ታሪኩ አባዳማ -በአገሪቱ ያለው አንድ ህግ ነው – እሱም መለስ ዜናዊ ፅፎት የሄደው የህወሃት ፕሮግራም ነው። ከዚያ በመለስ ህግ ተብሎ የታወጀ ማናቸውም ደንብ ከህወሃት ፈቃድ እና ፍላጎት ውጭ ከሆነ ተፈፃሚ አይሆንም። የህወሃት ፕሮግራም ህግ በሆነበት ሌላ የበላይ ህግ የለም። ስለሆነም የይስሙላው ሰነድ እንደ ህገ መንግሰት ለህወሃት ፕሮግራም እና አላማ ጭንብል ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም።

ለምሳሌ ይፋ በተፃፈው ህግ መሠረት “አንድ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ መሆኑ በህጋዊ ፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ ነፃ ነው” ቢልም ቅሉ በዚህ ስርዓት ህወሃቶች የጠረጠሩት ሁሉ ነፃ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ደረስ ወንጀለኛ ነው። ህወሃት የጠረጠረውን ‘ነፃ’ ነህ ብሎ የሚያሰናብት ፍርድ ቤት ይኖራል ብሎ መጠበቅ ደግሞ ህወሃትን ጠንቅቆ ካለመገንዘብ የሚመነጭ የዋህ ግምት ከመሆን አይዘልም። ፍረድ ቤት ይፈታ ሲል ህወሃት በበኩሉ አልፈታም ማለት እንደሚችል ደጋግሞ አሳይቶናል።

አንዳንድ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ የሆነ ዳኛ ጉዳይህን መርምሮ ነፃ ብሎ ቢያሰናብትህ እንኳ የህወሃት ዘበኞች ከፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ ዳግም እያዳፉ ወደ ወህኒ የመውሰድ ስልጣን እንዳላቸው በተግባር ደጋግመው አሳይተዋል። ምክንያቱም እነሱ የህወሃት ፕሮግራም ዘብ እንጂ የመንግስታዊ ስርአት ጠባቂ አይደሉምና ብይኑ የህወሃትን መሰረታዊ ፕሮግራም ተፃራሪ ሆኖ ሲገኝ ጠንቻቸውን እየሰበቁ ጣልቃ ይገባሉ።

ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ ህዝባዊ እምቢተኝነት የህወሃትን አከርካሪ እያናወጠ በቆየባቸው ያለፉት ሶስት ዓመታት በወያኔ ሰፈር አንድ አዲስ የሚመስል አይነት ነገር እየተንፀባረቀ እናያለን – አንዳንድ ወያኔዎች ይሄ አካሄድ በቀጥታ ወደ ፍፃሜያችን የሚወስድ በመሆኑ ስልት ቀይረን ሽርፍራፊ መብቶችን ለቀቅ አድርገን ስርአቱን ማቆየት አለብን የሚሉ የሚመስሉ ተቆርቋሪ ናቸው። የዚህ አቋም አራማጆች ካለ ወትራቸው ስለ አገር ፍቅር ስሜት ፣ ስለ ቆየው የኢትዮጵያ ህዝብ ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖር ታሪክ ፣ ስለ ‘ጨዋው እና አስተዋይ’ ህዝብነቱ ያለመታከት እያወሱ ይገኛሉ። በህግ የበላይነት መረጋገጥ ጉዳይ ላይም ያላሰለሰ ውትወታ እያደረጉ ይገኛሉ።

በመቀጠልም ህዝብ በደል የደረሰበት ስለ መሆኑ ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ መፍትሔ እንደማይመጣ ሳይቀር እየሰበኩ ነው። ሰርአቱ ተገቢ የማሻሻያ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባው የሚያወሱት እነኝህ ወገኖች ብዙም ርቀው ሳይሄዱ የህወሃትን የፈለጫ ቆራጭነት ስልጣን ለማስቀጠል በየጊዜው የሚፈፀሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደ መፍትሔ አማራጭ ደግፈው ትንታኔ ሲያቀርቡ እናገኛቸዋለን። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገቢ መሆኑን ፣ የህወሃት የስለላ አካላት ላይ ህዝብ በግብታዊነት የሚወስደውን እርምጃ በማውገዝ እጥፍ ይሉና ደግሞ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ህግ አያከብሩም እንጂ ቢየከብሩ ኖሮ ይህ ቀውስ አይደርስም ነበር ይሉናል። አንዳንዴ እንዲያውም የችግሩ ሁሉ መንስኤ የህግ በላይነት አለመረጋገጡ ነው በማለት ጉዳዩን በወያኔ ህገ መንግስት አለመተግበር የተነሳ እንደሆነ ይነግሩናል። ህወሃት እራሱን አሻሽሎ አገዛዙን መቀጠል እንደሚችል በዘወርዋራ በሸውራራ አካሄድ ይነግሩናል። በተለይ ሪፖርተር ጋዜጣ ያለመተከት ሲወተውት አስተውላችሁ ይሆናል።

ህጉ ቢከበር ኖሮ የሰላም ዋስትና ይሆናል የሚባለው በመንግስት አስፈፃሚ ሀይሎች ያልተከበረው ህግ ለመሆኑ የትኛው ነው። የፀረ ሽብር ህጉ ወይንስ የፕሬስ ህጉ? ወይንስ እነ ታዬ አፅቀስላሴ ህወሃት ባስታቀፋቸው ሰነድ እና መመሪያ ላይ ተመርኩዛው በአማተር ሙያተኛነት ያረቀቁት አንቀፅ 39?

ይኸው የወያኔ ‘ህገ-መንግስት’ አይደለም እንዴ ኢትዮጵያ ‘የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት’ ከሚል መንደርደሪያ ተነስቶ ፣ ዜጎችን በጎጥ እና ቋንቋ ሸንሽኖ ፣ አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋራው ፣ የሚወራረሰው ወይንም የሚመሳሰልበት አንዳችም ነገር እንደሌላ የሚያወሳው። ኢትዮጵያውያን በቋንቋ ተከፋፍለው አንዱ ለሌላው ባዕድ እና እንግዳ እንደሆኑ የሚተነትነው ‘ህገ-መንግስት’ በመከበሩ አይደለም እንዴ በከተማ እና ገጠር ‘መጤዎች’ ውጡ እየተባለ የንፁሀን ደም ሲፈስ የቆየው?

‘ህገ መንግስቱ’ በሚገባ ተግባር ላይ በመዋሉ እኮ ነው እስር ቤቶች የቁም ስቅል መቀበያ የሆኑት ፣ ጠዋት ማታ ጎዳናዎች በደም ጎርፍ የሚታጠቡት። ‘ህገ መንግስቱ’ በሰጣቸው ጥበቃ እና ዋስትና ላይ ተመርኩዘው አይደለም እንዴ ከግልገል እስከ ቱባ የህወሃት ሹሞች የአገሪቱን ሀብት በጠራራ ፀሀይ የሚዘርፉት ፣ በፕሮጀክት ስም ከባንክ ብድር በሚሉት የዘረፋ ስልት ስንት ቢሊየን ብር በወያኔ ካድሬዎች ተዘረፈ? ተወደደም ተጠላ ‘ህገ መንግስቱ’ የወያኔ ፕሮግራም ማረጋገጫ ነው እናም ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ ውሏል። በየእለቱ አለም ስለወያኔ የሚሰማው የተከማቸ የወንጀል ኤግዚቢት የሚነግረን ይህን ነው።

ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣባት እለት አንስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሰ ያለውን ጉዳይ እስቲ በጥሞና አስተውሉት። ወያኔ የመጣው ከጫካ ነበር – ባዶ እጁን ግን አልመጣም። ካነገበው መጠነ ሰፊ የብረት ትጥቅ ሌላ አገዛዙን የሚያቀላጥፍበት ሰነድ ጭምር ነው ይዞ የመጣው። ይህ ብቻ አይደለም… ያንን ሸክፎ ያመጣውን ሰነድ በሙሉ ልብ የሚያስፈፅሙ ፣ ከሰነዱ ጋር እጅጉን የሚተዋወቁ ፣ በጫካ ትግል ዘመናቸው በየረድፉ ሰነዱን በመተግበር በቂ ልምድ ያዳበሩ አባላቱንም ነበር ይዞ የመጣው።

ዛሬ የምታዩዋቸው እስር ቤቶች ፣ ማሰቃያ ጣቢያዎች ፣ ወህኒ ዘበኞች ፣ በየጎዳናው ላይ የንፁሀንን ደም የሚያፈሱት አረመኔዎች ትናንት በትግራይ በረሀዎች በሰው ዘር ላይ ተመሳሳይ ሰቆቃ ሲፈፅሙ የቆዩ ወያኔዎች ናቸው። ዘረፋን በሚመለከት ልብ ልንለው የሚገባን ቢኖር እነኘህ ሰዎች ጫካ በነበሩ ጊዜ እጃቸው የወደቀን የመንግስት ንብረት ፣ የሆስፒታል አልጋ ወይንም የልማት ተቋም ፣ ባንክ ፣ ተሽከርካሪ… ያገኙትን ሁሉ እየዘረፉ ለድርጅታቸው ሀብት ማከማቻ በማድረግ በቂ ልምድ ያካበቱ ናቸው። ያኔ ሆነ ዛሬ እነኝህ ሀይሎች ታማኝነታቸውም ሆነ አገልግሎታቸው ለዚያው ተኮትኩተው ላደጉበት የህወሃት ሰነድ ነው። ሰነዱ እንዲከበር የሚታገሉለትን ያህል እሱም ለነሱ በቂ የደህንነት ሽፋን በመሆን ያገለግላቸዋል። ቢገድሉ እንዳይጠየቁ ፣ ቢዘርፉ ስማቸው እንዳይነሳ ፣ ቢዋሹ እንዳይጋለጡ ፣ ሰቆቃ ቢፈፅሙ ተገቢ ሽፋን እንዲያገኙ… ሰነዱ ዋስትናቸው ነው።

በውድቅት ሌሊት የሰው መዝጊያ ገልብጦ ፣ ቤተሰብ እና ጎረቤት አሸብሮ ዜጎችን ማፈን እና ወዳልታወቀ ስፍራ መውሰድ ፣ ዘር ላይ ያነጣጠረ ፀያፍ ቋንቋ መጠቀም ፣ ሰብአዊነት የጎደለው ዘግናኝ የእስረኛ አያያዝ… የምንሰማው ነገር ሁሉ ትናንት በትግራይ በረሀዎች ወያኔ ሲፈፅም የቆየው እናም ላለፉት ሀያ ስድስት አመታት ‘በህግ’ ስም በቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲፈፀም የቆየ ሰቆቃ ነው። ጉዳዩ ለኛ እንግዳ ይሆንብን ይሆን እንደሁ እንጂ ለእነሱ ከቦታው ልዩነት ሌላ ድርጊቱ የነበረ እና በሰልጣን ላይ እስካሉ ድረስ የሚቀጥል እለታዊ ግዳጃቸው ነው።

ህወሃት የትግራይ ነፃ አውጭ በሚል ሲሰባሰብ በማንነታችን የተነሳ በደል ተፈፅሞብናል የሚል ሰበብ ነበረው። የዘር በደል ደርሶብኛል ፣ በትግራይ ዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተፈፅሞብኛል በሚል ተቀስቅሶ ጫካ ገብቷል። ህወሃት ይህንን ዘረኛ ነፃ የማውጣት ግብ ሲወጥን ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፖሊቲካ ላይ የተመሰረተ ድርጅት ወይንም መንግሰታዊ ስልጣን አልነበረም። አንድን ዘር ነጥሎ ለማጥቃት በግልፅም ሆነ በስውር የተነደፈ መንግስታዊ ፖሊሲም አልነበረም።

በአፄው ሆነ በደርግ ዘመን በአንድ ዘር ገናናነት የሌላው ዘር የጥቃት ሰለባ መሆኑን የሚያመለክት አንዳችም ጭብጥ አልነበረም። አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ከመሆን ሌላ አማራ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት ፣ የአማራ የሚባል ጦር ፣ አማራ የሚባል የንግድ እና ቸርቻሪ ተቋም ፣ አማራ የሚባል ቤተክርሲትያን ወይንም መስጂድ አልነበረም – ዛሬ ለህወሃት ምስጋና ይግባውና በዘር ጣሪያና ግርግዳቸውን ያጠሩ ተቋማት በየጎጡ ከተዋል – በወያኔ ዘመን ስፖርት ማዘውተሪያዎች ሳይቀሩ በዘር ቆጠራ እንዲደራጁ ተደርጓል። እግር ኳስ ሜዳ ለመውጣት ሲያስቡ የትኛውን ዘር ለመደገፍ እንደሆነ መወሰን ግድ ነው – ይህን ሳይወስኑ ሜዳ መሄድ ለተባራሪ ጥይት ሰለባ መሆንን ያስከትላል። አልፎ ተርፎ አውድ-ዓመታት በዘር ላይ ብቻ በተሰባሰቡ ሰዎች እየተከበረ ነው – የትግራይ ቀን በመቀሌ/በዋሺንግተን/ሎሳንጀለስ… በየዓመቱ ድል ባለ ድግስ ይታሰባል። ህወሃት ይህን ያህል ነው ኢትዮጵያን ያዘቀጣት።

በዘር ልዩነት የተነሳ እንዲሁም ተነጥሎ በዘር መደራጀት ፣ የሌላውን ዘር ነጥሎ ማጥቃት እና ተነጣጥሎ መባላት የመንግስት ዋና መርህ ሆኖ እየተሰራበት ያለ አገር ቢኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ህግ ፣ ህገ መንግስት እየተባለ ሌላውን ለማጃጃል የሚደረገው ውጣ ውረድ ሁሉ ወያኔ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ቃሉ መዘባበቻ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ብሎ የሚጠብቅ የዋህ ካለ እንጃ!

ትናንት ሆነ ዛሬ የዜጎች ትልቁ ወንጀል በህግ የበላይነት ካልሆነ በግለሰቦች እና በቡድኖች ፈቃድ አንገዛም ማለታቸው ነው። የህግ በላይነት ደግሞ በፎቆች ርዝመት ፣ በባቡር መስመሮች ስርጭት ፣ በግድቦች ስፋት የሚለካ የሚተካም አይደለም። ተፍጥሯዊ ሰብአዊ መብቶቻችን የህግ በላይነት እስኪረጋገጡ ፣ ህዝብ የፈቀደው የፖለቲካ ሀይል ስልጣን የሚይዝበት እና የሚወርድበት አግባብ እስኪሰፍን እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ለመታገል ቆርጠው ለተሰለፉ ሁሉ ክብር ይሁን።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *