በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም. የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ሁለት የዋልድባ መነኩሴዎች፣ ከማረሚያ ቤት አያያዝ ጋር በተገናኘ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

አባ ገብረየሱስ ኪዳነ ማርያምና አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት የተባሉት ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ፣ በማረሚያ ቤቱ የተሰፋ ዩኒፎርም ‹‹አንለብስም›› በማለታቸው ሲታሰሩ ከለበሱት ልብስ ሌላ መቀየሪያ ልብስ እንዳይገባላቸው በመከልከላቸው፣ ፍርድ ቤቱ መፍትሔ እንዲሰጣቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከመነኩሴዎቹ ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩ ተከሳሾች መንግሥት ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በገባው ቃል መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክሳቸውን አቋርጦ የፈታቸው ቢሆንም፣ ሁለቱ መነኩሴዎችና አንድ ሌላ ተከሳሽ ብቻ ክሳቸው እንዳልተቋረጠና እንዳልተለቀቁ ታውቋል፡፡

መነኩሴዎቹ ክስ የተመሠረተባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ) እና አንቀጽ 38ን፣ እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን ተላልፈዋል ተብሎ ነው፡፡ ተከሳሾቹ የተጠቀሱትን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ በ2008 ዓ.ም. በጎንደርና አካባቢው ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ታጥቀው የግንቦት ሰባት አባላትን የተቀላቀሉትን በመደገፍ፣ በማበረታታትና ገንዘብ በማቀባበል፣ እንዲሁም በውጭ ከሚገኙ የድርጅቱ አባላት ጋር የስልክ ግንኙነት አድርገዋል ተብለው መሆኑ በክሱ ተጠቁሟል፡፡

መነኩሴዎቹ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙና ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ገልጸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ግን ምስክሮቹን አላሰማም፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ለማሰማት ለየካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

reporter Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *