“Our true nationality is mankind.”H.G.

ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ተስማምተዋል – “ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እያመራን ነው፤ ለክፉም ለደጉም እንዘጋጅ ” ጃዋር

ዛጎል ዜና -ኢህአዴግን ለመጣል የሚካሄደው ትግል ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መዳረሱን አቶ ጃዋር መሐመድ ገለጹ።” ለክፉም ለደጉም እንዘጋጅ” ሲል ከቀድሞው የከፋ መስዋዕት ሊያስከፍል የሚችል አጋጣሚ ቢመጣ እንኳን ህዝብ በማምረሩ ወደሁዋላ ስለማይል ጠመንጃውን አስቀምጦ ኢህአዴግ ያለውን የመጨረሻ እድል እንዲጠቀም ጠየቀ። ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ከሚሉት በላይ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ መሆኗን በተግባር እያሳየ በመሆኑ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቃዋሚዎች ጋር እንደተስማማ ተነገረበት።

አቶ ጅዋር ከኦሮሚያ ኔት ዎርክ ጋር የሞያሌውን እልቂት አስመልክቶ ሲናገር ” የህዝብ ደም ፈልቷል” ብሏል። ሰላምዊ ሰዎችን መግደል ካለፉት ሶስት ዓመት ወዲህ እየተለመደ መሄዱን፣ ይህ የንጹሃን ደም ድፍን የኦሮሚያን ህዝብ ደም እንዳንተከተከው በመግለጽ ” ካሁን በሁዋላ ሞት እየፈራ ወደ ሁዋላ የሚያፈገፍግ የለም” ሲል ከነገ ረቡዕ ጀምሮ የሚተገበረው የትግል ስልት እንደሚሳካ እምነቱን ገልጿል። በኢህአዴግ በኩል ደግሞ ሁሉም ጉዳይ ዝግጅት እንደተደረገበት በመከላከያ ሰራዊት አባል ይፋ አድርጓል።

የኮማንድ ፖስቱን ወክለው መገለጫ የሰጡት ሌተናል ጄኔራል ሃሰን ኢብራሒም በኢህአዴግ ቴሌቪዥን ቀርበው እንዳስታወቁት ይህ አሁን ይጀመራል የተባለውን የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል እርምጃ ለማድረግ የሚደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ መረጃ እንዳለ ተናግረዋል። በሞያሌ በንጹን ላይ የደረሰውን ግድያ አስመልክቶ ድርጊቱ ” በስህተት” መፈጸሙን ለማስረዳት ብቅ ያሉት የጦር መኮንን መረጃው እንዳለ ቢናገሩም እንዴት እንደሚከሽፍ አልዘረዘሩም። ህዝብ የተለመደውን ትብብር እንደሚያደርግ ግን አመልክተዋል።

አቶ ጃዋር ህዝብ የሚሉትና መኮንኑ “ይረዳናል” የሚሉት ህዝብ እንዴት እንደሚገለጽ ግራ ቢያጋባም፣ ቀደም ብሎ በተሰላ ስልትና ስትራቴጂ የሚካሄደው ትግል እያደገ እንደሚሄድ አቶ ጃዋር አመልክተዋል። ” ሚስጢር የለም” ሲሉም መረጃውን ለህዝብና ለሚመለክታቸው አስቀድመን የምናሳውቀው አውቀን ነው። አሳውቀን በማድረጋቸውም ተጠቃሚ መህናቸውን ነው ያመለከቱት።

Related stories   አገርን የከዱ ተደመሰሱ፤ የሳተላይት መገናኛና መድሃኒት " ጁንታው" እጅ ሳይገባ ተያዘ

የኢኮኖሚ ልምሻ ውስጥ የገባውን ኢህአዴግ ወጪው እንዲጨምር ማድረግ፣ ገቢውን መቀነስና ይበልጥ ማንኮታኮት አግባብ በመሆኑ ትግሉ እያደገ መሄዱን፣ በሳቸው እምነት የትግሉ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መደረሱን አውስተዋል። ለፈሰሰው፣ እየፈሰሰ ላለውና ወደፊትም ለሚፈሰው ደም ምላሽ እንደሚሰጥም አክለው ገልጸዋል። አዲስና ዝርዝር ጉዳይ የሌለበት የሶሊዳሪቲ ፍንጭም ሰጥተዋል።

የነዳጅ አቅርቦቱ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክልሎች ባሉ የነጻነት ታጋዮችም ሊተገበር እቅድ መያዙን መረጃዎች እንዳሉ ያመላከቱት አቶ ጃዋር፣ አብሮ መታገል አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። አብሮ መታገል ወደፊት ለምትመሰረተው ኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል። ” እኛ ደሴት አይደለንም ” ሲሉ ኦሮሚያ ከሌሎች ህዝቦች ውጪ ብቻዋን የትም እንደማትደርስም አመላክተዋል። የትግራይ ህዝብን ከወትሮው በተለየ መልኩ መንከባከብና ከወያኔ ፕሮፓ ጋንዳ መለየት እጅግ ዋጋ እንዳለውም አስታውቋል።

ይህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ በተደጋጋሚ ለዓመታት ሲናገሩትና ሲወተውቱት የኖሩት ” ሁሉም ነጻ ካለወጣ ማንም ነጻ አይወጣም” የሚለውን መርሃ በሌላ አገላለጽ የተናገሩት አቶ ጃዋር ” ጊዜው አልቋል። ምንም ዓይነት ግድያና እልቂት ቢፈጸም ኢህአዴግን ከመፈራረስ አያድነውም” ብሏል።

Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤

አድፋጭ የሚባሉትና አብዛኛው የለውጥ አካላት የሚስማሙበት ሃሳብ አሁን አሁን እየጠራ መምጣቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ። በአማራ ስም የተደራጁ ቁጥራቸው ሰፊ የሆኑ ድርጅቶችና ማህበራት ወደ አንድ የመጠቃለላቸው ዜና፣ በኦሮሚያ ያረጁት የትግል መንገዶችና ድርጅት አመራሮች በቄሮ የህቡዕ አደረጃጀት መዋጣቸው፣ በባለጸጎቹ አገራት ዘንድ እንዲህ ያለው አካሄድ ድጋፍ ያለው መሆኑና ኢህአዴግ የመርህ ብሎኑ እየላላ መሄዱ ለእነዚህ አብላቻ አድፋጭ ሃይሎች ቀስቃሽ የፖለቲካ ቅመም መሆኑንም ያወሳሉ።

በቅርቡ የኦሮሚያ ኔት ዎርክ ላይ በተካሄደ ውይይት ” ኢትዮጵያ አዋላጅ ትፈልጋለች” በሚለው ውይይት ላይ አንድ ድርጅት ኢትዮጵያን ሊያዋልዳት አንደማይችል በቀረበው ክርክር ላይ በቀለ ገርባና ምረራ ጉዲና ይህንን ሃላፊነት ለመውሰድ እምነት የሚጣልባቸው ቢሆንም ከአማራ ክልል ግን ከብአዴን ሌላ እንደ ድርጅት ጎልቶ የወጣ አዋላጅ አለመኖሩ ተወስቶ ነበር።

በአገር ቤት የሚካሄደው ትግል ሌላ ስም ቢሰጠውም፣ ኢህአዴግ በዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አስቸኳይ አዋጅ ማወጁ ቀውሱ አንገት ድረስ መድረሱን በአለም አደባባይ ማመኑን፣ ይህም የተቃዋሚዎችን እምነት በመርህ ደረጃ መቀበሉን፣ ይሁን እንጂ የቀውሱ አፈታት ላይ ድርብ ችግር መፍጠርን አማራጭ አድርጎ መያዙን ነው ያወጀው ሲሉ በቀውሱ ላይ በሀግ የተደገፈ ማረጋገጫ መኖሩን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ይህ ችግር አድሮም ቢሆን የገባቸው የራሱ የኢህአዴግ ማገር የሆኑት ድርጅቶች የለውጥ አራማጅና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅ መሆናቸውን ለማወጅ ሲውተረተሩ መታየቱ፣ ለዚህም በግንባር የሚጠቀሰው ኦህዴድ መሆኑን ያመለክቱት ክፍሎች ህወሃት ውስጥ ነባር አመራሮቹ ከዚህ እሳቤ ጋር ሊገባቡ አለመቻላቸው ችግሩን እንዳገዘፈው ይናገራሉ። በህወሃት ውስጥ አዳዲስ አመራሮች እለምን እንደማይታዩና ነባሮቹን ራሳቸውን ጣኦት አድርገው የሚያቀርቡበት መክንያት እንደማይገባቸው ያክላሉ። ከዚያም አልፎ አባል ባልሆኑበት የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እየተገኙ የሚፈተፍቱበትን አግባብም እንደሚገርማቸው ይገልጻሉ። ጉባኤ ውስጥ የሚያንቀላፉና መድሃኒት የሚቅሙ ሰዎች እንደዚህ ጥላ የሚሆኑትስ እስከመቼና ለምን እንደሆነ ይጠይቃሉ።

አገሪቱ ቀውሷ ቀውስ በፈጠሩና ቀውስ እያባባሱ ባሉ ክፍሎች ለመፍታት ተገዳ በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ ናት። አዋጁ ደም እያፈሰሰ ነው። “በቃን” ያሉም ያመኑበትን የትግል ስልት እየገፉበት ነው። እስካሁን በተካሄደው የትግልና የአድማ መርሃ የደረሰውን ጉዳት ያሰላና በቁጥር አስደግፎ ያቀረበ የለም። ሁሉም ዓይነቱ ጫና ተካማችቶ ደሃውን እያነከተው ነው። አድማው በዚህ ከቀጠለ ደሃው ያልቃል። እናም መፍትሄው ልዩነት ሳይደረግ ተቀምጦ መነጋገር ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ያለው መንገድ ስደት፣ ሞት፣መፈናቀል፣ ንብረት ማውደም፣ እልቂት፣ ቂምና ችግርን ከማስፋት ውጪ ዘላቂ መላ አያመጣም፤ እየፈሩ ሲኖሩ የነበሩ ” የመጣው ይምጣ” የሚሉ ይመስላሉ። ሰው ከጠመንጃ ጋር ግብ ግብ ገብቷል። መዋቅር ፈርሷል። ሳይመሽ መነጋገሩ ያዋጣል። ቢዝነስ ቀዘቀዘ ብሎ ማላዘን፣ በተራ የድርጅት ፍቅርና ለወደድ ባይነት አድር ባይ መሆን አያዋጣም። አገሪቱ ታማለች!! 

 

Related stories   “የግድቡ ግንባታ ውሃ ይቀንስብኛል የሚለው የግብጽ ጩኸት የማጭበርበሪያና የተለመደ የሃሰት ክስ ነው››

 

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0