“Our true nationality is mankind.”H.G.

ብድር ለመመለስ የተገኘ ተራ

በበርካታ ወጥና የትርጉም ቴአትሮች ላይ ተሳትፏል። ኦቴሎ፣ ኤዲፐስ ንጉሥ፣ ሀምሌት፣ ቴዎድሮስ፣ የሠርጉ ዋዜማ፣ መቃብር ቆፋሪውና የሬሳ ሳጥን ሻጩ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለ ካባና ባለ ዳባ፣ መልዕክተ ወዛደር። በትዕይንተ መስኮት ከተወነባቸው ድራማዎች መካከል ደግሞ ያልተከፈለ ዕዳ፣ ያበቅየለሽ ኑዛዜ፣ ባለ ጉዳይ እና ገመና ቁጥር አንድ እና መለከት ጥቂቶቹ ናቸው።

በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሞገደኛው ነውጤ፣ ጥቁር ደም፣ ሳቤላ፣ የነበረው እንዳልነበረ የተባሉትንና ሌሎችንም አጫጭርና ረጃጅም ልቦለዶችን ቀልብን በሚገዛ የአተራረክ ስልት ተርኳል። ፊልሞችም ላይ አለ፤ ቀይ ስህተት፣ ጉዲፈቻ፣ የሴም ወርቅ፣ ፍቅር ሲፈርድ፣ አስርቱ ቀናት የተሰኙት ይጠቀሳሉ። ስሙ ሲጠራ ከልቡ ፈገግ የማይል፣ የማይወደውና የማያደንቀው የለም፤ አንጋፋውን የኪነጥበብ ሰው ፍቃዱ ተክለማርያም።
ጥቅምት 8 ቀን 2008ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር የፍቃዱ ስልሳኛ ዓመት የልደት በዓል በተከበረ ጊዜ ተዋናይና መምህር የሆኑት የክብር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) እንዲህ አሉ፤ «አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተዋንያን ለመቅጠር ፈልጎ ሲመርጥ ቁጥር አንድ ፍቃዱ ቀጥሎም ሱራፌል መመረጥ ችለዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፍቃዱን በጥበብ መሰላል ሲወጣ እንጂ ሲወርድ አይቼው አላውቅም። በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ውስጥ ፈርጥ ናቸው ከምንላቸው መካከል አንዱ ፍቃዱ ተክለማርያም ነው። በዚህም ያኮራል»
የኪነጥበብ ባለሙያዎች በጥበብ መናገርና መሥራት ስለሚያውቁበት በተመልካችና አድማጮቻቸው ለመወደድ ጊዜ አይፈጅባቸውም። ይህ የሆነው ያለስስት በሚሰጡት ሙያቸውና ለሙያቸው ካላቸው ፍቅርና ክብር ነው። ኪነጥበብ ደግሞ ወዳጇን ታከብራለች። የከፈለላትን ያህል ዋጋ ትከፍላለች ወይ? የሁሉም ጥያቄ ነው።
አሁን ላይ የፍቃዱ ተክለማርያምን ውለታና ብድር ለመክፈል ጊዜውና ተራው የደረሰ ይመስላል። ፍቃዱ ተክለማርያም የኩላሊት ህመም እንዳጋጠመው ታውቋል። ይህም አስቸኳይ ንቅለ ተከላ እንዲደረግለት የሚጠይቅ ነው ተብሏል። የሥራ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ ኩላሊት ለጋሽ ለመፈለግና ገቢ ለማሰባሰብም ሲነሱ የእርሱ ፈቃድ ግን ያ እንዳልሆነና «በእምነት እድናለሁ» ብሎ አሻፈረኝ ማለቱንም ሰምተናል።
ይህ ጉዳይ በይፋ የተነገረው ከፍቃዱ አድናቂና ወዳጆች ጆሮ የደረሰው ዕለተ ሐሙስ መጋቢት 6 ቀን 2010ዓ.ም ካዛንችስ በሚገኝ ሆቴል በፍቃዱ ወዳጆችና የሥራ ባልደረቦች የተቋቋመ ኮሚቴ ለመገናኛ ብዙኃን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ከኮሚቴው አባላት መካከል የሆነው የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ፤ «ይህ ዝግጅት እንዲዘጋጅ ፍቃዱ አልፈለገም። ሰው አታስ ቸግሩ፣ ከነክብሬ ልሙት፣ ዘርፉንም አታስደፍሩ» ማለቱን ነበር ያስታወሰው። ቤተሰቦቹ ግን አንድ ነገር አድርጉ ብለው እንድንሰበሰብ ሆኗል። እኛም አንተ መብት የለህም፤ የሕዝብ ሀብት ነህና በራስህ ላይ መወሰን አትችልም ብለን ይህን ዝግጅት አድርገናል።
የፍቃዱን ጤንነት ለመመለስ ኩላሊት ለመለገስ የቤተሰቡ አባላት በምስጢር ሞከርው በህክምና ጉዳዮች ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱም ተገልጿል። በመሆኑም ዋናው አንገብጋቢ ጉዳይ የኩላሊት ልገሳ እንደሆነ ተነግሯል።
ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት መምህር ውድነህ ክፍሌ ከኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ ነው። በንግግሩም መስጠት እንጂ መቀበል የማይወደው ፍቃዱ ወዳጆቹና የሚያውቁት ሁሉ በየእምነታቸው በጸሎት እንዲያስቡት እንደሚሻ ገልጿል። ፍላጎቱንም ለመፈጸም ውድነህ ጥሪውን አስተጋብቷል። «ፍቃዱ ምንም ሳይሰስት እንደሰጠ ነው፤ መቀበል አይፈልግም። እያመመውም እየሠራ ነው። አሁን ለሰጠን ሁሉ እንድንከፍል እኛ ነን ዕድሉን ያገኘነው» ብሏል።
አያይዞ ይህ በፍቃዱ ሰበብ የተነሳ ጉዳይ ሌሎች በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን ለማገዝና ለመርዳት የሚጠቅም እንደሆነ ሊታሰብ እንደሚቻልም አስገንዝቧል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በተገኙ ጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበዋል፤ ሃሳቦችም ተሰጥተዋል። በመግለጫውም ህክምናውን ከአገር ውጪ እንዲሆን ያስፈለገው ህመሙ ያለበት ደረጃ በአገር ውስጥ ህክምናውን ለማካሄድ የማያስችል በመሆኑ ነው ተብሏል።
የጥበብ ከያንያን ከብዙ ሰው ጋር ብዙ ጊዜያቸውን በሙያቸው አሳልፈው በኑሮና እንዲህ በጤና እክል ጊዜ ግን ለብቻቸው ይሆናሉ። ቴዎድሮስ ተሾመ ፍቃዱ «ተው አትጠይቁ» ሲል «ዘርፉንም አታስደፍሩ» ማለቱን አንስቷል። በእርግጥ እንዲህ ላሉ የጥበብ ሰዎች ሕዝብ እርዳታ ያደርጋል አይባልም፤ ብድሩን ይከፍላል፤ ውለታም ለመመለስ ዕድል ያገኛል እንጂ። ነገር ግን የዘርፉ ባለሙያዎች እጅ ለእጅ ተያይዘውና ተጋግዘው ዘርፉንና ራሳቸውን ማገዝ ይኖርባቸዋል። 
ባህርማዶ ሆኖ እንደሚታየው ዓይነት ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ ተሰሚ፣ በመንግሥትም ሆነ በሚመለከተው ሁሉ በተገቢ መንገድ የሚደገፍና ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ እስኪሆን ድረስ ዘርፉ በባለሙያዎቹ ጫንቃ ላይ ነው። ከማሰብና ከመፈለግ በዘለለ፤ በአንድ የኪነጥበብ ባለሙያ ህመም ጊዜ «ሆ!» ብሎ ከመነሳት ውጪ ቋሚ ነገር ለመሥራት ለሕዝብ ከሚቸሩት ጊዜ ሸርፈው ለራሳቸው ቢያደርጉ መልካም ነው።
ፍቃዱ ተክለማርያም በገንዘብ ለመደገፍ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ቁጥር 1000239345488 ገንዘብ ገቢ ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም ባህር ማዶ ላሉና «gofundme /ጎ ፈንድ ሚ/» በሚል ድረ ገፅ የኦንላይን የገቢ ማሰባሰቢያ በቴዎድሮስ ተሾመ ስም የተከፈተ ሲሆን፤ “please help save fekadu” በማለት ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል። ከዚህ ውጪ ሌላ የሂሳብ ቁጥር ለጊዜው እንዳልተከፈተና አዲስ ነገር ካለም ኮሚቴው ለሕዝብ የሚያሳውቅ መሆኑ ተጠቅሷል።
የኩላሊት ልገሳ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሰዎች 0911864396 አቶ ግርማ ተክለማርያም እንዲሁም 0913023444 ዮርዳኖስ ፍቃዱ ማግኘት ይችላሉ። የፍቃዱ ተክለማርያም የደም ዓይነት A ሲሆን፤ ልገሳ ለማድረግ የሚችሉ ሰዎች A ወይም O የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
ሊድያ ተስፋዬ – አዲስ ዘመን

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች
0Shares
0