ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሃይመማሪያም ” በቃኝ”አሉ – የመፍትሄው አካል ለመሆን? ከዜናው በላይ መነጋገሪያ የሆነው ” እስከዛሬስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ?” የሚለው ነው

ኢህአዴግ መቶ ከመቶ በሕዝብ ተመረጥኩ ሲል የምርጫ መኮንን የነበሩትንና ” ተሰው” የተባሉት የመለስን እግር ተክተው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሃይለማሪያም ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ተቀባይነት ሳያገኙ ቆይተው ዛሬ ” በቃኝ” ሲሉ መወሰናቸውን አስታወቁ። ዝርዝሩን በኢህአዴግ ፓርላማ ስንብት ላይ እንደሚናገሩ ቃል ገብተዋል።

በ”ሚመሩት” ድርጅት ቴሌቪዥን ቀርበው የ” በቃኝ” መግለጫቸውን የሰጡት አቶ ሃይለማሪያም እንደምክንያት ያቀረቡት ” የመፍትሄው አካል ለመሆን በመወሰኔ ነው” የሚል ነው። ዝርዝሩን ባያስቀምጡም ሕዝብ ያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ባላቸው ሃላፊነት ከመወሰን ይልቅ ሽሽት መምረጣቸው ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ለማሳካት አቅም እንደሌላቸው አመላካች እንደሆነ ተጠቁሟል።

ወደ ስልታን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱ በቡድን እንድትመራ ከመስማማት ጀምሮ ” ቅምጥ” የሚል ስያሜ እየትሰጣቸው የቆዩት አቶ ሃይለማሪያም አጣብቂኝ ውስጥ እንደነበሩና ድስተኛ እንዳልነበሩም የሚናገሩ ነበሩ። ቀድመ ታሪካቸው ከቤተክርስቲያን ጋር የተዋሃደና ሰዎች ወደ ፖለቲካ መስመር እንዳይሄዱ በቢተክርስቲያን ህብረት ሲሰብኩ እንደነበር የሚያውቁ ምስክሮች አቶ ሃይለማሪያም ውስጣቸው ካለው እውነት ጋር መጋጨታቸው የህሊና ጠባሳ እንደሆነባቸው አስተያየት ሲሰጡ ነበር።

” የጌታዬን ስም ልጠራ አይገባኝም” በሚል ተንበርክከው በማንባት ንስሃ በገቡ በዓመት ጊዜ ውስጥ ” ባለ ራዕዩን መሪ” የተኩት አቶ ሃይለማሪያም የቀድሞውን አለቃቸውን ” ውርስ” በአምልኮ ደረጃ እንደሚያስቀጥሉ ደጋግመው የሚናገሩ፣የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ ህዝብ ተከፍሎ የሚያልቅ እዳ እንዳለበት የተናገሩ፣ ንጹሃንን የገደሉና እየገደሉ ያሉ የሰራዊት አባላትን በአደባባይ ያመሰገኑና ያሞካሹ፣ የፖለቲካ እስረኛ የለም ያሉ፣ ድርጅታቸው በብቃት ማነስ አጠልሽቶ የገመገማቸው፣ ከስልጣን እንደሚለቁ አስቀድሞ ግምት የተሰጣቸው የአገር ” መሪ” ነበሩ።

” በቃኝ” ያሉበትን ደብዳቤ ለፓርቲያቸው ደህዴን እና ለኢህአዴግ አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ፣ በቅርቡ በሚደረገው የኢህአደኢግ ጉባኤም የመልቀቂያ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሚያገኝ የጠቆሙት አቶ ሃይለማሪያም፣ በኢህአዴግ ፓርላማ ፊት የመጨረሻ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ አስታውቀዋል። አያይዘውም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል። 

” አምኛለሁ፣ እምነቴ ነው” በሚል የሕዝብ ጥያቄዎች ሊመለሱ እንደሚገባቸው ያስታወቁት አቶ ሃይለማሪያም ” አሁን አገሪቱ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን አምነዋል። የቀድሞው መተሳሰብና አብሮነት ከህዝቡ እንዳይለይም ተማጽነዋል። አሁን ለተጀመረው የሪፎርሙ አካል በመሆን ሲሰሩ መቆየታቸውን፣ በስተመጨረሻም የመፍትሄው አካል ለመሆን ሲሉ ራሳቸውን በበቃኝ ማግለላቸውን ተናግረዋል።

በአንዳንድ የማህበራዊ ገጾች አቶ ሃይለማሪያም ” ተገደው መልቀቃቸውን” አመላካች መግለጫ መስጠታቸውን እየተናገሩ ነው። ምክንያት ሲያቀርቡም ” እሳቸው የመፍትሄ አካል ከሆኑ፣ መፍትሄው እሳቸውን ማስወገድ የሚል ሃሳብ አለበት ማለት ነው” ባይ ናቸው። አቶ ሃይለማሪያም ባላቸው ሃላፊነት ብሄራዊ የእርቅ ስብሰባ መጥራት ባለመቻላቸውና አሁን ያለው ቀውስ ስላሳሰባቸው ስልጣን መልቀቃቸውን የሚጠቁሙ ክፍሎች አሁንም ብቸኛው አማራጭና መፍትሄ ፍትህ ያለበት ብሄራዊ እርቅ ብቻ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

አቶ ሃይለማሪያም ወደፌት ጊዜና እድሉ ካላቸው መጽሃፍ ይጽፋሉ ተብሎ ይገመታል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤
0Shares
0
Read previous post:
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሙስና ሊከሰሱ ነው፤ ” …እነዚህ ሙከራዎች ሁሉ ወደየትም አይሄዱም” ኔታንያሁ

ፖሊስ እንደገለፀው በጉቦ፣ በማጭበርበር እንዲሁም እምነትን በመጣስ ለመክሰስ በቂ መረጃ እንዳለው ነው። በሀገሪቷ ቴሌቪዥን ጣቢያ...

Close