ግድያ እስርና እንግልት በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች እዚህም እዛም፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መፈታት፣የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን እለቃለሁ ማለት ሰሞነኛ ክስተቶች ናቸው፡፡ በቅድሚያ በደደቢት አውሬዎች ትዕዛዝ ከታጠቁት መሳሪያ በማይሻሉ ሰዎች ትዕዛዝ ፈጻሚነት በየማጎሪያ ስፍራዎች ስትሰቃዩ የከረማችሁ ወገኖቼ ….

ሁሉን እንደፈቃዱ በግዜው የሚያደርገው አንድዬ የማሪያም ልጅ እንኳን ከልጆቻችሁ ከሚስቶቻችሁና ከወዳጅ ዘመድ ለመቀላቀል አበቃችሁ፡፡ ነጻ አወጣችሁ አለማለቴ ነጻነት በሌለበት ሀገር ከእስር መፈታት ነጻ መውጣት አይደለምና ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከጠባቡ እስር ቤት ወደ ሰፊው የሚለው አነጋገር የተለመደ የሆነው፡፡

ሰው ሲታሰር ይበልጥ የሚጎዳው ቤተሰብ ነው፡፡ ታሳሪው አንዴ ለይቶለት በግፈኞች እጅ ወድቋልና “የማይቻለውን እንዳይቻል ችሎ” ( ይህች አባባል የዶ/ር ኃይሉ ዓርአያ ነች) ይኖራል፡፡ ቤተሰብ ግን ምን አደረጉት? ወዴት ወሰዱት? ዛሬ ምን ይፈጠር ይሆን?  ወዘተ የሚለው የእለት ተዕለት ጭንቀት፤ ከቦታው ርቀት አንጻር እየተመላለሱ መጠየቁ፣ ቀለብ ማቅረቡ ወዘተ በሚል የሚደርስበትን ስቃይ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ እናም የታሳሪ ቤተሰቦች የደረሰባችሁን ሁሉ የሚክስ ባይሆንም እንኳን ለዚህ አበቃችሁ እላለሁ፡፡ሌላ ምን ማለትስ ምን ማድረግስ ይቻላል፡፡

አቶ ኃይለማሪያም ከዚህ በላይ አሽከርነት በቃኝ ብለው በራሳቸው ወስነውም ይሁን፣ ጌቶቻቸው ህውኃቶች ሌላ ሴራአዘጋጅተውልን እሳቸውን ለታይታ ከተቀመጡበት ቦታ ገለል ማድርጉ አስፈልጓቸው ውጣና ልለቅ ነው ብልህ ተናገር ብለዋቸው ለጊዜው ባይታወቅም፤ድርጊቱም በስመ ጠቅላይ ምኒስትርነት ዘመናቸው ለሆነው ከተጠያቂነት ሊያድናቸው ባይችልም  የፈጸሙት ተግባር ግን ቀላል ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህን የርሳቸውን መልቀቂያ አቀረብኩ ጥያቄ ለሀገር እንደሚበጅ ትልቅ ፖለቲካዊ ጉዳይ አድርጎ መመልከት ብሎም አጀንዳ አድርጎ በዚህ መጠመድ አንድም ህውኃትን ያለማወቅ ውጤት ሁለትም ጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን የለውም የህውኃት አሻንጉሊት ነው ስንል ከነበረው የራሳችን ቃል ጋር መጋጨት ይሆናል፡፡

ህውኃትን ለማወቅ ያለመቻላችን ዋናው ምክንያት ራሳችንን በትክክል ማወቅ ያለመቻላችን ይመስለኛል፡፡ለማናቸውም ነገር ቀዳሚው ራስን ማወቅ ነው፡፡አበው ሲተርቱ “አፍ የሚጎርሰውን እጅ ይመጥነዋል እንዴት ሰው መጠኑ አቅሙ ይጠፋዋል” ይላሉ፡፡እኛ ግን አቅማችንን አላውቅ፣ መጠናችንን አንረዳ ብለን ስሜት ፍላጎታችን የአንደኛችን ከሌላኛችን ብቻ ሳይሆን የእኛው ከእኛው ጋር ጭምር እየተጋጨብን ከመግለጫ የዘለለ ተቃውሞ፣ ከውግዘትና ዋይታ ሊሻገር የቻለ ትግል ማድረግ ተስኖን ሰምና ወርቅ የሆነውን የወያኔ ንግግርና ድርጊት ሰሙን ብቻ እያየንና እየተከተልን ወርቁን ለመመርመር ስክነቱም አስተውሎቱም ርቆን እነርሱ በሚሰጡን አጀንዳ እየተጠመድን በሚወረውሩልን ኳስ እየተጫወትን ብዙ መልካም አጋጣሚዎችን በቀላሉ እንደዘበት አሳልፈናል፡፡

በዚህ ሁኔታ ፖለቲካውን እንተውናለን ያሉት አልሆንላቸው ሲል በእነርሱ ተስፋ የቆረጠውና በወያኔ አገዛዝ የተንገሸገሸው ህዝብ ራስ በራሱ እየተጠራራ ባካሄደው መራር ትግልና በከፈለው መስዋዕትነት እነሆ እስረኞችን ከማስፈታት አልፎ ተራራ እናንቀጠቅጣለን ይሉን የነበሩትን ሰዎች ለማንቀጥቀጥ በቅቶ ጠቅላይ ምኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቅርቤአለሁ የለውጡ አካል መሆን እፈልጋለሁ እንዲሉ አብቅቶአቸዋል፡፡አንድም ጋዜጠኛ በጣፈው ነገር አንድም ፖለቲከኛ በአቋሙ ምክንያት አላሰርንም፣ የፖለቲካም ሆነ የህሊና እስረኛ የምትሉት በእኛ ስር ቤቶች የለም እያሉ ሲዘባበቱብን የነበሩት ተንበርክከው ወደው ሳይሆን  እንዲፈቱ ስገደድ ችሏል፡፡

ወያኔን ለዚህ ያደረሰው ለውጥ ሽቶ የደደቢት ህልሙን አራግፎ ጥሎ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እንድታደርግ የበኩሉን ሊወጣ ተዘጋጅቶ ወዘተ ሳይሆን የህዝቡ አገዛዝ በቃኝ ማለት ለሥልጣኑ አስጊ ስለሆነበት ለመደለያም ቀን ለመግዣም ቢሆነን ብሎ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ትናንትም ሆነ ዛሬ ለሀያ ሰባት አመታት  ከወያኔ ሰፈር በኢህአዴግ ጭንብል  በአደባባይ ሲነገሩ የምንሰማቸውም ሆኑ  ሲፈጸሙ የምናያቸው ተግባራት በሙሉ እንደ እኔ አረዳድ ሰሞቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከሰሞነኛው እየተነገረም እየተደረገም ካለው በስተጀርባ በስውር የሚካሄድ ሊካሄድም የታቀደ እነዚህን እንደመንደርደሪያም እንደ ግዜ መግዣም የሚጠቀም የነገሩ ወርቁ የሆነው ስራም ሴራም የለም የሚል ካለ ወያኔን አለማወቅ ብቻ ሳይሆን የመጣንበትን ሀያ ሰባት አመታት ፈጽሞ መዘንጋት ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ እስረኛ በፈቱና ስመ ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ያፈልጋል እኔም የዚህ ለውጥ አካል መሆን እሻለሁ ባሉን ማግስት የደደቢቶቹ በጉልበት የመግዛት ቅዠት የታየበት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ እኛ ትናንትን በመርሳት ልክፍት የተያዝን ሆነን እንጂ  ወያኔ ያው ወያኔ ነው፡፡ በመሆኑም ከ ማእከላዊ በፊት የደደቢት አመለካከት በምትለው ጽሁፌ ለማለት እንደሞከርኩት የደደቢት እምነትና አመለካከት ከመሰረቱ እስከአልተናደ ድረስ ከዛ በመለስ የሚደረጉ ማናቸውም ነገሮች የድርጊቱ ሰሙ እንጂ ወርቁ አይደሉምና ለለውጥ አያበቁንም፡፡ስለሆነም ሰሙን ሳይሆን ወርቁን መፈለጉ መፈተሹ ነው ተገቢው ነገር፡፡

በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ እንኳን የሥልጣን መልቀቅ ነገር ተጭኖባቸው እንኳንም ሀገራዊ ቀውስ አጥለቅልቋቸው ወትሮም ንግግር የማይሆንላቸው የስም ጠቅላይ ምኒስትር የምለቀው ለውጥ ስለሚያስፈልግና የለውጡ አካል መሆን አለብኝ ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃም በድርጅትም የሥልጣን ሽግግር አስፈላጊ ነው፡ ወዘተ ማለታቸውን ሰምተን ብዙም  ሳይቆይ የወሬ ምኒስትሩ ነገረ ሌንጮ የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ እንግዳ ደራሽ ክስተት አለመሆኑን ተናግረው  ጉዳዩ ርሳቸውን ግለሰቡን አቶ ኃይለማሪያምን እንጂ ካቢኔያቸውን አይመለከትም አሉን፡፡ ጠቅላይ ምኒስትሩ ያቋቋመው የምኒስትሮች ምክር ቤት እሱ ሥልጣን ሲለቅ ባለበት የሚቀጥልበት አሰራር ህገ መንግሥታዊ ይሁን ደደቢታዊ ጋዜጠኞች ቢጠይቁልን መልካም ነበር፡፡ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ደግሞ በተራቸው የደኢህዴንም የኢህአዴግም አፍ ሆነው ብቅ አሉና ከአንጀት አለመሆኑን አነጋገራቸው እያሳበቀባቸው አቶ ኃይለማሪያምን አንቆለጳጰሱና ስለ ኢህአዴግና ስለሚመራው መንግሥት ጠንካራነት ነገሩን፡፡ ልብ በሉ በጥልቅ ታደስን ብለው  ሀገሪቱ ለዚህ ደረጃ የደረሰችው በእኛ የአመራር ድክመት ነው ያሉን ሰዎች ወራት ሳይቆጠር ድርጅታችንም መንግሥታችንም ጠንካራ ነው ሁሉን መቆጣጠር ችግሮችን ሁሉ መፍታት ይችላል ሲሉን ተሀድሶ ሲባል የነበረው ዝባዝንኬና እሱን ተከትሎ ሲነገር የሰነበተው ዲስኩር የነገሩ ሰም እንጂ ወርቁ አለመሆኑን ይህም ይጠቁማል፡፡ እናም ከወያኔ ሰፈር የሚነገር የሚሰራውን እንቆቅልሹን መፈተሽ፣ ሰምና ወርቁን መፈለግ፣ መረዳትና መላ መመምታት ካልተቻለ ዛሬም እንደትናንቱ ህዝብ በመስዋዕትነት የደረሰበት የትግል ጫፍ መልሶ መቀመቅ ይወርዳል፣ወያኔም ተንሰራፍቶ ይቀጥላል፡፡

አቶ ኃይለማሪያምን የጭዳ ዶሮ የሚሉት አይነት ማድረግ ካልሆነ በስተቀር እስካሁን የሆነውና እየሆነም ያለው በአቶ ኃይለማሪያም ድክመት ጥንካሬ የሚመዘን አይደለም፡፡ምን አልባት ከዚህ በኋላ ምን ሊቀርብኝ ብለው ትንሽ ወኔ አግኝተው፣ የሚያመልኩት አምላክም ረድቶአቸው፣ የልጆቻቸውና የባለቤታቸው  ጸሎትም ድፍረት ሰጥቶአቸው እኔ ስሙ እንጂ ሥልጣኑ አልነበረኝም ብለው የጓዳውን ምስጢር ይነግሩን ይሆን! ምንም ተባለ ምን ግን ከወያኔ በተጓዳኝ ያለን ሰዎች በማንም ተነገረ በማንም ተሰራ ምንጩ የደደቢት ወያኔዎች መሆናቸውን በመረዳት ፊት ለፊት ከምንሰማውና ከምናየው  ከሰሙ በስተጀርባ ወርቁን መፈለግ ያለብን ይመስለኛል፡፡

ጅብን ሲወጉ በአህያ ተከልሎ ነው እንዲሉ በአቶ ኃይለማሪያም ተከልለው እዚህ ያደረሱን ሰዎች ባሉበት ተቀምጠው የኃይለማሪያም መነሳት የሚያመጣው ፋይዳ አለመኖሩን፡፡ የጉልቻ መለዋወጥ ወጥ አለማጣፈጡን መረዳትና ከእንግዱህ  በኢትዮጵያ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ የሚባልበት ክስተት መደገም እንደሌለበት እና የትግሉ የመጨረሻ ምዕራፍ እስረኛ ማስፈታት፣ የኃይለማሪያም ሥልጣን መልቀቅ፤  ወያኔን በወያኔ መተካት ወዘተ ሳይሆን የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ የሚያስቀመጥ መሆን አለበት፡፡ አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ባለጠመንጃ የማይገፋው፣ ሴረኛ ሸውዶ የማይልፈው፣ አንባገነንነትን ሊያበቀል ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ሊሸከም፣ ዘረኝነትን ሊያስተናግድ ወዘተ የማይችል ሥርዓት መፍጠር መቻል መሆን ይኖርበታል፡፡

ስለሆነም በወያኔ ከሚነገር ከሚፈጸመው ውስጥ በግልጽ የሚታየንንና ፈጥኖ የሚረዳንን ሰሙን ብቻ አፈፍ በማድረግ አስተያየት ለመጻፍም ሆነ ለመናገር ሳንቸኩል፣በሌሎች መስዋዕትነት እየተገኘ ባለው ድል ፊታውራሪ ለመሆን ሳይቃጣንም ሰከን ብለን ወርቁን መመርመር ያስፈልጋል፡፡በተለይ ደግሞ የፖለቲካው ተዋናይ ነን የሚሉቱ ወገኖች የምንይልክን ቤተ መንግሥት ከቅርብም ከሩቅም  እያዩ ሆድና ጀርባ ከመሆን ወጥተው የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት እነርሱም በብቃታቸው ተመዝነው በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ሊሚመኙት ሥልጣን የሚበቁበት አለያም የሚያጡበት አስተማማኝ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሰረት በሚጣልበት ሁኔታ ላይ ነገ ሳይሆን ዛሬ ሥራ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የህዝብ ትግል ቢከሽፍና ቢመክን ዋንኛዎቹ የታሪክ ተጠያቂዎች እነርሱ ይሆናሉ፡፡መምራቱ አልሆነላቸውም ህዝብን ተከትሎ ትግሉን አቅጣጫ ለማስያዝ ለመጪው ስትራቴጂ ለመንደፍ አለመቻል ግን….?

በሌላ በኩል ኃይለማሪያምን የሚተካው እገሌ ይሁን እገሌ በሚል  በተለያየ መንገድ የሚንጸባረቀው አስተያየትም የትግሉን ግብ ሳይሆን የወያኔን ፍላጎትና መንገድ የተከተለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለውና አሁንም እየተከፈለ ያለው የሰው ለውጥ በመሻት አይመስለኝም፡፡የሥርዓት ለውጥ እንጂ፣ከደደቢት ትልም ከህውኃት አገዛዝ የመገላገል እንጂ፡፡የደደቢቱ የቅዠት ትልም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር እስካልተወገደ ድረስ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ተኩኖ አይደለም ሰው መልአክ እንኳን ጠቅላይ ምኒስትር ለመሆን ቢበቃ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፣በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ደደቢቶች በሥልጣናቸው መቀጠል አይችሉም፤ ወርደውም ዳግም ተወዳድረው ማሸነፍ አይሆንላቸውም፡፡ሥልጣን አጡ ማለት ደግሞ የሚያስከትለውን መዘዝ ከእኛ በላይ እነርሱ ያውቁታል፡፡ደደቢት እስከ ምንይልክ ቤተ መንግሥት ምን እየሰሩ እንደደረሱ ቤተ መንግሥት ተቀምጠው ሀያ ሰባ አመታት ምን አንደፈጸሙ እኛ የማናውቀው እነርሱ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚርዱበት ብዙ ጉዳጉድ እንዳላቸው መገመት አይከብድም፡፡

ስለሆነም ብረት የሚቀጠቀጠው እንደ ጋለ ነው እንዲሉ ከወያኔ ሰፈር በሚሰሙ በሚደረጉ ግዜ መግዣ ማዘናጊያ ድርጊቶች ሳይዘናጉ ይህ ውጤት እያስመዘገበና ያለ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለ ትግል መዳረሻ ግቡ ፍላጎትና ዓላማው የሥርዓት ለውጥ መሆኑ በግልጽ ተቀምጦ  መተማመን በመፍጠር የጋለውን ብረት  የሚፈለገውን ቅርጽ ለማስያዝ በአንድ  ልብና መንፈስ  እንዲህ ፍም መስሎ እንደ ጋለ መቀጥቀጥ ነው የሚበጀው፡፡

ሌላው ከታውሞው ጎራ በእጅጉ የሚፈለግ ነገር ቢኖር ከትናንት መማር ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ የየግል ፍላጎትና ህልማቸውን ወደ ጎን አድርገው ጠረጴዛቸው ላይ  ሀገርና ህዝብን አሰቀምጠው መምከር ይኖርባቸዋል፡፡ደርግ ለ17 አመታት ገዥነት የበቃው ተቃዋሚዎቹ እኛ ብለው ከመስራት እኔ እኔ በሚል ሽኩቻ በመጠመዳቸውና በመተላለቃቸው ነው፡፡ ወያኔም ሀያ ሰባት አመታት ሊገዛን የቻለው በተቀዋሚው አይንና ናጫ መሆንና ሆድና ጀርባ ሆኖ መቀመጥ መሆኑ አሌ የሚባል አይመስለኝም፡፡ ዛሬም ቢሆን የህዝቡን ትግልና ድል የራስ ለማድረግ የሚታዩ አዝማሚያዎች ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የሚያስገባ ቀዳዳ ከተገኘ ብሎ አድፍጦ ማድባትና ሌላውን  ጠልፎ ለመጣል ማሴርና መዶለት፣ህዝብ ለመሰረታዊ የሥርዓት ለውጥ መስዋዕትነት እየከፈለ የሥልጣን ፍርፋሪ በመሻት ለጥገናዊ ለውጥ ጎንበስ ቀና ማለት ወዘተ ሁሉም ከትናንት አለመማርን የሚያሳዩ እየወደቀ እየተነሳ ወያኔ በገዛዙ እንዲቀጥል የሚያግዙ አድራጎቶች ናቸውና ፈጻሚዎቹ ቆም ብለው ሊያስቡ፣ሌላውም ወገን ሀይ ሊላቸው ይገባል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *