ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

« የስልጣን እይታ ብልሽትና የፓርቲ መበስበስም ስላጋጠመን ነው ወደ ችግር የገባነው» ሽፈራው ሽጉጤ

የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው በሳምንት ጊዜ ውስጥ ፓርቲያቸው ለሚመራቸው ሚዲያዎች ሁለት የተለያዩ መረጃዎችን ሰጡ። ከአስራ አምስት ዓመት በሁዋላ በድጋሚ ፓርቲው መበስበሱን ተናገሩ። ኢህአዴግ አገራዊ ፓርቲ እንዲሆን ስምምነት መደረሱን፣ በስምመነቱ አጋር ፓርቲዎችም የሚካተቱበት ሁኔታ እንደሚታይ አመለክቱ። የአስቸኳይ ጊዜ ወታደራዊ አመራር አሰያየምን አስመልክቶ ፓርላማ ከመቅረቡ በፊት የአራቱ ፓርቲዎች አመራሮች ተስማምተው ነበር አሉ። ቀደም ሲል  ” በተባበረ” ድምጽ እንደተወሰነ ይፋ አድርገው ነበር። 

ራሱን ወደ ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብና አቅጣጫ መምራት እንደተሳነ የተነገረለት ኢህአዴግ ችግር በገጠመው ቁጥር ” በስብሻለሁ” ማለቱን ቀጥሎበታል። አቶ ሽፈራው አዲስ ነገር ባይናገሩም አንድ አገር የሚመራ ግንባር እዚህ ደረጃ ከደረሰ ምን እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል? አሃዳዊ ፓርቲ መሆንስ አሁን ከገባበት ቀውስ ያተርፈዋል? 

«የዓላማ ጽናት እና የሕዝብ ወገንተኝነት መሸርሸር ካለ አንድ ፓርቲም ይፈርሳል» ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ ምልልስ የሰጡት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙሉ ቃለ ምልልስ ሙሉ ቃል

ኢህአዴግ ባለፉት ወራት በተከታታይ ማለት በሚያስችል መልኩ የአገሪቱን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ደፋ ቀና ሲል መሰንበቱ ይታወቃል፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስም ራሱን ማየት የጀመረ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያም ዋናው ችግሩ ‹‹የስልጣን እይታ ብልሽት ነው›› ሲልም ራሱን መገምገሙ አይዘነጋም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ትልልቅ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ መክሮ ወሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል እስረኞች ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲለቀቁ መደረጉ እሙን ነው፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በትናንትናው እለትም ብሄራዊ ድርጅቶቹ የደረሱበትን ሪፖርት ለመገምገምና በሌሎች ጉዳዮች ላይም ለመምከር ስብሰባ መቀመጡ ይታወቃል፡፡ እነዚህንና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙትን ክስተቶች በመመልከት ስርዓቱ አደጋ ላይ ነው ሲል አምኖ ችግሮቹን ለመፍታት መንቀሳቀሱ ይታወቃልና እንዴት ነበር የተመለከተው?
አቶ ሽፈራው፡- በ1993 ዓ.ም የተካሄደው የታድሶ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ የሚከተለው ስርዓት ምንነትና የሚመራበት አቅጣጫ መስመር ምን እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ታህድሶ ጊዜ በግልጽ የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት በዚህ አገር በፍጥነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል የተባለው ነው፡፡
በዚህ መንገድ የኢትዮጵያ ተስፋ የሚሆነውና የዚህችን አገር እድል የሚወስነው ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ፈጣን ልማት ህዝቡ ተሳታፊ የሚሆንበትንና ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻት የግድ ይላል፡፡ ይህ ፈጣን ልማት በአንዴ ታይቶ የሚቆም ሳይሆን በየጊዜው ከደረስንበት የእደገት ደረጃ ጋር የሚመጥን፤ እየሰፋና እየዳበረ የሚሄድ ከመሆኑም በላይ በሂደቱ የሚሳተፉትን አካላት ሁሉ ተጠቃሚና ባለቤት የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡
በዚህም አገራችንን ከነበረችበት ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ጉስቁልና እያወጣን እንዲሁም ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተመጽዋችነት እያላቀቅን ራሳችንን የቻልን በባህላችን፣ በታሪካችን እንዲሁም በህዝባችን አቅም የምንኮራ ህዝቦች አገር እንሆናለን የሚል በግልጽ የተቀመጠ ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ መስመራችን ልማት ነው፡፡ ጠላታችን ደግሞ ድህነት ነው፤ የሚያደናቅፈንና ከልማት በተጻራሪ የቆመ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በየጊዜውና በየደረጃው የስርዓታችን አደጋ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ግምገማ ነው የተቀመጠው፡፡
ስለዚህ ከተሃድሶ ማግስት የተደረጉ ጉዳዮች አንደኛ መስመሩን መዘርዘር፣ የፈጻሚ ኃይሎችን አቅም መገንባት፣ ማሳመን፣ ማሰማራትና ወደተጨባጭ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ይህ የሆነው 1993 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህም ስልት እስከ 1996 በሚባል ጊዜ የመጀመሪያውን እድገት ማስመዝገብ የጀመርነበት ወቅት ነው፡፡
ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ደግሞ የሆነው ፈጣን ልማትን ያለማቋረጥ እያስመዘገብን መምጣታችን ነው፡፡ ፈጣን ልማቱ ባደገ ቁጥር ደግሞ ዴሞክ ራሲውም በልማቱ ልክ አይሁን እንጂ እያደገ የመጣበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ የህዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው የሄደው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ከዚህ ጎን ለጎን የኪራይ ሰብሳቢነት አቅሙም እየተጠናከረ ነው የሄደው፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ በህዝቡ የልማትና የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተቀሰቀሱ የመሞገት ፍላጎት በአግባቡና በፍጥነት መመለስ ባለመቻላችን ምክንያት ወደ ቀውስ፣ ግጭትና አለመረጋጋት የገባንበት ሁኔታ ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም ሚያዝያ ወር አካባቢ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በኋላ ላይም በ2007 ዓ.ም የተወሰነ አካባቢም ችግሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ምርጫ 2007 ከተጠናቀቀ በኋላ ያለማቋረጥ 2008 ዓ.ም የዜጎች ህይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ የሰላም ማጣትና መደበኛ የስራ እቅስቃሴ መስተጓጎል የጀመረበት ሁኔታ አጋጥሞናል፡፡
ይህ ችግር ለምን ተፈጠረ በማለት መቀሌ ላይ 2007ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ ባካሄድነው ጉባኤ ስርዓቱን በዋናነት በጥልቀት ለማየት ተገደናል፡፡ በመሆኑም የመልካም አስተዳደር ችግር ባለመፍታታችን፣ የህዝቡንም ጥያቄ በፍጥነት ባለመመለሳችን ነው ብለን ነበር አስቀምጠን የነበረው፡፡
ህዝቡ መሞገትና መጠየቅ ሲጀምር መመለስ ያቃተንና የልቻልነው በየደረጃው ያለው ኃይላችን የመልካም አስተዳደር ችግር ስላለበት ነው፡፡ ይህን መፍታት አለብን ብለን በመቀሌ ጉባኤ ተወስኖ የነበረው በአግባቡ ባለመመለሱ ምክንያት ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብተናልና፤ ራሳችንን መፈተሽ አለብን በሚል የ2008 ዓ.ም የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በመደረጉ ከክረምቱ ጀምሮ ወደስራ የገባንበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡
ግምገዎችን እንዳጠናቀቅን እየተከሰቱ የነበሩ ግጭቶች ሰፋፊ ስለነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በአንጻራዊነት የአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተወሰነ ደረጃ መረጋገት መታየት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ እንደገና በማገርሸቱ አሁን ላይ እንደገና የአስቸኳይ ጊዜ ሊታወጅ ግድ ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ብሄራዊ ድርጅቶቹ ከአንድነት ይልቅ የእኔነት ስሜት እየተንጸባረቀባቸው በመሆኑ ለመከፋ ፈላቸው ዋና ማሳያ ሆኗል ይባላልና ምንድነው ምላሽዎ?
አቶ ሽፈራው፡- ስርዓታችን በእድገት ውስጥ ያለ ነው፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ መታየት ያለበት ጉዳይ እያንዳንዱ ድርጅት አንድ ላይ ሆነን ለመታገል ስንስማማ አንድ ያደረገን ዓላማ መኖሩ ነው፡፡ ለዚህም የምንመራበትና የምንተዳደርበት ህገ ደንብ እና መመሪያ አለ፡፡
ስለዚህ ለእኔ ከባድ መስሎ የሚታየኝ ሰዎች እንዴት ነው ባህሪያቸውን እየገለጹ ያሉት የሚለው ሳይሆን ድርጅቶቻችንን ለዓላማችንና ለመርሃ ግብሮቻችን እንዴት ጸንተው ቆሙ የሚለው ነው፡፡ የህዝቦቻችን ጥቅሞቻቸውና መብቶቻቸው እንዲከበሩ እንዴት ተንቀሳቀሱ የሚለው ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ‹‹የምትወጣው በዚህ ነው፤ የምትገባው ደግሞ በዛኛው ነው›› ተብሎ በማሽን ተቆርጦ እንደተሰራ እቃ ይሆናል ተብሎም መታሰብ የለበትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዴ እንደ ደራሽ ውሃ ፈሰን ታሪክ በመቀየር የቆምንለትን ዓላማና መስመር ትተን መሄድ የለብንም፡፡ እኔ እንደሚገባኝ የቆምንለትን ወሳኙን ጉዳይ ማለት ዓላማና የዓላማው መሰረት በሚሸረሽርና በሚንድ መንገድ መሄድ በጣም መጥፎ ነው፡፡ ነገር ግን ከአዲሱ ትውልድ አዲስ አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጉዳዮችን ለማስተካከል ግን ለውጦች መኖራቸው ነውር አይደለም፡፡
ተደራጅተን የምንታገልበት ዋና ግቡ ህዝብን ለመጥቀም ብሎም አገርን በእድገት ለመለወጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ተገዢ መሆን አለበት፡፡ ማንም ከህዝብና ከአገር በላይ አይደለም፡፡ ለዚህ ስርዓት ነው የሚገዛው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሲሆን፣ በኢህአዴግ ህገ ደንብ አሰራር መሰረት ተወያይተን እንፈታለን፡፡ ግለሰብ ከሆነ ደግሞ በየብሄራዊ ድርጅቱ ይታረማል፡፡ ድርጅት ከሆነ ደግሞ በኢህአዴግ መድረክ ይታረማል ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነው ልዩነቶቻችንን የምናስተካክለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በወጣቱም ሆነ በሌላው ኃይል እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ ያለመስጠት ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፤ እነዚህን ችግሮች ደግሞ አንዱ የአመራሩ ነው ሲል ሌላው ደግሞ የስራ አስፈጻሚው ሌሎች ደግሞ የየሊቀመናብርቱ ነው ሲሉ ይደመጣሉና እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሽፈራው፡- ድርጅቱ ራሱን ከገመገመ በኋላ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን መውሰድ ያለብኝ እኔ ነኝ ብሎ ወሰዷል፡፡ እንደ ድርጅት የከፍተኛ አመራሩ ጉድለት ነው ብሎ ወስዷል፡፡ ከከፍተኛ አመራሩም የስራ አስፈጻሚው ነው ብሎ አምኗል፡፡ ይሁንና እያንዳንዱ ግለሰብ ግን የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡ ድርሻው ደግሞ ስኬትም ጉድለትም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ ላይ ብቻ የምንጠቁምበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እያንዳንዳችን ለመስመሩ የቆምን ሁሉ እኩል ባልደረቦች ነን፡፡ ልዩነታችን ስምሪት ብቻ ነው፤ እንደየስምሪታችን ልክ ደግሞ ኃላፊነትም ተጠያቂነትም አለብን፡፡ ስለዚህ ጥፋቱ የእከሌ አሊያም የእከሊት ነው ተብሎ የሚባል አይደለም፤ የሁላችንም ነውና፡፡ ግን ደግሞ በዋናነት የከፍተኛ አመራሩ ሲሆን፣ ከከፍተኛ አመራሩም ደግሞ የስራ አስፈጻሚው ነው፡፡ ስለዚህም በየነበረበት ራሱን እንዲፈትሽ ነው የተባለው፡፡ ችግሩ ከግንባሩ ሊቀመንበር ጋር ብቻ የሚጣበቅ አይደለም፡፡
አንዳንዴ ደግሞ መረዳት ያለብን ጉዳይ ተፈጠሩ የተባሉትን ችግሮች አንዳንዶቹን የቱንም ያህል ብንሰራ ልንፈታቸው የማንችላቸው ናቸው፡፡ የህብረተሰብ እድገት ለሚያመጧቸው ጥያቄዎች መፍትሄ እናመጣለን እንጂ፤ ችግር የሌለበትን ህብረተሰብ እንገነባለን አላልንም፡፡ ወደፊትም እንደዚህ ብለን ካሰብን ቅዠት ነው የሚሆንብን፡፡ ችግሮች ወደ ቀውስ እንዳይሻገሩ እናደርጋለን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ፈተን እንጨርሳለን ማለት አይደለም፡፡ በፈታን ቁጥር አዲስ ፍላጎት ይቀሰቀሳል፤ አንዱን እንፈታለን፤ እንዲሁ አዲስ ፍላጎት ይቀሰቀሳል፡፡ ይህ የማያቆም የህብረተሰብ የእድገት ለውጥ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ ወደ እውነታው ስንመጣ አሁን ችግሮች አሉብን፤ በውስጣችን የስልጣን እይታ ብልሽትና የፓርቲ መበስበስም ስላጋጠመን ነው ወደ ችግር የገባነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ማስተባበል የሚቻልበት እድል ያለ አይመስለኝምና ለችግሮቹ መፍትሄ ማምጣት የአመራር ኃላፊነት ስለሆነ በዚህ መንገድ ማየቱ መልካም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ ግንባር መሆኑ ነው መከፋፈሉን የሚፈጥርበት የሚሉ አካላት አሉና ውህድ ፓርቲ የመሆኑ ጉዳይ ከምን ደረሰ?
አቶ ሽፈራው፡- ውህድ ያልሽውን ለጊዜው እናቆየውና ኢህአዴግ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ መሆን አለበት የሚለው መወሰን አለበት፡፡ የችግራችን ምንጭ አንድ ያለመሆናችን አይደለም፡፡ እኛ ስልጣን ለመከፋፈል የተደራጀን ኃይል አይደለንም፡፡ በአንድ መርሃ ግብር ዙሪያ በተለየያ አካባቢ የተደራጀን ኃይሎች ነን፡፡ የተለያየ መርሃ ግብር የለንም፤ በሶስት ቋንቋ የተጻፈ አንድ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መርሃ ግብር ነው ያለን፡፡ ስለዚህ በመሰረታዊነት አንድ ስንሆን የሚለየን የቅርጽ ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ብሄራዊ አደረጃጀታችን በዘላቂነት አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን ከግንባርነት ወጥተን መሄድ ያስፈልገናል፡፡ የአሁኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ከዚህ በፊት በጉዳዩ ጥናት ይጠና ሲባል የነበረውን ጉዳይ ተነጋግሮ ማስተካከል አለበት የሚል ውሳኔ ወስኗል፡፡ በዚህ መሰረትም በአሁኑ የነሐሴ ጉባኤ አንድ የውሳኔ ሐሳብ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢህአዴግን ውህድ ማድረግ ብቻም ሳይሆን አጋር ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን ድረስ አጋር ሲባሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህስ በኋላ አጋር እየተባሉ ይቆያሉ ወይስ አይቆዩም የሚለውም ጉዳይ አንድ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ መቋጫ የሚያገኝ ነው የሚሆነው፡፡ ኢህአዴግም ግንባር ሆኖ ይቆያል አይቆይም በሚለውም ጉዳይ ላይ እንዲሁ፡፡
ይህ የውሳኔ ሐሳብ እንዴት ሊደራጅ ይችላል በሚለው ዙሪያ ቀጣይ መፍትሄንም የሚያቀርብ ይሆናል እንጂ የነሐሴው ጉባኤ ላይ አንድ አገራዊ ፓርቲ ላይመሰርት ይችላል፡፡ ነገር ግን እስከሚቀ ጥለው ጉባኤ አሊያም መሃል ላይ አገራዊ ፓርቲ እንዴት እንመስርት በሚለው ጉዳይ ላይ የመፍትሄ ሐሳብ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡
ይህ በራሱ ግን ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ በመርሃ ግብሩ ዙሪያ ያለው የዓለማ ጽናት እና የሕዝብ ወገንተኝነት መሸርሸር ካለ አንድ ፓርቲም ይፈርሳል፡፡ አሁን ባለንበት መርሃ ግብርም በጽናት እና በታማኝነት ለመስመራችን ኪራይ ሰብሳቢነት ሳይፈትነን ከቀጠልን ለውጡን ልናመጣ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ላለፉት 26 ዓመት ገዥ ፓርቲ ሆነን ቆይተናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም በስምምነት በዓላማ ጽናት በመሄድ በርካታ ችግሮችንም የፈታንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡
በቀጣይ የምናካሄደውም ጉባኤ ልክ እንደቀ ድሞው ሁሉ በጥልቀት ራሱን በማየት ችግሮችን እንዲፈታ ከነበረው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተጨማሪ ሌላ ተደራጅቶ ድርጅትን እንደገና የማጠናከር ስራ ይሰራል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሚደራጀው አካል ተግባር ግልጽ አሰራር ማበጀት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጸደ ቀበት ሒደት ‹‹የተጭበረበረ ነው›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ሁለት ሶስተኛ መሆን ያለበት ከጠቅላላው ከ547ቱ አባላት ነበር የሚሉም አካላት አልታጡምና እርስዎ እዚህ ላይ አስተያየትዎ ምንድነው?
አቶ ሽፈራው፡- እኔ አሁን ላነሳሽው ጥያቄ የምናገረው እንደ ምክር ቤት አባል ሆኜ ነው፡፡ የፓርቲው አቋምም ቢሆን ግልጽ ነው፡፡ ስርዓታችን ፓርላሜንታዊ ነው፡፡ ሰርዓታችን እያንዳንዱ ፓርቲ፣ የፓርላማ አባል ፓርቲውን ወክሎ የፓርላማ አባል ሆኖ ሲመረጥ የትም ዓለም የትኛውንም አይነት ስርዓት የሚከተል ቢሆን ፓርላሜንታዊ እስከሆነ ድረስ የፓርላማ አባል መጀመሪያ በአንድ አጀንዳ ላይ የአፈጻጸም ከሆነ መብቱ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሪፖርት በሚቀርብበት ጊዜ ገምግሞ ልክ ነው ልክ አይደለም በማለት የተለያየ አቋም መያዝ ይችላል፡፡
ነገር ግን ፖሊሲ ከሆነና የፓርቲው አቋም ከሆነ ግን በፓርቲ መድረክ ወደ ፓርላማው ከመግባቱ በፊት ባለው መድረክ ላይ ክርክር ያካሂዳል፡፡ በዛ መድረክ እስከመጨረሻው ድረስ ተከራክሮ ይተማመናል፡፡ በመጨረሻ ግን ፓርቲው አቋም ከወሰደ የፓርቲውን አቋም ይወስዳል እንጂ የተለየ አቋም አይዝም፡፡
ይህን ለማድረግ በምክር ቤት የፓርላማው ስብሰባ ከመጀሩ አስቀደሞ የፓርቲ መድረክ ላይ የኢህአዴግ የአራቱም ድርጅቶች ሊቀመናብርት ተገኝተናል፡፡ እንዲሁም አምስቱም የአጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊትም እያንዳንዱ የኢህአዴግ አራቱ አህት ድርጅቶች ለየብቻቸው ከየአባሎቻቸው ጋር መክረዋል፡፡
በመሆኑም የኢህአዴግ አራቱም ሊቀመናብርት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተንና ተስማምተን፤ አዋጁ በተባበረ ድምጽ እንደሚጸድቅ ወስነን ነው የተለያየነው፡፡ ይህ የአዋጁ መጽደቅ እንደየፓርቲያችን የአራታችንም አቋም ሲሆን፣ እንደግንባራችንም የስራ አስፈጻሚ ውሳኔና አቋም ነው፡፡ አራታችንም በጋራ ነው የወሰነው፡፡ ይህን ያደረግነው ደግሞ በዋዜማው የፓርላማ አባላት ሁሉ ባሉበት ሐሙስ እለት ነው፡፡
አዋጁ ከመጽደቁ አስቀድሞ ገና በመጀመሪያው ላይ አፈ ጉባኤው የተናሩትን ማስታወስ ካስፈለገ ከ547ቱ የምክር ቤት መካከል አራት ሰዎች በህይወት የሉም፤ አራቱ ደግሞ በተለያየ ምክንያት በአገር የሌሉ ናቸው፡፡ ቀሪ የሚሆነው 539 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 490 ሰው በዚህ ምክር ቤት ውስጥ አለና ምላዕተ ጉባኤው ተረጋግጧል ብለው ነው ስብሰባውን ያስጀመሩት፡፡ ይህንን በእለቱ ያሉት የመገናኛ ብዙኃን ሰምተዋል፡፡
ከዛ ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ አባላቱ በተባበረ ድምጽ ሳይሆን ድምጽ እንሰጣለን ባሉት መሰረት ነው ድምጽ የተቆጠረው፡፡ ሲቆጠር ቆጣሪዎቹ የፈጠሩት ስህተት አለ፡፡ በመሆኑም ለአፈ ጉባኤው ሲቀርብ የሆነው 88 ተቃውሞ፣ ሰባት ድምጸ ተዓቅቦ መሆኑን ሁሉም የሰማው ጉዳይ ነው፡፡ ከ490 ላይ የተጠቀሱት ቁጥሮች ሲቀነሱ የሚቀረው 395 ነው፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ ለ539 ሲካፈል 70 በመቶ ነው የሚሆነው፡፡ ሲቀንሱ ግን አፈ ጉባኤው የተናገሩት 346 ነው፡፡ ይህ ቁጥር ግን ለ490 አይደለም የተካፈለው፡፡ ከህግ አንጻር የሚያከራክር ጉዳይ አለ፡፡ አሁን ወደእዛ መግባቱ አስፈላጊ አልመሰለኝም፡፡ ይሁንና የተካፈለው ላልመጣውም ለ539 ነው፡፡ በእለቱ ለምሳሌ 49 ሰው አልመጣም፡፡ ይህ ድምጽ እንግዲህ ለሌሉትም ጭምር ነው የተካፈለው፤ እንዲያም ሆኖ 70 በመቶ ነው የሚያሳየው፡፡ ለ490 ቢካፈል ደግሞ 80 በመቶ ያህል ነው የደገፈውና በሁለቱም ቢሰላ ለአዋጁ መጽደቅ ለውጥ የለውም፡፡
ሌላው ደግሞ የእያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ሆነ የአጋር ደርጅት ማን ድምጽ እንደሰጠ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህም በካሜራ የተቀረጸ ጉዳይ በመሆኑ ካስፈለገ ተመልሶ ማረጋገጥ የሚቻል ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳይጸድቅ የፈለጉ አካላት የህዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዳይረጋገጥ የሚፈለጉ ናቸውና የፈለገውን ያህል ጽድቅ ብንሰራም ለእነሱ ኩነኔ መሆኑ አይቀርም፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ ‹‹ይጠቅ መናል›› ብሎ መንግስትና ድርጅት አምኖ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ሁለት ዙር ተወያይቶ የወሰነው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህም ስምምነት ላይ መድረስ ችሏል፡፡ በመሆኑም በእኔ እምነት በፓርቲዎቹ መካከል ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የ88ቱ አባላትን መቃወም አንዳንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው ሲለው ሌላው ደግሞ ከዚህ ቀደም እንዳጋጠመው አይነት የመስመር ዝንፈት ነው ይላሉ፤ በዚህስ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ሽፈራው፡- አንድ መታሰብ ያለበት ነገር በታሀድሶ ጊዜ የነበረውና የአሁኑ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ የመስመር ልዩነት ሲኖር ከጅምሩ አግባብነት ያለው ክርክርና ውይይት ኖሮ፣ የመስመር ልዩነት መኖሩን አስታውቆ፣ በልዩነቱ ላይ ድምጽ ሰጥቶ ተሸንፎ ወይ አሸንፎ፣ የራስ ሐሳብ የበላይነት ስላላገኘ ከማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ከምክር ቤት ወደ ካድሬው ሄዶ በመሸነፍ የወጣ ነው፡፡ ውህዳኑ የብዙሃኑን ውሳኔ ባለመቀበላቸው መብታቸው ተጠብቆላቸው ነው የሄዱትና ይህ ሌላ ታሪክ ነው፡፡
የአሁኑን በተመለከተ በታህሳሱ ስብሰባችን በድርጅቶች መካከል መጠራጠር እንደነበር ነው የሚታወቀው፡፡ ይህ መጠራጠር በከፍተኛ አመራሩ እንዲሁም ከስራ አስፈጻሚው ጀምሮ ታች ድረስ ተፈጥሮ እንደነበርና ይህን ችግር መፍታት እንዳለብን ተስማምተናል፡፡ በዚህ ጉዳይ አንዳንድ ድርጅቶች እስከ ካድሬ ድረስ ሄደው ችግሮችን በመፍታት፣ የሌሎች ድርጅቶች ካድሬዎችንም ጠርተው የራሳቸውንም ችግር ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር ያላቸውንም ግንኙነት በግልጽ ውይይት አድርገው ባቸዋል፡፡
በአንዳንዶቻችን ድርጅቶች ደግሞ ገና ስራ አልተሰራም፡፡ ስለዚህ የቤት ማጽዳት ስራው ገና አላለቀም ማለት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ነው የሰላም እጦት በማጋጠሙ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሄድ ላይ ሳለን ይህ ያጋጠመን፡፡ በእኔ እምነት ግን ጠቃሚ የሚመስለኝ በተከሰቱ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ውይይት በማካሄድ በድርጅታችን የመስመር ልዩነት ነው ወይስ የክስተት ነው የሚለው ላይ በደንብ መነጋገር አለብን፡፡
የተፈጸመው ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ስህተት እንደዚህ አይነት የመስመርና የድርጅት የመለያየት ጉዳይ አድርገን ባንወስደው መልካም ነው፡፡ ችግሮቹ በዝርዝር ቢፈተሹና ምንጫቸው ቢታይ እንዲሁም ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች ቢጠሩ ነው ወሳኝ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሚበልጡ ሌሎች ዋና አጀንዳዎች አሉና ይህን እየፈታንና በሂደትም የተፈጠርን ችግር በነበረው የመተራረም ባህላችን እናርመዋለን በዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የግንባሩ ሊቀመንበር ከሊቀመንበርነቱ ከተሰናበቱ በኋላ እጣ ፈንታቸው ምንድነው?
አቶ ሽፈራው፡- የተለየ አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ እንደ አንድ የኢህአዴግ ታጋይ በትግሉ ይቀጥላሉ፡፡ ስምሪታቸው ግን በአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚተዳደሩት መንገድ ይተዳደራሉ፡፡ ይህን የተመለከተ ህግ አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሽፈራው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

አስቴር ኤልያስ