“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሩሲያ እዳ ሰረዘች፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ተመሳሳይ አቋም ለመያዝና ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ መስማማቷ ይፋ ሆነ

ሩሲያ ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የክህሎትና ወታደራዊ የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግ ተገለጸ። የሃገራቱን የመንግስት ተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነት የማሳደግ ስራ፣ ሃገራቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ተመሳሳይ አቋም ለመያዝ እንደሚሰሩ፣ በአህጉሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶችም የአፍሪካ ሃገራት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግ፣ እና የ162 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የእዳ ስረዛ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላዝሮቭ ተናገሩ። 

ኢትዮጵያና ሩሲያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማሳደግ መስማማታቸውን ገለጹ። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮች በውይይታቸው ወቅት በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፥ ከውይይታቸው በኋላም የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር ወርቅነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ 120 አመታት ያስቆጠረው የኢትዮ- ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ላይ እየተጠናከረ ነው።

በውይይታቸው ወቅትም ሁለቱ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን በማሳደግ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም ለሰላማዊ ግልጋሎት የሚውል የኒውክሌር ሀይልን በጋራ ለማልማት ሀገራቱ ተስማምተዋል። በዛሬው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው ሀገራቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ጣቢያን ለመገንባት በድርድር ላይ ናቸው።

ይህ ጣቢያ የሚገነባውም የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በኢትዮጵያ በገነባችው የኒውክሌር ምርምር ማዕከል እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን፥ ድርድራቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ጣቢያው ግንባታ ይግባል ብለዋል። በስራውም ይህን ማዕከል የማስፋፋት እና የበለጠ ወደ ስራ የማስገባት ተግባርም የሚከናወን ሲሆን፥ የኒውክሌር ማብለያውም በዚሁ ማዕከል እንደሚገነባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተናግረዋል።

የኑውክሌር ጣቢያው ለሀይል እና ለጨረራ ህክምና አገልግሎት የሚያስፈልግ ሀይል ከማምረት ባለፈ፥ ለወደፊት ከኒውክሌር ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ለቀጠናው ሀገራት የምርምር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግልም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

ሃገራቱ በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረትና ሩሲያ 13 ሺህ ኢትዮጵያውያን መማራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሮቹ በአህጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት በምስራቅ አፍሪካና በሳህል ቀጠና አካባቢ እየተስፋፋ የመጣውን አሸባሪነትና ፅንፈኝነት በጋራ መዋጋት በሚያስችሉና ሌሎች ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርገዋል።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው፥ ሁለቱ ሃገራት ካላቸው የቆየ ወዳጅነት አንጻር የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ማሳደግ የጉብኝታቸው ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሃገራቱ መካከል የሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ላቭሮቭ፥ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በኒውክሌር ቴክኖሎጅና በሃይል ማመንጫ ግንባታ በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

ሩሲያ ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የክህሎትና ወታደራዊ የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅሰው፥ የሃገራቱን የመንግስት ተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነት የማሳደግ ስራ ይሰራልም ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈም ሃገራቱ በአለም አቀፍ መድረክ ተመሳሳይ አቋም ለማሳየት ይሰራሉ ብለዋል በመግለጫቸው። በአህጉሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶችም የአፍሪካ ሃገራት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግም በዚህ ወቅት አንስተዋል። በሚኒስትሮቹ ውይይት ላይ ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ162 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የእዳ ስረዛ ማድረጓም ተገልጿል።

ፋና ብሮድካስት

0Shares
0