ባለፈው ቅዳሜ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተከፈቱት ተኩስ ቢያንስ አስር ሰላማዊ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በርካታ የአካባቢው ሰዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ መሸሻቸውን ከሥፍራው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም በበላይነት የሚቆጣጠረው ግብረ ኃይል ሴክሬታሪያት ተወካይ የሆኑት ሌተናል ጄኔራል ሃሰን ኢብራሂም በመንግሥታዊው ቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ አምስት የሠራዊቱ አባላት በደረሳቸው የተሳሳተ መረጃ ምክንያት ተኩስ ከፍተው ዘጠኝ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎችን ሲገድሉ አስራ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ማቁሰላቸውን ገልፀዋል። አንድ ተጨማሪ ግለሰብ ሕይወቱ ያለፈው ተወካዩ ይህን ከነገሩን በኋላ ነው።

የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች የሚገኙበት ቡድን ወደ ሥፍራው ማቅናቱን እና ጥቃቱን ያደረሱት የሠራዊቱ አባላት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ተደርገው ምርምራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተወካዩ ጨምረው ተናግረዋል።

በሞያሌ አካባቢ አንድ ሻለቃ ጦር ሰፍሮ እንደሚገኝ እና ይህም ጦር የተሰጠው ግዳጅ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር እንደማይገናኝ የገለፁት ሌተናል ኮሎኔል ሃሰን የጦሩ አባላት ወደ አካባቢው የሚዘልቁ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላትን የመቆጣጠር ግዳጅ እንዳለው አስረድተዋል።

ወደ ሥፍራው ያቀኑት የሠራዊቱ አዛዦች የአካባቢውን ነዋሪዎች የማረጋጋት ሥራ ያከናውናሉ የተባለ ቢሆንም በርካቶች ቀያቸውን ለቅቀው ድንበር በማቋረጥ ወደ ኬንያ እየሸሹ መሆኑን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ይገልፃሉ።

የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አስቻለው ዮሃንስ በርካታ ቁጥር ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም ሸዋ በር እና ዜሮ አንድ የሚባሉ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከአካባቢው ሸሽተው ወደኬንያ መዝለቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት የሞቱትን ሰዎች ሲቀብሩና ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ሟቾችን ወደቀያቸው ሲልኩ እንደዋሉ የገለፁት አቶ አስቻለው ጥቃቱ የተፈፀመባቸው የከተማዋ አካባቢዎች የንግድ እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተዘግተው ጭርታ ነግሶባቸው እንደዋሉ ገልፀዋል።

በከተማዋ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ በኃላፊነት የሚሰሩ አንድ ግለሰብ ከሞያሌ ከተማ እና ከአጎራባች ቀበሌዎች ሸሽተው ወደ ኬንያ ያመሩ ነዋሪዎች ቁጥር አስር ሺህ እንደሚደርስ ግምታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የሞያሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በገጃ በበኩላቸው በትናንትናው ዕለትም ጫሜ በምትባልውና ከከተማዋ ጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኝ አካባቢ ተኩስ እንደነበረና ቢያንስ አንድ ሰው መቁሰሉን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

አቶ በገጃ ጉዳዩን በተመለከተ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር መነጋገራቸውን ገልፀዋል::

bbc amaharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *