“Our true nationality is mankind.”H.G.

ስንት ዓመት ለውሳኔ? ሜድሮክ ላይ ብይን ለምን አይጸናም? ዛሬስ የግድያ ማስፈራሪያና ሙከራ አለ?

ለዚህ ድረ ገጽ አዘጋጅ አቶ አርከበ ይህንን ብለው ነበር። ፒያሳ መካከል ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ የወሰዱትን ቦታ ከሊዝ ክፍያ ነጻ ነው። የተከፈለ ነገር የለም። ጉዳዩን ከኔ በላይ የሚያውቀው የለም” መሐል አገር ከንቲባው በሚወጡና በሚገቡበት፣ ባለልጣናት በሚመላለሱበት፣ ሕዝብ መተላለፊያ እያጣ በሚራገምምበት የከተማ እምብርት እንዲህ ያለ ተግባር መፈጸሙን ማጋለጥ ደግሞ አደጋ ነበረው።

በሼክ መሐመድ ዙሪያ ሪፖርተር ሲያወጣቸው የነበሩ መረጃዎች፣ ከመንግስት ሃላፊዎች፣ ከራሱ ከሚድሮክ ሰዎች፣ እዛው ሚድሮክ ውስጥ እርስ በእርስ መበላላት ከሚፈልጉ እና ከሁሉም ወገን ባሉ አገር ወዳዶች የሚገኙ ነበሩ። መርጃዎቹን በማስተባበል ሲሟገቱ የከረሙና መጨረሻ ላይ ወደ ሃይል የገቡት፣ ያስተባበሉት ጉዳይና ማስተባበያዎቻቸው፣ እንዲሁም ሲያስተባብሉ የነበሩት ሁሉም አሉ። አሁን በተወሳሰበ ጉዳይ እስር ላይ በመሆናቸው የሌሉት ዋናው ሰው ብቻ ናቸው። 

የአንድ ትውልድ እድሜ መሬት አጥሮ መኖር ህገወጥ ከመሆኑ ሌላ ጉዳዩን ለማስተባበል ልኡክ እየያዙ ከቢሮ ቢሮ ሲመላለሱ የኖሩት ሰዎች ዛሬ ላይ ምን ይሰማቸው ይሆን? ሲደረድሩ ለኖሩት ምክንያት ዛሬ ምን ማጣፊያ ያቀርባሉ? ኢህአዴግስ እስከመቼ ሲከላከል ይኖራል? አቶ ብርሃኑ አዴሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሃላፊ በነበሩበት ውቅት ስንት ውሳኔ እንዳስቀለበሱና ስንት መመሪያ እንደሰጡ ብዙ ተብሏል። አይበቃም? ለመሆኑ ግን አቶ ብርሃኑ የት ናቸው?

እጅግ እያፈርን የምንሰማቸው በርካታ ዜናዎች አሉ። ከእነዚህ ዜናዎች መካከል የሚድሮክ መሬት አጥሮ መያዝ ነው። ለምን እልባት አይሰጠውም? ምንድነው ችግሩ? የጥልቁ ተሃድሶ ይህንን አይመለክትም? በአንድ አገር ውስጥ ህግ የሚመላከታቸው እና የማይመለክታቸው ዜጎች አሉ የሚባለው እኮ ለዚህ ነው። ኢትዮጵያን እንዳሻቸው የሚጋልቧት ወረበሎች ተፈጥረዋል የሚባለው እኮ ይህ ነው። የመበስበስ አደጋ ምንጩ እኮ ህግን መጨፍለቅ ነው።

ያንገፈግፋል። ስታዲየም እናስገነባለን በሚል ምስኪን ደጋፊዎችን ቅራሬ እየጋቱ ስንት ዘመን ነው ማስታወቂያ የሚሰራው? ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ለሁሉም ለዚህ መነሻ የሆነውን የሪፖርተር ዜና ያንብቡ። ማስተባበያ ካለም እንጠብቃለን።

ሚድሮክ አጥሮ የያዛቸው 11 ቦታዎች ካርታ እንዲመክን ተወሰነ

  • ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥት ውሳኔ ይጠበቃል

በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የሚገኙት ሼክ መሐመድ አል አሙዲ በኩባንያዎቻቸው ተመዝግበው ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ 11 ቦታዎች ካርታ እንዲመክን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ውሳኔ፣ በከተማው አስተዳደር ካቢኔና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይሁንታ ካገኘ ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ 120 ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሊዝ ውል ማሻሻያ በማድረግ የግንባታ ማስጀመሪያ ቀን አራዝሞ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት 66 ፕሮጀክቶች በተሰጣቸው ጊዜ ወደ ግንባታ ገብተዋል፡፡ ወደ ግንባታ ካልገቡት መካከል 16 ያህሉ ውላቸው የተቋረጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ የመንግሥት ተቋማት የያዟቸው 4.76 ሔክታር ስፋት ያላቸው ናቸው፡፡ የሚድሮክና የዲፕሎማቲክ ተቋማት 29 ቦታዎች የተጠቃለሉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ንጉሥ ተሾመ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ንጉሥ እንደገለጹት ጽሕፈት ቤቱ በሚድሮክ ኩባንያዎች የተያዙ 11 ቦታዎችና በዲፕሎማቲክ ተቋማት የተያዙ 18 ቦታዎችም ካርታቸው መክኖ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ውሳኔ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማየት የመወሰን ጉዳይ የከተማው አስተዳደር ነው ሲሉ አቶ ንጉሥ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሚድሮክ ከተያዙ ቦታዎች መካከል መሀል ፒያሳ፣ ሜክሲኮ አደባባይ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎንና ካዛንቺስ ከኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አጠገብ የሚገኙ ቦታዎች ይገኙበታል፡፡

በአጠቃላይ ሚድሮክ በአዲስ አበባ ከተማ 54 ሔክታር ስፋት ያላቸውን 11 ቦታዎችን ለዓመታት አጥሮ ይዟል፡፡ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታው፣ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዓለማየሁ ተገኑ፣ እንዲሁም የሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በተገኙበት ጉብኝትና ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡

በወቅቱ አቶ አባተ ከዚህ በኋላ ሚድሮክ ወደ ግንባታ ካልገባ የሊዝ ውል ማሻሻያ እንደማይደረግ፣ ይልቁኑም ቦታው እንደሚነጠቅ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹በአስተዳደሩ በኩል የነበሩ ችግሮች በሙሉ ተፈተዋል፡፡ ስለዚህ ሚድሮክ ወደ ግንባታ መግባት ይኖርበታል፤›› በማለት አቶ አባተ ገልጸው ነበር፡፡

አቶ አብነት በበኩላቸው፣ የነበሩ ችግሮች መፈታታቸውንና በቂ በጀት የተመደበ መሆኑም ጭምር በመግለጽ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ተናግረው ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ግንባታ ባለመጀመሩ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት የቦታዎቹ ካርታ እንዲመክን ወስኗል፡፡

ነገር ግን ይህ ውሳኔ በከተማው አስተዳደርና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይሁንታ ካላገኘ ተፈጻሚ እንደማይሆን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት
0Shares
0