ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባል ስያሜና የሥልጣን ቦታ አስተዳደሯ ውስጥ ያስተዋወቀችው በ1936 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከጣሊያን ወረራና ከነፃነት ወዲህ ሥራ ላይ በነበረው ሕግ መሠረት፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በንጉሠ ነገሥቱ የበላይ አዛዥነት ሥራቸውን የሚያካሂዱ ነበሩ፡፡

የሚኒስትሮች የምክር ጉባዔ (ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት) ሰብሳቢም ንጉሠ ነገሥቱ ሲሆኑ፣ እሳቸው በሌሉበት ጊዜ ግን የዚህን ጉባዔ ሰብሳቢና ፕሬዚዳንት የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዙት ሚኒስትር ነው፡፡ የ1936 ዓ.ም. ሕግ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን አቋቋመ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚኒስትሮች ሁሉ የበላይ አደረገ፡፡ ከዚያ በፊት በጽሕፈት ሚኒስቴር ሥር የነበሩትን ሥልጣናት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዛወረ፡፡ በሁለተኛው ዓመት በቁጥር 12 ነጋሪት ጋዜጣ በወጣው የነሐሴ 25 ቀን 1935 ዓ.ም. የመንግሥት ማስታወቂያ (ሹመት) ቁጥር 16/1935 መሠረት፣ ክቡር ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡

ከዚያ ወዲህም በ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና በእሱም መሠረት በወጣው የ1958 ዓ.ም ትዕዛዝ መሠረት የሚኒስትሮች፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር ወሰነ፡፡ አቋቋመ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ሌሎች ሚኒስትሮችን መርጦ ለመሾም (ለመሻርም) ሥልጣን ያለው ንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሚኒስትር ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ከእሱም በላይ ለንጉሠ ነገሥቱ ኃላፊ/ተጠሪ ነው፡፡ እስከ 1966 ዓ.ም. መጨረሻ በዘለቀው በዚህ ሕገ መንግሥታዊና የሚኒስትሮችን ሥልጣንና ተግባር በወሰኑ ሕጎችና ድንጋጌዎች መሠረት (በዚያው ጊዜ በተለይም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የማቋቋሚያ ቃል ኪዳን ቋንቋ) የአገርም የመንግሥትም መሪ ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ፡፡ በአገሪቱ ግዛት ላይ ሙሉ ገዥነት የነበረው ንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡ የመንግሥት የበላይ ሆኖ በአገሩ ጉዳዮች ሁሉ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡ የመንግሥት ሥራ የሚሠራባቸውን የመሥሪያ ቤቶችና የሚኒስትሮችን ሁሉ የሥራ አኋኳን አቋቁሞ የሚወስነው፣ የመሥሪያ ቤቶችን ባለሥልጣናት የሚሾመው በማዕረግ የሚያሳድገው የሚያዛውረው ከሥራ የሚያግደው የሚሽረውም እሱ ነው፡፡

ፓርላማው እየተስማማበት ጦርነት ለማወጅ ሥልጣኑም የእሱ ነበር፡፡ ለሰላም ጊዜና ለጦር ጊዜ የሚያስፈልገውን የጦር ኃይል የሚወስነው፣ የጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዥም ስለሆነ የጦሩን ኃይል የሚያደራጀው፣ የሚያዘው፣ ለጦር መኮንኖች ማዕረግ የሚሰጠው ማዕረግ የሚያሳድገው፣ የሚያዛውረው ወይም የሚያሰናብተው፣ እንዲሁም የጦር ጊዜ አስተዳደርን የጦር ሕግን ወይም ‹‹አገር የሚጠበቅበትን አስቸኳይ ነገር›› የሚያውጀው፣ በመንግሥት ግዛት መከላከያ ወይም በግዛቱ አንድነት ላይ አደጋ የሚያመጣውን ነገር ለማስወገድና መከላከያውንም አንድነቱንም ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው ለንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡

በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲው ዘርፍም ከውጭ አገር ጋር የሚደረገውን ግንኙነት የበላይ ሆኖ የሚመራው አምባሳደሮችንና መልዕክተኞችን እየሾመ የሚልከው ከውጭ አገር እየተሾሙ የሚመጡትን የሚቀበለው፣ ከውጭ መንግሥት ጋር ያለውን ክርክር ሕጋዊ በሆነና በሰላማዊ መንገድ የመወሰን፣ እንዲሁም ፀጥታና የጋራ መከላከያ በሚጠበቅበት ረገድ ከውጭ አገር መንግሥታት ጋር ተባብሮ የመሥራት መብት፣ ወዘተ. የንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. የተቋቋመው የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን አውርዶ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት እንንዳይሠራ አገደ፡፡ ራሱን ባቋቋመበት (በኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የተቋቋመበት የመስከረም 2 እና የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግንና የሊቀመንበሩን ሥልጣን ለመወሰን የወጣው የመስከረም 5 ቀን 1967 አዋጅ) ሕግ መጀመርያ የርዕሰ ብሔርነትንና የርዕሰ መንግሥትነትን ሚናና የሥራ ድርሻ ለየ፡፡ ንጉሡ ርዕሰ ብሔር ከመሆኑ በስተቀር በአገሪቱ አስተዳደርና ፖለቲካ ውስጥ ሥልጣን አይኖረውም ሲል ወሰነ፡፡ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ንጉሡ ካሉበት አገር መጥተው ሥርዓተ ንግሡ እስኪፈጸም ድረስ የርዕሰ ብሔሩን ተግባር ‹‹ቀዋሚ [ቋሚ] በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ›› ደግም ርዕሰ መንግሥት ሆኖ መንግሥቱን ይመራል ብሎ አወጀ፡፡ በርዕሰ ብሔርና በርዕሰ መንግሥት መካከል የተፈጠረው የሚናና የሥልጣን ልዩነት ግን ብዙ አልዘለቀም፡፡ መጋቢት 8 ቀን 1967 ዓ.ም. በአዋጅ ለንጉሡ የተጠበቀው ‹‹መብት››፣ እንደ ልዑል/ልዕልት ያሉ የነጋሲ ዘር ማዕረጎች ሲሰረዙ ‹‹ኢትዮጵያ ለወደፊት የሚያስፈልጋት የመንግሥት ዓይነት በሕዝብ ይወሰናል›› ሲባል የርዕሰ ብሔርና የርዕሰ መንግሥቱ ሥልጣን መልሶ ደርግ ላይ ተደበላለቀ፡፡ በመላው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘመን (እስከ 1979 ዓ.ም. መጨረሻ) ሥራ ላይ በዋለው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግንና የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው ሕግ መሠረት፣ ርዕሰ ብሔሩና ርዕሰ መስተዳድሩ የደርጉ ሊቀመንበር ሆነ፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥም እሱ ነው፡፡

ከ1980 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን መቆጣጠር ድረስ ባለው ጊዜ የቆው ‹‹ሪፐብሊክ››ም የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት (እዚህም ላይ ሌላ የስያሜ ለውጥ መጣ) ርዕሰ መንግሥት ማለትም ‹‹Head of State›› ነው፡፡ ሪፐብሊኩን በውስጥና በውጭ ይወክላል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው በማለት፣ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን የንጉሠ ነገሥቱን የደርጉንና የሊቀመንበሩን ሥልጣን ሰጠው፡፡ በኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማለትም መስተዳድሩ የሪፐብሊኩ ከፍተኛ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ሆኖ ቢቋቋምም፣ ከበላዩ ሌላ አስፈጻሚ የሥልጣን አካል (የመንግሥት ምክር ቤት፣ ፕሬዚዳንቱ) ያለበት አካል ነው፡፡

ድኅረ 1983 ዓ.ም. በሽግግሩ ወቅት ቻርተር መሠረት የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት ሊቀመንበርን ራሱን ‹‹የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር›› አደረገ፡፡ ከቻርተሩ በኋላ በወጣው የሽግግሩን መንግሥት ፕሬዚዳንት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ፕሬዚዳንቱን ርዕሰ ብሔር፣ እንዲሁም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አደረገ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መርጦ ሹመቱን በተወካዮች ምክር ቤት ያፀድቃል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ሚኒስትሮችን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ሹመታቸውን የሚያፀድቀው ፕሬዚዳንት፣ አላስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የሚኒስትሮችን ምክር ቤትን የመሰብሰብ ሥልጣንም አለው፡፡

በተመለከትነው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት ከቢትወደድ መኮንን እዳልካቸው ጀምሮ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድን . . . ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን፣. . . ጨምሮ ታምራት ላይኔ ድረስ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የርዕሰ መስተዳድርነት ሥልጣን፣ የርዕሰ መንግሥቱ/የርዕሰ ብሔሩ ተቀጥላ፣ በእ ሱፈቃድ የሚኖር ሥልጣን ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በእጅጉ የተለወጠው ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 45 መሠረት የኢፌዴሪ ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው ከተባለ በኋላ ነው፡፡ አቶ መለስ በዚህ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ስም ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ ፕሬዚዳንት በነበሩበት በሽግግሩ ወቅት ከነበራቸው ሥልጣን ያስቀሩትና የተውት የሽግግሩ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ሊቀመንበርነታቸውን ብቻ ነው፡፡ እሳቸው መርቀው ባቋቋሙት አሠራርና በሕግም ጭምር በሚፈቀደው መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር ነው፡፡ የአገሪቱ የአስተዳደርና የፖለቲካ ሥልጣን ባለሙሉ ሥልጣን እሱ ነው፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትን ሥልጣን የተረከበ የመጀመርያው ርዕሰ መስተዳድር ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ በሕግ ያቋቋመውና ይኖረኛል የሚለው የተለያዩ የመንግሥት የሥልጣን አካላት እርስ በርስ የሚገናዘቡበትና የሚቆጣጠሩበት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ግን፣ ባለፉት 23 ዓመታት የመሰከርናቸው አደጋዎች እያዳገሙ ተከሰቱ፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ እስከ 2004 ዓ.ም. ይዘውት የቆዩት ሥልጣን ከዚያ በፊት እስከ እሳቸው ድረስ ከነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሥልጣን በፍፁም የተለየ ነበር፡፡ ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ የተዋጣላቸው አገሮች ከሚያውቋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሮችም በጣም ይለያል፡፡ የዚህ ምክንያት የፓርቲያቸው የኢሕአዴግ የእኔ ብቻ ባይነትና ሁለመናነት ነው፡፡ የኢሕአዴግ ወደ ፍፁማዊ አገዛዝ መውረድ ነው፡፡ የድርጅቱ እንዲህ መሆን ለራሱ ለፓርቲውም፣ ለአገሪቱም በእሳት ተበልቶ የመጥፋት አደጋ ምክንያት ሆነ፡፡ የአገር ህልውና ከኢሕአዴግ ጋር ብቻ እንዲጣበቅ ስለተደረገ፣ ከኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ የወጣ ዴሞክራሲ ማደራጀት ስላልቻለ ነው፡፡

የአቶ መለስ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የሥልጣን ዘመን የነበረውን ከባቢ አየር በጥቂቱ እንመልከት፡፡ አቶ መለስ የኢሕአዴግም ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ የኢሕአዴግ ማለትም የድርጅቱ (እንደ ፓርቲ) አባላት የፓርቲው የገደል ማሚቱዎች ናቸው፡፡ የድርጅቱ አቋምና አካሄድ ፈታይ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር ነው፡፡ የፓርቲው ቁንጮ አመራር የመንግሥታዊ ሥልጣኑም ጉልላትና ቁንጮ ነው፡፡ ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ ሕግ ተርጓሚውን የመሾምና ሌላው ቀርቶ መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃንን የመምራት እኛን የመወከል ሥልጣን አለህ የተባለውና በኢሕአዴግ ተመራጮች የተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት ዞሮ ዞሮ በፓርቲው የበላይ መሪ መዳፍ ውስጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግን የሚመሩት አቶ መለስና ጥቂት ግለሰቦች የመንግሥቱን ሥራ አስፈጻሚ አካል ይመራሉ፣ በኢሕአዴግ የግንኙነት ‹‹መስመር›› በኩል ደግሞ በፓርላማው ውስጥ ያሉትን ተወካዮች ፓርላማውን ራሱን ያዛሉ፡፡ መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን ይሰፍሩላቸዋል፡፡ በአጭሩ ሥራ የማስፈጸሙን፣ ሥራ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ የማውጣትና ዳኛ የመሾም (ሕገ መንግሥቱ ለተለያዩ የመንግሥት የሥልጣን አካላት ሆን ብሎ ያደላደላቸውንና ያከፋፈላቸው ሥራ ሁሉ) በአንድ ቡድን ውስጥ እንዲያም ሲል በአንድ ግለሰብ እጅ ውስጥ፣ ሆነ፡፡ በተለይም ከ1993 ዓ.ም. የኢሕአዴግ (የሕወሓት) ቀውስ ወዲህ ሁኔታው በግለሰብ አሸናፊነት እንደተጠናቀቀና እንደ ተመረቀ፣ ‹‹ሰውየውን›› ቀና ብሎ የሚያይ የገዛ አንደበቱን የሚያምን እንደሌለ መነገሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ሁኔታው በዚሁ ቀጠለ፡፡ የፍፁማዊው አገዛዝ አደጋም ሥር እየሰደደ፣ እያፈጠጠና እየፈነዳም ቆየ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የመበስበስ ወይም የመሰነጣጠቅ ችግሩ የራሱ የፓርቲው ችግር ብቻ ሆኖ የሚቀርበት ሁኔታ የለም፡፡ ማለትም ፀረ ዴሞክራሲን የማስፈን ሙከራ ሲታይ፣ የገዥው ፓርቲ ፍላጎት ከሕዝብ ፈቃድ ሲቃረን ሕዝብ ሳይሸማቀቅ የሚቃወምበትና ገዥውን ፓርቲ ለብቻ ለይቶ አውርዶ ዘጭ የሚያደርግበት፣ ገዥው በእምቢተኛነት እቆያለሁ የማይልበት የመከላከያውና የፀጥታው ኃይል የቡድናዊ ፖለቲካው ተቀጥላ አድርጎ መጠቀም የማይቻልበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ባዶ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ባለመገንባቱ የመንግሥት አውታሮች ከቡድን ታማኝነት ሳይላቀቁ የእነሱም ኢሕአዴጋዊነት ሳይቋረጥ የገዥው ፓርቲ ዳፋ የአገር ዕዳ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

አቶ መለስ የሞቱት በዚህ መካከል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርቲውን፣ ጦሩንም ምክር ቤት የሚባለውንም ሁሉንም የሚቆጣጠረውና ተቀጥላው ያደረገው መሪ ሞት፣ ድንገተኛና አስደንጋጭ መሆኑ አልቀረም፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን የያዙት በዚህ ሁሉ መካከል ነው፡፡ እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑም እውነተኛው የማዘዝ ኃይል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ወጥቶ የጦርና የደኅንነት አውታሩን ወደ ሚቆጣጠሩት ሰዎች አካባቢ መንሸራተቱም አውቶማቲክ ሆነ፡፡

ሽግግሩ ግን ይህን ያህል ብቻ ‹‹ማስተካከያ››ዎችን አድርጎ የተጠናቀቀ አልነበረም፡፡ የአውራው በድንገት መሄድ ለታናናሾቹ መተያየትና እህስ እህስ መባባል በር መከፍቱ አልቀረም፡፡ በዚህ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉት የፍትጊያ ዝንባሌዎች  ከእነ መልካቸው አስቀድመው ሊታወቁ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላም እነዚህ ናቸው ብሎ ዘርግፎ የነገረን የፓርቲ ግምገማ የለም፡፡ በታማኞች መሀል የሚነሳ ልሙጥ የሥልጣን ፍላጎት፣ በአዲሶቹና በነባሮቹ መካከል ያለ ክፍተት፣ በመሪነት በተቀመጠው/በተቀመጡት ሰዎችና ከጀርባ ባሉት ባለኃይሎች መካከል የሚፈጠረው የመተማመን ክፍተት ሁሉ የፍትጊያ መገለጫ ነው፡፡ በአቶ መለስ ታማኝነት ውስጥ አድፍጦ የኖረ ከተቃዋሚዎች ጋርም ሆነ ከተገለሉ ሰዎች ጋር የተያያዘ የፍትጊያ ዝንባሌም አድብቶ ሊሆን ይችላል፡፡ አቶ መለስን የተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዕድልም በተጠቀሱትና በሌሎችም የፍትጊያ ዝንባሌዎች አመጣጥ፣ ብርታትና አዘማመድ የሚወሰን መሆኑ ያኔም ከአምስት ዓመት በፊት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ዛሬም የማይታወቀው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በ‹‹ፈቃዳቸው›› ሥልጣኑን የለቀቁት ምን ሆነው ነው? የሚለው ነው፡፡

ሁለት ጥግ የያዙ ‹‹ምናልባቶችን›› መስጠት ይቻላል፡፡ የጀርባ ትዕዛዝ እየተቀበለ፣ ምሪት ሲከት ‹‹ዋ!›› እየተባለ፣ አልረባ አለ ከተባለም ታምሜያለሁ ወይም አልቻልኩም አለ ብሎ ዘወር የሚደረግ አሻንጉሊት መሆን አንዱ የግምት ጫፍ ነው፡፡

ሌላው የግምት ጫፍ በአመራር ብልኃት፣ በምክር ቤትና በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት በማትረፍ፣ የአንጃ ዝንባሌዎችን ወደ ራስ እየመነዘረና አንገት እያስደፋ ሥልጣን ያለው መሪ መሆን ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጫፎች መካከል ደግሞ ረገብ ያሉ አማራጮች ይኖራሉ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ከምን የመነጨ ነው? በዕውቀት በተለይም በእውነት ላይ ተመሥርቶ መመለስ ያለበት ነው፡፡

አንዳንዶች የአሁኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን መልቀቅ ጨምሮ ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የተዘረገፈውን ችግር ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ጋር ያያይዙታል፡፡ ድኅረ 2007 ዓ.ም. አደባባይ የወጡትን ተቃዋሚዎች የደገሱት ብልሽቶችና ሕገወጥነቶች ግን ቀድሞም የነበሩና የአቶ መለስ ዜናዊም እጅ ያሉባቸው ናቸው፡፡ የአቶ መለስ ሞት ያጎደለው ነገር ቢኖር ሁሉንም ለጥ ሰጥ አድርጎ መዳፍ ውስጥ ያስገባና ትንሹንም ትልቁንም የፖለቲካ ቅያስ የሚያወጣና የሚያስፈጽም ሰውን ነው፡፡ እሳቸው ካለፉ በኋላ የእሳቸውን ቅያሶች በደፈናው ሙጥኝ ማለት ከዚያ በዘለለ በጥራዝ ነጠቅነትና በመሰል መሙላት የተሸፋፈነ የሥልጣንና የአንድ ፍላጎትም መስለክለክ ተደማምሮ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ያደረሰን ይመስላል፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በገዥው ፓርቲ ውስጥ ‹‹ተቃውሞን›› (የተቃውሞ ኃይልን) ፈጥሯል፡፡ በክልሎች መካከል ከዚህ በፊት ለዓመታት ሲያጋጥም ከነበረው የተለየ፣ በተለይም በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል የተፈጠረው ንቁሪያና ሕዝብ ያፈናቀለ፣ ደም ያፋሰሰ ግጭት የብዙዎቹን የፖለቲካ አሀዶች የእርስ በርስ ግንኙነት ለዋውጦታል፡፡ በአገሪቱም ውስጥ አለመረጋጋትና ፍጥጫ ተከስቷል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና ክልሎችን በሚገዙ ቡድኖች መካከል የፖለቲካ መቋሰልና መናናቅ ስለመኖሩ እንድንጠረጥር የሚያደርግ ያልተለመደ ነገር እያየን ነው፡፡ 

ከዚህ በፊት ሲያሳስበን የቆየው (ከዚህ በፊት የምንለው ከ2008 ዓ.ም. ኅዳር ወዲህ ያለውን ጊዜ ነው) ኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲን ማጥለቅ›› የሚለው ነገር ፍቺው ምንድነው? የሚለው ጥያቄና አንድምታው ነበር፡፡ ኢሕአዴጎች፣ የኢሕአዴግ ሰዎች ‹‹ተሃድሶ የማጥለቅ›› ትርጉም ሕዝብ የማገልገል ቃል ኪዳንን የማደስ ጉዳይ ብቻ ከሆነ፣ ይህ ከሌላው ዋና አንገብጋቢ ጉዳይ ይልቅና ይበልጥ በሕዝብ ተመራጭና ተከባሪ ለመሆንም ሆነ የተነሳውን ቁጣ ለማብረድ ብለው የሚያደርጉት ፓርቲያዊ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ነው ብለን ተስፋ ቆረጥን፡፡ የምንሻው ከኢሕአዴግ ፈቃድ፣ መሃላና ቁርጠኝነት ውጪ የሚኖር ዴሞክራሲ ነውና፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የኢሕአዴግ ተሃድሶ ማለት አይደለምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥያቄ እንዳፈጠጠ ይቆያል ብለን አዘንን፡፡ ኢሕአዴግ በዚያችው የራሱ ተሃድሶ ውስጥ ራሱን በመደበቅ ተወስኖ የሚቀር ከሆነ ችግር ነው ብለን ፈራን፡፡ በሌላም በኩል የሕዝብንና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተሳትፎና አመኔታ በቆነጠጠ መልክ ዴሞክራሲ የሚያሻቸውን የአውታራት ገለልተኝነት የማነፅ ሒደት ውስጥ ለመግባት ኢሕአዴግ የተግባር ቁርጠኝነት ካሳየ ደግሞ ድላችን ብዙ ነው ብለን ተስፋ አደረግን፡፡ በዚህም መካከል የአቶ ኃይለ ማርያምን ከሥልጣን መልቀቅ ውሳኔ ሰማን፡፡ ይህ ለእኔ የባሰ ያስፈራራል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የያዙት ዓይነት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን እንደ ንጉሡና እንደ ደርግ ጊዜ ተራ የሚኒስትር፣ የዋና ሚኒስትር፣ የሚኒስትሮች ሁሉ ሚኒስትር ተራ ሥልጣን አይደለም፡፡ የኢፌዴሪ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዋና የሥልጣን መገኛ ሥፍራ አድርጎ አቋቁሟል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ርዕሰ ብሔር ከመሆን በስተቀር በአገሪቱ አስተዳደርና ፖለቲካ ውስጥ ሥልጣን የለውም፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር በድንገት ሲሞትም፣ በድንገት ሥራ ሲለቅም የደነገጥነው፡፡

የአቶ መለስ ድንገተኛ ሞት ሁሉንም ስላስደነገጠና ‹‹ስላስማማ›› ተከታዩን ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጥ አሠራራችንና ሕጋችን ብዙም ሳይጋለጥ ሁሉንም ነገር እንደነገሩ ተወጣነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ሥራ የለቀቁት የሥራ ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ በመሆኑ፣ በዚህ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው የፓርቲ መተዳደሪያ ደንብና የአገር ሕግ ውስጥ ‹‹ስንኖር›› አላየንም፡፡ ያ ሁሉ የታኅሳስና የጥር ወር አምሳያ የሌለው የግምገማ መግለጫና ማብራሪያም ይህን መጪ ክስተት በጭራሽ አላመላከተንም፡፡

አቶ መለስና አቶ ኃይለ ማርያም በሥልጣን ዘመናቸው ሁለቱም ደጋግመው የሚሉት አንድ ‹‹አንቀጸ – እምነት›› ነበራቸው፡፡ ድርጅቴ በመደበኝ ቦታ እሠራለሁ፣ ሊስትሮ ሁን ቢለኝ እሆናለሁ የሚል፡፡ አቶ መለስን ፓርቲያቸው ተለዋጭ ምደባ ሳያደርግላቸው አለፉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያምን ሥራ ልቀቅ፣ የመፍሔው አካል ሁን ያላቸው ፓርቲያቸው ነው? የትኛው? ክልላዊው? አገራዊው? ይህ ሁሉ ሚስጥር ነው፡፡

ከዚህ በላይ የሚያሳስበው ደግሞ የዚሁ ተቀጥላ የሆነው የተተኪያቸውን አመራረጥ የሚመለከተው የፓርቲና የመንግሥት ሕግ ራሱ አሁንም ገና እና እንደገና የ‹‹እርስዎም ይሞከሩት›› የሁሉም መረባረቢያና መሻኮቻ ሆኖ ያልለየለት መሆኑ ነው፡፡ የአስኳቿይ ጊዜ ሁኔታ በታወጀበት፣ ‹‹ከአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ፈቃድ ውጪ በፀጥታ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል አካል ወይም ሌላ ኃይል ለሕዝብ ይፋ የሚሆን መግለጫ መስጠት የከተለከለ ነው›› የሚል ድንጋጌ የያዘ መመርያ በተነገረበት አገር፣ ፓርላማው ምንም እንዳልተፈጠረ ከጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ማግሥት ጀምሮ ዛሬም እረፍት ላይ ነው፡፡

ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲፀና የተደነገገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ መፅደቅ ስላለበት፣ ፓርላማው እረፍቱን አቋርጦ መጠራቱ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ፓርላማው በእረፍት የተቋረጠውን ሥራውን ሲጀምር ግን የአንድ ኢሕአዴግ ፓርላማ ሳይሆን የአራት ኢሕአዴጎች ሆኖ እንደሚታይ ከወዲሁ ምልክቶችና ጥርጣሬዎች፣ እንዲሁም ሥጋቶች አሉ፡፡ ከእረፍት የሚመለሰው ፓርላማ ‹‹ልዩነቶችን›› አቻችሎ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታውን ካፀደቀው ደግሞ ከዚህ በኋላ ሁለት ወራት የቀረው የ2010 ዓ.ም. የአካባቢ ምርጫ ከምንጊዜውም በባሰና የተቀባበለ ወጥመድ ባለበት ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ ከወዲሁ የተፈረደበት ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ reporter Amharic

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *