ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብቻውን መፍትሄ አያመጣም -አዲስ ዘመን

መንግሥት አገሪቱን ወደ ነበረችበት ሰላምና ፀጥታ ለመመለስ ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቅ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ይገኙበታል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የመፍትሄ አካል ለመሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው ለመነሳት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ እርምጃዎች ምን ያህል መፍትሄ ያመጣሉ?


ታራሚዎችን መፍታት፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸው የመነሳት ጥያቄም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  በራሳቸው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት ማምጣት ባይችሉም፤ እርምጃዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ መንግሥት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ከቀጠለ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
     በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ኑሩ መሀመድ፤ መንግሥት የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲል ታራሚዎችን መልቀቁ፣ ጠቅላይ 
ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው ለመነሳት ጥያቄ ማቅረባቸውም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ  አንድ እርምጃ ቢሆንም ብቻቸውን ግን ዘላቂ መፍትሄን ሊያረጋግጡ አይችሉም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው መነሳት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር በማድረግ በአገሪቱ ያለውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደቶች እንደሚያጎለብት የሚናገሩት አቶ ኑሩ ይህ በቀጣይም መለመድ እና መዳበር ያለበት ተግባር ነው ብለዋል፡፡  ሆኖም ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ የሚያነሳቸውን ዘርፈብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአግባቡ በመለየት መፍታት ይገባል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ተይዘው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች በምህረት መለቀቃቸው መንግሥት በአገሪቱ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው የሚያመለክቱ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ኑሩ ይህም ቢሆን ግን የመፍትሄው አንድ አካል እንጂ በራሱ መፍትሄ አይደለም ይላሉ፡፡ 
በሌላ በኩል ችግሮች ሲፈጠሩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም አሁን የታወጀው አዋጅ ግን ጊዜውን የጠበቀ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋነኛ አላማ የአገር ሰላምና ህልውና ማረጋገጥ፣ የዜጎች መብት እንዲከበር ማድረግ እና ሰላም ማስከበር ቢሆንም አዋጁ  አንዳንድ ከተሞች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ በህብረተሰቡ አዕምሮ ላይ ሌላ ስጋት ይፈጥራል ይላሉ፡፡  
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ገብረዮሐንስ፤ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎችን መፍታት፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መልቀቅና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ለውጥ ባያመጡም፤ ለታለመላቸው ጉዳይ መዋል ከቻሉ ግን በአገሪቱ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማምጣት ግብዓት እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡
እንደ መንግሥት መሪ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ በተለይ የሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ሲያጋጥም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ መውረድ አለብኝ ብለው መወሰናቸው ትክክል መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን አገሪቱ ያለችበት ችግር የሚፈታው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መውረድ ብቻ ሳይሆን በሚተካው ሰው ውሳኔና በኢህአዴግ  መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ ሰላምና መረጋጋት የሚመጣው አዲሱ መሪ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲችል ነው፡፡ 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዋናነት የሚያስፈልገው በመደበኛ መንገድ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ሲከብድ መንግሥት የሚያወጣው ሲሆን፤ አዋጁ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚችለው መንግሥት በተለመደው አሰራር እንዳይሰራ ያደረጉትን ጉዳዮች በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ በአግባቡ መፍታት ከቻለ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ይጠቅሳሉ፡፡ አለበለዚያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጠረውን ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ችግር ለመግታት እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚቀመጥ አለመሆኑን ያብራራሉ፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለመጠበቅ በተለይ በየደረጃው ያለውን አመራር አቅም ማጎልበትና ችግሮችም ከሥር ከሥሩ እየተፈቱ የሚሄዱበትን አግባብ መፍጠር ተገቢ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኑሩ አስፈፃሚ አካላት በሳይንስም ሆነ በተግባር አቅማቸው መጎልበት እስካልቻለ ድረስ የሰዎች መለዋወጥ መፍትሄ አይሆንም ባይ ናቸው፡፡  
በአገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በተደጋጋሚ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበር የሚያስታውሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን፤ መንግሥት ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎችን የፈታው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት አስቦ ከሆነ በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ግን በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣል በሚል ምክንያት ብቻ ከሆነ ግን ለውጥ እንደማይመጣ ያመለክታሉ፡፡
ታኀሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን ለሁሉም ሰፊ ለማድረግ  የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ አስታውቀዋል። ቀደም ሲል በወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ማረሚያ ቤት የቆዩና ፍርድ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ሰዎችም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንደሚፈቱ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት መንግሥት እያደረገ ባለው ጥረት የመፍትሄ አካል ለመሆን ከመንግሥትና ከድርጅት ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውንና መልቀቂያ ማስገባታቸውን የገለፁ ሲሆን የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ደግሞ ህገ መንግሥቱን ከአደጋ ለመከላከል በአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 
አሁን ባለው ሁኔታ በህዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዲፈጠር መሰረታዊ ለሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን ምሽ መስጠት ተገቢ ነው ያሉት አቶ ኑሩ ለዚህም ተተኪዎቹ መሪዎች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡አለበለዚያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሌላ የመብት ጥሰት ሊዳርግ እንደሚችልና በአዋጁ ስም  የመብት ጥሰቶች እንዳያጋጥሙ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል፣ብለዋል፡፡ 
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ገለፃ፤ በአገራችን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲሰፋ በማድረግ ልዩነቶችን ሊያስተናግድ የሚችል የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መፈጠር አለበት፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ካላደገና የዴሞክራሲ ተቋማት አቅም ካልተገነባ መንግሥት አመኔታ እያጣ ይመጣል፡፡ ተቃዋሚዎችም በተገፉ ቁጥር የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ይሄዳል ፡፡ አሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ በመሆናቸው የመንግሥት ቁርጠኝነት ከታከለባቸው የታለመውን ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ይቻላል፡፡

ዜና ትንታኔ
መርድ ክፍሉ

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል