ዛሬም ድረስ ደፋ ቀና እያለ የቀጠለውን ‹‹በጥልቀት መታደስ›› ያመጣው የትግል ግፊት ነው፡፡ ከኢሕአዴግ የሚገኘውን በጥልቀት መታደስ ለእሱ ቁርጠኝነትና መሐላ ሳይተው ኢሕአዴግን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ማሯሯጥ ግድ ነው፡፡ 

      ኢሕአዴግን አስፈላጊ የሚያደርገው ሌላም ምክንያት አለ፡፡ ኢሕአዴግ በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ አዕምሮ ሙሽት ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አሻራውን አሳርፏል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መልክዓ ምድር ቀይሯል፡፡ የብሔረሰብ መብትን አነሰም በዛ የተመረኮዘ የአስተዳደር ይዞታ አሸናሸንን፣ የፓርቲ አደረጃጀትንና የሥልጣን አያያዝን ያመጣ ሕገ መንግሥት ተክሏል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአገሪቱ የልማት ግስጋሴ ጀማሪም ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ተቃውሞና ድጋፍ እንዳፈራ ሁሉ፣ ሕገ መንግሥቱም ደጋፊና ተቃዋሚ አፍርቷል፡፡ እንዲያውም የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩትንና ‹‹ሕገ መንግሥቱ ሊያሠራ ይችላል፣ ተግባራዊ የሚያደርገው ታጣ እንጂ›› የሚሉትን የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ወስደን፣ ‹‹ለሰላማችን ጠንቅ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ነው›› ከሚሉት የተቃዋሚ ክንፎች ጋር ስናነፃፅር እነዚህኞቹ በቁጥር የሚያንሱ ናቸው፡፡ ወይም የሚያንሱ ይመስላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በራሱ ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ወደ ጎን የማይባሉ አስፈላጊ ሰበዞች ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ዴሞክራሲን ተጋግዞ የመገንባት ዕድል ዕውን የመሆን ተስፋ የሚኖው “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› በሚል ጥያቄ በኩል ሳይሆን፣ ያለውን ሕገ መንግሥት የጋራ መገናኛ በማድረግ በኩል እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ እናም በሽግግር መንግሥት ጥያቄ አማካይነት ካለው ሕገ መንግሥት ለማምለጥ መሞከር ለተከፋፈለ የፖለቲካ ንጠት በር መክፈት ነው፡፡

      ኢሕዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርጋቸው ሌላም ሰበዝ አለ፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን አወጣጡና ‹‹በአዲስ›› አገዛዝ ግንባታው የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ ኃይል ከእነ ርዕዮተ ዓለሙ በዋናነት የተጠቀመ መሆኑ፣ አውታረ አገዛዙን ገለልተኛ እነፃ ገና የጎደለው መንታ ተፈጥሮ (ከውስጥ ባሻ/በጨነቀ ጊዜ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችል ኢሕአዴጋዊ ቡጥ፣ ከውጭ ደግሞ ‹‹የዴሞክራሲ›› ቅርፊት) እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችን ተግባራዊ ሕይወት ከሲታ እንዲሆን ያደረገው፣ የኢሕአዴግንም በሥልጣን ላይ መቆየት በሕዝብ ድምፅ ብቻ የማይወሰን እንዲሆን ያደረገው ይኸው የቡጥና የቅርፊት አለመጣጣም (የቡጡ ቅርፊቱን ለመጫን መቻሉ) ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፓርቲ በምርጫ ድምፅ ቢሸነፍና ሽንፈቱን ተቀብሎ ከሥልጣን ለመውረድ የተስማማበት ሁኔታ ቢከሰት እንኳ፣ ከአገዛዙ የሥልጣን ኃይል ውስጥ ዘራፍ ብሎ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ምናልባት ሁሉ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በአጭሩ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የኢሕአዴግ ሰበዝ (ፋክተር) ለበጎም ለክፉም ውጤት መዋል ይችላል፣ እንዳያያዛችን፡፡

  ሰላማዊ ዕድል እስካለ ድረስ የሚፈለገው ቡጡ ቅርፊቱን እየመሰለ እንዲመጣ መልካዊውን “ዴሞክራሲ” ወደ ሥጋነት የሚቀይር ግንባታ እንዲካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ተግባር የዴሞክራት ተቃዋሚዎችን ያህል የኢሕአዴግ ዴሞክራቶች ሚና አስፈላጊ ነው፡፡ በምርጫ ጨዋታ ዴሞክራሲን የማደላደል ቀዳዳ ኢሕአዴግ አይሰጥም የሚል መከራከሪያ አይረታም፡፡ ከዚህ በፊት በ1997 ዓ.ም. ቀዳዳው ተገኝቶ ገና ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በተቃዋሚ በኩል የታየው ጅልና ጀብደኛ አቅራሪነት ሳይጀመር አበላሽቶታል፡፡ አሁንም ኢሕአዴግ በአስደንጋጭ ቅዋሜ ተገፍቶ ዴሞክራሲን አጠልቃለሁ እያለ ነው፡፡ ደጋፊም ተቃዋሚም እዚህ የማጥለቅ ሒደት ላይ አፍጧል፡፡ በዚህ ‹‹ዴሞክራሲን በማጥለቅ›› ሒደት ውስጥ ተቃዋሚዎች ብልህ ፖለተከኛነትን አውቀውበት ከኢሕአዴግ ያነሰ ግን ጉልህ የሕዝብ ድምፅ ቢያገኙ እንኳ ትልቅ ድል ነው፡፡ ምክንያቱም የድምፁ ውጤት ፋይዳ ለዴሞክራሲ ናፋቂዎች ዴሞክራሲን ሥጋና መልክ፣ እንዲሁም የሕዝብ ባህል አድርጎ በመገንባት ረገድ ተግባብቶ ለመሥራት ጥሩ ዕድል በማስገኘቱ እንጂ በቡድኖች የሥልጣን ትርፍና ኪሳራ አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግን በድምፅ ቢበልጡ እንኳ ከጠቀስነው የዴሞክራሲ ጥንቁቅ (የትግግዝ) ግንባታ የራቀ ስኬት አይኖርም፡፡ የድምፅ ብልጫው የሚያመጣው አዲስ ዕድል ቢኖር የፖለቲካ እርቅ እንቅስቃሴን የበለጠ ሰሚ እንዲያገኝ ማድረጉ ነው፡፡ በድምፅ አሸንፎም የፖለቲካ እርቅ አቀንቃኝ መሆን ለምንድነው? ኢሕአዴግን ለማቄል? ወይስ  ለፅድቅ ነው? ይህ ያልተገለጠላቸው ይኖሩ ይሆናል፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ኢሕአዴግን ማታለልም አይደለም፣ የፃድቅ ቸርነትም አይደለም፣ የዴሞክራሲን ዕድል ላለማስቀጨትና ደም አፋሳሽ የእሳት መንገድን ለማምለጥ የሚያስፈልግ ክፍያ ነው፡፡

ዴሞክራሲን ብዙዎች እንሻለን፡፡ በፌዴራላዊ ሥርዓት መፍትሔነትም (በአወቃቀር ላይ ከፍላጎት በቀር) አጠቃላይ ስምምነት አለ፡፡ ኢሕአዴግ አሻራውን ባሳረፈበት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሁሉም ጅምር አለ፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ ዋናው የትግል ተግባር የተጀመረውን፣ ድምሩን ከሕዝብ ፍላጎትና ከአዋጭነቱ ጋር አገናዝቦ ማቃናትና ሙሉ ማድረግ ነው፡፡

ትግሉና የተግባሩ ክንዋኔ ግን ኢሕአዴግን በመለመንና በማባበል ብቻ የሚገፋ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ዛሬም የደግሞ ጥልቀ ተሃድሶው ከ2008 ዓ.ም. ክረምት ተነስቶ ታኅሳስና ጥር 2010 ዓ.ም. ውስጥም ከገባ በኋላ የዴሞክራሲን መሠረት በአግባቡ የማንጠፍ ፍላጎት ያለው መሆኑ፣ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደወደቀ ነው፡፡

የኢሕአዴግ አያያዝንና ተግባሮች እንደሚያሳዩት አሁንም ኢሕአዴግን በጉልህ ትግል ማሯሯጥ ግድ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ራሱን ዴሞክራሲን አጠልቃለሁ፣ የፓርላማ ውክልና አሻሽላለሁ፣ እስረኛ እፈታለሁ፣ ሥራ አጥነትና በደልን አቀልላለሁ የማለት ደፋ ቀናው የመጣው ከትግል ግፊትም ነው፡፡ የትግል ግፊቱ ደግሞ የፓርቲ ለፓርቲ ጭምር ነው፡፡ ከሕዝብ ትግል አኳያ በውድመት የቀለመ አመፅ ተስፋን እንዳመጣ ሁሉ የማነቆ መጥበቅን (አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወዘተ) አስከትሏል፡፡ የትግል መንገድን በቅጡ መቃኘትና መለወጥ ማለትም የትግል አቅምን የሚያጠናክር፣ ገዥውን ቡድን ወደ አዎንታዊ መደፋፈር የሚስብ፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የዴሞክራሲ ዝንባሌ እንዲፋፋ የሚያግዝ፣ በምርጫ የመሸነፍና ከሥልጣን ወርዶ የመወዳደርን አስፈሪነት የሚገፍ የትግል ዘዴ ላይ መሰማራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

በዚህ ጎዳና ውስጥ በነፃ መደራጀትን በየፈርጁ ማጎልበት የሐሳብና የንግግር ነፃነትንና የሰላማዊ ሠልፍ መብቶችን ከመተናነቂያነት ይልቅ፣ የሚብሱ ጥያቄዎችን ጠንቀኛ ጥፋቶችንና መፍትሔዎችን አጉልቶ ለማሳየት የመገልገል አርቆ አስተዋይነት ያመጣል፡፡ ከዚህ ሌላ የፓርቲዎች ተፎካካሪነት መዳበር የምርጫ ውጤት ከሚያስገኘው መሸናነፍ በበለጠም ጤናማ የምርጫ ዘመቻን መለማመድ፣ እንዲሁም ከሸፍጥና ከኃይል ተግባር የፀዳ የምርጫ አስፈጻሚነትንና ታዛቢነትን ለማካሄድ መብቃት ዴሞክራሲን ሥር ማስያዝ መሆኑን አውቆ ማሳወቅና ወደ ተግባር መቀየር በራሱ ለዴሞክራሲ ድል ነው፡፡ ይህ ድል ዕውን መሆንና መፅናት የሚችለው ግን በፓርቲዎችና በሕዝብ ውስጥ በተለይም በወጣቱ ዘንድ ኩርፊያን፣ ጥላቻን፣ መፈራራትንና ግትርነትን የማሸነፍ መሠረታዊ ድልን ተቆናጦ እስከመጣ ድረስ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ጥረታችን ሁሉ የእምቧይ ካብ ይሆናል፡፡

በእርስ በርስ የሕዝብ ግንኙነት ውስጥ የገባንና የተጠራቀመን መርዝ የሚነቅለው ይህ ትልቅ የእርቅ ሥራ፣ መንግሥትን ደጅ የማያስጠናና አዋጅን የማያስጠብቅ በራስ ቁርጠኝነት ብቻ ተፋፍሞ ለንቀትም ለእብሪትም የማይመች ትልቅ የኅብረት ጉልበትን የሚያቀዳጅ ሒደት ሲሆን ነው፡፡ ጥላቻንና መፈራራትን ከእነ ዝባዝንኬዎቻቸው መበጣጠስ በሌላ ገጽታው ሰንሰለት እየበጣጠሱ ነፃ መውጣት ነው፡፡ ሰንሰለትን ለመበጣጠስ መቻልም በራሱ ራስንና ኅብረተሰቡን ለዴሞክራሲ ማሟሸት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *