ሙሉ መግለጫው እንዲህ ይነበባል – የሚንስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ አወጀ። የሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከዛሬ የካቲት 9/2010 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽድቋል ። የሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሕገመንግስቱን እና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል በተዘጋጀ የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት መንግስት ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅ፣ የአገርን ሰላምና ደህንነት የማስከበር እና የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት እውን በማድረግ የዜጎች በነጻነት የመዘዋወር፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕገመንግስታዊ መብታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን አንዳንድ አከባቢዎች ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚጥስና ለአደጋ የሚያጋልጥ ብሎም የህዝቦች በአንድነት አብሮ የመኖር እሴቲን የሚንድ፣ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የስራ እንቅስቃሴን የሚያስተጋጉል፣ የህግ የበላይነትን የሚያዳክም፣ በምትኩ ደግሞ በሀይል የታገዘ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ስርዓት አልበኝነት የሚያነግስ፣ የበርካታ ንጹሀን ህይወት ያጠፋና ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃትና የህዝቦች መፈናቀል እየደረሰ፣ የአገራችን ኢኮኖሚ እየተጎዳ፣ ንብረት እየወደመ፣ የህዝቡን በሰላም ወጥቶ መግባት እየታወከ እንዲሁም ይህ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተራዘመ መሄዱን በመገንዘብ፣ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት የሕግ ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግላቸው በተለያዩ መድረኮች ጥያቄ በማቅረባቸው፣ በሕገመንግስቱና በሕገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተጋረጠውን ይህን አደጋ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን እና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ የሚያስችል የአስኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።
ስለሆነም በኢፌዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 93(1) (ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። አዋጁ በሚንስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ከዛሬ የካቲት 9/2010 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ህወሓት፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጠላት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *