“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ማንነቴን ብቻ ሳይሆን ስሜንም ተነጥቄያለሁ” መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ

በጌታቸው ሽፈራው — እየተፈፀመብኝ ያለው የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በመሆኔና የወልቃይት ማንነቴ የተነጠቀው በሕወሓት ስለሆነ፣ ኦፊሰር ካህሱ ደግሞ ነባር የሕወሓት ታጋይ ስለነበር እና በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ ሕወሓት ተከዜን ተሻግሮ ወደ ወልቃይት ሲገባ የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት ወልቃይት እና ሁመራ የሚገኝበት ምክንያት የለም በሚል ስቃወም ስለነበር ነው። በየጊዜው ሲነሱ በነበሩ ግጭቶችም ከፍተኛ በደልና ጉዳት ሲያደርሱብኝ የቆዩ በመሆኑ አሁንም ያንን ለመድገም እና በእኔ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ የተደረገ ሴራ ነው።

Ethiopian political prisoner, Mebratu Getachun.

— ማንነቴን ብቻ ሳይሆን ስሜንም ተነጥቄያለሁ

የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ

(ሙሉ ማመልከቻውን ከሥር ይመልከቱ)

ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት

አዲስ አበባ

የመዝገብ ቁጥር 188745

ታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓም

አመልካች አቶ መብራቱ ጌታሁን አለሙ

ጉዳዩ:_ እየተፈፀመብኝ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም

እኔ አመልካች ትክክለኛው ስሜ እና በመታወቂያዬ ላይ የሰፈረውም “መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ” ነው። ይህ ትክክለኛው ስሜ እንዲመዘገብልኝ በችሎት በተደጋጋሚ አመልክቼ ችሎቱ ሊያስተካክልልኝ ባለመቻሉ ሕዳር 14/2010ዓም በተፃፈ ማመልከቻ ከመጠየቄ በተጨማሪ “ስሜ አማርኛ ነው የትግሬ ስም የለኝም” በማለት በችሎት ላይ በመናገሬ ብቻ የቂሊንጦ እስር ቤት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅሞብኛል።

1) ሕዳር 17/2010 ዓም የቂሊንጦ እስር ቤት ከምሽቱ 3:00 ካለሁበት የማደሪያ ክፍል ተጠርቼ “እንዴት “በትግሬ ስም አልጠራም ብለህ በችሎት ትናገራለህ?” ተብዬ ዛቻና ማስፈራሪያ ተፈፅሞብኛል።

2) በዚህ ዛቻ መሰረት ሕዳር 26/2010 ዓም “እንዴት በትግሬ ስም አልጠራም ብለህ በችሎት ትናገራለህ” ተብዬ ዛቻና ማስፈራሪያ ከደረሰብኝ በኋላ ከዛቻው አንዱ ጨለማ ቤት አስሮ ማሰቃየት ስለነበር 24 ሰዓት ሙሉ ብርሃን በማይገኝበት ጨለማ ቤት ውስጥ አስገብተው፣ የእስረኞች ማስተዳደሪያ ደንብ ውጭ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመብኝ እገኛለሁ።

3)እኔ የታሰርኩበት ጨለማ ቤት በስቃይ ብዛት አእምሯቸውን ስተው የሚያደርጉትን የማያውቁ ንፁሃን ያሉበት ሲሆን፣ ለእስረኞች አያያዝ የወጣውን ደንብ ቁጥር 138/99 በሚፃረር ሁኔታ ሰብአዊ መብቴ ተጥሷል። በተጠቀሰው ደንብ አንቀፅ 3(2) ሥር “የተላለፈባቸው ቅጣት የሚጥለው ገደብ ከሌለ በቀር ሰብአዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ ማድረግ” ይልና፣ በአንቀፅ 6ሥር ደግሞ “ታራሚዎች የሚኖሩባቸው ሆነ የሚታሰሩባቸው ክፍሎች መፅሐፍ ለማንበብ የሚያስችል በቂ ብርሃን እና ለጤንነት ተስማሚ የሆነ አየር የሚያስገቡ መስኮቶች እና በሌሊት መፅሐፍ ለማንበብ የሚያስችል የዓይንን ጤንነት የማይጎዱ መሆን ይኖርበታል።” በማለት በአስገዳጅነት ደንግጓል። ነገር ግን ቂሊንጦ እስር ቤት የእስረኞች አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ኦፊሰር ካህሱ ሕጉን በመጣስ 24 ሰዓት ሙሉ ጨለማ እና አእምሮ ሕሙማን ሰዎች በዘፈቀደ የሚኖሩበት ክፍል ውስጥ ጤንነቴን ለመጉዳት ፣ እኔም አእምሮዬን እንድስት ታስቦ ግፍ እየተፈለመብኝ እገኛለሁ።

እኔ በእስር ቤት ውስጥ አንደም ጥፋት አጥፍቼ አላውቅም እንጅ ባጠፋ እንኳ ቅጣት ሊወስን የሚችለው በደንቡ አንቀፅ 37 እና 38 ከተዘረዘሩት የዲሲፕሊን ጥፋቶች ሲፈፀሙ በአንቀፅ 39 መሰረት ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን የቅጣት ውሳኔውም የተቀጭውን የይግባኝ መብት ለመጠበቅ ሲባል የሚሰጠው በፅሑፍ እንደሆነ በደንቡ በግልፅ ተመልክቷል። በዚህ ደንብም ሰብአዊ መብትን የሚጥሱ የቅጣት ዓይነቶች የሉም። ደንቡ ተጥሶ ሲገኝ ወደተለየ ክፍል መውሰድ ቢቻልም በደንቡ አንቀፅ 3(2) እና አንቀፅ 6(1) እና (2) ሥር የተደነገጉት የሰብአዊ መብቶች ግን ፈፅሞ አይጣሱም። በእኔ ላይ እየተፈፀመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ግን፣

1ኛ) እስር ቤቱን ደንብ የጣስኩበት ጊዜ ስለሌለ
2ኛ) ቅጣቱ ከደንቡ ውጭ ከመሆኑ በላይ ለዚህ ቅጣት ምክንያት ሆኖ በቃል የተነገረኛ “ከችሎት ላይ ስሜ የአማራ ነው፣ የትግሬ ስም የለኝም” ብለሃል የሚል ነው።

በችሎቱ የተናገርኩት ደግሞ እውነት ከመሆኑም በተጨማሪ ማንነቴን ከመነጠቄ በላይ ስሜንም ጭምር በመነጠቄ ቢያንስ ለጊዜው ስሜን ለማስተካከል ለችሎት ማመልከቴ ጥፋት ስላልሆነ እና በችሎት ፊት ለምናገረው ማንኛውም ንግግር ደግሞ እስር ቤቱ የዲሲፕሊን ቅጣት ለመወሰን የሚያስችለው የሕግ መሰረት ስለሌለ በኦፊሰር ካህሱ እየተፈፀመብኝ ያለው የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በመሆኔና የወልቃይት ማንነቱን የተነጠቀው በሕወሓት ስለሆነ፣ ኦፊሰር ካህሱ ደግሞ ነባር የሕወሓት ታጋይ ስነበር እና በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ ሕወሓት ተከዜን ተሻግሮ ወደ ወልቃይት ሲገባ የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት ወልቃይት ሁመራ የሚገኝበት ምክንያት የለም በሚል ስቃወም ስለነበር ነው። በየጊዜው ሲነሱ በነበሩ ግጭቶችም ከፍተኛ በደልና ጉዳት ሲያደርሱብኝ የቆዩ በመሆኑ አሁንም ያንን ለመድገም እና በእኔ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ የተደረገ ሴራ ነው። አንድም ለቅጣት የሚያበቃ ጥፋት አልፈፀምኩም። የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ።

በሌላ በኩል ማዕረጋቸውን የማላውቀው የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች፣ግርማ የተባለ በተደጋጋሚ የሚዝትብኝ ሲሆን አብዱራዛቅ የተባለው ደግሞ ከ1000 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ሊጠይቁኝ የመጡትን ቤተሰቦቼን እንዳይገቡ ከልክሎ ሳይጠይቁኝ እንዲመለሱ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ሕዳር 14/2010 ዓም በነበረው ችሎት ከችሎቱ ፊት ከክፍለ ሀገር የመጡትን ዘመዶቼን ማግኘት እንድችል ጠይቄ ከችሎቱ ውጭ በእስረኞች ማቆያ ቦታ እንዲያገናኙኝ በችሎት የተነገራቸው ፖሊሶች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመፈፀም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በችሎቱ ፊት ደግሞ ዘመድ እንዳይጠይቅ አልከለከልንም ብለው ዋሽተው ከሄዱ በኋላ ዘመዶቼ እንዳይጠይቁኝ ተከልክዬ እገኛለሁ።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ፍርድ ቤት በአደራ ያስቀመጣቸውን እስረኞች ሙሉ መብት የማስከበር ሕገ መንግስታዊ ግዴታ ስላለበት የእስር ቤቱ አስተዳደር ደግሞ በአደራ ያስቀመጣቸውን ሰብአዊ መብት ማክበር ሲገባው በተቃራኒው ሕገ ወጥ ተግባር እየፈፀመብኝ ስለሆነ የእስር ቤቱ ኃላፊ፣ ኦፌሰር ካህሱ፣ ግርማ እንዲሁም አብዱራዛቅ የተባሉ የእስር ቤቱ ፖሊሶች በፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ፣ በእኔ ላይ እየተፈፀመብኝ ያለው የመብት ጥሰት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ለተፈፀመብኝ በደልም ፍርድ ቤቱ ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙብኝን እንዲቀጣልኝ አመለክታለሁ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት
0Shares
0