አገሪቱ ከሁለት ዓመታት በላይ የገባችበት የቀውስ አዙሪት፣ በተለያዩ ገጽታዎች የተለያዩ ክስተቶችን እያስተናገደ ነው፡፡ የወቅቱን ፈታኝነት በሥጋት የሚመለከቱ ያሉትን ያህል፣ ከሥጋት ባሻገር የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለው ተስፋ የሚያደርጉም አሉ፡፡ ወቅቱ ያረገዘው ሥጋት ፈተናውን እንዳከበደው እርግጥ ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ ግን አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያላጋጠማት ፈተና፣ ያላየችው መከራና ሥቃይ የለም፡፡ አገርን ሊወሩ ከመጡ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች፣ እስከ ውስጣዊ የሥልጣን ትግልና ትንቅንቅ በርካታ ጦርነቶችና ግጭቶች ተካሂደውባታል፡፡ ለማመን የሚከብዱ ፈተናዎችን በቆራጥና በአይበገሬ ልጆቿ አማካይነት መጋፈጥ የቻለችው ይህች ታሪካዊ አገር፣ በአሁኑ ትውልድም እውነተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት አያቅታትም፡፡

ሰው ሠራሽ ችግሮችን በመግባባት ለማቃለል ወይም ለማስወገድ የሚቻለው ከምንም ነገር በላይ ቅንነት ሲኖር ነው፡፡ በተለይ ለአገርና ለሕዝብ ዘላቂ ህልውና ሲባል ቅን መሆን ከባዱን ፈተና ለማለፍ ይጠቅማል፡፡ ቅንነት እየጠፋ መካረርና ለመጠፋፋት መፈላለግም ሆነ፣ ለፋይዳ ቢስ እልህና ግትርነት ሰፊ ጊዜ መስጠት የሚጎዳው አገርን ነው፡፡ በጥበብና በብልኃት ክፉ ጊዜን መሻገር መቻል ሲቻል አገርን ችግር ውስጥ መክተት አይገባም፡፡

ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በዋነኝነት የፖለቲካ ሥልጣን ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ያለ ማንኛውም አካል የመጨረሻ ግቡ ሥልጣን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሥልጣን ለማን ጥቅም የሚለው ጉዳይ ግን ትኩረት ማግኘት አለበት፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር ካልተደገፈ ከባድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ በዝግ በር የሚካሄደው ውይይትም ይባል ንትርክ፣ ሕዝብን ማዕከል ካላደረገ ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚመራ መሆኑ ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ አገሪቱ የገጠማትን ፈተና በብልኃት ማሳለፍ የሚችል መሪ ለመሰየም ቅንነት ያስፈጋል፡፡ ይህ ቅንነት ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ ሕዝባዊነት የሚለካው ስለተናገሩት ሳይሆን በተግባር ሲኖሩበት ነው፡፡ እንኳንስ በርካታ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በነበረበት ወቅትም ሕዝብን ማዳመጥ አለመቻል ያደረሰውን ቀውስ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ያለፉት ትውልዶች በአርቆ አሳቢነትና በአስተዋይነት ተሻግረዋቸው ያለፉዋቸውን ፈተናዎች የሚገነዘበው የዘመኑ ትውልድ፣ ከአያቶቹና ከቅድመ አያቶቹ ልምድ ካልቀሰመ የመማሩ ፋይዳ ምንድነው? ችግሮች ሲያጋጥሙ እየተንደረደሩ ወደ ግጭትና ቀውስ ከመግባት ይልቅ፣ ለአገር ህልውና ሲባል በሰላማዊ መንገድ መፍታት ለምን ያቅታል ብሎ መጠየቅ እንዴት ይቸግራል? ችግሮችን ብቻ በማራገብ ሕዝብን ከማሳቀቅና አገርን ከማተራመስ አንዲት ቅንጣት የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቦ እንነጋገርበት ማለት ማንን ገደለ? ትልቁ አበሳ የቅንነት መጥፋት ነው፡፡ ቅንነት በሌለበት እንዴትስ መነጋገር ይቻላል?

ኢትዮጵያ በታላቁ የዓድዋ ድል ምክንያት የአፍሪካ ብሎም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት እንዳልተባለች፣ ለአፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያ እንዳልሆነች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴዋ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት እንዳልሳበች፣ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖባት የመረጋጋት ማጣቀሻ እንዳልነበረች ዕድሜ ልኩን በማያድገው ፖለቲካዋ ምክንያት የኋልዮሽ ጉዞ መጀመሯ ቅን ዜጎቿን ያሳስባል፡፡ የአስተዋዩ ሕዝብ የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች እየተናዱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በየቦታው ሲፈጸሙ ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝተነት ኮስምኖ አካባቢያዊ ማንነቶች እየፈረጠሙ የሕዝቡ የጋራ እሴቶች ዋጋ ቢስ ሲሆኑ ያስከፋል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን በብሔር መነጽር ብቻ እየታየ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሲገፉ ማየትም ያንገሸግሻል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ አዙሪት ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡ ይቻላልም፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ለአገር ህልውና በቅንነት ማሰብ ግድ ይላል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዙም ሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች እልህና ቁጣ ከቀላቀለበት አሰልቺ ንትርክ ወጥተው፣ ሕዝብ የሚፈልገውን ለማሳካት በቅንነት መነጋገር አለባቸው፡፡

ለአንድ አገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መግባት ከባድ ነው፡፡ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሰላም ማስፈን ካልተቻለ አገር የሚመራው መንግሥት ከባድ ችግር ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ የቀውሱ ትክክለኛ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ እንኳን መግባባት አልተቻለም፡፡ በየቦታው የታዩት ተቃውሞዎች የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ የንግድ መደብሮች፣ መሥሪያ ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ባንኮች፣ ወዘተ ሲዘጉና የሕዝብም ሆኑ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቶች ሲቋረጡ በዜጎችም ሆነ በኢኮኖሚው ላይ ከባድ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ሌላው ቀርቶ ወትሮም በችግር የሚማቅቁ በዕለት ገቢ ብቻ የሚተዳደሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ይራባሉ፡፡ በአዋጁ መሠረት ሕግ የማስከበር ሥራ ሲጀመር ደግሞ በሚፈጠር ውዝግብ የሚደርሰው አደጋ ያሳስባል፡፡ መነጋገርና የጋራ መግባባት መፍጠር ልማድ ባልሆነበት አገር ውስጥ፣ መሪው የማይታወቅ ተቃውሞ ያደረሰውን ጉዳይ ከበቂ በላይ ማየት ተችሏል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከችግሮች ተምሮ የተሻለ ነገር ለማምጣት አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚጠቀምባቸውን የመፍትሔ ማፈላለጊያ ዘዴዎች መዋስ እንኳ አልተቻለም፡፡ በሕዝቡ ውስጥ እንደ ብሔሩ፣ እምነቱና ባህሉ በርካታ ችግር መፍቺያ ዘዴዎች አሉ፡፡ እነዚህን አገር በቀል ዕውቀቶች ገሸሽ በማድረግ በየተገኘው የመገናኛ ዘዴ ማላዘን ለአገር አይጠቅምም፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› እንዲሉ፣ ቅንነት በመጥፋቱ ብቻ የንፁኃን ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል፣ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ ይህም ያሳዝናል፡፡

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደሞከርነው ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ከሕዝብ በላይ ምንም የሚቀድም የለም፡፡፡ ሕዝብ ደስ የሚለው አገሩ ሰላም ስትሆንለት ነው፡፡ ስትበለፅግለት ነው፡፡ ዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብቶቹ ተከብረው በአገሩ ጉዳይ ዋነኛ ባለቤት ሲሆን ነው፡፡ ሰላሙ እየተናጋ፣ ደኅንነቱ አደጋ ውስጥ እየገባ፣ በስንት ትግል የሚያኖረው ሕይወቱ እየተመሰቃቀለ የአገሩ ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ ሲሆንበት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ጊዜያዊና ኃላፊ እንዲሆኑ ሕዝቡ ውስጥ ያሉ እሴቶች ሊከበሩ ይገባል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት፣ በቀቢፀ ተስፋ መላምቶች ወጣቶችን ለጥፋት ማሠማራት፣ ከመቀራረብ ይልቅ እልህ ውስጥ የሚከቱ አጉል ድርጊቶችን መፈጸምና አገርን የባሰ ቀውስ ውስጥ የሚዘፍቁ እኩይ ተግባሮችን በፍጥነት ማቆም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለዓመታት ተሞክረው ያልተሳኩ ፍጥጫዎችንና ግጭቶችን በማበረታታት የተጠመዱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ በዚህ መንገድ ሥልጣን ይገኛል ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል፡፡ ሞኝ ይመስል ከስህተት አለመማር ደግሞ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ንፁኃንን እያስፈጁ ለስታትስቲክስ ማሟያ ማድረግ ወንጀል ነው፡፡ ቅንነት ከጎደለው አዕምሮ የሚጠበቅ ስለሆነም ለአገር ህልውና አይጠቅምም፡፡

አሁንም በኢትዮጵያ ለመሠረታዊ ለውጥ የሚያግዙ አቅም ያላቸው ዜጎች በአገር ውስጥም በውጭም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አቅም ጥበብን ከብልኃት ጋር አዛምደው ሲጠቀሙበት ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ በመጀመርያ አገር ለምትባለው የጋራ ቤት ማሰብ፣ አርዓያነት ያለው ሥነ ምግባር መላበስ፣ ለዴሞክራሲ መሠረታዊ እሴቶች ዋጋ መስጠት፣ ከአድልኦ አስተሳሰብ በመላቀቅ ሰብዓዊ ፍጡራንን እኩል ማስተናገድ፣ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል እውነተኛውና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ማግኛ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ማመን፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከልብ መሥራት፣ ከአመፃና ከውድመት ድርጊቶች መታቀብ፣ ሕዝብን ማክበርና ለፈቃዱ መታዘዝ ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ይህ ምኞት የሚሳካው ግን በዋዛ አይደለም፡፡ በበርካታ አደናቃፊ ችግሮች የተከበበ ነው፡፡ ሆኖም ለአገር ማሰብ ከተቻለ ከፀሐይ በታች የማይቻል ነገር የለም፡፡ መሰሪነትና ሴረኝነት በተፀናወተው ፖለቲካችን ለቅንነት አንድ ስንዝር ቢገኝለት ይኼ ከባድ ወቅት በጥበብ ይታለፋል፡፡፡ ቅንነት በስፋትና በጥልቀት ሲናኝ ደግሞ ኢትዮጵያ አገራችን አንገቷን ካስደፋት ቀውስ ውስጥ በፍጥነት ትወጣለች፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ያለው ሕዝባችን ደስ ብሎት በነፃነት እንዲኖር በቅንነት መነሳት የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ፈተናው ከባድ ቢሆንም 

የሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ ነው 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *