ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው እና ኃይለገብርኤል አያሌው

በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ቅጥ ያጣ ዘረኝነት ኢትዮጵያ ሃገራችን በታሪኳ አይታ ወደማታውቀው የትርምስና የጭለማ ዘመን የደረሰችበት ሁኔታ ላይ ከወደቀች ቆየች:: የአማራው ህዝብም በማንነቱ ምክንያት በተከፈተበት የጥላቻ ዘመቻ ለከፋ የህልውና አደጋ ተጋልጦ ሃገሩንና አብሮነቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል በታላቅ ትዕግስት መሪር መስዋዕትነትን እየከፈለ ቆይቷል::

የትግራይ ወያኔዎች በተለይ የአማራውን ሕዝብ  በሁለንተናዊ መልኩ አዳክሞ ለበቀል አገዛዛቸው የተመቸ እንዲሆን ባለፋት 27 አመታት ያልተቋረጠ ጥቃት ሲያካሂዱበት ቆይተዋል:: የአማራውም ማህበረሰብ በኢትዮጵያውያዊነቱ ፍጹም ጸንቶ ለሺህ ዘመናት የኖረ በመሆኑ በጎሳ ተደራጅተው ሲያዋክቡት እንደነሱ በማንነቱ ተደራጅቶ እራሱን እንዳይከላከል ባህሉና ሃገራዊ አመለካከቱ ግድ ብሎት ቆይቷል:: ይህ የአማራው ወገናችን ትዕግስትን እንደፍርሃት የቆጠሩት ወያኔዎች ስውርና ይፋ የጥቃት አድማሳቸውን በማስፉት የከፈቱበትን ጥቃት አስቀድመው በተረዱ ሃቀኛ ወገኖች አማራውን አደራጅተው ለመብትና ነጻነቱ ለማሰለፍ በብዙ መስዋዕትነት የታጀበ ትግል ቢያካሂዱም በአማራው ማህበረሰብ ውስጥ ብሄረተኛ አመለካከት ለማስረጽ ፈታኝ በመሆኑ በተገቢው ወቅትና ሁኔታ ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ሳይችል በመቅረቱ ለራሱም ሆነ ለሃገሩ ሕልውና ስጋት ላይ አድርሶታል።

የሁኔታዎች መለዋወጥ የህወሃት እብሪት ወለድ የጥቃት እርምጃ እየከፋ መሄድ ያሳሰባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በተለያየ አህጉር በመሰባሰብ በአማራ ስም ድርጅቶች ማቋቋማቸው ይታወቃል።  ሆኖም የድርጅቶች ቁጥር ቢጨምርም ሕዝባችን ካለበት ሁኔታና ትግሉ ከሚጠይቀው ሁኔታ አንፃር ድርጅቶቹ ያሉበት ቁመና ያን ያህል አመርቂ ባለመሆኑ የተበታተነውን ትግል ቢሰባሰብ ትልቅ አቅም መፍጠር እንድሚቻልና እንደሚገባ  ከየአቅጣጫው ጥቆማ ሲሰነዘርበት ቆይቷል::

በዋሽንግተን ሲያትል ላይ በተደረገው ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የአማራው መደራጀት ለኢትዮጵያ  ሕልውና እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን በማስረገጥ በሻለቃ ዳዊትና በፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የቀረበው ጠንካራ ንግግር ጥቂቶችን ሲያስቆጣ ለብዙዎች ግን ዋና የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር። ከዚያም እለት ጀምሮ ሂደቱን ለማደናቀፍ ብዙ የስም ማጥፋት ውርጅብኝ ቢመጣም ፤ ብዙሃኑ ባቀረብንው ሃሳብ ደስ በመሰኘቱና እንድንገፋበት በማበርታታቱ ፤ እኛም ይህን የሕዝብ ጥያቄ በማክበርና ከምናየውም ሁኔታም በመነሳት በግል ተነሳሽነት በመንቀሳቀስ በአማራ ስም የተደራጁትን ፤ በኢትዪጵያ አንድነት ፤ በሕዝብ እኩልነት የሚያምኑትን ሁሉንም ድርጅቶች በአንድ  የጋራ ግንባር ወይም ሕብረት ጥላ ስር በማሰባሰብ  በመለስተኛ ፕሮግራም አንድ ጠንካራ የአማራ ሕዝብ ተጠሪ የሆነ ተቋም ለመፍጠር በመነሳት አቅማችን የፈቀደውን ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርገናል::

የአማራ ሕዝብ ስም የተደራጁትን ተቋማት በመጀመሪያ መሪዎቹን ለብዙ ሰዓታት በተናጥል በአካልና በስልክ ግንኙነት በተደጋጋሚ ግዜ ወስዶ በማነጋገር ወደ ጋራ ውይይት መድረኩ እንዲመጡ ረጅም አድካሚና ትግስት አስጨራሽ ጥረት ተደርጏል:: በመጨረሻም የሁሉም  ፈቃደኝነት ከተገኘ በሗላ በተደረሰው ስምምነት መሰረት በዋሽንግተን የድርጅቶች ግንባር መስራች ስብሰባ ለመጥራት ተችሏል::

በሴምቴምበር 9, 2017 በፓርክ  ቪው ማርዮት ሆቴል ቨርጂኒያ እኛ ስማችን ከታች የቀረበው ግለሰቦች አደራዳሪነት የስድስት የፖለቲካና የሲቪክ ማህበራት ከ20 በላይ ተወካዮች በተገኙበት  የአማራ የፖለቲካ ሃይሎች ግንባር ለመፍጠር ሙሉ ቀን የፈጀ ሰፊ ውይይት ተደርጏል:: በውይይቱም መጨረሻ ጉባዔተኛው በተስማማበት ሃሳብ መሰረት የግንባር ምስረታው እንዲቀጥል ፤ አደራዳሪዎቹም የሂደቱ አካል እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ በመስማማት የግንባር ምስረታውን ለማቀላጥፍ እንዲረድ ሂደቱን የሚያስተባብሩ ጊዜያዊ የኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲመረጥ ውሳኔ ላይ ተደረሰ ። ስብሰባውም ሲጠናቀቅ ሻማ በርቶ የእግዚያብሔር ስም ተጠርቶ በእውነት ለወገናችን ለመቆም ቃላችን የማይለወጥ አቋማችን የማይናወጽ ስለመሆኑ ቃለመሃላ ገብተን ነበር ።

ይህ ጠቅላላ ስብሰባ የአማራን ድርጅቶች በአንድ ማእከል ማሰባሰብን በተመለከተ በፅንሰ ሀሳቡና በአመሰራረቱ  የተስማማባቸውን መስረት በማድረግ በ Sept 30, 2017 ከአንድ ድርጅት በስተቀር የሁሉም ተወካዮች በተገኙበት የሙሉ ቀን ስብሰባ በዚያው ሆቴል ተደረገ:: ሻለቃ ዳዊት የአቀራራቢዎቹ ስራ እዚህ ላይ ስለሚያከትም ኮሚቴው  የራሱን ሊቀመንበር እንዲሰይም ጠየቁ:: የኮሚቴው አባላት እርስ በእርሳችን ገና ስለማንተዋወቅ እስከ ግንባሩ ምስረታ ድረስ ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ በሙሉ ድምፅ ተጠየቁ። ካሉበት ቦታ እየተመላለሱ ይህንን ለመስራት ያለውን የወጪና የጊዜ ችግር ቢያመለክቱም ኮሚቴው በሙሉ ድምፅ  ስለጠየቀ ጥያቄውን አክብረው ተቀበሉ።

የግንባር ምስረታው ሂደት ቀጥሎም የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ግንባሩ የሚመራበትን የፓለቲካ ፕሮግራም ፤ መተዳደሪያ ደንብና የዲስፕሊን መመሪያን ለማዘጋጀት ስራ ተከፋፍሎ ለቀጣዩ መስራች ጉባኤ ዝግጅቱን አጠናቆ እንዲቀርብ ተወስኖ ስብሰባው በሰላም ተበተነ:: ከዚያን ጊዜ በሁዋላም ብዙ ቴሌ ኮንፈረንሶች ተካሄዱ:: በመጨረሻም ኮሚቴዋችም ስራቸውን አጠናቀው ለሶስተኛ ጌዜ Nov 11, 2017 Washington DC ስፕሪንግ ፊልድ  ቨርጂኒያ የአንድ ቀን ሙሉ ስብሰባ በማድረግ በእለቱ የተዘጋጁት ሰነዶችን  በማጽደቅ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማለፍ ተስፋ ተደርጎ ነበረ።  ነገር ግን  በእለቱ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሻለቃ ዳዊት በቤተሰብ እክል ምክንያት ስብሰባውን ለመምራት መገኘት አልቻሉም ነበር። የእለቱን ስብሰባ  በሌላ አባል እንዲመራ የተደረገ ቢሆንም ውይይቱ   ከጽንሰ ሃሳብ ክርክር ወርዶ በቃላት አተረጓጎም ላይ  አሰልቺና  የተራዘመ  የውይይት ግዜ በመውሰዱና  አጀንዳውን መጨረስ ባለመቻሉ ወደ ቀጣይ  ስብስባ እንዲተላለፍ ተደረገ። ከተለያየ የአሜሪካ ግዛት የመጡት ልዑካንም   ወደ መጡበት   ያለውጤት ተመለሱ።

ከርቀት ከወጪና ከግዜ አኳያ እንደገና ሰነዱን ለማጽደቅ በአካል ለመገናኘት ባለመቻሉ ቀጣዩም ስብሰባ በቴክኖሎጂ እንዲሆን በተወሰነው መሰረት በኖቬመበር 11  በሰነዶቹ ላይ ያለው ውይይት ቀጥሎ የግንባሩ ስራ አመራር ቁጥርና ድልድል ላይ ያልተጠበቀና መርህ የሳተ ሃሳብ በማቅረብ የውይይቱ መንፈስ መስመሩን እንዲስት ያደረገ ሁኔታ ተፈጠረ። ይህውም አንደኛው የግንባሩ አባል ድርጅት የአመራር ድልድል ሲደረግ በድርጅት አቅም ልክ መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ አቀረበ። ይህም ነጥብ ያነሱት ወገኖች እኛ የተሻለ አቅም ያለን በመሆኑ አብላጫውን የግንባሩን አመራር መያዝ አለብን ወደሚል መደምደሚያ ደርሰው ግትር አቋም ይዘው ጸኑ። ከታዳሚ ውስጥም ይህ ሃሳብ ለመዳኘት የሚያስቸግርና ከተነሳንለት ሃገር ቤት ያለውን ወገን ድጋፍ ከመስጠት የዘለለ ግብ የማይኖረውን ተቋም ለመመስረት እንጂ ሹመት አይደለምና ስለወገን ስንል እንስማማ የሚል ድምጽ በማየሉ ከተሳታፊዎች የቀረበን ሃሳብ ለመመለስና ለመከራከር ባለመፈለግ ስብሰባውን እረግጠው በመውጣት እራሳቸውን ከሂደቱ አገለሉ።

በዚህም ጨዋነት የጎደለው አድራጎት ያዘኑት የግንባር አመቻች ኮሚቴው ሰብሳቢ  ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ  ሕዝብና ሃገር ጭንቅ ላይ ባለበት ግዜና ሁኔታ ላይ ሆነን በአንድ ድምጽ ለወገናችን ለመናገር እንዴት እንዲህ እንለያያለን በማለት በሁናቴው እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው ራሳቸውን ከኮሚቴው ሰብሳቢነት አነሱ።

ይህ አድራጎት  ተገቢ አይደለም እንደገናም ውይይቱ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን ባሉ ቀና አባላት ግዜያዊ የኮሚቴ ሰብሳቢ በመሰየም የተለዩት ወገኖች እንዲመለሱና ውይይቱን ቀጥለው የግንባሩ ምስረታ እውን እንዲሆን ባለመታከት ሞክረው ነበር።  ሆኖም ያቀረቡትን የማሸማገል ጥረት ምላሽ ባለመስጠት ላስዩት  ጨዋነት የጎደለው አድራጎት በማዘን ለታሪክም ለሃቅም እንዲሆን ሶስት የሲቪክ ድርጅቶች እንደተቋም በጉዳዩ ላይ በየድርጅታቸው ከተወያዩ በሗላ ለመጨረሻ ግዜ ቅሬታቸውንና  ጥያቄያቸውን በደብዳቤ በማቅረብ ግልባጩንም ለሁሉም የግንባሩ ተደራዳሪ አባላት በማሳወቅ ወገናዊ ድርሻቸውን ተወጥተዋል።

የአማራው ሕዝብ የገጠመው ፈታኝ ሁኔታ ከመቼውም ግዜ በላይ በከፋበት ወቅት በእንቅፋቶች መብዛት ተስፋ ሳንቆርጥ የጀመርነውን ጥረት የቀሩትን ድርጅቶች እስከ መጨረሻው ለማገዝ የምንችለውን ስናደርግ ቆይተናል። በዚህም ሂደት እንዳየነው አንዳንዶቹ ድርጅቶች የቀረበላቸውን ሕዝብን አንድ ሆነው የማታገል ጥሪ ለመመለስ የሚስችል አቅም ፤ ተቋማዊ አደረጃጀትና የወቅቱን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚመጥን አጀንዳና ዘመኑን የሚዋጅ አስተሳሰብ በማጣት ፤ በጋራ ለመቆም እንዳይችሉ መሰረታዊ ችግር መኖሩን ታዝበናል።  ሆኖም ምንም በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉት ድርጅቶች የተፈለገው ውጤት ላይ ባይደርሱም ይብዛም ይነስ አቅማቸው በፈቀደና በተረዱት መጠን ለወገናቸው ድምጽ ለመሆን ጥረት በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። እንዲሁም ትብብር እንዲፈጥሩ በአመቻችነት ለተነሳነው እድል ሰጥተው እስከተወሰነም ግዜም  ቢሆን አብረውን ቆመዋልና ልባዊ ምስጋና በዚህ አጋጣሚ እናቀርባለን።

የተከበራችሁ ወገኖቻችን ይህንን መግለጫ በደምሳሳው ያቀረብነው ፤ የማንንም ድርጅትና ግለሰብ ስም ለማንሳት ያልፈለግነው የማስረጃና የመረጃ ችግር ኖሮብን ሳይሆን በአጠቃላይ ሃገራችንና ሕዝባችን ካሉበት ሁኔታ አንጻር ትግሉን ላለመጉዳትና አላስፈላጊ የእርስ በርስ መወዛገብን ለማስቀረት በሚል ነው። ነገር ግን ሁኔታውን ለማጥናት ለወደፊት እውነታውን ማወቅ አለብኝ ለሚል ልናቀርበው የምንችል የተሟላ ከመነሻ እስከመድረሻው ያካተተ ሰነድ ለታሪክም ለማስረጃም በእጃችን ይገኛል። ከዚህ በተረፈ ከሁሉም ጋር ያለን መልካም ግንኙነት እንደተጠበቅ እንደሚቆይ ያለን እምነት ጽኑ ነው።

‘’ላም እሳት ወልዳ እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት ‘’ አበው እንዲሉ ወገናችን የአማራው ሕዝብ በታሪካዊ ጠላቱ የትግራይ ነጻ አውጪ ወያኔ የሚደርስበትን ግልጽና ስውር ዘመቻ ተደራጅቶ እንዲመክት መርዳት ለማንም የምንተወው አልሆነም። በመሆኑም  አማራው እራሱንም እናት ሃገሩን ኢትዮጵያንም ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በእኩልነት አስከብሮ እንዲኖር መጀመሪያ አማራው በአማራነቱ መደራጀት እንዳለበት በጽኑ በማመን ጥረታችንን ሳናቆም በመቀጠላችን ይህው በመጨረሻ በወጣቶች የተገነባ ልምድ ባላቸው ነባር ታጋዮች የታገዘ በሃሳብ ጥራትና ሁኔታዎችን በመረዳት ላይ የቆመ አንድ አማራ የፖለቲካ ሃይሎች ግንባር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ አድርሰናል። የአባቶቻቸውን ወግ ፤ ልማድ ፤ ባህልና ወኔ ትጥቃቸው ያደረጉ የአማራ ወጣቶች ንቅናቄ እና ሰፊ ተሞክሮ ያላቸውን በቀድሞ የመዐሕድ አመራሮች የተመሰረተው የአማራ ትንሳዔ  በማጣመር አንድ አማራ በሚል  የሚታወቀውን ድርጅት በመጨረሻ መመስረት ተችሏል።

አንድ አማራ በሃሳብ ዳብሮ በተቋማዊ አደረጃጀቱ ታርቆ ፤ በስነምግባርና ፤ በሞራል ልዕልና ጎልብቶ ፤ በምሁራን ምክርና ሃሳብ ፤ ተረድቶ የአማራውን ትግል ለመደገፍ በቅርቡም በዋሽንግተን ዲሲ የምስረታ ጉባዔውን በማድረግ አመራሮቹን ከሕዝብ ጋር በማስተዋወቅ ወደ ትግሉ ጎራ ለመቀላቀል መዘጋጀቱን በትህትና ለአማራው ወገናችን እናበስራለን። የእኛም ስራ እዚህ ላይ ተጠናቆ በምክርና በሃሳብ  አንድ አማራን እንደምናግዝ  እንገልጻለን ።

ድል ለሕዝባችን!!

ኢትዮጵያን እግዚያብሄር ይባርክ!!

ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ

ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው

ኃይለገብርኤል አያሌው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *