ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ቅርስነቱ የሚያወዛግበው የቴዎድሮስ አደባባዩ ሴባስቶፖል

በመኪኖች ጭስ እንደታፈኑ ውለው ከሚያድሩት የአዲስ አበባ ሐውልቶች እና ቅርሶች መካከል የሚመደበው የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ዙሪያ ገባውን በላስቲክ ሸራ ተሸፍኗል። ዓይን የለውም እንጂ ዓይን ቢኖረውማ እዚህም እዚያም ከተቆፋፈሩት የከተማዋ መንገዶች በሚመጣው አቧራና በተሽከርካሪዎች ከሚወጣው ጭስ ብሌኑ ደም ለብሶ እናየው ነበር። የአደባባዩን የብረት አጥር እየዘለሉ ገብተው ከመድፉ ላይ ተንተርሰው ውሎና አዳራቸውን የሚያደርጉ ጎዳና ተዳዳሪዎች ተጎራብተውት ይኖሩ ነበር። አዲስ አበባ ቸርችል ጎዳና የሚገኘው ቴዎድሮስ አደባባይ ።

በእድሳት ላይ ከሚገኘው አደባባዩ ዙሪያ ከአንድ አዛውንት ጋር ቆመን አካባቢውን እየታዘብን ነው። መስቀለኛ መንገድ ላይ የተተከለው አደባባይ ከመሃሉ ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ በመቅደላ ያደረጉትን ጦርነት የሚያስታውሰውን የአፄ ቴዎድሮስን መድፍ የሴባስቶፖልን አምሳል ይዟል።
በሃሳብ ወደ መቅደላ አምባ ልውሰዳችሁ። ትክክለኛው ሴባስቶፖል የተሰኘው ትልቁ መድፍ አፈጠባብ ስለነበር በጦርነቱ ወቅት አንድ ጊዜ ባሩድ ጎርሶ እንደተፋ በመተርተሩ የሚጠበቅበትን ጥቅም እንዳልሰጠ ይነገርለታል። ትክክለኛው ባለታሪክ ሴባስቶፖል በደቡብ ወሎ መቅደላ ተራሮች ላይ ተቀምጦ የታሪክ ተቆርቋሪ ማጣቱን በጉስቁልናው ያሳብቃል። ሌሎች ለጦርነቱ የዋሉ አነስተኛ መድፎችም ራቅ ራቅ ብለው ሐረግ ሬሳ ወርሷቸው፤ እንክብካቤ ጎሏቸው ለትዝብት ተቀምጠዋል። 
ትክክለኛውን ታሪክ የተሸከሙት እነዚያ መድፎች አስታዋሽ አጥተው ወደመሬት እየሰመጡ ያየ ሰው የአዲስ አበባው አምሳለ ሴባስቶፖል በኩራት ተገትሮ ሲያይ የታሪክን መዛባት ያስተውላል። እነዚያ አውነተኛ መድፎች ታሪካቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ሲገባ የአዲስ አበባው አምሳለ ሴባስቶፖል ለእድሳት ከፍተኛ ገንዘብ ሲመደብለት መስማት ደግሞ «የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ…» የሚለውን ሀገራዊ ብሂል ያስታውሳል። 
መንግሥት በመዲናዋ ለሚገኙ ጥንታዊ ቤቶች እና ሐውልቶች ዕድሳት የሚውል 30 ሚሊዮን ብር መመደቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል። እድሳት ከሚደረግላቸው መካከል የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ አንዱ ነው። 
ድንገት ከአጠገቤ የነበሩ አዛውንት «ምኑ ነው ይሄ ቅርስ ተብሎ የሚታደሰው» የሚል ሃሳብ አነሱ። «እንዴት?» አልኳቸው። «እውነተኛው ባለታሪክ መቅደላ ላይ ባዶ እግሩን ቆሟል። ይሄኛው ፋብሪካ ሰራሽ ግን ከተማ መሃል በክብር ይታያል በማለት መለሱልኝ። ሃሳቡን እንዲያብራሩልኝ ጠየኳቸው። «አንድ ጎብኚ መጥቶ ይሄ መድፍ የማን ነው? ብሎ ቢጠይቅ አንዴት አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር የተዋጉበት መድፍ ነው ልንለው እንችላለን? ቢያንስ ከአጠገቡ የታሪኩ ባለቤት የአፄ ቴዎድሮስ ምስል ተቀርጾ መታየት ነበረበት» የሚለውን ማብራሪያ ጨመሩልኝ። ይህን ጉዳይ በባለሙያ ዓይን ማብራራት ነበረብኝና ባለሙያ ፍለጋዬን ተያያዝኩት። ብዙዎች  ከቴዎድሮስ አደባባይ ቅርስ ተብሎ የመመዝገብ ጉዳይ አይዋጥላቸውም። እንደ አዛውንቱ ከመድፉ ጎን ሐውልቱ የታለ? የሚል ሃሳብ ያላቸው ሰዎች በረከቱብኝ ።
ደራሲ እና መሀንዲስ ኢንጂነር ታደለ ብጡል የአዲስ አበባው መድፍ በአደባባዩ ሲቆም የነበሩ የታሪክ እማኝ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አፄ ኃይለስላሴ የአጼ ቴዎድሮስን ቴአትር ከተመለከቱ በኋላ የአገር ባለውለታ መሆናቸውን በመገንዘብ የሴባስቶፖል መድፍ እና የንጉሱ ሐውልት እንዲቆም ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ያስታውሳሉ። ነገር ግን የእራሳቸውን ስም ማስጠራት የሚፈልጉ ሰዎች ከአቃቂ የጥይት ማምረቻ ፋብሪካ በይድረስ ይድረስ ያሰሩትን የመድፍ መሰል አምጥተው በአደባባዩ በማቆም ሐውልቱን ሳያሰሩ መተዋቸውን በቁጭት ይናገራሉ። 
«የብረት አሎሎ ማቆም ቅርስ አይሆንም» የሚል ቅሬታ በመገናኛ ብዙሃን ማቅረባቸውን የሚያስታውሱት ኢንጂነር ታደለ፤ መድፉ ብቻ ቢቆም እንኳን ትልቁን የአፄ ቴዎድሮስን መድፍ አምሳያ ሆኖ መሰራት እንደሚገባው ይገልፃሉ። በተለይም መቅዳት ካስፈለገ ሴባስቶፖል አፈ ጠባብ መድፍ በመሆኑ መሰንጠቁን የሚያሳይ ሆኖ ለእይታ መቅረብ ነበረበት። እስከአሁን ድረስ በስህተት የቆመው መድፍ ብቻውን በአዲስ አበባ አደባባይ መቀመጡ በቂ ባለመሆኑ አፄ ቴዎድሮስ የውጭ አገር ዜጎችን አዘው መድፉን ሲያሰሩ የሚያሳይ ወይንም መድፉ ተጎትቶ ወደ ተራራማው ቦታ ሲወሰደ የሚያሳይ ተደርጎ በአግባቡ መቀረጽ እንደነበረበት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሃሳብ አቅርበዋል። 
«በመሆኑም የአዲስ አበባውን አቅልጦ መጣል እና የመቅደላውን ዋናውን መድፍ በአግባቡ መንከባከብ ይገባል» ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ቅርስ ብሎ ለመጥራት መስፈርቱን የማያሟላ፤ የፋብሪካ ምርት የሆነ እና የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያለው በመሆኑ ማደሱ አስፈላጊ እንዳልሆነም ያስረዳሉ። ይልቁንም የንጉሱን ምስል ቀርፆ ከመድፉ ጋር ቢያስቀምጡት ለጎብኚዎችም ሆነ ለታሪክ ተረጂዎች ግልፅነት ያለው ቅርስ ማድረግ ይቻላል። አዲሱን ትውልድ ስለ አገር አንድነት እና ስለታሪክ አስፈላጊነት እንደ ምሳሌ አድርጎ ለማስረዳት እንደሚያስችል ኢንጂነር ታደለ ይመክራሉ። 
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያም በ1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ላይ የሚታየውን መድፍ ቅርስ ብሎ መጥራት እንደማይቻል ይናገራሉ። አንድ ሃብት ቅርስ ሊባል የሚችለው በእውነተኛው ታሪክ ጥቅም ላይ የዋለውን ተመሳሳይ ሲሆን እና ረጅም ዕድሜ ሲያስቆጥር ነው። በአደባባዩ የቆመው መድፍ ግን በዘመኑ ኢትዮጵያውያን የተጠቀሙበትን መድፍ የማይመስል እና በፋብሪካ ተመርቶ የቀረበ አጭር ዕድሜ ያለው ነው። በተጨማሪም አሁን ያለውን መድፍ ብቻ ያለንጉሱ ሐውልት ባዶውን ማቆሙ በታሪክ አዋቂዎች እና በጎብኚዎች ዘንድ ትዝብት ውስጥ የሚጥል መሆኑን ይገልጻሉ።
«የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እና የሰማዕታት ሐውልቶች ላይ ምልከታ ቢደረግ የታሪኩ ባለቤት የሆኑ ሰዎች እና ሐውልቱ በአንድ ላይ የተቀረጹ ናቸው። በመሆኑም የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ላይ ያለው መድፍም የታሪኩ ባለቤት አፄ ቴዎድሮስን ከአጠገቡ በመቅረጽ ማቆም ለትውልድ እና ለአገር አንድነት የሚበጅ ሥራ ይሆናል» በማለት ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። 
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃ ከፍተኛ አርክቴክት ሰላማዊት ጌታቸው ግን የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ላይ የቆመው መድፍ «የታለመለትን መልዕክት እስካስተላለፈ ድረስ ቅርስነቱ አያጠያይቅም» ባይ ናቸው። አርክቴክት ሰላማዊት አንዳንድ ሰዎች መድፉን እንደቅርስነት መጠቀም አይገባም ሲሉ እንደሚሰሙ ይናገራሉ። የአዲስ አበባው መድፉ ከተሰራበት ጊዜ ጀምሮ አጭር ታሪክ ያለው መሆኑ ቢታወቅም ዕድሜውን ብቻ ሳይሆን ማስተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት እና ምሳሌነቱን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ሐውልቱ ለምሳሌነት ከፋብሪካ መሰራቱንና ከአጠገቡ የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት አለመኖሩን በመመልከት ቅርስ ሆኖ መቀመጥ እንደሌለበት በግልም ከበርካታ ሰዎች ክርክር አዘል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ያስታውሳሉ። እርሳቸው ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ አቋማቸውን ማስቀመጥ ቢያቅታቸውም ነገር ግን ከቅርስ ጥበቃ እና ደህንነት አንፃር ተመሳሳዩን መስሎ መሰራት ነበረበት በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ። መድፉ ምንም ይሁን ምን የተፈለገውን ታሪክ ማስተላለፍ ከቻለ ቅርስ ብሎ ለመጠበቅ እንደሚገባም ይናገራሉ። የአፄ ቴዎድሮስ አደባባዩ ቅርስ የተፈለገለትን የጦርነቱን መልዕክት እና የታሪክ ክፍል እያስተዋወቀ በመሆኑ ዕድሳቱ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። የቅርሱን ንጽህና እና ውበት በመጠበቅ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግም ያስረዳሉ። 
እንደ አርክቴክቸር ሰላማዊት ገለጻ፤ የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ንጽህናው ያልተጠበቀ ቦታ ሆኖ ነበር። በአካባቢው የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚተኙበት እና የሚውሉበት በመሆኑ መጸዳጃም ጭምር ሆኖ ቆይቷል። ስለሆነም ዕድሳት የሚደረግለት የአካባቢውንም ንጽህና ከመጠበቅ አኳያ ነው። የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰጠው ትኩረት በባለሙያዎች ጥናት ተደርጎበት ለእድሳት ጨረታ ወጥቶ ሥራው እየተሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። አደባባዩ አጥር እና መድፉን ጭምር በማስዋብ ጥሩ እይታ እንዲኖረው የማድረግ ሥራም በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። ለእድሳቱ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ተበጅቶለታል።

ዜና ሐተታ – ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን