ስቴፈን ሊቪትሰኪና ሉካን ኤ ዌይ “The Myth of Democratic Recession” በተሰኘ ጥናታቸው የኮሙዩኒስት ሥርዓትን የተሸከመችው መርከብ መናወጥ ስትጀምር፣ በርካታ አምባገነኖች ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ምዕራቡ ዓለም ሊበራል ዴሞክራሲ ራሳቸውን ወረወሩ ይላሉ፡፡ ለሁለቱ ምሁራን ይህ ዓይነቱ ያልታሰበበት ‹እግሬ አውጪኝ› በሁለት ገፊ ምክንያቶች የመጣ ነው፡፡ የመጀመርያው የሶቪየት ኅብረትን መፈራረስ ተከትሎ በርካታ የታዳጊ አገሮች አምባገንን መሪዎችን የገንዘብ ችግር መግጠሙ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ ባልጠበቁት ፍጥነት እየከነፈ ከደጃፋቸው መድረሱ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በርካታ ምሁራን ዓለም ከዚህ በኋላ ከዴሞክራሲ ውጪ ከሌላ ርዕዮተ ዓለም ጋር የመቀላቀል ዕድል አይኖራትም ሲሉ መጻፋቸውን ተያያዙ፡፡ የፖለቲካው ዓለም አዳኝም ገዳይም ሊበራል ዴሞክራሲ ብቻ ነው የሚል ትርክትን በየቦታው ለፈፉ፡፡ ፍራንሲስ ፉኩያም የታሪክ መጨረሻና የመጨረሻው ሰው በተሰኘው መጽሐፉ ይህንኑ እውነት ለዓለም አረጋገጠ፡፡

በይናገር ጌታቸው

ፌርማታው ያልታወቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ከፊሉ ወገን ገዥው ፓርቲ አከርካሪው ተሰብሯል፣ ከዚህ በኋላም ድጋሚ ሊያንሰራራ አይችልም የሚል ሐሳብ ሲሰነዝር የቀረው ኃይል መሪ አልባው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከሰፌድ ላይ ሩጫነት የዘለለ ሚና የለውም ሲል ይተነትናል፡፡ ከሁለቱ ጎራ በተለየ መንገድ የሚያዘግመው ሌላኛው ወገን ደግሞ አሁን ያለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የትኛውንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚበትን ነው ሲል ይደመጣል፡፡

 እነዚህ መላምቶች ሁሉም ሰው ከቆመበት የፖለቲካ አስተሳሰብ አንፃር ከተመለከታቸው የሚያስኬዱ ቢሆንም፣ የጋራ እውነት የመሆን አቅም ግን አይኖራቸውም፡፡ ከዚህ በመነሳት ከላይ የቀረበውን የነገዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ እሳቤ በጥያቄ ለመፈተሽ እንሞክር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄያችን መደላድል የሚሆነን ግን አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አለ፡፡ ኢሕአዴግ ምን ዓይነት መንግሥታዊ ሥርዓት ነው?  ለጥያቄው የምንሰጠው ምላሽ የነገዋን ኢትዮጵያ ምሥል በደብዛዛውም ቢሆን የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡

የደበዘዘውን እውነት ለማጥራት ግን አሁንም ሌሎች ጥያቄዎችን እናስከትል፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ ጥያቄ ምንድነው? የነገው ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ፈተና ይገጥመዋል? የወቅቱስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ፌርማታው የት ነው?

የመንደሪን ፖለቲካዊ ጨዋታ በኢሕአዴግ ቤት

ስቴፈን ሊቪትሰኪና ሉካን ኤ ዌይ “The Myth of Democratic Recession” በተሰኘ ጥናታቸው የኮሙዩኒስት ሥርዓትን የተሸከመችው መርከብ መናወጥ ስትጀምር፣ በርካታ አምባገነኖች ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ምዕራቡ ዓለም ሊበራል ዴሞክራሲ ራሳቸውን ወረወሩ ይላሉ፡፡ ለሁለቱ ምሁራን ይህ ዓይነቱ ያልታሰበበት ‹እግሬ አውጪኝ› በሁለት ገፊ ምክንያቶች የመጣ ነው፡፡ የመጀመርያው የሶቪየት ኅብረትን መፈራረስ ተከትሎ በርካታ የታዳጊ አገሮች አምባገንን መሪዎችን የገንዘብ ችግር መግጠሙ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ ባልጠበቁት ፍጥነት እየከነፈ ከደጃፋቸው መድረሱ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በርካታ ምሁራን ዓለም ከዚህ በኋላ ከዴሞክራሲ ውጪ ከሌላ ርዕዮተ ዓለም ጋር የመቀላቀል ዕድል አይኖራትም ሲሉ መጻፋቸውን ተያያዙ፡፡ የፖለቲካው ዓለም አዳኝም ገዳይም ሊበራል ዴሞክራሲ ብቻ ነው የሚል ትርክትን በየቦታው ለፈፉ፡፡ ፍራንሲስ ፉኩያም የታሪክ መጨረሻና የመጨረሻው ሰው በተሰኘው መጽሐፉ ይህንኑ እውነት ለዓለም አረጋገጠ፡፡

እንዲህ ያለውን የፖለቲካ ትንበያ ስህተትነት ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው በሁለት መንገድ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ የመጀመርው ብዙ የዓለማችን ምሁራን ከአምባገንን ሥርዓት በኋላ ሌላ አምባገነን ሥርዓት አይፈጠርም ብለው ማሰባቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው አምባገነን ሥርዓቶች ሳይወዱ በግድ በጊዜው ብቸኛ ልዕለ ኃያል ከሆነችው አሜሪካ ለመሻረክ ከዴሞክራሲ የተሻለ አማራጭ የላቸውም ብለው ማሰባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የዓለም ፖለቲካ በታሰበው ሳይሆን ባልታሰበው ቦይ ፈሰሰ፡፡ ኢራን አብዮት አካሂዳ ከሌላ አምባገነን መሪ ጋር ተዋወቀች፡፡ የቅርብ ጊዜ ምሳሌዋ ሊቢያም አምባገነን መሪን ሸኝታ ከብተና ደጃፍ ደረሰች፡፡ በዚህ የተነሳም የዓለም ፖለቲካ አዲስ መልክ መያዙ ተረጋገጠ፡፡

 ለሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲው የመንግሥት አስተዳደር ፕሮፌሰር ሊቪትሰኪና ለቶሮንቶው ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ኤ ዌይ ትንቢቱ ላለመሳካቱ በቂ ገፊ ምክንያት ነበረ ይላሉ፡፡ ይህ ገፊ ምክንያት አንድም በተለያዩ አገሮች ያሉ አምባገነን ሥርዓቶች የድኅረ ኮሙዩኒዝምን ዓለም መላመዳቸው ሲሆን፣ አንድም ዓለም በፍጥነት ከአንድ ልዕለ ኃያል ወደ ብዙ ልዕለ ኃያሎች መቀየሯ ነበር፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ደግሞ በርካታ አምባገነን መሪዎች የራሳቸውን የዴሞክራሲ ፍኖት እንዲያበጁ ዕድል ሰጧቸው፡፡ በበሰበሰው የአምባገንን ሥርዓቶች ፍግ ላይ የተዘራው የሊበራል ዴሞክራሲም የራሱን መልክ ይዞ በቀለ፡፡ የመንደሪን አምሳያው ይህ አዲሱ ሥርዓት ሎሚ ነው ሲሉት፣ ብርቱካን ብርቱካን ነው ሲሉት፣ የሎሚ ጣዕም እየሰጠ ድንበር ታጣለት፡፡ ከፊል አምባገነናዊ ከፊል ዴሞክራሲያዊ የሆነው አዲሱ ዲቃላ የዓለም ፖለቲካ መንገድ ብዙዎች ባልጠበቁት መንገድ በተለያዩ አገሮች በፍጥት ተዛመተ፡፡

ወቅትን ጠብቀው ምርጫ በማካሄድ የሥልጣን ዘመንን ማደላደልም ለብዙ አምባገነኖች የአደጋ ጊዜ መንሳፈፊያ ሆናቸው፡፡ እንዲህ ያለውን አዲስ መንግሥታዊ ሥርዓት ላሪይ ዲያምንድ “Election without Democracy” በተሰኘ ጥናቱ የይስሙላ ዴሞክራሲ (Pseudo Democracy) ብሎ ሲጠራው፣ ስቴፈን ሊቪትሰኪና ሉካን ኤ ዌይ ደግሞ ተወዳዳሪ አምባገነናዊ ሥርዓት (Competitive Authoritrianism) ብለው ሰይመውታል (ይህ ስያሜ ብዙ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተወዳዳሪ አምባገነናዊ ሥርዓት ቅይጥ ሥርዓቶች ከመምጣታቸው በፊት የነበረ በመሆኑ ነው)፡፡ ፋሪድ ዘካርያ “The Rise of Iliberal Democracy” በተባለ ጥናቱ በአንፃሩ እንዲህ ያለውን ቅይጥ መንግሥታዊ ሥርዓት ኢሊበራል ዴሞክራሲ ሲል ይጠራዋል፡፡ ይህን ቅይጥ ሥርዓት ከዚህ በፊት ባቀረብኩት ጽሑፌ ላይ እኔም ሐሳዌ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚል ስያሜ መስጠቴ ይታወሳል፡፡ ሐሳዌ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ፍትሐዊ ምርጫን ማካሄድ፣ በሰባዓዊ መብቶች አያያዝና የዴሞክራሲ ምኅዳርን ማስፋት በሚሉት መሥፈርቶች ከተመዘኑ ቢያንስ በአንዱ የሚወድቁ ናቸው፡፡ በዚህ ሥርዓት የተቃኙ አገሮች ሁሉም ማለት ይቻላል በቀደመው ዘመን የኮሙዩኒዝም ተከታይ የነበሩ በመሆናቸው፣ ለብዙ ምሁራን ሐሳዌ ዴሞክራሲ ወደ መደበኛው ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ጉዞ የጀመሩ አገሮች መለያ ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ ነገር ግን የተጠበቀው ሳይሆን ቀረ፡፡

ኢትሀን ቢ. ካፒስተንና ናታን ኮንቨርስ “Why Democracy is fail?” በተባለ ጥናታቸው ላይ ቅይጥ መንግሥታት ወደ ዴሞክራሲ ጉዞ የጀመሩ ሥርዓቶች ሳይሆኑ፣ ራሳቸውን የቻሉ ሥርዓቶች መሆናቸውን ይሞግታሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሙግታቸውም በአኃዝ የተደገፈ ሆኖ ከ46 ያህሉ ምርጫ ከሚያካሂዱ የአፍሪካ አገሮች፣ 26 ያህሉ የዚህ ማሳያ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ካየንም ከዚህ የሚርቅ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ አስኳል የነበረው ሕወሓት እስከ 1981 ዓ.ም. ድረስ በይፋ የኮሙዩኒዝም ሥርዓትን ይደግፍ የነበረ ሲሆን፣ የዓለም ፖለቲካ አሠላለፍ መቀያየር አስገድዶት ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ እሳቤ መንደርደር ጀመረ፡፡ ገብሩ አሥራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በተባለ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ሕወሓት በተለይም ሊቀመንበሩ አቶ መለስ ዜናዊ በወርኃ መጋቢት 1982 ዓ.ም. አሜሪካ ደርሰው ከመጡ በኋላ በየአቡጀዲው የተጻፈው የኮሙዩኒዝም መፈክር እየተሰበሰበ ተደበቀ፡፡

ከሲአይኤው ፖል ሔንዝ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተማሪነቴ ዘመን ካልሆነ ማርክሲዝምን አድንቄ አላውቅም ብለው ዓይናቸውን በጨው ታጥበው የተሟገቱት አቶ መለስ፣ አገራቸው ሲመለሱ የተሳፈሩበት የኮሙዩኒዝም ፖለቲካ ርዕዮት የትም እንደማያደርሳቸው እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ላደጉበት ርዕዮት ባሪያ በመሆናቸው ግን ኮሙዩኒዝምን መጥፊያዬ ነው ብለው አሽቀንጥረው አልጣሉትም፡፡ ይልቁኑም በልባቸው ላይ የኮሙዩኒዝምን ርዕዮተ ዓለም ነስንሰው ከላዩ ላይ ዴሞክራሲን ዘሩበት፡፡ የዚህ ውጤትም በሌላው ዓለም እንደተለመደው ኢሕአዴግን የሐሳዌ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት አደረገው፡፡ የኢሕአዴግ መንታ ልብ ዓመታት መጥተው ዓመታት ቢሄዱም የሚሸነፍ አልሆነም፡፡ ኢትሀን ቢ. ካፒስተንና ናታን ኮንቨርስ  እንደገለጹት፣ ቅይጥ የሆነው ኢሕአዴግ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመለወጥ ይልቅ በራሱ መንገድ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከአዲሱ ዴሞክራሲ ባህል በተዋሰው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ እየተጓዘም ፌዴራሊዝሙን ተገበረ፡፡ የፓርላማ አብላጫ ወንበር አሸንፎ መንግሥት ሲመሠርትም በዚህ የፓርቲው ዓመል የተለየ ሐሳብን ማንሳት ነውር እየሆነ መጣ፡፡ ሊበራል ሕገ መንግሥት ቢያወጣም በመንታ ልቡ የተነሳ የታሰበውን ያህል የፖለቲካ ነፃነት ታጣ፡፡

ኢሕአዴግ ቅይጥ ሥርዓትን እንደመከተሉ መጠን የምዕራቡ ዓለም የዴሞክራሲ መሠረቶችንም ለመተግበር ሞከረ፡፡ ለመገናኛ ብዙኃን ሳንሱርን በማስቀረት የመጫወቻ ሜዳውን አሰፋ፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም በየፊናቸው ከኢሕአዴግ ጋር በምርጫ ለመወዳደር ጉዞ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን የሥርዓት ለውጥን የሚፈጥር ምርጫ በዚህች አገር ሳይከናወን አዕላፍ ዓመታት አለፉ፡፡ እዚህ ላይ ሌላ ተቃርኖ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎቹ ቅይጥ ሥርዓትን የተከተሉ መንግሥታት የኢሕአዴግን ያህል ጊዜ በሥልጣን ላይ ለመዝለቅ አልቻሉም፡፡ ኢትሀን ቢ. ካፒስተንና ናታን ኮንቨርስ  እንደሚሉት 68 በመቶ የሚሆኑት ቅይጥ መንግሥታት በመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት ወደ ዓመድነት ከስመዋል፡፡ በሰፊው ከተመለከትነውም 83 በመቶ የሚሆኑት ቅይጥ መንግሥታት ከአሥር ዓመት በላይ መዝለቅ ተስኗቸው ወድቀዋል፡፡

ከእነዚህ እውነቶች አንፃር ከተመለከትነው ኢሕአዴግ ከብዙዎቹ ቅይጥ መንግሥታት በተለየ ለበርካታ ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየ ፓርቲ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ኢሕአዴግ ከበርካታ ሥርዓቶች በተለየ ለ27 ዓመታት በሥልጣን ላይ የመቆየቱ ሚስጥር ምንድነው? (እነዚህ ጥያቄዎች ለሰፊ ምርምር የሚጋብዙ በመሆናቸው በሌላ ጽሑፍ በስፋት ብመለስባቸው የተሻለ ይመስለኛል)፡፡ ለዚህ አጭር ጽሑፍ መሸጋገሪያ እንዲሆነን ግን ትኩረታችንን አንድ ነገር ላይ እናሳርፍ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኙ አሌክስ ዲወል (ፕሮፌሰር) እ.ኤ.አ በ2015 ለንባብ ባበቃው “The Real Politics of the Horn of Africa” መጽሐፉ አደጋ ባንዣበበት ምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በሰላም የመኖሯ ሚስጥር የአቶ መለስ የፖለቲካ አመራር ውጤት ነው ይላል፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በውሉ የሚተነትነው ክርስቶፈር ክላፋምም (ፕሮፌሰር) እ.ኤ.አ. በ2017 ለንባብ ባበቀው “The Horn of Africa” ሥራው ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ የመዝለቁ ሚስጥር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለመሆናቸው ይተርክልናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ከብዙ በጥቂቱ ኢሕአዴግን ከሌሎች ቅይጥ መንግሥታት በተለየ ሁኔታ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ በማድረጉ በኩል፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድርሻ የጎላ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኙ አሌክስ ዲወል ኢሕአዴግ የከበደው የቤት ሥራው አቶ መለስን ማጣቱ ነው የሚለውም ለዚህ ነው፡፡ አቶ መለስን ማጣቱ ብቻውን ግን የኢሕአዴግ መንሸራተት ጉዞው ማሳያ አይደለም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ወዳጅ የነበረው ፕሮፌሰር ዲወል እንደሚነግረን ራሳቸው አቶ መለስ ኢሕአዴግ የቁልቁለት ጉዞ እንደገጠመው ተረድተው ነበር፡፡

የመጨረሻው መጀመርያ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከማለፋቸው ሦስት ወራት በፊት በነበረ የፓርቲው ፖሊሲ ቢሮ ስብሰባ ላይ አቶ መለስ የነገው ኢሕአዴግ አደጋ ውስጥ ስለመሆኑ በግልጽ ተናግረው እንደነበረ አሌክስ ዲወል በመጽሐፋቸው አብራርተዋል፡፡ ትክክለኛ የልማት ስትራቴጂዎችን ነድፈን እየተንቀሳቀስን ቢሆንም፣ የታሰበውን ያህል ግን አልተጓዝንም የሚለው የአቶ መለስ ሐሳብ በዋናነት የስትራቴጅካዊ አመራር ዕጦት የፓርቲው የወደፊት ሥጋት መሆኑን የለየ ነበር፡፡  ፕሮፌሰር ዲወል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ኢሕአዴግ የስትራቴጅካዊ አመራር ችግር ገጥሞታል የሚለውን አስተያየት ሲሰነዝሩ ሁለት ማሳያዎችን ማቅረባቸውን ይተርካሉ፡፡ የመጀመርያው ፓርቲው የራሱ ሐሳብ አመንጪዎች የሌሉት በመሆኑ እየመከነ ሄዷል የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው የኢሕአዴግ አባላት በራሳቸው የችግር ምንጭ ወደ መሆን እየተሸጋገሩ መጥተዋል የሚል ነበር፡፡ ለእነዚህ ሁለት ሥጋቶችም ኢሕአዴግም ሆነ አመራሩ በፍጥነት መፍትሔ ነው ያለውን አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ አሳስበዋል፡፡

አቶ መለስ ሕልፈታቸውን የሚያውቁ በሚመስል መልኩ ስለነገው ፓርቲያቸው መሠረታዊ ችግር ይህን ተናግረው በሕይወት መቆየት የቻሉት ለሦስት ወራት ብቻ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ኢሕአዴግ ከሕመሙ ጋር ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ኢሕአዴግ የሚተማምንባቸውን የልማት ስትራቴጂዎች የጫነው መኪና ካለአሽከርካሪ ወደፊት ገሠገሠ፡፡ አንድና ሁለት ዓመታትን በተለመደው መንገድ ቢጓዝም ከዚያ በኋላ ግን ፍጥነቱን ቀነሰ፡፡ ኢሕአዴግ የህልውናዬ ምንጭ ልማትና ዴሞክራሲ ነው ቢልም አሽከርካሪ የሌለው መኪናው ግና ከልማቱ ጋር መጋጨት ጀመረ፡፡ ልማት እየተገታ ሲመጣ አገራዊ ናዳው ይበልጥ ይቀርበናል የሚለው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መከራከሪያ ህሉው እየሆነ ሄደ፡፡ ኢሕአዴግ በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝባዊ ተቃውሞ መፈተን ጀመረ፡፡ እዚህም እዚያም የፍትሕና በእኩል የመልማት ጥያቄ በኢትዮጵያ መሰማቱ ቀጠለ፡፡

እዚህ ላይ ግን ሌላ ተቃርኗዊ ጥያቄን ክላፋም ያነሳል፡፡ በኢትዮጵያ ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩት ፋብሪካዎች አዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ እንዲህ ከሆነ ኦሮሚያ ላይ ፍትሐዊ የመልማት ጥያቄ እንዴት ሊነሳ ቻለ? ምላሹ ድንገት በጆን ማርካኪስና ዶናልድ ሌቪን ሙግት ውስጥ ራሳችንን አጥምቀን እንድንገኝ ያስገድደናል፡፡ ማርካኪስም ሆኑ ዶናልድ ሌቪን ያለፉት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ መነሻው አማራ፣ ኦሮሞና ትግራይ የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄ የወለደው ነው ይላሉ፡፡ የምሁራኑን ሐሳብ በዚህ ዘመን ስንቃኘው ያለፉት 27 ዓመታት መሠረታዊ ጥያቄም አናሳ ቁጥር ያለውን ሕዝብ የሚወክለው ሕወሓት አብዛኛው ሕዝብ ላይ የወሰደው ብልጫ ነው ወደሚል ድምዳሜ ይወስደናል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ክርክር ክላፋም ራሱ የተሻለ መሟገቻን ያቀብለናል፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ለተነሳው ፖለቲካዊ ቀውስ አንዱ ምንጩ አብላጫው የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ተገፍቻለሁ የሚል ቂም በልቡ ማኖሩ ነው፡፡

በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ከተመለከትን፣ ወሳኙ ጉዳይ የእኔ ብሔር አገር ይምራ የሚል እንደነበር ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ፍንጩ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቀውስ በታሪክ የሥልጣን ይገባኛል አተያይ ሙሉ በሙሉ እንድናያው የሚያስችል አይደለም፡፡ ለዚህ ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ኢሕአዴግ ቤት የሚሰማ ታሪክ ሲሆን፣ ሌላኛው ከውጭ ወደ ውስጥ የሚፈስ መከራከሪያ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ቤት ያለው መሠረታዊ ታሪክ በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባስመዘገቡ አገሮች ሲሰተዋል የነበረ በመሆኑ አዲስ ነገር የሌለው ጊዜያዊ ችግር ነው የሚል ነው፡፡ አቶ በረከት ስምዖን በቅርቡ በኢቢሲ ቀርበው በስፋት እንዳብራሩት ፈጣን ዕድገትን የጀመሩ አገሮች ዕድገቱን በጀመሩ ከ12 እስከ 15 ዓመታት ውስጥ በከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ተመተዋል፡፡ የቻይና፣ የታይዋንና የደቡብ ኮሪያን ተሞክሮ የሚያስታውሰው የአቶ በረከት መከራከሪያ፣ የወቅቱን የአገሪቱን ፖለቲካው ቀውስ ጊዜያዊ ያደርጋል፡፡ ይህ መከራከሪያ ከመሬት ድንገት የተገኘ የማምለጫ ሙግት ሳይሆን፣ በምሁራዊ ሐሳብም የሚደገፍ ሆኖ ይተስተዋላል፡፡ ሀብታሙ አለባቸው “The Ethiopian Characteristics of Ecconomic Growth and the  Politics of Grwoth Bumps” በተባለ ጽሑፉ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት አስደናቂ ነው ቢባልም የፖለቲካ ቁርሾ የማይፈጥር ግን አይደለም ይላል፡፡ ይህ ቁርሾ በፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚቃኝ በመሆኑ በፖለቲካው ውስጥ የራሱን ቦታ ይዞ ወደፊት ይመጣል፡፡ በዚህ ጎራ ላሉ ወገኖች የዛሬዋ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻም ሆነ መፍትሔ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማቱን ማስቀጠል ነው፡፡

 ከዚህ ጎራ የሚለየው ከውጭ ወደ ውስጥ የሚፈሰው ሌላው የፖለቲካ ቀውሱ መላምት ደግሞ ጥያቄው ፖለቲካዊ ነው፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ይሰጠው በሚል ሙግት የተዋጀ ነው፡፡ ለእነዚህ ወገኖች የዛሬዋ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በብቸኝነት የተጓዘበት የፖለቲካ ቁልቁለት ጉዞ ፌርማታ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ መፍትሔው የሥርዓት ለውጥ ብቻ መሆኑ ዕሙን ይመስላል፡፡ ነገር ግን ጥቅል ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችን በፊት ከላይ የተበተኑትን የአገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያቶች ለመሰብሰብ እንሞክር፡፡ ኢሕአዴግ የስትራቴጅካዊ አመራር ችግርና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የፈጠረው መሆኑን አስረግጦ ስላብራራ ይህን በአንድ ጎራ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ከዚህ የራቀው ወገን ደግሞ ታሪክን ዋና መሣሪያው አድርጎ ነገን ይተነብያል (የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄውም ሆነ ኢሕአዴግ በተሳሳተ አቅጣጫ ተጉዟል ትርክቶች በታሪክ ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው)፡፡ ከሁለቱ የፖለቲካ ኃይሎች እሰጥ አገባ ወጥተን ሌላ  ሦስተኛ መከራከሪያ እናንሳ፡፡ ይህ መከራከሪያ ሕዝቡን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ መነሻና መድረሻውም በኢትዮጵያ ለሚታሰበው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የሚሆን ማኅበረሰብ ተፈጥሯል ወይ የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ዘመናዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ባተለች እንጂ፣ የዘመናዊ ማኅበረሰብ ባለቤት ለመሆን አልታደለችም፡፡ ዘመናዊ ማኅበረሰብ በአመክንዮ ላይ የተመሠረተ የግለሰብ ነፃነትን የሚያከብርና በሐሳብ ብዝኃነት የሚያምን መሆኑ ከሞላ ጎደል የሚያስማማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ከእነዚህ መሠረታዊ የዘመናዊ ማኅበረሰብ መመዘኛዎች አንፃር ከተመለከትነው ዘመናዊ የሚባል አይደለም፡፡

እንዲህ ከሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምን ላይ ነው እንዲበቅል የሚፈለገው የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ የዚህ ጥያቄ ምላሽም ከላይ ያነሳነውን የአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ምላሽና የነገዋን ኢትዮጵያ አቅጣጫ ይወስናል፡፡ ከላይ ያጠቃለልናቸው የፖለቲካ ቀውሱ መነሻዎች ላይም ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ተጨማሪ ምክንያት ሲሆን ተጨማሪ የመፍትሔ አካልነቱን ማወጁ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ስለነገዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ስናወራ ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ጋር መጋፈጥ ይኖርብናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ነገሮች መሀል የተገኘነው እኛ ብቸኛው የመፍትሔው አካል መሆናችን ዕሙን ነው፡፡ ከላይ በስፋት የተመለከትነው የዛሬ ፖለቲካችን ድምር ችግር መነሾ የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም የመወስን አቅሙ የጎላ ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሐሳብ ስናነሳም በዋናነት ከእነዚህ ችግሮች ማዶ ያለችውን አገር ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር የረዥም ጊዜ ህልሟ የሚፈታው የተጠቀሱት ድምር ችግሮች ሲቃለሉ ቢሆንም፣ ዛሬ አጣብቂኝ ውስጥ ያለችውን አገር ዕጣ ፈንታ በመወሰን ደረጃ ግን አሁንም ኳሱ በኢሕአዴግ እጅ እንደሚገኝ ዕሙን ነው፡፡  ይህች በኢሕአዴግ እጅ ያለች አገር ነገዋ ወዴት ታመራለች? መፍረስ? ወይስ መታደስ?

የነገዋ ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ እጅ

በኢሕአዴግ እጅ ስላለችው የነገዋ ኢትዮጵያ ስናወራ በቅይጥ መንግሥታዊ  ሥርዓት (ሐሳዌ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) ስለምትተዳደር አገር እያወራን መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነ ሐሳዌ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የተከተሉ አገሮች መጨረሻ ምን ይሆናል የሚለው ጥያቄ ዋና ማጠንጠኛችን ይሆናል፡፡ ስቴፈን ሊቪትሰኪና ሉካን ኤ ዌይ (The Myth of Democratic Recession) በተሰኘ ጥናታቸው ሁለት አሠርታትን ከተሻገሩ በኋላ ሥልጣናቸውን ያጡ የሐሳዌ ዴሞክራሲ አራማጅ አገሮች ቁጥር አናሳ ቢሆንም አይወድቁም ግን ለማለት አልደፈሩም፡፡ ምክንያቱም ፔሩና ፓኪስታን ይህን ዕውነት ይንዳሉና፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግና የነገዋን ኢትዮጵያ ስናነሳ ገዥው ፓርቲ ከዓለም በተለየ ሁኔታ ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ ከቆየ በኋላ ሊወርድ እንደሚችል መገመቱ ነውርነት የለውም፡፡ ለዚህ ድምዳሜ የምንበቃ ከሆነ ደግሞ ከሐሳዌ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች በኋላ በአገሮች ምን ዓይነት ሥርዓቶች ተፈጠሩ የሚለውን መመልከቱ የነገውን ዕጣ ፈንታችንን ይጠቁመናል፡፡ ስቴፈን ሊቪትሰኪና ሉካን ኤ ዌይ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው አፍሪካ ውስጥ በሐሳዌ ዴሞክራሲ ውስጥ የነበሩ አገሮች የሥርዓት ለውስጥ ሲያመጡ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ እንደሚያመሩ ይጠቁማሉ፡፡ 63 በመቶ የሚሆኑ አገሮችም ዴሞክራሲን አስበው ባደረጉት የሥርዓት ለውጥ የባሰ አምባገነናዊ ሥርዓትን ስለመፍጠራቸው ያስረዳሉ፡፡ የሁለቱ ምሁራን መከራከሪያ በውስጡ የተለያዩ መመዘኛዎችን የያዘ ነው፡፡ ፓርላሜንታዊና ፕሬዚዳንታዊ፣ እንዲሁም ብዙ ብሔር ያለባቸውና የሌለባቸው እያለ በተናጠል ለመመዘን የሚሞክረው ጥናቱ፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ወደ ወታደራዊ ሥርዓት ለመመለስ ቅርብ ያደርገዋል፡፡

ይህ በኋሊዮት ላይ ያለ ጉዳይ ገቢራዊ ይሆናል? አይሆንም? የሚለውን የሚወስነው ግን የፖለቲካ መጫወቻውን በእጁ የያዘው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከስድስት ዓመታት በፊት የተሰጠውን የአቶ መለስ የቤት ሥራ አሁንም መመለስ አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም ኢሕአዴግ  የስትራቴጅካዊ አመራርም ሆነ የፓርቲ መበስበስ  ችግር ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ውስጥ ቢገኝም የሕዝቡ ተቃውሞ በተደራጀ መንገድ እየተመራ ባለመቆየቱ እስካሁን በሥልጣነ መንበሩ ላይ ቆይቷል፡፡ ይህ ዕድል አሁንም ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ተስፋ በጣሉ በርካታ ዜጎች የተነሳ ሙሉ በሙሉ የተሟጠጠ አይደለም፡፡ ከዚያስ? የነገው ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያንና የኢሕአዴግ ህልውና ይወስናል፡፡ ኢሕአዴግ ቤት ያለውን የስትራቴጂካዊካዊ አመራር ዕጦት ለመፍታት የሚመጣው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተግባር የተፈተነ ሊሆን ይገባል፡፡ በእርግጥ በዚህ ሰዓት ሥልጣነ መንበሩን መቆናጠጥ ብዙ የራስ ምታቶች እንደሚኖሩበት ዕሙን ነው፡፡ ወቅታዊውን እሳት ከማጥፋት ባለፈ የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት መሞከሩ ኃላፊነትን ሳይቀር ሊያሳጣ የሚችል፣ ከዚያም ከፍ ሲል ለአጭር ጊዜም ቢሆን አገሪቱን አደጋ ውስጥ የሚከት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ከዚህ የተሻለ አማራጭ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ፕሮፌሰር ዲወል እንደሚሉት የነገዋ ኢትዮጵያ መንገድ ፖለቲካን ንግድ ባደረጉ ኃይሎች በብዛት የሚፈተን ነው፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ቢዝነስ በኢሕአዴግ ውስም ሆነ ውጭ የሚስተዋል ነው፡፡ ኢሕአዴግ ቤት ያሉ ኃይሎች አሁንም ከሥልጣናቸው በሚያገኙት ጥቅም መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ያሉ ዕድሉ ደርሷቸው የፖለቲካ ንግዱን ያልጀመሩ ወገኖችም አገር ማዳናኑ ላይ ሳይሆን የነገ ንግዳቸውን ያስባሉ፡፡ ይህ እውነት ከኢሕአዴግ ውጭ ላለውም ጎራ የሚሠራ ነው፡፡ በውጭ ዓለም ያሉ የፖለቲካው አራማጆችና አክቲቪስቶችም ፖለቲካን ንግድ አድርገው መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በአማካይ እስከ 80 ሺሕ ዶላር ዓመታዊ ገቢ የሚያስገኝላቸውን የአክቲቪስትነት ሥራም ሆነ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተጠና የፖለቲካ ቢዝነስ ፕላን ወደፊት ማራመዱን ይመርጣሉ፡፡ ፕሮፌሰር ዲወል የፖለቲካ ንግዱን ለመግታት ኢትዮጵያ እንደ መለስ ዓይነት መሪ ያስፈልጋታል የሚል ሐሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

የፕሮፌሰሩ መከራከሪያ አቶ መለስ በወታደሩም በሲቪሉም የሚፈሩና የሚከበሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ንግድ በውሉ የተረዱ ከመሆናቸው የሚመነጭ ነው፡፡ በዛሬው ኢሕአዴግ ውስጥ የዲወል መፍትሔ የሚሠራ አይመስልም፡፡ ስለዚህም ሌላ አማራጭ እንፈልግ፡፡ ኢሕአዴግ በወታደሩም ሆነ በሲቪሉ የሚፈራ እንኳን ባይሆን የሚወደድ መሪ ይፈልግ፡፡ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አስታርቆ የሚይዘው ስትራቴጅካዊ የሆነው የነገ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ቢያንስ እንደ አገር እንድትቀጥል የማድረግ ዕድል ይኖረዋል፡፡

Reporter Amharic ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mar.getachew@gmail.com ማግኘት ይቻላል

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *