የወቅቱ የኢትዮጵያ ለውጠኞች ገና ከተማሪ ጀብደኝነት ራሳቸውን ሳያላቅቁ፣ ለምዕራቡም ሆነ ለምሥራቁ ጌታ በጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ማደር ያው ኋላቀርነት መሆኑን በቅጡ ሳይረዱ የየካቲት ሕዝባዊ አመፅ ድንገት ደረሰባቸው፡፡ በማርክሲዝምና በሶሻሊስታዊ የለውጥ መንገድ መማረካቸው (በደርግ አገዛዝ ከተማረሩ በኋላና ዛሬ ምዕራባዊ ዴሞክራሲንና የ‹‹ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ››ን መፈለግ እንደማያስገርም ሁሉ) ከነበሩበት ጊዜ አኳያ አስገራሚ አልነበረም፡፡

የጊዜው ተራማጆች በደርግ ፈንታ ሥልጣን ላይ ቢወጡ ኖሮ የአንድ ፓርቲ አገዛዝና መንግሥታዊ የኢኮኖሚ መዋቅሩ አይቀሬ የነበረ ቢሆንም፣ የሕዝብ ድጋፍ አግዟቸውና በሒደት ክፉና ደጉን እየለዩ የተሻለ ዕድገት የማሳየት ምናልባት ይኖር ነበር፡፡ ወታደራዊውን አገዛዝ ከላይም ከሥርም ተባብሮ የመታገል አስተዋይነት አጥተው፣ እዚያ ምናልባት ላይ ሳይደርሱ መንገድ ላይ መቅረታቸው ግን በምንም ማመካኛ የማይፋቅ ጥፋት ነበር፡፡ ጥፋቱ እንዳለ ሆኖ ለሕዝባችን የተሻለ ፍትሐዊ ሕይወት እናቀዳጃለን በሚል ሙሉ እምነትና ስሜት የተካሄደው አሳዛኝ መስዋዕትነት ግን እያሳዘነም እያስቆጨም ተከብሮ የሚኖር ነው፡፡

በእርስ በርስ መጠማመድ የእርስ በርሳቸውንና የደርግን ጭካኔ አጡዘው መርገፋቸው፣ ከመሬት ከበርቴውና ከመኳንንቱ መመታትና ከልዕለ ኃያላዊ ጌታ መቀየር በስተቀር አገሪቱ ወደ ድቀት ጉዞ እንድትንደረደር አድርጓል፡፡ ውድቀቱና ድቀቱ በኢኮኖሚ ኋላቀርነት መዳከር፣ በወታደራዊ አምባገነንነት መደቆስ፣ በባህል መላሸቅና በፍርኃት መቆራመድ ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚህ ያለፈና ለዛሬ የተረፈ ጠንቅና ጉዳት አስከትሏል፡፡ ለዴሞክራሲ ለውጠኛነት የሚሆን የትግል ቅስምና የለውጠኛ ጥሪት አገሪቱን ያሳጣ አደጋም ነበር፡፡ ይህም እስከ ዛሬ የተሻገረ፣ ዛሬም ድረስ አብሮን ያለ ጣጣና ጠንቅ አስከትሏል፡፡ ዛሬ የሚተናነቀንን መሠረታዊ ችግር ያስከተለው እሱ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ትግል ተጠቃ፣ ተንኮተኮተ፡፡

ከ1966 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. ኅብረ ብሔራዊ ትግል ከተንኮታኮተ በኃላ በክልልተኛነት የተጣበቡ ትግሎች ዋና ተዋናዮች እየሆኑ መጥተው፣ ይህንንም የሚቀይር ትግል መጉደሉ በብዙ ጣጣዎችና ጠንቆች ለመተብተብ አብቅቶናል፣ ለአሁኑ ጠንቀኛ ጎጆኝነትም ዳርጎናል፡፡

የኅብረ ብሔራዊ ትግሉ ተንኮታኩቶ በተቃውሞ መድረኩ ላይ ብሔርተኛ ቡድኖች ብቻ መታየታቸው፣ ኢሕአፓና መኢሶን በነበሩበት ጊዜ አስታዋሽም ያልነበረውና ምኞታዊ የታሪክ አተረጓጎምና ጥያቄ ያነገበው ኦነግ በኦሮሞ ጉዳይ ተጋፊ አልባ ሆኖ ብቅ ማለቱ፣ እንደ ኦነግ በጠባብ ዓላማና በሐሰተኛ ግንዛቤ የተሞሉት ሻዕቢያና ሕወሓት የመላ ኢትዮጵያን ሕዝቦች ዕጣ ፈንታ ወሳኝ የሆኑበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ የበፊቱንና የተደቆሰውን ኅብረ ብሔራዊ ሰብስብና ትግል አላስፈላጊነት የሚያሳይ ሳይሆን ከ1968 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. ትግል ላይ የወረደው ፍጅትና ምንጠራ ያደረሰውን የጉዳት ክብደት የሚገልጽ ነው፡፡ ደርግ አክ እንትፍ ተብሎ መክኖ የገዛ ጦር ኃይሉ ለ‹‹ወንበዴዎች›› መረጃ፣ መሣሪያና ስንቅ እስኪሰጥና በሺዎች እየተናደ እስኪከዳ ድረስ (በወታደራዊ ግልበጣ እንኳ መፈንገል ተስኖ) በሬሳው ‹‹መግዛቱ››፣ በድፍን ኢትዮጵያ የተጠላውን ማርክሳዊነት ያነበንብ የነበረውና መጀመርያ ከአንድ ጠባብ አካባቢ የመጣውና ኋላም ኢሕአዴግ ሆኖ (ከ1982 ዓ.ም. በኋላ) የተደራጀው ቡድን የመላ አገሪቱን ሥልጣን ከደርግ መረከቡ፣ አክሱም የየመኖች ሥልጣኔ ነበር በማለት የገዛ ታሪክን እስከ መሻር ያበደ ክህደትን ከጉያው የሚፈለፍል ቡድን ደግሞ በኤርትራ ላይ በገዥነት የተቀመጠበትና የኢትዮጵያ ‹‹አጋር›› የሆነበት ታሪክ መፈጸሙ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ትግል የቱን ያህል አዘቅት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይናገራል፡፡

ከዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥትን (State) በቡድን፣ በብሔርተኛ የትግል ታሪክ አመለካከትና የሥልጣን ጥቅም አምሳል መቅረፅ መጣ፡፡ ከቡድንና ከክልል ጋር የተጣበቁ ኩባንያዎች ረቡ፡፡ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ሁለት አገሮች አድርጎ የቆረጠ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ደግሞ እንዳይቀራረቡና እንዳይተባበሩ ያደረገ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥም (በአገር ውስጥም በውጭም) ክፍልፋይ ሽኩቻዎችን ያባዛ፣ ያተለቀና ያገዘፈ፣ ለረዥም ጊዜ በአንድ አካባቢ ተወላልደው የኖሩ ዜጎችን መጤና ነባር ብሎ በዳኝነት ላይ ሳይቀር ያበላለጠና ያንጓለለ፣ ከሌላ ብሔር የመጣ ኢንቨስተር እንደ አጥቂ ታይቶ እንዲጉላላ፣ ካፒታልን እያበዛ ሥራ በማስፋፋት ፈንታ ትርፍ ወደ ሌላ በማሸሽ አጭር ግብ ምክንያት ልማት እንዲቀጭጭ ያደረገ፣ በሃይማኖቶች ውስጥ ሳይቀር በወንዝና በብሔር ልጅነት መሳሳብን ያመጣ የጠባብ አመለካከትና ጥቅመኝነት ነገሠ፡፡ ሙስና መጥፊያ ያጣውና በተሰማራበት ኃላፊነት ዕውቀትና ችሎታውን ሳይሰስት ለበጎ ውጤት የሚሠራ ቅንና ታታሪ ሰው ኢሕአዴግ መንግሥት ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ከባድና የማይቻል የሆነው፣ መጀመርያውኑም የዕውቀትና የችሎታ መመዘኛ አስፈላጊነቱ ‹‹ቀሪ›› የተደረገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ዛሬም ከ27 ዓመት በኋላ ይህ የሥር የመሠረት ችግራችን የሚያስከፍለን ዕዳ እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የፍዳውም አዝመራ እየታየ ነው፡፡

የራስን ማንነት ማወቅ፣ የሌላውን ማንነት ማወቅ፣ በመፈቃቀድ የጋራ ማኅበረሰብ መገንባትና የማንነት አካባቢን ማልማት የተሰኙ አገዳዎች ያሉት የገዥው ፓርቲ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ክፍለ አኅጉራዊና አኅጉራዊ መተሳሰብን ለሚሻው ሰፊ እውነት ይቅርና ለኢትዮጵያም የውስጥ ህልውናና ሥምረት የሚያንስና የሚጠብ ነው፡፡ አደገኛና አዳላጭም ነው፡፡ የሚያላትመንም ‹‹የማንነት አካባቢን››፣ የመገኛ ምድርን ወይም ብሔራዊ ክልልን ብቻ የማልማት አደራ የሚያስታጥቀን ብሔርተኝነት ነው፡፡ የልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ተወላጆች ሁሉ ሥራና ኑሮ በየመገኛ ብሔር የተገደገደና ሊገደብ የማይችል እንደ መሆኑ፣ የትም ኑር የትም ሥራ ዞሮ መግቢያህን ማልማት ግን አትርሳ የሚል ‹‹ንቃት›› የወንዝ ልጅና ባይተዋር/መጤ የሚሉ መከፋፈልንና ከብሔራዊ ተወላጅ ውጪ የሆነን ሰው አጫራሽ አድርጎ ማየትን ተገቢ የሚያደርግ አደጋ ነው፡፡ ዘርዘር አድርገን ጠጋ ብለን እንመልከተው፡፡

በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕቅዶች የብዙ ሰዎችን ጥቅም አቀራርቦ መያዝና ብዙዎችን ለመሳብ መብቃት ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ሲተያይ በብሔርተኝነት ተቧድኖ ድጋፍ መፈለግ ከሁሉም የቀለለ ነው፡፡ የፖለቲካ ትግል ልምምድ ትንሽም የሌላቸው፣ ይህ ይቅርና የፖለቲካ ንድፈ ሐሳባዊ አስተሳሰብ ያላበጁ ሰዎች ፕሮግራም ልትባል የማትችል ወረቀት አዘጋጅተው ብሔርተኛ ብሶትን እያንጎራጎሩ የብሔር ድርጅት ነኝ ሲሉ አጋጥሟል፡፡ የብሔርተኛ መንገድ የሚጋጩ አስተሳሰቦች ያላቸውን ሰዎች፣ ዴሞክራቶችና ፀረ ዴሞክራቶችንና ፋሽስታዊ ዝንባሌ ያላቸውን ጭምር  በብሔር ተቆርቋሪነታቸው ብቻ አብረው መንጋፈፍ እንዲችሉ የተመቸ ነው፡፡ ብሔርተኛ አስተሳሰብና አደረጃጀት በተዘረጋበት ሥርዓት ውስጥ ምርጫ ቢካሄድም፣ መራጩ ሕዝብ ፓርቲዎችን ባላቸው ፕሮግራም ከማማረጥ ፈንታ በአመዛኙ ብሔር ብሔረሰቡን ‹‹ይወክላል›› ለተባለ ቡድን ዕጩዎች ድምፁን የመስጠት ሁኔታ ውስጥ ይወድቃል፡፡

አመለካከቱ ሙሉ ለሙሉ በብሔርተኝነት ገደብ ውስጥ የገባ ሰው ብሔሩን ከሌላ ብሔር ጋር በእኩል ዓይን ለማየትና ለመመዘን ይሳነዋል፡፡ የብሔሩን ወግና ባህል በሒስ ዓይን ከማየት ይልቅ እንደወረደ መካብ ያጠቃዋል፡፡ የብሔሩን ባለታሪኮች ጥሩ ሥራቸውን የማብዛትና ድክመታቸውን የመከለል/የማሳነስ ፍላጎት ይስበዋል፡፡ የበላይ ከነበረ ብሔር ወይም ገዥ መደብ ጋር ብሔሩ የነበረውንና ያለውን ታሪክ በመረዳት ረገድም፣ በደልና ጥቃትን የማነፍነፍና ከዚያ አኳያ አዛብቶና አጡዞ የመተርጎም ፍላጎት የምልከታና የማሰብ ሚዛኑን እየታገለ ያስቸግረዋል፡፡ ብሔራችን ተበድሏል፣ እነዚህና እነዚህ አልተሟሉለትም የሚባለው ነገር ብዙ አየር እየተሞላ አንዳንዴም የትግል ሁለንተና ሆኖ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያገናኙ ዓበይት ጥቅሞች እንዳይጤኑ ሊሸፍን የሚችለው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ያለው የአብሮነት፣ የእኩልነትና የልማት ትግል ምልከታ ውስጥ ሳይገባ የሚካሄድ የድሮና የዘንድሮ የበደል ድርደራ ወደ ቅያሜ የሚያንሸራትት ድጥ አለው፡፡ ከትምክህት ወገኖች ጋር መተራረብ ታክሎበት በፈላ ስሜት መታወር ሊከተል ይችላል፡፡ በአገራችን ተሞክሮ መሰል ችግር እንግዳ አይደለም፡፡

የብሔር ብሔረሰብ ካባ መጎናፀፍ የብሔር ወገንተኝነትን ያጠበቀ ስሜታዊ ድጋፍ የሚገኝበት ጥሩ መደበቂያ መሆን ስለሚችል (አሁን እንደተረጋገጠው ደግሞ ስለሆነ)፣ ሥልጣን ፈላጊዎችና ሙሰኞች ሽፋን አድርገው ይነግዱበታል፡፡ እነሱ የፈጠሩት ድርጅት የያዘውን አቋም የብሔር ብሔረሰቡ አቋም ያደርጉታል፡፡ ድክመታቸው ሲተች በእነሱ ላይ የተወረወረውን ትችት ብሔር ብሔረሰባቸው ላይ እንደተወረወረ አድርገው ለማምታታት ይመቻቸዋል፡፡ ‹‹ድሮም . . . እየተባልክ ትዘለፍና ትናቅ ነበር ዛሬም ይኼው . . . ›› እያሉ ስሜት ውስጥ መክተት የተለመደ ዘዴያቸው ነው፡፡ ለማምታታትም ጠቅሟቸዋል፡፡  ምክንያቱም ብሔርተኛ ተቧድኖና እንቅስቃሴ የቡድን ማንነትና ፍላጎትን ከብሔር ብሔረሰብ ማንነትና ፍላጎት ነጥሎ በማየትና በመረዳት በኩል የበኩሉን አሳሳችነት ይፈጥራል፡፡ ብሔር ብሔረሰብን በደፈናው ሥራዬ ብሎ የሚያወግዝና የሚሳደብ የከተማ እብድ በኢትዮጵያ ሊታይ የቻለው (ከደርግ ውድቀት በኋላ) ከዚህ አሳሳችነት የተነሳ ነው፡፡

ለቅስቀሳ የሚውለው በደል ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ የሚመለከት ሲሆን፣ እንኳ የሁላችንም ችግርና ጥቅም ነው ከማለት ይልቅ የብሔርተኛ ትግል የራሱን ብሔር ብቻ የሚመለከት አስመስሎ በተናጠል የመጮህ ፀባይ ያጠቃዋል፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ የተናጠል ብሔርተኛ ጩኸት ሲሆን፣ ሌላው ወገን የራሱ ብሔርተኛ ንቅናቄ ወይም ሌላ የትግል አማራጭ ከሌለው በስተቀር ድርሻው ተመልካችነት ይሆናል፡፡ የብሔርተኛ ንቅናቄ በተፈጠረበት አካባቢ ያለ ውሁድ ኅብረተሰብ በተለይ ገዥ የሚባል ብሔር አባላት በተመልካችነት ላይወሰኑና ምንም በደል ባይደርስባቸውም የብሔርተኛ እንቅስቃሴ መፈጠሩ ብቻውን ሥጋታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ብሔርተኛ እንቅስቃሴው ክልላዊ ሥልጣን ሲይዝም ሥጋታቸው ይቀጥላል፡፡ ትምክህትም ሰለባውን ያበዛል፡፡ የብሔርተኛ ትግሉ ተገንጥሎ የመውጣትን ጥያቄ የጨመረ ከሆነ ደግሞ መገንጠልን ከማይደግፍ ወገን ጋር በሞላ መቃረን ይፈጥራል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች የትግል ኃይል ይከፈላል፡፡

የትኛውም ዓይነት የብሔር ብሔረሰብ ብሔርተኛነት በውስጤ ያለ ሀብትና ጥቅም ቅድሚያ ለብሔር ወገኔ ይሁን የማለት ቁልቁለት አብሮት ይኖራል፡፡ በዚህ ቁልቁለት ከተንደረደሩ ማረፊያው አድሎኝነት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ከተወደቀ ከሌላው በበለጠ ለብሔር ብሔረሰብ ወገን መታመንና ከሌላው አብልጦ የብሔር ብሔረሰብ ወገንን ማቅረብና መጥቀም ይመጣል፡፡ ጥቅቅሞሹ በግልጽና በድብቅ መንገድ ወደ ልዩ ልዩ የሥራ መስክ፣ ወደ ትምህርት ምዘና፣ ወደ ኢንቨስትመንትና የመሬት ምሪት ሊሻገር፣ የፖሊስና የዳኝነት ሥራውን ሊበክል ይችላል፡፡ ሲበክልም ታይቷል፡፡ የአድሎኝነት ችግር መኖር ከ‹‹ሚዳላለት›› ብሔር ውጪ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቅሬታ ላይ ይጥላል፣ የእኩል ዜጋነት እምነታቸውን ይሰብራል፡፡ ትምክህተኛና ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ መስመሮችን ያነሳሳል፡፡ አድልኦ ባልተፈጸመበት ሥፍራና ጊዜም በይሆን ይሆናል መጠራጠርና ማማት እንዲራባ ያደርጋል፡፡ ሐሜቱ ደግሞ በፈንታው የብሔርተኛ ሹምን እልህ እያጋባ ማናለብኝነትንና አድሏዊነትን ያባብሳል፡፡ ይህ ሁሉ የአካባቢውን ሰላማዊ ኑሮና ልማት የሚበድል ነው፡፡

በደሉ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ‹‹የሚዳላላት›› ብሔር የተጠቃሚነት ስም ይትረፈው እንጂ ተበዳይነቱ በእሱ ይብሳል፡፡ አድልኦን ፈቅዶ እስከተቀበለው ወይም እስካልተቃወመው ድረስ የነፃነትንና የእኩልነትን ጣፋጭነት ማጣጣም አይችልም፡፡ በራሱም ላይ አድልኦ ይጠራል፡፡ በብሔር የተጀመረው ማዳላት የዘመድ፣ የትውውቅና የሽርክና ድር እየሠራ ይስፋፋልና ‹‹የብሔር ወገኖች››ም የአድልኦ ተጠቂነት አይቀርላቸውም፡፡ እንዲያውም ‹‹የብሔር ወገኔ››፣ ‹‹ለብሔሬ የቆመ›› ባይነት ሚዛናዊ አስተውሎቱን እያደበዘዘበት የጥቅመኞች መነገጃ መሆኑን ለማጤን ከሌላው የበለጠ ጊዜ ሊወስድበትና ብዙ ሊጠቃ ይችላል፡፡

በአድሏዊነትና በጥበት ስሙ የጎደፈ የአስተዳደር አካባቢ ወደ ሥፍራው ሊመጣ የሚችለውን ተወላጅ፣ ያልሆነ አልሚ የማስቀረት ጉዳትም ያስከትላል፡፡ የክልል ልማት በክልል ተወላጅ የአገርም ልማት በአገር ተወላጅ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በዛሬው የግሎባላይዜሽን ዘመን ልማት ሊሳካ ከተፈለገ ባለሀብትንና ባለቴክኖሎጂን ከየትም ይሁን ከየት እየሳቡ ልማትን እንዲያስፋፋ የመንከባከብ ብልህነት ያስፈልጋል፡፡ አገርነት ይቅርና አኅጉርነት ጠብቦ የብሔር፣ የአገርና የአኅጉር ድንበር ሳይገድባቸው በተያያዙ ጥቂት ግዙፍ ኩባንያዎች ሥር በምትመራ ዓለም ውስጥ ሆነን የብሔር ብሔረሰብ ዕድልንና ልማትን በትንሽ ክልል ደረጃ ከማሰብና ‹‹የብሔር አባሎቻችን ክልላችሁን አልሙ›› ከሚል ጠባብ ማዕቀፍ ማለፍ አይበዛብንም፡፡

የተጠቃቀሱት የብሔርተኝነት አደጋዎች፣ ድጦችና የትምክህት ችግሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ሲበዛ በተግባር ታይተዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ የአገሪቱ ዋና መሠረታዊ ችግር ሆነዋል፡፡ ክልልተኞች፣ ወገንተኞችና ትምክህተኞች በሚፈጥሯቸው ቅራኔዎችና ፍርኃቶች ውስጥ መኖር የሚስማማው ሕዝብ የለም፡፡ መንግሥት ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ እየሮጠ ሁከት በማብረድና በማስታረቅ ችግሮቹን መጨረስ አይችልም፡፡ መንግሥትን ለእንዲህ ዓይነት ‹‹መንከውከው›› እንኳን ብቁ አልሆነም፣ የገለልተኝነት ዕጦት አለበት ተብሎም ይከሰሳል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ጋር መኖር ግድ አይደለም፡፡ ይልቁንም እነዚህ ችግሮች አያኖሩንም፡፡ ብሔርተኛነት የብሔር ወገንን ከአስተዳደራዊና ከሙስና በደሎች የማዳን ውስጠ ባህርይ የለውም፡፡ የብሔርተኛ በዳይ ሞልቷል፡፡ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት፣ ለሰላምና ለብልፅግና የሚደረገው ትግል የልዩ ልዩ ብሔርተኛ ድርጅቶችን መፈጠርና መቀጠል የግድ አስፈላጊ አያደርገውም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ራስን የማስተዳደር፣ በቋንቋ የመማርና የመሥራት ባህል የመንከባከብና የማበልፀግ መብቶች ተፈጻሚነትም ከኅብረ ብሔራዊ አመለካከትና አደረጃጀት ጋር የሚጋጭና ብሔርተኛነትን ትክክል የሚያስብል አይደለም፡፡

ብሔርተኛ ቡድኖች በግንባር ተያይዘው ሊሠሩ መቻላቸውም ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀትን አይተካውም፣ ወይም አላስፈላጊ አያደርገውም፡፡ በኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀትና በብሔርተኛ አደረጃጀት መካከለል መሠረታዊ የአመለካከት ልዩነት አለ፡፡ ልዩነቱን ለመረዳት በአንድ ፕሮግራም ዙሪያ ልዩ ልዩ የብሔር ብሔረሰብ አባላት ያደራጀ ድርጅትና ብዙ ብሔርተኛ ድርጅቶች በአንድ ምክር ቤት ውስጥ ቢቀመጡ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች እጥረትና ርዝማኔ መገመት ያግዛል፡፡ የብሔር አደራጃጀት ዛፍ ዛፉን የማየት ባህርይ ያጋደለበት ሲሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ግን የዛፉን ስብስብ (ደኑን) የማየት ባህርይው ያመዝንበታል፡፡ የብሔር ቡድኖች ቢያያዙ የየአካባቢ ፕሮግራሞቸውን ሳይጥሉ ነው፡፡ በኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ውስጥ ሲገቡ ግን የሚኖረው አካባቢያዊ ጥቅሞችን ያቻቻለ አንድ አገራዊ የፓርቲ ፕሮግራም ነው፡፡ የብሔር ቡድኖች ዓላማቸውን የተቀበሉ የብሔሩ ወገኖችን በየበኩላቸው በአባልነት የሚይዙ ሲሆኑ፣ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅት ግን የብሔርና የቋንቋ ልዩነት ሳያደርግ ዓላማውን ተቀብለው የሚተገብሩ ዜጎችን የሚያሰባስብ ነው፡፡

በብሔር ብሔረሰቦች የእርስ በርስ ግንኙነቶች ውስጥ የሚንፀባረቅ ጥርጣሬና ሥጋትን ለማዳከምና ትምክህትን ለማምከን፣ ግለሰባዊ ፀቦችን ከግልነት እንዳያልፉ ለማድረግ የተሻለ አቅም የሚሰጥም ይኼው አደረጃጀት ነው፡፡ አግላይና ተገላይ አስጎንባሽና አጎንባሽ ማኅበረሰብ ሳይኖር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመትጋት የሚቀና፣ በመተላለቅና በመፈናቀል ፍርኃት መበርገግ የሚደርቅበት፣ በብሔር ድርጅትነቴ ወኪልህ ነኝ እያሉ ለማደናገር የማይመች ጎዳና ነው፡፡ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ አደረጃጀት ቢዞርም የአንዱ ወይ የሌላ ብሔር አመዛኝነት በሚታይባቸው ክልሎች ውስጥ የፓርቲው ቅርንጫፍ በአንድ ብሔር አባላት መዋጡ፣ በሥልጣን አያያዝም ላይ ይህ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ወገናዊ የመጠቃቀም ሙከራዎችም በቶሎ የሚጠፉ አይሆኑም፡፡ ነገር ግን ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ የሚያሳየው ባህርይ ከብሔርተኛ ፓርቲ በጣም የተለየ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊነትን ከስም ጌጡ ይልቅ እስትንፋሱ ያደረገ፣ ኅብረ ብሔራዊነትንም በስብስቡ ያሟላ ድርጅት ለወገናዊነትም ሆነ ለትምክህት አይመችም፡፡ የአመለካከት ማዕዘኑ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ የማየት፣ የማሳተፍና የማዳመጥ ባህርይ ስላለው ከሌላው አደረጃጀት በተሻለ ተማምኖና ተጋግዞ አድሏዊነትን ለመዋጋት የሚያስችል ነው፡፡

ንዑሳን ክፍሎች ወይም ውሁዳን ወገኖች በቁጥር ከሚያይሉት ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተጣጥሞ ለመሥራት፣ በፓርቲው ውስጥና ከፓርቲው ውጪ መብቶቻቸውን ለማስከበር፣ አድሏዊነት እንዲጋለጥና እንዲታረም ለማድረግ በበለጠ ይበረታታሉ፡፡ ‹‹ስደተኛ››፣ ‹‹በአገሬ መጥቶ›› የሚሉ ጥበቶችንና የእነዚህ ተቃራኒ የሆኑ ትምክህቶችን እየበጣጠሱ፣ በየትኛውም ሥፍራ ዜጎች እየሠሩና ካፒታላቸውን እያንቀሳቀሱ ልማትን ለማንደርደር ከብሔርተኛ አደረጃጀት በጣሙን የተሻለ ነው፡፡ ይህ ሰባኪ የማያስፈልገው እውነት ነው፡፡ የጎሰኛ አድልኦን በጎሰኛ አድልኦ መመከትና ማሸነፍ እንደማይቻል፣ እነ እንትና ካዳሉ እኔስ ለምን አላደርገውም የሚል ጉዞ ጥፋት መሆኑ ከተሞክሮ ታይቷል፡፡ ብሔርተኛ ድርጀቶች በክልል ደረጃ ሥልጣን ይዘው በጎሰኝነት የቱን ያህል እንደነጎዱ፣ በግንባር ስም ተሸፍኖ የፌዴሬል መንግሥት ዋና ገዥ ቡድን ቢኮንም ከጎሰኛ የሥልጣን ቁጥጥርና ዘረፋ እንዳልተመለጠ እስኪያቅር ታይቷል፡፡ ሥልጣን ላይ ገና ያልወጡ ብሔርተኛ ድርጅቶች ስለብሔርተኝነት ድጥ ለመማርና ከወዲሁ ለመስተካከል የ27 ዓመት ልምድ አያንሳቸውም፡፡ በዚህ ረገድ የዛሬ አሥር ዓመት በሰኔ 1999 ዓ.ም. የተወሰኑ ቡድኖች የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መፍጠራቸው ጥሩ ጅምር ነበር፡፡

ኢሕአዴግ የጎሰኝነት ችግር ማለትም ጎሰኛ አድሏዊነት ወይም ብሔረሰባዊ የጥቅቅም ሥራ መኖሩን ቢያምንምና እታገለዋለሁ ቢልም፣ የችግሩን ጥልቀትና ማቃለያ ለራሱም የጨበጠው አይመስልም፡፡ ለሕዝብም ፍርጥ አድርጎ አላወጣውም፡፡ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ተብሎ ከተሾመውና ከተሸለመው የኢሕአዴግ እሳቤ በተቃራኒ አክራሪ ብሔርተኝነት የሚባል ነገር መስማት የጀመርነው ገና አሁን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡

ኢሕአዴግ የባለ 21 ብሔራዊ ድርጅቶችን ግንባር (ደኢሕዴግን) በ1995 ዓ.ም. ወደ ደኢሕዴን ቢለውጥም ለጎሰኝነት መስፋፋት የሚመች አመለካከትና አደረጃጀት የሚያራባው እርሱ ራሱ በመሆኑ፣ ከችግሩ የመውጣቱን አቅጣጫ እንኳ ማየት አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶች ወደ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ቢገቡ፣ የዘረዘርናቸውን የብሔርተኝነት ጠንቅ ለማስወገድ ትልቅ ዕርምጃ በሆነ ነበር፡፡

በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም መዋሀድ ዓላማው እንደነበር ኢሕአዴግ ገልጾ ነበር፡፡ መስከረም 21 ቀን 1999 ዓ.ም. የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሰጡት ቃለ ምልልስ የመዋሀዱ ግብ እንደተጠበቀ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ገና እንደሆነና የሚያስገድድ ሁኔታ እንደሌለ ነግረውን ነበር፡፡

ጉዳዩ ‹‹በቁም ነገር›› መልሶ የተነሳው ባህር ዳር ላይ በተካሄደው የኢሕአዴግ ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በ2005 ዓ.ም. ነው፡፡ በወቅቱ ዜና ሆኖ በሰማነው መረጃ መሠረት ጉዳዩ እንደገና መነሳቱን፣ በተለይም ደግሞ ከኢሕአዴግ መሥራችና ጎምቱ አባላት መካከል አንዱ አቶ ሥዩም መስፍን ጉዳዩ ከተወዘፈበት ተነስቶ በሰፊው ተጠንቶ ለተመሳሳይ የድርጅቱ መድረክ እንዲቀርብ አሳስበዋል ሲባል ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ከሞላ ጎደል ከድፍን አምስት ዓመት በኋላ ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና ላይ ኢሕአዴግ ከግንባር ወደ አንድ ወጥ ድርጅት የሚያደርገው ሽግግር በጥልቀት የመታደስ ሒደት ውስጥ ከተለዩት ጉዳዮች መካከል አንዱና መሠረታዊው መሆኑ ተነገረን፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ወጣቶች ሊግ ኢሕአዴግ ከግንባር ወደ አንድ ወጥ ድርጅት ለሚያደርገው ሽግግር ምሳሌ ሆኖ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ›› የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲገልጹ ሰማን፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት አቶ መለስ ዜናዊ አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊንየም መርቀው ያስጀመሩት ይህ አዲስ ሺኛ ዓመት ‹‹አገራችን ሐረርን የምትሆንበት መባቻ ነው›› በማለት ነበር፡፡ አቶ መለስ፣ ‹‹የመቻቻልና የፍቅር ተምሳሌት›› ያሏት ሐረር ለዚህ ምሳሌነትና ክብር የበቃቸው የተሰባጠሩ ነዋሪዎቿ የተሳሰበ ትስስር ለማዳበር በመቻላቸው ነው፡፡ አሁንም አዲሱ ሺኛ ዓመት ከተጀመረ ከአሥር ዓመት ወዲህ ‹‹አገራችን ሐረርን የምትሆንበት መባቻ ነው›› መባሉ ከልብ ከሆነ ከፖለቲካ ጥለኝነት፣ ከጠባብ አስተሳሰብና ኢትዮጵያን ካስጨነቀና ከጠበበ ስብስብ ማውጣት የግድ ነው፡፡

የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ (መስከረም 1999 ዓ.ም.) ድርጅቱ የሚመራባቸውን አጠቃላይ የአደረጃጀት መርሆዎች በሚወስንበት ክፍሉ (II/2) ‹‹ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አገር እንደ መሆኗ የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት አሰባስቦ ለማታገል የሚቻለው፣ ግለሰቦችን በተናጠል በሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ሳይሆን የድርጅቶች በተለይ የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች ግንባር በሆነ አደረጃጀት አማካይነት ነው፤›› ይላል፡፡

ኢትዮጵያ ግን ከዚህ የሠፈሩበትን ወይም የመገኛ ምድርን ከአስተዳደር ይዞታነት ይልቅ የአንዱ ብሔረሰብ የብቻ ምድር አድርጎ ከመረቀው ከዚህ አደረጃጀት መውጣት አለባት፡፡ እስካሁን የተከተልነው አደረጃጀት በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደበትንና እንጀራና ልጆች ያፈሩበትን የትኛውንም ሥፍራ አገሬ ብሎ መቁጠርን አበለሻሽቶብናል፡፡ አሠራሩ በየሥፍራውና በየአካባቢው ከአንድ ክልል ያለፈና ተመልሶ ሊለቀም የማይችል ሥርጭት ያላቸው የተለያዩ የአማራ፣ የትግራይ፣ የጉራጌ፣ ወዘተ ማኅበረሰቦችንና ግለሰቦችን ያለቤታቸው የሚኖሩ ባይተዋሮች ወይም ሁለተኛ ዜጎች አድርጓል፡፡ የማፈናቀልና የግጭት መነሻም ሆኗል፡፡

በዛሬው የተሳሰረ ዓለም ውስጥ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ እምብርት ውስጥ ቁርጥራጭ አገር መሆንን መብት አድርጎ በሚያቋቋም፣ አደረጃጀት ውስጥ ልኑር ማለት በእሳትና በትርምስ ውስጥ መኖርን ድህነትንና ጉልበት የለሽነትን እንደ መብት መቁጠር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እንቢ ማለት አለብን፡፡ ደርግ ያንኮታኮተውን ኅብረ ብሔራዊ ትግል መልሰን ማቋቋምና በክልልተኝነት የተጣበቡ ትግሎች ዋና ተዋናዮች የሆኑበትን ሁኔታ መቀየር፣ ኢሕአዴግንም ለኅብረ ብሔራዊ ትግል ‹‹ወደፊት በሉለት!›› ብለን መገፋፋትና መታገል አለብን፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *