ከዶቸቨለ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ምሁራኑ ከአሁን ቀደም ተሞክሮ ዘላቂ ውጤት ያላመጣው እንዲህ ዓይነቱ አስገዳጅ ድንጋጌ ፖለቲካዊ ቀውሱን ከማባባስ ሌላ የሀገሪቱንም ህልውና ከባድ አደጋ ውስጥ ሊከት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ::

የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት ሰላማዊ ሽግግር እና የለውጥ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ ሁለት ምሁራን ገለጹ:: ምሁራኑ በኢትዮጵያ ለተከሰተው ፖለቲካ ቀውስ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እንዲሁም ሃገሪቱን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ለዕውነተኛ ለውጥ የመዘጋጀት እና ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ የሽግግር ሥርአት ለመመስረት መድረኮችን የማመቻች ሃላፊነት አለበት ብለዋል።  የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች የሚያፍኑ አሳሪ ህጎችን ማውጣትም ችግሩን ይበልጥ እንደሚያባብሰው ነው ምሁራኑ ያስገነዘቡት:: መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቀሪ እስረኞችን እንዲፈታ እና ለመጨቆኛ ይጠቀምባቸዋል ያሏቸውን የፕሬስ፣ የፀረ ሽብር እና የሲቪክ ማህበራት ህጎችም በአፋጣኝ እንዲሰርዝ ጠይቀዋል :: 

በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ግጭት እና ፖለቲካዊ ቀውስ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለእስር ዳርጓል :: የበርካቶችንም ህይወት አጥፍቷል ንብረትም አውድሟል :: ከ 100 ሺህዎች በላይ የሚልቁ የሃገሪቱ ዜጎችንም ለስደት እና ከሚኖሩበት የትውልድ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል :: ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ በሃገሪቱ አንዳችም የፖለቲካ እስረኛ የለም ሲል ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ የሚደርስበትን ነቀፌታ ሲያጣጥል ቆይቷል ::ይሁን እና በሃገሪቱ ዳር እስከዳር የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመፅ እና አለመረጋጋት ተከትሎ ውስጣዊ

Asfa-Wossen - deutschsprachiger Autor und Unternehmensberater (picture-alliance/dpa/E. Elsner)

ችግሮቹን በመገምገም ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል የተፈረደባቸውን እና የክስ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚዎችን የክስ ሂደት በማቋረጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ እሥረኞችን እየፈታ ነው:: ምንም የፖለቲካ እስረኛ የለም በተባለባት ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል ብቻ ከ 30 ሺህ በላይ ሰዎች መፈታታቸው ሲሰማ ብዙዎችን ማነጋገሩ አልቀረም::

የኢትዮጵያ መንግሥት ከእስረኞች ፍቺ ጎን ለጎን የዜጎችን መሰረታዊ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሳሪ ነው የተባለ ለ 6 ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ደንግጓል :: ከዶቸቨለ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ምሁራኑ ከአሁን ቀደም ተሞክሮ ዘላቂ ውጤት ያላመጣው እንዲህ ዓይነቱ አስገዳጅ ድንጋጌ ፖለቲካዊ ቀውሱን ከማባባስ ሌላ የሀገሪቱንም ህልውና ከባድ አደጋ ውስጥ ሊከት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ :: ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳዮች ልዩ አማካሪ እና የፖለቲካ ተንታኝ ከእንዲህ አይነቱ የችግር አዙሪት ለመውጣት ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ እርቅ ማካሄድ ሰላማዊ የሽግግር ሥርአትን ማስፈን እና በትክክለኛ ፍትሃዊ ምርጫ የመድብለ ፓርቲ መንግስትን ማቋቋም ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ :: ከዚህ ውጭ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፈን መሞከር ለመንግስትም ለሃገሪቱም አይበጅም ብለዋል :: ጊዜው በጣም እየረፈደ ነው :: መንግሥት ይህን ተገንዝቦ የብሔራዊ እርቅን እና መግባባትን ጠቀሜታ ከማንኳሰስ ይልቅ ለድርድር እና ለውጥ እንዲዘጋጅም ዶክተር አስፋወሰን  አሳስበዋል ::

ገዥው የኢህአዲግ መንግስት በቅርቡ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአሜሪካ መንግስት የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም ዓለማቀፍ ተቋማት ኮንነውታል:: የጀርመን መንግስትም ሁሉን

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV (picture alliance/AP Photo/ltomlinson)

አቀፍ ንግግር ከሁሉም ወገኖች ጋር እንዲጀመር ኣሳስቧል :: ህጉ መንግሥት ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ቆርጬ ተነስቻለሁ ሲል የገባውን ቃል የሚጻረር መሆኑን የሚገልጹት የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እና የሲቪክ ማህበራት በበኩላቸው በሃገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች የተገደሉ ወገኖችን የሚያጣራ የተባበሩት መንግስታት ግብረሃይል ፈቃድ እንዲሰጠው በአሜሪካ መንግስት ለቀረበለት ጥሪ እስካሁን ይፋዊ ምላሽ ባልሰጠው የኢሃዲግ መንግስት ላይ ኤች አር 128 ወይም ሴኔት ሪዞልሽን 168 የተሰኘው የኢትዮጵያን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚመለከተው ረቂቅ ድንጋጌ የፊታችን ፌብርዋሪ 28 በአሜሪካ ሴኔት እንዲጸድግ ግፊታቸውን አጠናክረዋል :: ድንጋጌው የመንግስትን ባለስልጣናት ከሃገር ሃገር የመዘዋወር መብትን ሊገድብ ይችላል ነው የሚባለው :: በአሜሪካ ሴንት ሜሪ ዩኒቨርሲቲ መምህር የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ልማት መፍትሄዎች የፕሮግራም እና ኦፕሬሽንስ ሃላፊ እንዲሁም የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር ሃሰን ሁሴን ሃገሪቱ የተደቀነባት አደጋ አስፈሪ ነው ይላሉ :: ከአሁን ቀደም ተሞክሮ የከሸፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ለበለጠ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉት ባለሙያው መንግስት ገቢራዊ ያደረጋቸውን የፕሬስ የፀረ ሽብር እና የሲቪክ ማህበራት አወዛጋቢ ህጎች በአስቸኳይ እንዲሰርዝ ጠይቀዋል :: መንግስት ቀሪ እስረኞችን ያለምንም ቅድመሁኔታ መፍታት አለበት የሚሉት ፕሮፌሰር ሃሰን ለፍፁም ዲሞክራሲያዊ ለውጥ መዘጋጀት እና የገባውን ቃል ማክበር የሚገባው ሲሆን በሂደትም ከሁሉም ወገኖች ጋር ብሔራዊ እርቅ እና ድርድር ማካሄድ ይኖርበታል ሲሉ ይመክራሉ ::

ገዥው መንግስት ኢሃዲግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገቢራዊ ከሆነ በኋላ በሃገሪቱ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን አስታውቋል :: የጊዜያዊ መንግስት ምስረታንም ፈጽሞ የማይታሰብ ሲል መግለፁ ይታወሳል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *