ውይይቱን ያዘጋጁት በኢትዮጵያ የኤርትራ ምሁራን ተወካዮችና ሴሌብሪቲ ኢቨንትስ እንደሆኑ፣ የሴሌቭሪት ኢቨንትስ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ገብረ ሊባኖስ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች የኤርትራን ሕዝብ ወክለው የሚደራደሩና የሚከራከሩ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና ምሁራን እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በዕለቱም በኢትዮጵያና በኤርትራ የሰላም ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል፡፡

በስብሰባው ኤርትራውያን ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉ፣ ኢትዮጵያን በመወከል ደግሞ ምሁራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ በዚህ ስብሰባ ከአንድ ሺሕ የሚበልጡ ኤርትራውያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡

ተቋርጦ የነበረውን የኢትዮጵያና የኤርትራን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማስቀጠልና በሁለቱ አገሮች መንግሥታት ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ በሴሌብሪቲ ኢቨንትስ አዘጋጅነት ባለፉት ሁለት ወራት የሁለቱ አገሮች ምሁራን በአገሮቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ከሁለት ጊዜ በላይ ምክክር ማድረጋቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ከሃምሳ ሺሕ በላይ ኤርትራውያን በአዲስ አበባ እንደሚኖሩ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ በሁለቱ መግሥታት የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ ተቋርጦ የነበረውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማስቀጠል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እንዳሉ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረውን የሁለቱን አገሮች የምሁራን ውይይት ከፍ በማድረግና ቀሪ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና የጎረቤት አገሮች መሪዎችን በማሳተፍ፣ የመንግሥታትን ልዩነት በማጥበብ ለመሥራት እንደታቀደ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላምም ሆነ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ 20 ዓመት የሞላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን በተመለከተ ሲከተል የነበረውን ፖሊሲ ለመቀየር ዝግጅት እያደረገ እንደነበር መናገሩ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን አዲሱ ፖሊሲ ምን ዓይነት ይዘት እንዳለው እስካሁን አልታወቀም፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ወር ለአገሪቱ ሚዲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀውስ መፈጠሩን፣ የቀውሱ ፈጣሪ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው በማለት መኮነናቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የአቶ ኢሳያስን መግለጫ ፍሬ ቢስና ትኩረት ከመፈለግ የመጣ ነው በማለት ማጣጣሉ ይታወሳል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ፍላጎት እንደሌለው ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ የዘርፉ ተንታኞች ሲናገሩ ቢሰማም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በግል ተቋማትና በውስን ምሁራን አነሳሽነት መንግሥታቱ ዕርቅ ፈጥረው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲቀጥል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አሉ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *