ዶክተር አብይ አሕመድ አደባባይ ብቅ ባሉባቸው ጥቂት ግዚያት ውስጥ የአብዛኞችን ቀልብ ስለመሳባቸው ክርክር የለም። ንግግራቸው ብቻ ሳይሆን

politicsSS

ፎቶ ሪፖርተር

የሚያነሱዋቸው ሃሳቦችና ሃሳቦቻቸውን የሚያስደግፉባቸው መረጃዎች ” መጽሃፍ መጽሃፍ” እንደሚሸቱ ያስረዳል። ለዚህም ይመስላል ሰሚ አግኝተዋል።

በተቃራኒው ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል። የህወሃት አፍቃሪ አጀንዳ ቀራጮች በሳምንቱ መጨረሻ ዶ/ር አብይ አስቸኳይ አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው የኢህአዴግ ፓርላማ ላይ አለመገኘታቸው ሩጫቸውን እንደጨረሱ እንደሚቆጠር ጽፈዋል። ስብሰባውን መቅረታቸው የፖለቲካ ይቅርታ የማያሰጥ መንሸራጠት እንደሆነም አመልክተዋል።

በስፋት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከየድርጀቱ ሊቀመንበር ሆነው ከተሰየሙት መካከል ዶከተር አብይ በሁሉም መስክ የተሻሉ፣ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ የሚወክሉ፣ ኢትዮጵያዊ ስሜታቸውን በውብ ስብዕና መግለጽ የሚችሉ፣ በሁሉም ረገድ ሰፋ ያሉ፣ የለውጥ ሃይል ማስተባበር የሚችሉና በድርጅታቸው ኦህዴድ አዲስ መርሃ መሰረት በአገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ ማናቸውን ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ተቀምጠው መነጋገር የሚችሉ ስለመሆናቸው ነው።

የኦህዴድ ወቅታዊ ጉዞና አቋም ያልተመቸው ህወሃት፣ የአቶ ለማ መገረሳ ህዝባዊነትን የሚቀሰቅስ ንግግርና ድጋፍ ጋር ተዳምሮ በኦህዴድ ቤት የሚነፍሰው ንፋስ ያልተመቻቸው ዶክተር አብይን ለማናናቅ ሲሞክሩ ታይቷል። አቶ በረከት በስማቸው ያሰራጩት ጽሁፍ ዶክተር አብይ ላይ ከቀረቡት ሁሉ ለየት ያለ ሲሆን፣ የሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ያለመቀበል ስሜት ስለመኖሩ በግልጽ ያስረዳ ነው።

ምንም እንኳን ጽሁፉ የሳቸው እንዳልሆነ አቶ በረከት ቢናገሩም ጽሁፉ ከዛ ስለመውጣቱ የሚያምኑ እንዳሉት ” ህወሃት አብይ ላይ ፍሬን ይዟል” እናም ደመቀ መኮንን ወደ ፊት ገፍቷል። በዚሁ ዶክተር አብይን በሚያወግዘውና በሚያናንቀው የበረከት ጽሁፍ ደመቀ መኮንን ” የተፈተኑ” በሚል ጓዳዊና ካድሬያዊ መመጻደቂያ ቃል ተሞካሽተዋል።

የአስቸኳይ አዋጁ ከታወጀ በሁዋላ የጠቅላይ ሚኒስርነቱን ቦታ አስመልክቶ ኦህዴድን የመግፋት ሃስብ መጠናከሩን የሚያሳዩ ምልክቶች የታዩ ቢሆንም የዛሬው ለየት ያለ ሆኗል። ሁለት የተለያዩ መረጃዎችን በሳምንት ጊዜ ውስጥ ያስነበበው ሪፖርተር ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህወሃት ሰውን ጥቀሶ ደብረጽዮን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚወዳደሩ ይፋ አድርጓል። ባለፈው ሳምንት ጋዜጣው ህወሃት ከውድድሩ ውጪ መሆኑን ጋዜጣው ማስነበቡ የሚታወስ ነው። 

ያኔ ጥንት መለስ ” ሲሰው” / ሞቱ ላለማለት ነው/ ድንገት ወደፊት የመጡትን ዶክተር ደብረጽዮንን ያለመና ያሰበ አልነበረም። ጎልጉል የተባለው የድረ ገጽ ጋዜጣ ደብረጽዮን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ የጻፈው በመለስ “መሰዋት” ማግስት ነበር። በውዝግብ እና በጌቶች ጫና አቶ ሃይለማሪያም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ሲወሰን አገሪቱ በቡድን እንደትመራ በቀረበው መሰረት ከአራቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስሮች መካከል ደብረጽዮን ዋናውን የኢኮኖሚ ቁልፍ ስልጣን የያዙት እሳቸው ነበሩ። 

ደብረጽዮን በኢህአዴግ ውስጥ ያላቸው ጣላ፣ በደህንነቱ ተቋም ውስጥ ያላቸው መዳፍ የገዘፈ ስለመሆኑ ያተተው ጎልጉል ” ስውሩ ሰው” ሲል ነበር የገለጻቸው። ይህንኑ በሚመሰከር መልኩ እሳቸውም ከመለስ ሞት በሁዋላ የኢህአዴግ ” አብሪ ኮከብ፣ የህወሃት ማራዶና” በሆናቸውን አረጋገጡ። በሁሉም ቦታ እሳቸው ሆኑ። 

ዛሬ የመፍትሄው አካል ለመሆን በሚል ደርዙ በማይገባ ምክንያት ስልጣናቸውን በቀጠሮ ለመልቀቅ መወሰናቸውን ይፋ ያደረጉት አቶ ሃይለማሪያምን ለመተካት በተጀመረው የድርጅት የውስጥ ትርምስ የደብረጽዮን አመጣጥ አቶ መለስ “ሲሰዉ” ለምን ህወሃት ዳግም አልተመረጠም ለሚሉት አኩራፊዎች መልስ ለመስጠት ፣ ወይም ህወሃት ቦታውን አይፈልገውም የሚለው ገለጻ የህወሃትን ፋይዳ አሳንሶ የሚያሳይ በመሆኑ ባይመረጡም ተሳታፊነታቸውን በማጉላት የስነ ልቦና ማመጣጠን ለማከናወን ይመስላል።

ከዚህ ውጪ ግን የምርጫ ውዝግቡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ማዕከላዊ ሚዛኑ የሚጥብቅበት ቡሎን መላሸቁ / ስፓናቶ/ ለመሆኑ ማስረጃ አድርገው የሚወስዱ ያሉትን ያህል፣ አሁን የታየው ያለው የምርጫ ውዝግብ ጤነኛ ሲስተም ቢኖር ፍላጎትን የመግለጽ ከመሆኑም በላይ የመለስን ዲክታተርነት የሚያሳይ እንደሆነም የሚጠቁም አልታጡም። የመለስን ሌጋሲ እናስቀጥላለን የሚሉት ወገኖች ዛሬ ላይ መለስ የቀበሩት የቦንብ አይነቶች እየፈነዳዱ ሲያቃጥሉን በይፋ ይቅርታ በጠየቁ ነበር ሲሉም ሃሳብ የሰጡ አሉ።

ሪፖርተር ስለደብረጽዮን ተወዳዳሪነት የሚከተለውን ዘግቧል።

አራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚወዳደሩ ታወቀ፡፡

አራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ማለትም የሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቃነ መናብርት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚደረገው ውድድር እንደሚሳተፉ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቅርቡ የኦሕዴድ ሊቀመንበር የሆኑት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኰንን እና የደኢሕዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ  ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ግምት የተሰጣቸው እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው እንደሚቀርቡ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣  ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ይወዳደራሉ፡፡  ከዚህ በፊት በኢሕአዴግ ምክር ቤት ይሁንታ በማግኘት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሕወሓት ተመርጦ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም በምክር ቤቱ ይሁንታ ከተገኘ ለኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚወዳደሩ አመራሩ ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ መረጃዎች የሕወሓት ሊቀመንበር ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደማይወዳደሩ ሲናገሩ ቢሰማም፣ ‹‹የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ሐሳብ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሕወሓት ዕድሉን ካገኘ ሊቀመንበሩን በዕጩነት ከማቅረብ የሚያግደው ነገር የለም፤›› ሲሉ አመራሩ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትርነትና ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ለመነሳት ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች  ሊቃነ መናብርት በዕጩነት እንደሚቀርቡ ይታወቃል፡፡

ለኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ለአገሪቱ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከፍተኛ ተወዳዳሪ ለመሆን አዲስ ሊቀመንበር የመረጠው ኦሕዴድ፣ ከዚህ በፊት የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳን አንድ ደረጃ ዝቅ በማድረግ ዶ/ር ዓብይን በሊቀመንበርነት መምረጡ አይዘነጋም፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ ጀምሮ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ ሚዲያዎች እሳቸው ይሆናሉ በማለት፣ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀሱ ሲዘግቡ ነበር፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንድ ወር ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ አቶ ደመቀን በሊቀመንበርነት እንዲቀጥሉ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርና የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ይሆናሉ የሚል ግምት እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡

ለአገሪቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ግምት የተሰጣቸው ሌላው ዕጩ አቶ ሽፈራው ሲሆኑ፣ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ24 ቀናት ባደረገው ስብሰባ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧቸዋል፡፡

አቶ ሽፈራው ከዚህ በፊት የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበርና የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አቶ ኃይለ ማርያም ከኃላፊነት ለመነሳት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ለተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይወዳደራሉ ተብሎ ብዙም ግምት ሲሰጣቸው ባይሰማም፣ በዕጩነት እንደሚቀርቡ ግን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፎቶ ክሬዲት ሪፖርተር

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *